Leave a comment

ባለጉዳዩ ሼክ ዓላሙዲን ባይሆኑስ?


ባለጉዳዩ ሼክ ዓላሙዲን ባይሆኑስ

ባለፉት 27 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸዉ ገዢዎቻችን የአገሪቱን ሃብትከወረሱበት ሥልት አንዱ፣ ትን ሽ ይሉኝታ ሲሞክራቸዉ፤ የዘረፉትን በሌለች ስም እንደተያዙ በማስወራት ነዉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ በሼክ ዓላሙዲን ሥም እንደታያዘ የሚወራለት ሃብት በርካታ ነዉ፡፡ ይህ ጉደኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይመዘግባል፣ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ያስተላልፋል፡፡ ያንን ቀን ግን ግዝአብሄር ይከልክል እንጂ ሁሉም እየሳቀ ነዉ የሚያስተላልፈዉ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከሼኩ፣ በአካባቢያቸዉ ካሉ ሰዎችና፣ ሰራተኞች እያመለጠ የሚወጣዉ መረጃ ሲታይ ጉዳዩን በሚገባ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ቢገባም ዝም ብሎ ማለፍ ያስቸግራል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የቃረምኩት ይህንን ይመስላል፡፡ ገዢዎቻችን በፕራይቬታይዝሽን ሽፋን “ሼክ ዓል ዓሙዲን ገዙት” ብለዉ በማስወራትና፣በማደናገር የዘረፉት የሃገር ሃብት ብዙ እንደሆነ ይወራል፡፡ በዚህም ለይስሙላ ያህል፣ ድርጅቶቹ በከፍተኛ የመንግሥት ወጪ ዋጋቸዉ ከተተመነ በሁዋላ ሌሎች ገዢዎችን በማግለልና፣ ብዙ ጊዜም በማስፈራራት ሽያጭ ይፈፀማል፡፡ ለዚህ ጠቋሚ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዱ ዉሽዉሽ ነዉ፣ ስለሚባል የሰማሁትን ላካፍላችሁ፡፡ በርካሽ ገንዘብ ወደ ግል እንደተላለፈ ከሚታወቁት የሃገር ሃብቶች አንዱ የዉሽዉሽ ሻይ ተክል ነዉ፡፡ ልማቱ ከተለመደዉ ዉጭ የተላለፈበትን እና፣ እዉነት አለመሆናቸዉን የሚመለከተዉ ሊያረጋግጥ የሚገባዉ ተጓዳኝ ፍንጮች እነሆ፤

1. የዉሽዉሽ የሽያጩ ሰሞን፣ እንዲህ ሆነ፡፡ ታዲያ ጎጅብን ተሻግረዉ የማያዉቁት ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ባልተለመደ መልኩ፣ ከሥስት ባልበለጡ ተሽከርካሪዎችና፣ ከተወሰኑ ሚስጥረኛ ጓዶቻቸዉ ጋር ብቻ በመሆን፣ ወደ ዉሽዉሽ ተጉዘዉ እንደተራ ሰዉ በእርሻ ልማቱ ዉስጥ በድብቅ አደሩ፡፡ ጉዞዉ በሚስጥር በመሆኑ፣ ከዉሽዉሽ ሌላ የቀረዉን የካፋንም ሆነ የጅማን አካባቢ ሳይጎበኙ ተመልሰዋል፡፡ አድረዉም ማሣዉንና ፋብሪካዉን መጎብኝታቸዉ የተረጋገጠ ነዉ፡፡ ከዚህ ጉብኝት በሁዋላ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ዉሽዉሽ ለዓል-ዓሙዲን ተሸጠ ተብሎ ተወራ፡፡ በዚያ ሰሞን ሌሎች ኢንቨስተሮች እርሻዉንና ፋብሪካዉን ጎብኝተዉ ለግዥ እየተዘጋጁ፣ ዶክመንትም እያዘጋጁ ነበር፡፡ ሽያጩም መንግሥት ያሰማራዉ ገማች ከገመተዉ ዋጋ በጣም ባነስ መሆኑን ብዙዎች ያወሳሉ፡፡ ይህ በአቶ መለስ የቅርብ ክትትል፣ ትዕዛዝና፣ በዝቅተኛ ገንዘብ የተወረሰ የሃገር ሃብት፣ የዓል ዓሙዲን ነዉ ነዉ እየተባለ በአካባቢዉና በማዕከል በተሰማሩ ተላላኪዎቻቸዉ አማካይነት ቢወራም፣ ብዙዎች ግን ልማቱን የዘረፈዉ፣ ኢፈርት፣ ትልማ ወይም የአቶ መለስ ቤተሰብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ተከታትሎ የደረሰዉ ብዙ ስለሆነ መንግሥት ከፈለገ ያጣራዉ፡፡

2. ከዚያም፣ ሰራተኞቹ ከለመዱት ዉጭ በደልና ግፍ ሲበረታባቸዉ፣ እንደተወራላቸዉ “ባለቤቱ ሼህ ዓልዓሙዲን”፣ ከሆኑ ያስተካክላሉ ብለዉ፤ ራሳቸዉ ቀርበዉ የሰራተኛዉን ችግር እንዲሰሙና፣ መፍትሄ እንዲሰጡ ጠይቁ፡፡ ሼኩ ግን የዚህ ልማት ጉዳይ እንደማይመለከታቸዉ አረጋግጠዉ ችግራችሁን ፍቱ አሉ፡፡ ዉስጡን የሚያወቁና የታዘዙ ተላላኪዎችና ምስለኔዎችም፣ የሰራተኛዉን ጥያቄ በዉይይትም፣ በሃይልም አረገቡት፡፡

3. ወሬዉ መብዛቱና የወቅቱ ሁኔታ ያበረታታዉየዉሽዉሽ ህዝብ ደግሞ ሰሞኑን በአደባባይ በሰልፍ ወጥቶ፣ “ይህንን የሃገር ሃብት ህዝቡ ወይም መንግሥት ሊጠቀምበት ይገባል፣ አሁን ግን የወያኔ መፈንጫ ሆኗል፣ በሰራተኛዉም ላይ ግፉ በዝቷል፣ ለአካባቢያችንም ምንም አልጠቀመም” በማለት ድምፁን አሰምቷል፡፡ ይህመ በተለመደዉ የተላላኪዎች ቡድን አማካይነት ረገበ፤ ግን መቼ ይረሳል፣ ማንስ ያምናል ?

4. አሁንም የልማቱ ይዞታ ወደ ገበሬዉ ድንበር ሲጠጋ፤ በተላላኪዎቹ ካድሬዎች በኩል፣ የአካባቢዉ ገበሬዎች ሻይ አልምተዉ ለፋብሪካዉ ቢሸጡ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኙ ተቀስቅሰዉ፣ ያላቸዉን ቡናና ሌላም ማሳ በሻይ ቅጠል ተኩት፡፡ ሆኖም ገበሬዎቹ ከዚሁ ፋብሪካ ዉጭ ለማንም እንደማይሸጡ ስለሚታወቅ፣ ምርታቸዉን ለፋብሪካዉ ነፃ በሚባል ገንዘብ እያስረከቡ ነዉ፣ እናም ሌላ ቁስልና ቂም፡፡

5. ከዚህ ሌላ፣ ለሼክ ዓል ዓሙዲን ተሸጠ ተብሎ ከተሚወራላቸዉ ሃብቶች አንዱ፣ እዉነቱ ግን ብዙዎች ቀድሞዉንም ያልተቀበሉት እርሻ፣ የጎጀብ የፍራፍሬ እርሻ እንዲህ ሆነ፡፡ የአካባቢዉ ወጣቶች፣ ምናልባትም የሰሙትን ሁሉ ስለሚያምኑና፣ በርግጥም መሬቱን በተሻለ ሁኔታ እናለማለን ብለዉ ተቆጣጥሩት፡፡ በወቅቱም ባለቤት ተብሎ ለመደራደር እንዲሁም ያለዉን ንብረት ለማንሳት ጊዜ ለመጠየቅ የቀረበዉ ግን ሼክ ዓል ዓሙዲን ወይም ተወካያቸዉ ሳይሆን፣ ሌላ ያልተጠበቀ አካል ነበር፡፡

ለማጠቃለል፤ መቼም ህዝባችን ብዙ ጊዜ ስለተሰረቀ ማንንም ቢጠራጠር አይፈረድበትም፡፡ ግን ደግሞ ከሚወራዉ ስንነሳ፣ የመረጃችንን ዉሸትነት ከማረጋገጥ ይልቅ፣ ይህንንና እንደህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች በጥልቅ ጥናትና፣ ማስረጃ ማስደገፍና በህግ ፊት ተቀባይ ማድረግ አድካሚ ነዉ፡፡ለዚህም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች ግን መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ፣ በራሱና አቅም ያለዉን ዓለም-አቀፍ ተቋም በማሳተፍ ጭምር ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ የለዉጥ ሂደቱ ተጠናክሮ፣ ተጠያቂነት ሲጎለብት፣ እነዚህና የመሰሉ ብዙ ነገሮች ቢጣሩ የተዘረፈዉ ሃብት ጉዳይ ሁሉ ግልፅ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ለማንኛዉም ተመሳሳይ ፍንጮች እንደሚያሳዩት፣ የጉማሮ ሻይ ልማት፣ የበበቃ፣ የቴፒና የሊሙ የቡና እርሻዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተወረሱ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ስለዚህ የሼኩ ጉዳይ ይቆየን፡፡
ለማንኛዉም ቢሆን እንኳን ሼኩ ልማቱን ለወ/ሮ አዜብ እንዲያወርሱ የተመኘሽዉ፣ ቀድሞዉንም ታይቶሽ ሊሆን ስለሚችል ብዙም አልተሳሳትሽም፡፡
ከG.C
ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Advertisements
Leave a comment

በአዲስ አበባ ዙርያ ስለተከሰተዉ የሕይወት መጥፋትና የህዝብ መፈናቀል አስመልክቶ ከደቡብ ምዕራብ ኢትህዮጵያ ሕዝብ ህብረት የተሰጠ መግለጫ


በአዲስ አበባ ዙርያ ስለተከሰተዉ የሕይወት መጥፋትና የህዝብ መፈናቀል አስመልክቶ ከደቡብ ምዕራብ ኢትህዮጵያ ሕዝብ ህብረት የተሰጠ መግለጫ

በቅርቡ ከክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትና በሃገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ በሃገራችን ኢትዮጵያ የመጣው የለውጥ ተስፋ በህዝባችን ላይ የፈጠረው ታላቅ የመብት፣የነፃነት፣የደህንነትና የዴሞክራሲ ተስፋ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ካሳዩት የድጋፍ መግለጫዎችና አቀባበሎች ለማየት ተችሏል።የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረትም ከጠቅላይ ሚንስተራችን ጎን በመሆን ሁለንታናዊ ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳቱን በተለያዮ አጋጣሚዎችና መድረኮች አረጋግጧል።

የለዉጡ ሂደት በይቅርታና በፍቅር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ላለፉት 28 አመታት በስልጣን ላይ የነበረዉ መንግስት ሲያራምድ ከነበረዉ የዘርና፣ የብሔር ተኮር ከፋፋይ የፖለቲካ አካሄድ አንጻር ህዝባችን በሚያስደንቅ ሁኔታ ኢትዮጵያውነቱን የሚፈልግ፣ በፍትህ፣ ሰላምና፣ በዴሞክራሲ መተዳደር የሚሻ መሆኑን በመግለፅ እጅግ የተቀራረበበት ጊዜ ነው። ሆኖም በለዉጡ ጥቅማቸዉ የተነካባቸዉ ግለሰቦችና ቡድኖች አንዲሁም አክራሪ ብሄርተኞችና በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት ለዉጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እኩይ ሴራዎችን በመፈፀም በወገኖቻችን ህይወትና ንብራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በቅርቡ በጅጅጋ፣ በሻሸመኔ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሻካ ዞን በቴፒ ዙርያ የተካሄዱትን ጥቃቶች መጥቀስ ይቻላል።

አነዚህ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ከመነሳታቸዉም በላይ በመንግስት በኩል ሲሰጡ የነበሩ ምላሾች እጅግ የዘገዩና ህዝቡ በፈለገዉ ሰዓት መድረስ ያልቻሉ ናቸዉ። ተመሳሳይ ጥቃቶች አንዳይደገሙ ለመግታት የታሰበና እየተወሰደ ያለ በቂና አስተማማኝ እርምጃ አይታይም። ጅጅጋ እንደነበረዉ ጥቃት፣ ይሄንን የአዲስ አበባ ዙርያ ጥቃት አስደንጋጭ የምያደርገዉ አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ በተለይ በአብዛኛዉ ከደቡብ ኢትዮጵያ በመጡ ዜጎቻችን ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው። ሁላችንም የአንድ ዜጋ ጉዳትና ሞት የሁላችንም መሆኑን ተገንዝበን ልናወግዘውና እንዲህ አይነቱን አሰቃቂ ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድራችን ለማስቆም በአንድነት መነሳት ይኖርብናል።

በዚህ አጋጣሚ በተለያዮ የአገራችን አካባቢዎችና እንዲሁም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድርጊቱን በመኮነን ለተጎዱ ወገኖቻችን አጋርነት ማሳየታቸውን እያመሰገንን አብሮነታችን በዚሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ በተለያዩ ሀገሮች በመዘዋወር በእስር ቤት የቆዩትን አትዮጵያውያንን በማስፈታት የዜጋ ህይወት ዋጋ ያለዉና በገንዘብ ከሚገመት ሀብት የላቀ መሆኑን አሳይተዉናል። በዚህ መንፈስ፣ አሁን ለጊዜዉ ሁሉ ነገር ቆሞ የሀገራችን የጸጥታ ሁኔታ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠዉ ድርጅታችን አጥብቆ ያሳስባል። ህዝባችን የደህንነት ዋስትና ሳይኖረዉ የምንገነባዉ ወይም ልንገነባ የምናስበዉ ሥርዓት ያለመሠረት አንደተገነባ ቤት በአጭር እድሜ የሚፈርስ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

የአንድ ሀገር መንግስት ግንባር ቀደምት ኅላፊነቶች የሀገሪቱን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስከበርና፣ የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ናቸዉ። ስለዚህ በአስቸኳይ የኢትዮጵያ መንግስት በህዝባችን ላይ ጥቃት ባካሄዱና ተመሳሳይ ጥቃት ሊያካሄዱ በሚችሉት ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ፣ ለሕዝቡ ደህንነት ዋስትና መስጠት የሚችል መንግስት መሆኑን አድያረጋግጥ አጥብቀን አንጠይቃለን።

የደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ሕዝብ ህብረት

Leave a comment

ኑ የጋራ ቤታችንን በደቦ አብረን እንስራ!!


ኑ የጋራ ቤታችንን በደቦ አብረን እንስራ!!!

 

ሰሞኑን ውድና ብርቅየ ከሆኑ የደምኢሕህ ኣባላት መካከል ኣንዱ የሆነው ኣቶ ኣማኑኢል ካርሎ በተደጋጋሚ Kaffamedia ድህረ ገፅ ላይ ጠቃሚ ሀሳቦችና ኣስተያየት ዘርዘር ባለ መልኩ ሲያቀርብ ተመልክቻለሁ::

 

ሌሎችም ኣቶ ብርሁኑ ወ/ስንበት ኣቶ ተስፋየ ወ/ሚካኢል ኣቶ ጎዲ ባይከዳና ኣቶ ያሮን ቆጭቶ በተለያየ ወቅት ገንቢ ኣነቃቂና ኣስተማሪ የሆኑ ጽሑፎችን በማሰራጨት መረጃዎችን በማካፈል ባጠቃላይ የህዝቡን ብሶት በማሰማት ታግለው በማታገል ላይ ይገኛሉ::

 

በመቀጠል ተጨባጭ የሆነ ኣስተዋፅዖ በማድረግ ያለ የሌለ ጊዜኣቸውን ገንዘባቸውን ጉልበታቸውና እውቀታቸውን በነፃ በመለገስ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሰንቀው ለተነሱበት ዓላማና ራዕይ ከሩቅ ሆነው የወገናቸውን የልብ ትርታ በማዳመጥ ብሶቱ ጭቆናውና በድህነት ኣሮንቋ ውስጥ ተዘፍቆ የፍትህ ያለ እያለ ሲጮህ ሰሚና ተቆርቋሪ ሆነው የትግሉ ኣጋር በመሆን ለሚመለከተው ክፍል ጥያቄዎቻቸው ቢያቀርቡም ተቀባይነት ባለማግኘታቸውና ይባስ ብሎ የሥርኣቱ ተገዥ በሆኑ ካድሬዎችና ለሆዳቸው ባደሩ ባንዳዎች በደረሰባቸው ወከባ ከሚወዱትና ከሚቆረቆሩለት ህዝብ ተለይተው በውጭ ሀገር ተሰደው መታገልን እንደኣማራጭ ወስደው እነሆ በኣይነቱ የመጀሙሪያ የሆነ ድርጅት “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት (ደምኢሕህ)” መሥርተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ::

 

ውድ ወገኖቼ

እኔ በግሌ ለነዚህ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የማይሞከረውን የጭቆና ቀንበር ከወገናቸው ጫንቃ ላይ ለኣንዴና ለመጨረሻ ከሥሩ መንግለው ለመጣል ፈር ቀዳጅ የሆኑ ውድና ብርቅየ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ኣብራክ የተገኙ የቁርጥ ቀን ልጆች ላዱረጉትና በማድረግ ላይ ላሉት ኣስተዋፅዖ ከፍ ያለ ምሥጋና ሳቀርብላቸው ከታላቅ ኣክብሮት ጋር ሲሆን ብዙዎቻችሁ ሀሳቤን ትጋሩኛላችሁ የሚል እምነት ኣለኝ::

 

በነገራችን ላይ እነዚህ ግለሰቦች ይህን ድርጅት ሲመሰርቱ ኣንዳንዶቻችሁ እንደምታስቡን የግል ጥቅምና ዝና ወይም ሹመትና ሥልጣን ናፋቂ ሆነው ሳይሆን ወገናቸው ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ጭቆናና እንግልት በገዛ ምድሩ ላይ ሰርቶ እንዳይኖር ኢኮኖሚያዊና ሳይኮሎጂካዊ ተፅእኖ ታውጆበት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት መሰል እህትና ወንድሞቹ በእኩል ኣይን ሳይታይ በሀገሩ ላይ ሰርቶ የመኖር የመማር የመበልፀግና የማደግ መብቱ ተገፎ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኃላ እየተራመደ ከማጡ ወደ ድጡ እየወረደ መቶ ኣመት ሆንው:: ዛሬም የለውጡን ችቦ ለማቀጣጠል ጥረት ቢያደርግም ከመንግሥት በኩል ለሌሎች እየተደረገ ያለው ድጋፍና ማበረታታት ሲደረግለት ኣይታይም (ምክንያቱ ግልፅ ባይሆንም):: ዛሬም ከቀየው እየተፈናቀለ መሬቱ ለሌሎች ይታደላል:: ኣያት ቅድመ ኣያቶቹ ከወራሪወቹ ጋር ተፋልመው ኣልበገር ብለው መስዋዕት የከፈሉበት ዳር ድንበሩ ተደፍሮ ከማንኛውም መሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን የትምህርትና የእውቀት እድል ተነፍጎት ወደ ፊት እንዳይሄድ መብቱን እንዳያስከብርና ጥያቄ እንዳይጠይቅ ኣፉን ተሸብቦ ገዚው መደብ የራሱ ልጆች መልሰው እንዲወጉት በጥቅማ ጥቅሞች በመደለል የራሳቸውን ህልውና ሸጠው ህዝቡ በማንነቱ እንዳይተማመን የበይ ተመልካች ሆኖ ተነሳ ሲሉት የሚነሳ ተቀመጥ ሲሉት የሚቀመጥ ተንቀሳቃሽ ፍጡር /robot እንዲሆንላቸው ተደርጓል:: ምሁሩም እዳር መቆምን የመረጠ ይመስላል::

 

ይህ ነው ደምኢሕህ እንዲያቋቁሙ የገፋፋቸው እንጂ እነሱማ ዴሞክራሲ የሰፈነበት እንኳን የሰው የእንስሳት መብት የተከበረበት ከየትኛውም ዓለም ይምጣ በህጋዊ መንገድ እስከ ገባ ድረስ የዘር የፆታ የቀለምና የሀይማኖት ልዩነት ሳይደረግበት በእውቀቱና በኣቅሙ በየትኛውም ቦታ በነፃነት ተዘዋዉሮ ሠርቶ የሚኖርበት ዓለም ውስጥ ናችው ምንም የጎደለባቸው ነገር የለም:: የሚታገሉትም ይህን መሰል ሥርዓት ወደ ህዝባቸው ለማስረፅ ነውና ከጎናቸው በመቆም ላልሰማ እናሰማ ላላወቀ እናሳውቅ እላለሁ::

 

በዚህ ኣጋጣሚ ማንኛውም የድርጅቱን ኣላማ የሚደግፍ የለውጥ ኣራማጅም ሆነ ኢሃድግን ሲደግፉ የኖሩ ወገኖቻችን ድርጅቱ የህዝባችን ድምፅ ስለሆነ ምንም እንኳን ላለፉት 27 ዓመታት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በፍላጎትም ሆኑ ተገዳችሁ ከህዝብ ጎን ሳይሆን ከተቃራኒ ጎራ የነበራችሁ ዘመኑ የፍቅርና የይቅርታ ስለሆነ ፊታችሁን ወደ ወገኖቻችሁ ጊዜው ሳይመሽ መልሱና የበደላችሁትን ህዝብ ካሱ “ኑ የጋራ ቤታችንን በደቦ ኣብረን እንስራ”:: እንረዳዳ ኣንድ ሆነን ኣብረን እንቁም መለያየት ኣይበጀንምና በኣንድ እጅ የሚያጨበጭብ ሰሚ የለውም እንወያይ እንመካከር ልዩነትን እናጥብብ ከሌሎች እንማር “ትግራይ ኦነግን ማስተናገድ? የኦነግም መስተናገድ መቻቻልን ያሳየናል እያለ ጅርጅታችሁ በሩን ክፍት ኣድርጎ ይጠብቃችኃል “ኣይጥና ድመት ተስማምተው በጋራ ሲገባበዙ እኛ ኣንድ ህዝቦች ስንሆን መናቆር ምን ኣስፈለገ? በተለይ ምሁራኖች እባካችሁ ወደ ኣንድነት ኑ ጎራ ለይታችሁ የጎሪጥ መተያየት ከናንተ ኣይጠበቅምና::

 

ድርጅቱን የጀርባ ኣጥንት በመሆን በሀሳብ በሞራል በገንዘብ በጉልበትና እንዲሁም ከካፋ ሚዲያ በተጨማሪ መረጃ በማስተላለፍ እየረዱ ያሉ ሁለት ብርቅየ ወጣቶች መካከል::

 

1ኛ/ ህዝቡን ለረጅም ኣመታት በሶሻል ሚድያና በራሱ የተለያየ ድህረ ገፅ ከፍቶ በማንቃትና በማደራጀት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የሚገኘውን ወጣት ቁምላቸው ኣምቦ

 

2ኛ/ የተጠየቀውን ብቻ ሳይሆን ያልተጠየቀውን ጭምር ድጋፍ በመስጠት በማንኛውም ጊዜ ከድርጅቱ ጎን የቆመ ዋልታና ምሱሶ የሆነውንና ኣደባባይ ቆሞ በቪድዮ ለቴፒ ህዝብ ጉዳይ ድምፅ ያሰማ ብቸኛው ኣክቲቪስት ወንድወሰን ግዛው

 

እነኚህ ሁለት ወጣቶች በግሌ ኣመሰግናቸዋለሁ ኣከብራቸዋለሁ:: ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል እላለሁ::

 

በመጨረሻ ሀሳቤን ለማጠቃለል በሶሻል ሚዲያው ላይ ኣንዳንድ ወጣቶች ኣላስፈላጊ ቋንቋዎችን በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት ሲጠቁሙ ይታያሉ:: ይህ በጣም ኣስፀያፊና ኣሳፋሪ ስለሆነ እባካችሁ ሃሳብን በሀሳብ ሞግቱ እንጂ ፀያፍ ቃላት ስትለዋወጡ ያስገምታችኃልና ታቀቡ:: ተጠቃሚዎቹ ትንሽም ቢሆን ፊደል የቆጠራችሁ ናችሁና::

 

ዛሬ ኣንድ መፅሐፍ ላይ ያነበብኩትን ላካፍላችሁና ሁሳቤን ልቋጭ

“He who does not have the courage to speak up for his rights cannot earn the respect of others” Rene G. Torres

 

የደቡብ ምዕራብ ህዝብ ያልተሰማው ቀደም ብሎ እንደ ቄሮና ፋኖ ድምፁን በድፍረት ኣደባባይ ወጥቶ ባለማሰማቱ ይመስላል:: ዝምተኛን ልጅ እናቱ ትረሳዋለች ይባል የለ!!!!

 

ዝም ኣንበል ለመብታችን በጋራ እንታገል!!!

ቸር ይግጠሙን!!!! Share በማድረግ ተባበሩ::

ከፋንታዬ መኮ

ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a comment

የቡና ቀን International Coffee Day


የቡና ቀን

International Coffee Day to be Celebrated in Ethiopia, the Land of Origin of Coffee, For The First Time in November 2018 Under The theme “Taste the Finest Coffee in the Land of Origins”.
Ethiopia is the land of origin of coffee and has the most diverse and highly sought after premium coffee in the world. The celebration will ​bring together coffee producers, roasters, exporters, researchers, writers and coffee lovers from all over the
world​ and will include an ​exhibition​, a ​conference​ and ​a coffee tour to Kaffa​, ​the region where coffee first originated and spread
to the world.​ To this end, Ethiopian Holidays has prepared special coffee tour packages for participants in the International Coffee Day Celebration.

እጅግ አስደናቂ ዜና ነው.ይህን የመሰለ ትልቅ አጋጣሚና ዕድል ልያመልጠን ጨሪሶ አይገባም። ግዜዉ አጭር ስለሆነ አስቸክዋይ መረባረብ ይደረግበት። ዝግጅቱን በተመለከተ አዲስ አበባ ላይ ዝግጅት ተደርጎ የነበረዉ ሐምሌ ዉስጥ ነበር። ለክልሉና ለዞኑ መንግስት አንዲዘጋጁ ተብሎ የተላለፈ መልክት አንዳለ አላውቅም። በኔ በኩል ባጋጣሚም ቢሆን ይህ መረጃ ደርሶናልና ተረባርበን አንዘጋጅ።
በምን መልኩ አንዘጋጅ በማለት ሳስብ ቆይቼ፣ የራሴን አስተያየት አንደምከተለዉ አቅርቤአለሁና አባካችሁ በጎደለዉ ሞልታችሁ በትልቁ ባለበትነታችንን ለዓለም አናሳዉቅ።

1። ስለዚህ ሰዓሊዎችና ገጣሚዎቻችን ግዜአቸውን ሰውተው ይሳሉ, ይግጠሙ። በስዕልና በግጥም ቡናና ባህላችንን ይቅረፁ።

2። የሙዚቃ ባለሙያዎቻችንም አስካሁን ካሉት ዘፈኖች መርጠዉ፣ አዳዲስ ዜማዎችን ጽፈዉ የቡናን ቀን ለማክበር አዲስ አበባ ለሚሰባሰቡት አንግዶችና ወደካፋ ለጉብግንት ለሚመጡት በማቅረብ ዝግጅቱን ያድምቁ። ይህ ሁሉ በጀት ስለሚጠይቅ የዞኑ መንግስት ከማዕከላዊና ከክልሉ መንግስት በኩል ያለዉን በጀት ተረባርቦ በማምጣት የስራ። በተጨማሪ ሁላችንም አጃችንን ዘርግተን መዋጮ በማዋጣት ዝግጅቱን በምያስፈልገዉ ሁሉ መደገፍ ወሳኝ ነዉ።

3። የታወቁ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች በአካባቢዉ ካሉን አኒmቀማቸዉ፣ ከሌሉ ከሌላ ቦታ ተከራይተን፣፣
ሀ)፣ የቡና ተክልን በተለያየ መልኩ፣ የተፈጥሮ የቻቃ ቡናን፣ የጔሮ ቡና ከቆንጆ የገጠር ጎጆ ቤት ጋር። ፍሬ
የተሸከሙ የተለያዩ የቡና ተክሎች ፎቶግራፍ ተነስተዉ በፖስተር ይዘጋጁ።

ለ)፣ ማክራን, ጉርጉቶን, በዩነስኮ የተመዘገበውን ደናችንንና ሌሎችም ታዋቂ የተፈጥሮ ቅርሶቻችንን የተለያዩ
ፎቶግራፎች ተነስተው በትላልቅ ፖስተሮች ታትመው ይዘጋጁና በኤግዝብሽኑ አዳራሽ ይሰቀሉ።

ሐ)፣ ቡና ስሙን ያገኘበት በኩራት የምንጠራው ስማችን KAFFA ና MAKIRA backgroundኡ ምርጥ
ፎቶግራፍ በያዘ ፣ በትልቅ ፖስተር ላይ ይታተሙ።

መ)፣ ትክክለኛዉን የቡናን ታርክ የያዙትን በ 13ኛ ክፍለ ዘመን የነበሩትን የካፋ ነገስታት የእኔ ንጉሥ አቦል
ታርክ የሚያያሳዩ ጽሑፎችም አርቲስትክ በሆነ መልኩ በእንግልዝኛና በአማርኛ ተጽፈዉ በትላልቅ ፖስተሮች ተለትፈዉ ጎብኝዎች ያንብቡ። ጎብኚዎቹ በቅድምያ የሚጎርፉት ወደ አኛ ወደ Land of Orgin or “The Actual Land of Origin” exihibit ስለሆነ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት አለብን።

ሠ)፣ ፍረሽ በዕለቱ የተለቀመ ምርጥ አረን􏰀ዴ፣ ብጫና, ቀይ የቡና ፍሬዎች በ3 የተለያዩ ሰፌዶች ተዘጋጅተዉ በኤግዝብሽኑ ይቀመጡ፣

ሸ)፣ ከባህላዊ እቃዎቻችንም ከባህል ሙዜማችን ተዉሰን በጥንቃቄ ይዘን በአግዝብሽኑ ላይ ባህላችንን እናስተዋዉቅ።

ቀ)፣ የንጉስ ጋክ ሻሮቺ ፎቶግራ በሰፊዉ ጥሩ የስዕል ችሎታ ባላቸዉ ሰዓልያን በሰፊዉ ተስሎ ወይም ጥራት ያለዉ original photo ከተገኘ በስፋት ተሰርቶ በትልቅ ፍሬም በኤግዝብሽኑ ይሰቀል። ከጎኑም “መለያየት ሞት” ነዉ በሚል ርዕስ በደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ከተጻፈዉ ላይ ስለ ጋኪ ሻሮቺ የተጻፈዉ የእንግልዝ ጦር ከአፄ ምኒልክ ጋር ስላለዉ ጦርነት አንርዳ ስሏችዉ ጋክ ሻሮቺ የተናገሩት አጠቅሰዋለሁ “ ተጽፎ ይቀመጥ።

በዚህ መልኩ የቡና ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር በኤግዝብሽኑ ላይ ትልቅ የማሳያ ቦታ ይዘን በሰፊው በመገኘት አስደናቂ ኤግዝብሽን አናሳይ።በሰፊዉ በሰአልያን ተስሎ ወይም ጥራት ያለዉ enlarge ቢደረግ ጥራቱን የማይለቅ ፎቶ ከተገኘ ከዚህ ጋር የተያያዘ conference ስላለ በ universityና በተለያየ መስሪያ ቤት የምትሰሩ የካፋና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኙ ምሁራን በአጠቃላይ በconference ላይ ለመሳተፍ አሁኑኑ አፋልጋቺሁና መረጃ ፈልጋችሁ አዘጋጆች ጋር ሄዳችሁም ቢሆን ካሁኑ ተመዝገቡ። ከቆያችሁ ቁጥሩ ሊሞላ ይችላልና ፍጠኑ። ስብሰባዉ ባለቤቶች ያልተገኙበት ቢሆን ስድብ ነዉ የሚሆነዉ። ተገኝታችሁም ትክክለኛዉን የቡና ታሪካችንን አስተምሩ።

እንግድህ በደንብ ተዘጋጅተን ሆቴሎች ገንብተን፣ የአይሮፕላን ማረፍያም አሰርተን በሰፊው ከደጃችን በየግዜው ጉብኚዎችን እስክንጋብዝ ድረስ ለInternational Coffee Day ለሚመጡት እንግዶች በሚናዘጋጀው ኤግዝቪሽን ማንነታችንን አስተምረን በጉጉት መጥተው የቡናን ምድር ካፋን እንዲጉበኙ እናድርግ:: የቡና ሙዝዬማችንንም በዚህ አይነቱ ትልቅ ዕድል ለማሳተፍና ጎብኚዎችን አርክቶ ለመሸኘት የጎደሉ እቃዎች ተሟልተው ዙሪያው በሚገባ ፀድቶ ደረጃውን ጠብቆ ይዘጋጅ፣ ሙዝየሙ ይህንን ለማድረግ ለካስ በጀት ያስፈልገዋል። ይህንን እድል ተጠቅመን በአስቸኳይ በባህል ሚኒስቴር መዋቅር ገብቶ በጀት እንዲመደብለት እናድርግ። የሚናስተናግደው የሀገሪቱን እንግዶች ስለሆነ በጀት መመደቡ ግዴታ ስለሚሆን ካሁን ስራችንን እንጀምር። አሁንም የዞኑ አስተዳደርና የባህል መምሪያዉ ሚና አዚህ ላይ አጅግ ዎሳኝ ነው።

በአስቸክዋይ ሰርተን ይህችን የባህል ሚኒስቴር ምክንያት አንድፈጥር የማትመቸዉን አድል አንጠቀም።
ከዞኑ መንግስት ጋር ምክክር ተደርጎ ካሁኑ ስራና ዕቅድ ይጀመር. ይህ በህልማችን ብቻ ስናልም የነበረውን ዕድል ፈጣሪ እውን ልያደርግልን ነውና እኒረባረብ። እንደዚህ አይነቱ ፕሮግራም ሲዘጋጅ ለዝግጅቱ መንግስት የሚመድበው ከፍተኛ በጀት ይኖራል። የጉብኚዎቹ መድረሻ ተብሎ የተጠቀሰው Land of Origin፣ Kaffa ስለሆነ. ከባጀቱ የጉብኝት ቦታዎችን ማዘጋጃ የሚሆን ድርሻ ልኖር ግድ ይላል። ይህንን በጀት የዞኑ መንግስት አደራ በግዜ ተከታትሎ ያስገባና እንግዶቹ World Class የሆነ ጉብኝት እድርገው እንዲመለሱና ለወደፊት ሌሎችን እንዲልኩልን እናድርግ። የመጀመሪያ ጉርሻ ካልጣፈጠ አፒታይት ይዘጋልና የመጀመሪያ የጉብኝት ልምዳቸው ድንቅ ይሁን።

ይህ ዜና ዛሬ እንቅልፍ የሚነሳ ደስታ ነው የሆነልኝ። የካፋ ትንሳኤ, የቦንጋ ትንሳኤ እልፎም የደቡብ ምእራብ እትዮጵያና የኢትዮጵያችን ትንሳኤ እውን የሚሆንበት ግዜ ቅርብ ነው::

የጉብኝት ቦታዎችን ካዘጋጀን፣ መንገድና መገናኛ ከተስራ፣ ቦንጋ/ማኪራ የመጣ የውጭ ጎብኚ፣ ሚዛንና ማጂን፣ ሻካ/ቴፒ/ማሻ ደርሶ ድንቅ ተፈጥሯችንን ሳይጎበኝ አይመለስምና ጠቅላላ የደቡብ ምዕራብ ህዝብ በዚህ በዓል ከፍተኛ ተሳትፎ አናድርግ።
ስማችንን መጥራት በሚፈልጉት ሆነ በማይፈልጉት መጠራት የሚጀመርበት ግዜ ቅርብ ነው.
አንግድህ የህዝባችን መብት አያልን የምንጮሄዉ አንደዚህ አየነቶቹ የህዝባችን የባለቤትነት መብቶች ይጠበቁ ብለን ነዉ። አሁን አድሉ ሲደርስ አደራ ዎደሁላ አናፈግፍግ። ተረባርበን ይህንን አድል ተጠቅመን ባለበትነታችንን ብቻ ሳይሆን ከባለቤትነት ጋር አብሮ የሚመጣዉን ኃላፊነትም ጭምር መወጣት አንደምንችል አናሳይ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ከንቀት ክልል ወጥቶ የራሱ ክፍለሀገር ይኑረው.
​”አሁን የሚካሄደው ጦርነት የወንድማማቾች
ጦርነት ነውና የእናንተ እርዳታ አያስፈልገኝም። እኔ ምኒልክን ካሸነፍኩ አገሩን በሙሉ አስተዳድራለሁ፤እሱ ካሸነፈኝ አገሩን በሙሉ ይግዛ። እርዳታ የምጠይቃችሁ የውጭ ጠላት ሲመጣብኝ ብቻ ነው።” ምንጭ፦ መለያየት ሞት ነው በአለማየሁ ገላጋይ ገጽ ፪፫ ኑና ተጋግዘን የሁላችንን ቤት እንገንባ!

የትውልድ አካባቢያችን ካፋና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንድሁም ውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘለአለም ይኑሩ.
ከአማኑኤል ካርሎ ጋኖ
ካፍ ሚዲያ Kaffamedia

Leave a comment

ከራሳችን ላይ ውረዱ


ከራሳችን ላይ ውረዱ

የሰው ልጅ የሚዉለድበትና የሚሞትበትን ቦታ ቀንና ዘመን ከማን መወለድ እንደሚፈልግ መምረጥ ኣይችልም:: የመምረጥ እድሉ ቢሰጠን ብዙዎቻችን ከሃብታም ቤተሰብ ብንፈጠር ከታዋቂ ቤተሰብ ብንወለድ እንመርጥ ነበር ከራሴ ጀምሮ:: የሰው ልጅ መኖሪያውን መምረጥ ይችላል:: በህይወት ዘመኑም ምን መሥራት እንደሚፈልግ ምን ኣይነት የህይወት ጏደኛ መያዝ እንዳለበት በትምህርትም ምን መማርና ማን መሆን እንደሚችል ቢሳካም ባይሳካም በራሱ ምርጫ መሄድ ይችላል:: መምረጥ የማይችለው ዘሩን ቀለሙንና ፆታውን ሀገሩን የትውልድ ቦታውን ነፃነቱን ሲሆን የሚታደለው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው::

እኛ በተለያየ የዛሬይቱ የኢትዮጵያ ምድር ላይ ስንፈጠር በኛ ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ምንም እንኳን ሁላችንም የኣዳምና ሔዋን ልጆች ብንሆንም ኣሁንም ደም ሥጋና ኣጥንታችን ኣንድ ነው:: ይህም የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ ሊደነቅ ይገባል:: በሂደት በተፈጠረው የነገድ ክፍፍል ኣፍሪካ እሲያ ኣውሮፖና ኣሜሪካ እንዲሁም በተለያየ የዓለም ክፍል ተሰራጭተን በመኖር ላይ እንገኛለን:: ቀለማችን ባህላችንና ወጋችን ቋንቋችን ኣለባበሳችንና ኣመጋገባችንም ተመሳሳይነትና ልዩነት ኣለው::

ባይገርማችሁ ያኔ ድሮ በልጅነቴ የፈረንጅ ፎቶ በወረቀት ላይ ሳይ ፈረንጅ ሰው ሳይሆን መልኣክ ይመስለኝ ነበር:: እህል የሚበላ ውሀ የሚጠጣ የሚታመም ወይም የሚሞት ኣይመስለኝም ነበር እንደማንኛውም ሰው:: እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቻችን የእኔ ኣይነት እይታ ዛሬም ድረስ እንዳላችሁ እገነዘባለሁ:: ፈረንጅ ሁሉን የሚያውቅና ቆዳው ስለነጣ ብቻ ከኛ የተሻለ የሚመስለን ኣለን:: ለራሳችን ሰው ምን ቢማር ያን ያህል እውቅናና ኣክብሮት መስጠት የተለመደ ኣይደለም:: የራሳችንን ማጣጣል የውጭውን ማንገስ እንወዳለን::

በርግጥ ፈረንጅ በኣንዳንድ ነገሮች ይበልጠናል:: ኣንዱ ሲሰራ ለመልካም ስራው እውቅና ሰጥቶ ያበረታታል:: እኛ ኣንዱ የሰራውን እናፈርሳለን እንጂ ጎሽ በርታ ኣንልም:: ፈረንጅ እውቀቱን ያካፍላል እኛ ግን ከኛ በላይ ኣዋቂ እንዲኖር ኣንፈልግም እውቀታችንን ለትውልድ ከማስተላለፍ ይልቅ ይዘን እንቀበራለን:: ለልጆቻችን እንኳን ኣናስተላልፍም:: እኛ ኣንዱ ሲገነባ ሌሎቻችን ከሥር ከሥሩ እየሄድን እናፈርሳለን:: መንግሥታት በተለዋወጠ ቁጥር ህገ መንግሥት እንቀይራለን ለራሳችን ኣገዛዝ በሚያመች መልኩ:: ብቻ ስንገነባ ስናፈርስ እንደ ልጆች እቃ እቃ ጨዋታ ስንጫወት ፈረንጅ ብልጡ በኛ ሥራ እየሳቀ በኣንድም ሆነ በሌላ መልኩ ዘመድ መስሎ ይጠጋንና ጥሬ ሀብታችንን ጠራርጎ በመውስድ ወደ እንዱስትሪ ውጤት ይለውጥና መልሶ ለኛን በውድ ዋጋ ይሸጥልንና ሀገሩን ያሳድጋል:: የደቡብ ምዕራብ ደን ተጨፍጭፎ ኣረብ ሀገር ወይም እስያ ተወስዶ የኢንዱስትሪ ውጤት ወደሀገራችን ቢገባም የካፋ ህዝብ ግን ተጠቃሚ ኣይደለም:: የካፋን ቡና ስታር በክስ (Starbuks) የተባለው ድርጅት በተዘዋዋሪ ከሲዳማው ይርጋጨፌ ኣስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ከሚደረግለት ቡና ላኪ ጅርጅት በኣለም ገበያ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጎ የቡናው ባለቤት ካፋ ግን መንግሥትና ግብረ ኣበሮቹ ባቀነባበሩት ሴራ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ከጨዋታ ውጭ እንዲሆን ተደርጎ የበይ ተመልካች እንዲሆን ተወስኖበት ኣንድ እግር ቡና የሌላት ኤርትራ በኣንድ ወቅት ቡና ኢክስፖርት እንድታደርግ ተደርጏል:: ይህ ህዝብ የደረሰበትና እየደረሰበት ያለው ግፍና በደል ተዘርዝሮ ኣያልቅም:: ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልና::

ሰሞኑን ደግሞ ከወደ ሀገር ቤት የቡና ቀን ተቆርጦ በኢትዮጵያ ኣየር መንገድ ኣስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የቡና ቀን ሊከበር ሽር ጉድ እየተባለ ነው:: በእርግጥ ኣየር መንጉዱ ሰላምታ በተሰኘው መፅሔት ላይ ኣንድ እትሙ ላይ ቡናን ለማስተወወቅ ሞክሯል::ከኣየር መንገዱ ቀድመው የውጭ ፀሐፍት ቡናን ለዓለም ኣስተዋውቀዋል:: ኣየር መንገዱ ግን ለዚህ የቡና መገኛና የኢኮኖሚ ዋልታ ለሆነው ካፋ ለውለታው ለምን ሌላው ቢቀር የሀገር ውስጥ በረራ የኣየር ማረፊያ ኣልሰራለትም ??? ለምንስ የቲኬት መሸጫ ቢሮ ከፍቶ ካፋን ለምን ለጎብኚዎች ኣላስተዋወቀም?? የቡና ሙዝየም ሲሰራ ምን ኣስተዋፅኦ ኣርጏል?? ካልሆነስ ኣሁን የቡና ቀን ብሎ ሽርጉድ ማለቱ ለካፋ ህዝብ የሚያመጣው ምን ፋይዳ ኣለ ወይስ ኣላሙዲንን እግዚአብሔር ቢያላቀን ሌላ ኣላሙዲን ልታመጡብን ይሆን?? ጠርጥር ነው በቅርቡ ዶ/ር ኣቢይ በድብቅ በቃል ኣቀባያቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የህዝብ ማወያየት ሰበብ እሳቸውም የጫካ ቡናውን ኣካባቢ ጎብኝተው ህዝቡን ግን ሳያጉኙት ተመለሱ የሚል ሀሜት ነበር:: እውነቱን እነሱና እግዚአብሔር ያቀዋል ከሆነ ለምን? የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ኣዜብም እንዳይታወቅባቸው በእስልምና ሃይማኖት ልብስ ተከናንባ በሚዛንና በቴፒ ጉብኝት ኣድርገዋል እየተባለ ይታማል:: ይህ ወሬ ከየት እንደመነጨና ለምን እንደተወራም ግልፅ አይደለም:: በዚያው ሰሞን ታዲያ እናንተ ሰዎች እባካችሁ ከህዝቡ ራስ ላይ ውረዱ!!! የቡናውን ቀን እኛ በተመቸን ጊዜ እናዘጋጀዋለንና እጃችሁን ስብስቡ:: መበዝበዝ በቃን ይላል የደቡብ ምዕራብ ህዝብ::

በቱጨማሪ ከኛ የወጡ ፈረንጅ ኣንላቸው የፈረንጅ ሥራ ኣይሰሩ ኣልተማሩም ኣንላችው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፕሮፌሰርነት የደረሱ ወገኖቻችን የወጡበትን ህብረተሰብ ከመርዳት ይልቅ ሥልጣን ሲይዙ ደሀው ገበሬ በማዳበሪያ ዕዳ ማንቁርቱን ተይዞ (በነገራችን ላይ የደቡብ ምዕራብን የመሰለ ለም ምድር ማዳበሪያ ለምን ኣስፈለገው???) ከኣቅሙ በላይ የተጣለበትን ግብር ከፍሎ ነጋዴው የተጣለበት ታክስ ሰማይ ጠቀስ በመሆኑ ሱቁን እስከ መዝጋት ደርሷል:: ራሱ ሳይመገብ ልጆቹን ኣብልቶና ኣልብሶ ኣስተምሮ ሥልጣን ላይ ሲቀመጡ ከባለሥልጣን ጋር በመመሳጠር እከክልኝ ልከክልህ ሆነና ለህዝቡ ብሶትና እሮሮ ጆሮ ዳባ በማለት ዳር ላይ ቆሞ የሚመለከት ብዙ የተማረ ወገን ኣለ:: ለመሆኑ የመማር ጥቅሙ ምንድነው? ኣንዲት እናት እሳቸው ፊደል ኣልቆጠሩም ነገር ግን የሀገራቸው ጉዳይ ያንገበግባቸዋል:: ቶሌቪዥን ላይ ተተክለው ነው የሚውሉት እና ምን ኣሉ መሰላችሁ “እኔ ባለመማሬ በጣም ይቆጨኝ ነበር ኣሁን ግን ባለመማሬ እግዚአብሔርን ኣመሰገንኩት” ኣሉ ለምን ብላቸው ኣሁን እንደማየው ሀገራችንን እየበጠበጡ ያሉት ተማርን የሚሉት ናችው:: ድሮ በሰላም ተስማምተን በፍቅር እንኖር ነበር ዛሬ ግን ኣንዱ ኣንድ ሀሳብ ሲያመጣ ሌላው ይቃወማል::ዘጠና ዘጠኝ ቦታ ተከፋፍሎ እኛንም ግራ ኣጋባን የተማረው ብለው ኣማረሩ:: እውነት ኣላቸው ኣሁንም ኣንዱ ሲገነባ ሌላው እየናደ ከ2010 ወደ 2011 ብንሸጋገርም ኣሁንም በኣዲሱ ዓመት ማግስት በኦነግ ደጋፊዎችና በሌሎች መካከል ኣዲስ ኣበባ ላይ የተነሳው ግጭት ኣባባላቸውን ያጠናክረዋል:: መማር እንዲህ ከሆነ ያለመማር የሚበጀው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: የዱቡብ ምዕራብ ምሁራን እባካችሁ ወዱፊት ኑና ህዝባችሁን ታደጉ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ:; ምነው ሳይንቲስት ኢንጅነር ቅጣው እጅጉን ሞት ባይቀድመው ኖሮ:: ሰው ብቻ ኣይደለም የካፋ ጠላት ሞትም የኛ ጠላት ነው:: ጋኪ ሻሮችን የመሰለ ጀግና ንጉሣችንን ነጠቀን በዛ ብሎ ደግሞ ስንት ራዕይ የሰነቀውን ቅጣውን:: በቃ ተውን እንደመዥግር ተጣብቃችሁ ደማችንን ኣትምጠጡ:: ደማችን ኣልቋል እስቲ ሄድ በሉና ህዝቡን ተመልከቱት:: ሥጋው ኣልቆ በኣጥንቱ የቆመ ህዝብ ነው:: ለቆጮ ምሥጋና ይግባውና ተራብኩ ብሎ ኣደባባይ ወጥቶ ኣለመነም:: በነገራችን ላይ ልመናን የሚጠየፍ ኩሩ ህዝብ ያለው ደቡብ ምዕራብ መሆኑን የምታውቁ ስንቶቻችሁ ትሆኑ??? ይህ ብቻ አይደለም ከጥንት ጀምሮ የራሷ ታሪክ ያላት ሚክርቾ(ምክር ቤት) ጊጄ ራሾ (ገንዘብ ሚ/ር) ካተመራሾ (ከንትባ) ናሌ ጣኦ (ፍ/ቤት) የዋሻ ጉርጉቶ የተፈጥሮ ድልድይ ለምለምና አረንጓዴ ደኑ የቀርቀሀ ሀብቱ የፍል ውሀ እና ወዘተ ያላት ውብ ምድር ነች!!
ከፋንታዬ መኮ
ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a comment

ለምን የካፋ ሕዝብ የራሱ ድርጅት አስፈለገው?


ለምን የካፋ ሕዝብ የራሱ ድርጅት አስፈለገው?

 

ቀደምት አባቶች “የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ” ብለው የተረቱት ያለ ምክንያት አይደለም:: የካፋ ሕዝብ ከምንሊክ ወረራ በሗላ የራሴ የሚለው ተቋም ባለመኖሩ ላለፉት መቶ አመታት ሲዘረፍ ኖሯል:: ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕዝባቸውን ለመታደግ የካፋ የቤንች ማጂ እና የሸካ የቁርጥ ልጃች ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረትን በሰሜን አሜሪካ ከመሰረቱ እነሆ ሦስት ዓመት ተቆጥሯል:: በቅርቡ ወደ ሃገራቸው ገብተው ከሕዝባቸው ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት ያደርጋሉ:: ለሕዝባቸውም እንደ ምሰሶ የሚቆም ታላቅና በሕዝባችን ልብ ውስጥ ለዘላለሙ ፀንቶ ያሚቆየውን ድርጅት ይመሰርታሉ:: ከአሁን በሗላ ሕዝባችን በራሱ ድርጅትና ልጆች እንጂ በማንም ድርጅትና ሞግዚትነት አይመራም::

 

የካፋ: ህዝብ: የአመራር: ጥያቄ::

 

I. ችግሩና ታሪካዊ መሰረቱ፤

 

ካፋ ሃብታምና ለምለም አገር ነበር፡፡ ከዉጭ ዜጎች በስተቀር፣ ብዙ የተከበሩ የታሪክ ምሁራን ጭምር ደፍረዉ መፃፍ ወይም መናገር ያልቻሉት እዉነታ፤ ካፋ አስከ 1900 ዎቹ ምዕት-ዓመታት ድረስ በነበረዉ ዘመን፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ ከተካተቱት አካባቢዎችና፣ ህዝቦች፣ በአንፃራዊነት በሰለጠነ አደረጃጀት፣ የመንግሥት አወቃቀርና አመራር የተደራጀ ነበር፡፡ ሆኖም የካፋ ለም መሬትና ሃብት “እንደሌሎቹ ሃብታም አካባቢዎች ሁሉ የጥቃቱ ምንጭ ሆነ”፡፡ ይህ ሃብት እስከ 1889 ዓ.ም. በተደጋጋሚ ለተደረጉና ካፋ በብቃት ለመከታቸዉ ጦርነቶች፣ ምክንያት እንደሆነ በብዙዎች ተፅፏል፡፡ ምንም እንኳን የተሰነዘሩበትን ተደጋጋሚ ጦርነቶች እስከ 1889 ድረስ፤ በብዙ መስዋዕትነት እና ጀግንነት እየመከተ ህልዉናዉን ጠብቆ ቢቆይም፣ በ1889 ግን ይህ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም፣ በተደጋጋሚ ድል እየሆነ የተመለሰዉ ጦር የተለየ ሁኔታ ላይ ደርሶ፣ጊዜዉም ተለዉጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊዉ ጦር በ1888 ዓ. ም. የአድዋ ጦርነት፣ ከጣሊያን ሰራዊት በርካታ ትጥቅ አፍሶ ነበር፡፡ ለራሳቸዉ ዓላማ ሲሉ የተሰባሰቡ፣ አዉሮፓዊያን የጦር ባለሙያዎች ድጋፍም ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ እነዚህ አዉሮፓዊያን ግን ከዓድዋ ጦርነት በፊት፤ የካፋን ንጉሥ በማማለል ምንሊክን በካፋ በኩል ለመዉጋት ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ የካፋ ንጉሥ ግን፣ “ ይህ የወንድማማቾች ጉዳይ ስለሆነ፣ በእኔ በኩል ምንሊክን አትወጉመ……..” ብሎ ሲመልሳቸዉ፣ የሃይል ሚዛኑን አይተዉ፣ ለምኒልክ የጦርነት ሂደት፣ በተለይም በካፋ ወረራ ወቅት ጉልህ ሚና ተጫዉተዉ ነበር፡፡ ስለሆነም የካፋ መንግሥት መዉደቅ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡ ንጉሡም ቢሆኑ ወደዉግያዉ የገቡት በዉስጥ ሴረኞች ተፅዕኖ ነበር፡፡ ዝርዝሩን የሚመለከታቸዉ የፃፉት ስለሆነ፣ ለትምህርት እንዲሆን ምንጮቹን ማየት ይጠቅማል፡፡ ለማንኛዉም ካፋ በአራት አቅጣጫ፣ በዘመናዊ መሣሪያና፣ በአዉሮፓዊያን የጦር መኮንኖች ድጋፍ በተደረገበት ጦርነት ወደመ፡፡ በዚህ እልህ አስጨራሽና አዉዳሚ ጦርነት፣ የታሪካዊዉ የካፋ መንግሥት ህልዉና ሲያከትም፣ የህዝቡም የባርነት ዘመን ጀመረ፡፡ ቀጥሎም ነፃነቱን ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱን፣ ክብሩንና፣ ስብዕናዉን በሙሉ ተገፈፈ፡፡ ከሌሎች በተመሳሳይ መንገድ በማዕካላዊ መንግሥት ከተጠቃለሉ ህዝቦች ሁሉ በተለየ ሁኔታ፣ ከፖለቲካ ተገልሎ፣ ከማህበራዊ እና እኮኖሚያዊ ልማት ከመገለል በላይ ወደ ለየለት አገልጋይነትና ባርነት ወረደ፡፡ መሬቱ፣ ንብረቱ፣ ክብሩ ተነጥቆ ከቀዬዉ በመፈናቀል፣ ሲሰደድና በሰፋሪዉ፣ በወታደሮችና በገዢዎች ከሰዉ በታች ተገዛ፡፡ ይህ ሁሉ የህልዉና ማጣትና፣ ቀጥሎም በዉስጥም ጉዳይም፣ ራሱን ማስተዳደር በመከልከሉ፣ የደረሰዉን ሁሉ መናገር ቀርቶ፣ ማሰብም ይጨንቃል፡፡

 

ይህ ሁሉ የመደራጀት፣ የራስ አመራርና የራስ አስተዳደር ያለመኖር ዉጤት ነበር፡፡

 

የካፋ ህዝብም፣ በአዲሱ አስተዳደር ሥር ሆኖም መብቱን ለማስጠበቅ ጥረት ከማድረግ ተቆጥቦ አያዉቅም፡፡ ለዝርዝሩ በዚህ ጉዳይ የተፃፉትን ማንበብና፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማነጋገር ይጠቅማል፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ጥረቶች ተወሰኑ ቆራጥ የህዝብ ወገኖች በአነስተኛ ቡድኖች የተደረጉ ከመሆን ያለፈ፣ በሚገባ በተደራጀ ዝግጅት፣ ባለመሆናቸዉና፣ ለስኬት አልበቁም፡፡ ምንም እንኳን፣ በዉስጡ የተሰገሰገዉ ሃይል፣ የካፋን ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደቀደምቶቹ ሁሉ ቢገድቡም፣ በወታደራዊዉ መንግሥት ጊዜ፣ በመሬት ለአራሹ ሰበብ፣ የካፋንም ህዝብም በአንፃራዊነት ቢያንስ ባለመሬት ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም ለተሻለ ልማት እድሉ አልተሰጠዉም፣ ጥቂት የአካባቢዉ ልጆች ሃሳብም ቢሆን፣ በተሻለ ሁኔታ በተደራጁ አደናቃፊዎች ሲከሽፍ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ፣ በ20ኛዉ ክ/ዘመን መጀመሪያ በዉጭ ሰዎችና፣ በገዢዎች የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ጭምር እየተነቀሉ ሲወሰዱ፣ ህዝቡ ከመታዘብ ዉጭ አቅም አልነበረዉም፡፡

 

ይህም ሁሉ አሁንም የመደራጀት፣ የራስ አመራርና የራስ አስተዳደር ያለመኖር ዉጤት ነበር፡፡

 

በመጨረሻ ግን ካፋ ህልዉናዉንና፣ መሬቱን ማለትም የሃብት መሰረቱን፣ ያጣዉ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ነዉ፡፡ ለሃብትና ለመሬት ዘረፋ እንዲመቸዉ፣ ኢህአዴግ ካፋንና አጎራባች ህዝቦችን ከፖለቲካ ሥልጣን ዉጭ በማድረግ፣ ከሚወራለት የፌደራል ሥርዓት አሰራር ዉጭ፣ በዉስጥ ጉዳይ ጭምር እንዳይወስን አደረገ፡፡ በመጀመሪያ ፣ ከአካባቢዉ የመለመላቸዉን ካድሬዎች በራሱ ቅኝት አስተምሮ፣ በብሄር አደራጀ፡፡ ከዚያም በደቡብና፣ በካፋ አካባቢ የተመሰረቱ ተቃዋሚ ድርጅቶችን፤ “ኦነግ ሊዉጣችሁ ነዉ” ብሎ አስፈራርቶ “የደቡብ ህብረት” የተባለ ድርጅት እንዲመሰርቱ አደረገ፡፡ ከዚያም ራሱ የፈጠራቸዉን፣ የክልል ባለሥልጣናት ደግሞ፣ “ተቃዋሚዎች ቀደሟችሁ” በማለት፣ “የደቡብ ግንባር የተባለ (አሁን የደቡብ ንቅናቄ) ድርጅት” እንዲመሰርቱ አድርጎ፣ ቀጥሎም የደቡብ ክልልን እንዲመሰርቱ አደረገ፡፡ በርግጥ ከህብረቱም ከግንባሩም ለዓላማዉ የተመቻቹም ሆነ፣ ቀዝቃዛ ስሜትና ተቃዉሞ የነበራቸዉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የህብረት አባል የነበረ፣ ግን እስካዛሬም ለራሱ ክልል እየታገለ ያለዉን፣ የሲዳማ ህዝብ በምሣሌነት መዉሰድ ይቻላል፡፡

 

ይህ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የተደራጀን ህዝብ አመራርና፣ በተናጠል የሚደረግ ጉዞን ለማነፃፀር ይረዳል፡፡

 

በዚህም ካፋ እና አጎራባች ህዝቦች ከሺህ ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘዉ ደቡብን ሲቀላቀሉ፣ ሴራዉም፣ ለቀጣዩ አፈናና ዝርፊያ ዝግጅት መሆኑ አሁን ግልፅ ሆኗል፡፡ በራሳቸዉ ሲተዳደሩ የነበሩ፣ አሁን ግን ከአዋሳ ርቀት ሌላ፣ እንደማንኛዉም ክልል፣ የራሳቸዉን ፖሊሲ፣ ህግና ደንብ እንዳያወጡና እንዳይተገብሩ፣ የራሳቸዉ አመራር እንዳያቋቁሙ ሆነ፡፡ በደቡብ ክልልና የበላያቸዉ ሆኖ፣ ከሚመራቸዉ የህወሃት ቁልፍ ሰዉ በሚሰጥ ትዕዛዝ የሚፈልጉትን ሁሉ አደረጉ፣ ህዝቡም ወደ ባሰ ድህነት ወረደ፡፡ ደቡብ፣ በየደረጃዉ ተላላኪዎቹን እየመደበ ሲፈልግ አወረደ፣ የፈለገዉን መሬት በተለይም ጥቅጥቅ ደን ወረሰ፣ ግንድና ጣዉላ ነገደ፣ በወታደር እያሰገደደ የማይጠቅመዉን ማዳበሪያ ለገበሬዉ አደለ፣ ክፍያዉንም ጥሪቱን በማሸጥ አስከፈለ፣ ወጣቱ መሬትና ሥራ አልባ ሆኖ ሲቦዝን የሚፈልገዉን በመሬቱ አሰፈረ፣ ለአካባቢዉ ከዉጭ ጭምር የተገኘ ሃብትና ድጋፍ አደናቀፈ፣ ሌላም…. ወዘተ. አደረገበት፡፡

 

ይህ ሁሉ፣ እንደሌሎች ህዝቦች፣ ከግል ሥልጣንና ጥቅም ይልቅ ለህዝቡ የወገነ፣ ለእዉነት፣ ለህሊናዉና፣ ለህግ ተገዢ የሆነ ለህዝቡ የቆመ ድርጅትና ተከራካሪ ድርጅትና አመራር ባለመኖሩ ነዉ፡፡

 

የህዝቡን ብሶትና ግፍ፣ ነፃነት ለማምጣት የሚያደራጅ፣ የሚያስተምረዉና የሚመራዉ አካል ባለመኖሩ ነዉ፡፡ በየግላቸዉ የሚንጨረጨሩ ግለሰቦች መኖራቸዉ ባይካድም፣ የተደራጁ ባለመሆናቸዉ ጥረታቸዉ የትም አልደረሰም፡፡

ህዝቡም፣ ጫናዉን መሸከም ስለከበደዉ፣ ባጋኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ስሜቱን መግለፅ ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ ለደቡብ ንቅናቄ ሊ/መንበርና፣ ለአፈ-ጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል፣ የክልል ጥያቄን ጨምሮ፣ ደረሰበትን ዘረፋና በደል በምሬት አቅርቧል፡፡ ቢሆንም ይህንን ጥያቄ ክልሉና አለቃቸዉ የፈጠረዉ ተላላኪ ሊያከሽፍ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ሥልጣንና ጥቅም የተሰጣቸዉ አስፈፃሚዎች፣ የአገዛዙ ምስለኔዎችና ሹመኞች ሃላፊነታቸዉን ይወጣሉ፡፡ የወቅቱ ለዉጥም ከዚህ ሥልጣንና ጥቅም ስለሚነቀንቃቸዉ፣ የህዝቡን ጥያቄም ሆነ ማንኛዉንም የለዉጥ ሂደት ማደናቀፋቸዉ አይቀርም፡፡ ምናልባትም ቆዳቸዉን ለዉጠዉ በአዲስ መልክ ሥልጣን መቆናጠጥ፣ ለዉጡን ማሰናከልና፣ ህዝቡን መደፍጠጥ መቀጠላቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ ይህንንም ለማገለጥና ለዉጡን ለማገዝ የሚችል ድርጅት ስለሌለ፣ በግላቸዉ የሚታገሉ ንፁሃንም ብዙ መጓዝ አይችሉም፡፡

 

ይህም የተደራጀ፣ ለህዝቡ ወገናዊና ተዓማኒ ድርጅትና አመራር ባለመኖሩ እየቀጠለ ያለ ግፍና ጫና ነዉ፡፡

 

ህዝቡ ከዚህ የሚያወጣዉ በቁርጠኝነት ተማምኖበት የሚከተለዉ ድርጅትና አመራር ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አዲስና ተዓማኒ ድርጅትና አመራር ካልተፈጠረና ህዝቡን ካልመራዉ፣ የካፋ ህዝብ እስካሁን ካጣዉ ጥቅም በባሰ ሁኔታ ወደ ዉድቀት ማምራቱ የማይቀር ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተፈጠረዉን አጋጣሚ ተጠቅሞ በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ፣ የለዉጡ አካል መሆን፣ አስተዋፅኦ ማድረግና፤ ከለዉጡም ተጠቃሚ መሆን፣ ወቅታዊ ጥያቄ ነዉ፡፡ የመደራጀቱ መነሻም የቆየዉን የህዝቡን ጥያቄ መመለስ እንጂ፣ በማንም ግፊት አይደለም፡፡

 

ዓላማዉ ደግሞ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ቢቻል ለምሥራቅ አፍሪካ አንድነት ነዉ፡፡ ጤነኞች ሁሉ፡ ለዚህ መሰረታዊ መርህና ግብ ሊቆሙ ሲገባ፣ በመከባበርና በፍትሃዊነት ሊሆን ግን ይገባል!!

 

 

II. የአመራር አማራጮች፣ ሥጋቶችና፣ ዕድሎች

 

II.1. ለዉጡ በኢህአዴግ አማካይነት እንዲመጣ መጠበቅ፤

 

ኢህአዴግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃዉ የተመደቡ ካድሬዎችና ከአስተዳዳሪነት እስከ ኤክስፐረትነት እየተቀያየሩ ያሉት፣ በኢህአዴግ ዉስጥ ራሳቸዉን ያደራጁ፣ በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበሩ፣ የጓደኛሞች ስብስብ ነዉ፡፡ ይህ ቡድን ገፍቶ፣ ግምገማ ሲበረታባቸዉ በመደጋገፍ መሰረታዊ ወንጀላቸዉን በቡድናቸዉ አማካይነት ተደባብቀዉ ምንም መሰረታዊ ጉዳት ሳይደርስና መጠየቅ ሣይኖርበት፣ ከሃላፊነት ለጊዜዉ እንዲገለሉና ይደረጋሉ፡፡ በዚህም ወቅት ጥቅማቸዉ ተጠብቆ ዝቅ ባለ የሃላፊነት መደብ ተሸሸገዉ ይቆያሉ፡፡ ሆኖም ጉዳያቸዉ ሲረግብ ቀስ በቀስ፣ በቀሩትና በተረፉት፣ ምናልባትም ከፍ ወዳለ ቦታ ተመድበዉ በቆዩ የቡድን አባሎቻቸዉ ተጎትተዉ በተሻለ ቦታ፣ ወደ ወሳኝ ቦታቸዉ እየተመለሱ የቆዩ ናቸዉ፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን አካባቢዉን የሚዘዉሩት በአንድ ወቅት በመሃላ ተሳስረዉ የተሰባሰቡ በቡድን የተሳሰሩ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ ከነበረበት ከፍተኛ ሥልጣን የተወገደ አባላቸዉ እንኳን ቢሆን በወቅቱ ሥልጣን ላይ ባይሆንም፣ ሁሉም ወሳኝ መረጃ ከነዚሁ አባላቱ ይደርሰዋል፡፡ በዓመታት ባዳበሩት የድርጅት አሰራርና ልምድ፣ የቢሮክራሲ ልምድ፣ ሥልጠናና፣ ሥልት ተጠቅመዉ በየወቅቱ የሚነሱ የአካባቢዉን ጥያቄዎች ተረባርበዉ የማለዘብ ሥራ በጋራ ይሰራሉ፣ የተዳፈነ ተግባራቸዉ እንዳይወጣ ይረባረባሉ፡፡ በአፈ-ጉባኤዋ የተመራዉ ስብሰባ ላይ ህዝቡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብዙ የጠየቀ ቢሆንም ይህ ቡድንና ሰንሰለቱ ግን አሁንም ተኮፍሰዉ በየመድረኩ ታይተዋል፡፡ ምናልባትም የለዉጡን ሂደት በተመለከተ አለቆቻቸዉ ሃላፊነት የሰጡት ለእነርሱ፣ አዲስ እየተመረጡ ነዉ የተባሉትም የእነርሱ ታዛዥና ጉዳይ አስፈፃሚ አለመሆናቸዉን ለማረጋገጥ ገና ነዉ፡፡ ሆኖም ግን ሰንሰለቱ በሥልጣን ላይ የሌሉትን ጭምር ይዞ መቀጠሉንና ዉዥንብር እየፈጠረ እንደሆነ የሚያሳዩ ጭምጭምታዎች አሉ፡፡ ይህ ቡድን በየወቅቱ እይተዋለደ፣ ተስፋፍቶ በአካባቢዉ ምንም ዓይነት መሰረታዊ ለዉጥ እንዳይመጣ ተብትቦ የያዘ ስለሆነ እነዚህን ይዞ፣ ለዉጥ በኢህአዴግ አማካይነት ይመጣል ማለት የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ካፋና አጎራባች ዞኖች ዉስጥ እንደሌሎች አካባቢዎች የሚታመንበት የለዉጥ ሃይል አለመከሰቱ፣ አሁን በማዕከል ደረጃና በሌሎች አካባቢዎች፣ ከሚታየዉና ከመሪዎቹ ከሚነገረዉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ አኳያ ሲታይ አለመታደል ሲሆን አሁንም አካባቢዉ ሌላ ዕድል እንደሚያመልጠዉ አመላካች ነዉ፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በአካባቢዉ ያሉትን እስካሁን ህዝቡን ያስመረሩ አባላቱን ሙሉ በሙሉ በአንዴ ጠራርጎ በአዲስ ይተካል የሚል ግምት አይኖርም፡፡ ምሁራንና ሃቀኛ የአካባቢዉ ልጆችም ከአሁን በሁዋላ በኢህአዴግ ይታቀፋሉ፣ ጠቅላይ ሚ/ሩ የሚሉትን አይነት አካሄድና አመራር ቢመኙም በድርጅቱ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ለዉጥ ይመጣል ብለዉ ይጠጋሉ ወይም አምነዉ ይቀርባሉ ማለት ከባድ ነዉ፡፡

 

II.2. ከኢህአዴግ ጋር የሚደጋገፍ አዲስ ሃይል፤

 

የአካባቢዉ ህዝብ በመሰረታዊነት፣ የኢህዴግ መርህ ተቃዋሚ አይደለም፡፡ በማንነቱ የተበደለና የተናቀ በመሆኑ በአግባቡ ቢተገበር ኖሮ ባህሉን፣ ታሪኩንና ቋንቋዉን ማሳደግ ሚፈልግ ነዉ፡፡ መሬትን በተመለከተም በተፃፈዉ ህግ መሰረት ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፣ በቂ የራሱ መሬት ኖሮት፣ የወልና የመንግስት ተብለዉ የተከለሉ፣ የግጦሽና የደን መሬቶችን፣ ከራሱ ማሳ በላይ ጠብቆ የሚያለማ ሥራ ወዳድና ታታሪ ህዝብ ነዉ፡፡ ጥቃቅን በደሎች እየተደራረቡም ቢሆን በሂደት ይስተካከላል በሚል በትዕግስት የቆየ ህዝብ ነዉ፡፡ በተለያየ መንገድና በተለይም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በሰፈራ ከመጡ በርካታ የኦሮሞ፣ አማራ፣ የትግራይ ተወላጆች ጋር፣ እንዲሁም በራሳቸዉ ጊዜ እየመጡ ከሰፈሩ በርካታ ህዝቦች ጋር በሰላም የሚኖር የአብሮነት ምሣሌ የሆነ ህዝብ ነዉ፡፡ ለዘመናት ከአያት፣ ቅድመ-አያቶቻቸዉ ጀምሮ የጠበቁትንና የሚሳሱለትን ጥቅጥቅ ደን በአጭር ጊዜ ሲዘርፉና ሲያወድሙም በአግባቡ የሚለማ ከሆነ፣ በሚል ትዕግሥት ሲታዝቡ የቆዩ ህዝቦች ነዉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአካባቢዉ ችግር በአሁኑ የኢህአዴግ የለዉጥ ጉዞና በተፈጠረዉ ሃገራዊ የተስፋ ጭላንጭልና ዕድል ብቻ የማይፈታ፣ በአካባቢዉ በተከማቹ የአካባቢዉ የኢህአዴግ አባላትና በክልሉ ባሉ አለቆቻቸዉ ምክንያት፣የተገመደ ዉ ስብስብ ችግር ስለሆነ፣ በኢህዴግ በኩል ሊለወጥ የሚችል አይመስልም፡፡

አዲስ ድርጅት ተመስርቶ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ ሊሰራ ይችላል ወይ የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም እንዳይባል ደግሞ ኢህአዴግ ራሱ ከአንድ አካባቢና ህዝብ የወጣ፣ ከአንድ በላይ አባል ድርጅት ማቀፍ ስለማይፈቅድ ዕድሉ የመከነ ነዉ፡፡ ምናልባት የሚቻለዉ የትብብር መንገድ፣ ኢህአዴግ በያዘዉ የመለወጥ መንገድ ከቀጠለ ፣ በማዕከልና በተወሰኑ ክልሎችና አካባቢዎች የሚታየዉ አዝማሚያ ከቀጠለና፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ከተቻለ ሌላዉ አማራጭ ሊኖር ይችላል፡፡ ይኸዉም፣ ኢህአዴግ በአባላቱ አማካይነት ከደረሰዉ ግፍ አኳያ፣ በዚህ አካባቢ የማሸነፍ ዕድሉ አነስተኛ ስለሆነ፣ አካባቢያዊም ሆነ አገር አቀፍ ድርጅት እንደሌሎቹ ማሸነፉ ስለማይቀር፣ አጋር ድርጅት ሆኖ ግን ነፃነቱን አስጠብቆ መቆየት ከቻለ፣ ለአገሪቱ፣ ለኢህዴግ፣ ለመጪዉ ድርጅትም ሆነ፣ ለአካባቢዉ ህዝቡ የሚበጅ ይሆናል፡፡

 

II.3. የተሻለዉ፣ ዘላቂዉና ተመራጩ መንገድ፤

 

ተጨባጩ ሁኔታ ሲታይና ቃል የተገባዉ ዲሞክራሲያዊነት ተግባራዊ ከሆነ፣ በአካባቢዉ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በአዲስ መልክ የሚደራጅ ሃይል፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራጅተዉ ግን ደግሞ የአካባቢዉን ህዝብ ጥያቄ ከግምት የሚያስገቡ ድርጅቶች ተጠናክረዉ በአካባቢዉ ሥልጣን ቢይዙ ይመረጣል፡፡ ካለዉ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ይህ ቅድመ- ሁኔታ ከተሟላ፣ በአካባቢዉ ባሉ፣ መልካም ስም ባላቸዉ የአካባቢዉ ምሁራን የሚመራ፣ ህዝባዊ ወገንተኛና ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያን፣ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎችና፣ ገበሬዎች የተሳተፉበትና፣ በተለይም ለዉጥ ፈላጊ የለዉጥ አራማጅ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ የሚመሰረት ድርጅት ይመረጣል፡፡ የህ ዓይነቱን ድርጅት መስርቶ ማጠናከር አድካሚ ቢሆንም፣ በዚህም ሆነ በዚያ ግን ሥልጣን መያዙ የማይቀር ነዉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጅትዕዉን ከሆነ ደግሞ አካባቢዉንና ህዝቡን ከሌላዉ የኢትዮጵያዊ አካባቢዎች እኩል እንደሚያለማና እንደሚያሳድግ መተማመን ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጅት፣ ከሁሉም በላይ በባለሙያ የሚመራ፣ የሃገሪቱን ህግ የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን በትጋት የሚጠብቅ፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ ለሌሎች አካባቢዎች ምሣሌ የሚሆን አሰራር የሚያሳይ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም፣ ቀጣዩ የአካባቢዉ አስተዳደር ፈተና ከባድና ዉስብስብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ህዝቡና በተለይም አሁንስ በቃኝ ብሎ የተነሳዉን ህዝብና ወጣት በብልህነት ማሳተፍፈ የሚችል ከአካባቢዉ በቀለ ድርጅት ለዉጥ ለማምጣት ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ የአካባቢዉ ህዝብ ደግሞ ጨዋ፣ ጠንቃቃና ራሱን በራሱ አደራጅቶ የሚጠብቅ ስለሆነ፣ ተገቢዉን የሚያምነዉን ፖለቲካዊ አመራር ካገኘ ካፋም ሆነ ሌላዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተስፋ ብሩህ ኢንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ የአካባቢዉ ህዝብ ለዓመታት በሰንሰለት ታስሮ፣ አካባቢዉ ሃብቱ ሲዘረፍና መብቱ ሲረገጥ የቆየ መሆኑ በአደባባይ ስለወጣና፣ ብሶቱን ማቅረብ ስለጀመረ፤ ያለዉ አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ከሚታየዉ አጓጊ ለዉጥ፣ እና ከተፈጠረዉ አመቺ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከህዝቡ አደረጃጀትና ንቃተ-ህሊና አኳያ ሲታይ ወቅቱ አሁን መሆኑን ያሳያልና፣ መፍጠን ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ ወደ ሁዋላ መመለስ በማይችልበት መስመር ዉስጥ መግባቱ ግልፅ ነዉ፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ያግበሰበሳቸዉን አባላት እስከሚያጠራ ጊዜ ይወስዳል፡ አካባቢ በቀልና በህዝቡ ተዓማኒ ድርጅት ካልመጣ፣ አሁንም የ27 ዓመቱ የጅቦች ቡድን በለመደዉና ባካበተዉ ልምድና ሥልት፣ እንደእባብ ቅርፊቱን አዉልቆ፣ ከለዉጡ ሃይል ጋር ተለጥፎና ተመሳስሎ፣ የህዝቡን ጥያቄ እንደሚነጥቅና እንደሚያኮላሽ፣ ህዝቡንም ለባሰ ጥያቄ ልያነሳሳና፣ ምናልባትም ወደ አደጋ ሊያመራ ይችላል፡፡ ፡ እስካሁን ማመን የምንችለዉ በጣም ጥቂት አመራሮች የሚናገሩትንና የበላይ አመራሩ ተግባራዊ እያደረገ ያለዉን ብቻ ነዉ፡፡ ከሚመሰረተዉ ድርጅት ከሚጠበቁት፣ በአካባቢዉ ያሉ ንቁና፣ ዝግጁ፣ በመረጃ የተሞሉ ወገኖችን ማሳተፍ፣ ቃል የተገባዉ ለዉጥ በተግባር እስኪዉልና፣ የክልል ጥያቄን ጨምሮ ገና ያልተነሱ ጉዳዮች እስኪመለሱ፣ በሰለጠነና በተረጋጋ ሁኔታ መታገልና ጥያቄዉን መቀጠል ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡ የሚየምነዉ፣ ህጋዊ ድርጅት ከአካባቢዉ መፈጠርና አማራጭ ሆኖ መገኘት ለአካባቢዉ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር አቀፉ የለዉጥ ሂደት ድጋፍ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡

ከG.C

ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a comment

ዎሆ ምሽራቻ


እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን
ዎሆ ምሽራቻ
ዋማ ዲጎና ናቶቸ ናቶች ቤዲቶተ!!!

ለጎንጋ ህዝብ በያላችሁበት
መጪው ኣመት የሰላም የፍቅር የኣንድነት
የተበተኑት የሚሰበሰቡበት
የተሰደዱት የሚመለሱበት
በግፍ የታሰሩት የሚፈቱበት
የተጎዱ የሚካሱበት
ፍትህ ዴሞክራሲ የምንቋደስበት
ዓላማችን ግብ መቶ ህዝባችን ኣንድ ሆኖ በመቆም የርስ በርስ ግጭት ኣብቅቶ በልማት ጎዳና ተጉዘን ህዝባችን የሚበለፅግበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ::
በዚህ ኣጋጣማ የካፋ ንጉሠ ነገሥት የታቶ ጋኪ ሻሮችን 121ኛ የጀግንነትና ኣልበገር ባይነት ለመዘክር በግጥም መልክ የቀረበው ሥነ ፅሑፍ ለማስታወሻ እንዲሆንና ወጣቱ እንዲማርበት ይረዳል ብየ የድርሻየን ለመወጣት ሞክሬኣለሁ::
መልካም ኣዲስ ኣመት

የደቡብ ምዕራቧ ለምለማቷ ምድር
ዘምርልሼለሁ ሆኜ ከሰው ሀገር
ኣሉሽ ታላላቅ ጀግኖች ስማቸው የተረሳ
መስዋእት የሆኑ ባንቺ የተነሳ
ኣኩሪ ታሪክ ሰርተው ያለፉ በጋራ
ተፋልመው የወደቁ ከሚኒሊክ ጋራ
ስማቸው እንዳይጠራ ተሰርቶባቸው ደባ
እንደወጡ የቀሩ በኣዲስ ኣበባ
ተነሳ ተናገር ኣንተ ሀብተ ጊዮርጊስ
ቀየው ድረስ ሄደህ ቤቱን ስታፈርስ
እጅህን ስትዘረጋ እጁን ለማሰር
ጋኪ እጁን ኣልሰጠም በመተባበር
ኣንተ ንጉሥ ብትሆን እኔም ነኝ ንጉሥ
ከቶ በምንም መንገድ ካንተ የማላንስ
ወዲያ ውሰድልኝ ያንተን ብር ሰንሰለት
ኣለኝ የራሴ ወርቅ ከመጣም እስራት
እጅ ኣልሰጥም ኣለ ቆመና በኩራት
እንደምን ይረሳል ይኸ ታላቅ መሪ
ኣልበገር ያለ ለመጣው ወራሪ
እጁን ያሳሰረ በወርቅ ሰንሰለት
ብቸኛዋ ምድር ትልቅ ታሪክ ኣላት
ታዲያ ምን ያደርጋል እኛም ረሳናት
ኃላ ቀር የሚባል ስም እስኪወጣላት
እግዚኣብሔር ይመስገን ጊዜ ተለውጧል
ጎርማሾ ተነስቶ ኣለሁልሽ ብሏል
ተኝቶ የነበር ለመቶ ኣመት
ገና ዛሬ ነቃ ኣለሁልሽ ሊላት
ሰሜን ኣሜሪካ ደምኢሕህ ተመስርቶ
ለፍትህ ለኩልነት ሊሠራ በርትቶ
ቃል ኪዳን ገባልሽ ሊሠራ ሀገር ገብቶ
ተነስቷል ጎርማሾ ሸሚዙን ጠቅልሎ
የኣንድነት ችቦ ለኩሶ ኣቀጣጥሎ
ያልበገር ባዩን የጋኪን ኣላማ
እዳር ኣደርሳለሁ ምንም ሳላቅማማ
ብሎ በመነሳት ገስግሷል ወደ ፊት
እንደ ንብ ተነስቷል ሊሠራ ባንድነት
ተነሱ ልጆቿ የደቡብ ምዕራብ
ጎጀብና ጊቤ ነው ኣሉ ድንበራችን
ኣይፈርስም በደባ ባህልና ቋንቋችን
እንዳትቆራረስ ክብሯ እንዳይደፈር
ባንድነት እንቁም እንደ ድር እናብር
ቃል ኪዳን ገብተናል ልንቆም ላንድነቷ
ተመልሳ እንድትቆም በታላቅነቷ
ከወደቀችበት ከማጥ ልናወጣት
ምሽራቻ ብለን ልንዘምርላት

ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘላለም ትኑር!!!
ድል ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ከፋንታዬ መኮ
ካፋ ሚዲያ kaffamedia