Leave a comment

የፊታችን ምርጫ ቀልድ ነዉ – መድረኩ ግን መሳተፉ ይበጀዋል !


የፊታችን ምርጫ ቀልድ ነዉ – መድረኩ ግን መሳተፉ ይበጀዋል !
ግርማ ካሳ
(muziky68@yahoo.com)

ሚያዚያ 24 ቀን 2002 ዓ.ም

የ2002 ምርጫ ሊደረግ ከአንድ ወር በታች ቀርቶታል። ገዢዉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ መንግስት «ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሆን ለማድረግ የነበረኝን ቁርጠኝነት እያሳየሁ ነዉ» ይላል። የአዉሮፓ ሕብረት ታዛቢዎችም ምርጫዉን ለመታዘብ አዲስ አበባ ገብተዋል። መድረኩ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ በመቱ፣ በወልቂጤ፣ በደብረ ብርሃን፣ በደሴ፣ በወልዲያ፣ በኮምቦላቻ እንዲሁም በተለያዩ የአዲስ አበባ ወረዳዎች ታላላቅ ሕዝባዊ ስበሰባዎችን እያደረገ ነዉ። በአቶ ኃይሉ ሻዉል የሚመራዉ መኢአድ በአዋሳ፣ በአቶ ልደቱ የሚመራዉ ኢዴፓ ደግሞ በአለታ ወንዶ፣ ጎንደርና ባህር ዳር ሕዝባዊ ስብሰባዎች ያደረገ ሲሆን የምርጫ ዘመቻቸዉን አጧጥፈዉታል።

በአገር ቤት ያለዉ ይሄን ሲመስል፣ በዉጭ አገር በአንዳንድ ማእዘናት ምርጫዉን ቦይኮት የማድረግ (በምርጫዉ ያለመሳተፍ) ጥሪ እየቀረበ ነዉ። የግንቦት ሰባትን ንቅናቄ ደጋፊዎችን ጨምሮ አንዳንድ የተቃዋሚ ወገኖች «ምርጫዉን ሕወሃት/ኢሕአዴግ አሸንፎታል። ከምርጫዉ እራስን ማግለል ያስፈልጋል» የሚል የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከከፈቱ ቆይተዋል። በምርጫ ሊገኝ የሚችል አንዳች ዉጤት እንደሌለ ይናገራሉ። በቅርቡ በከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍል ድህረ ገጽ ላይ በወጣ አንድ ጽሁፋቸዉ አቶ ሃብታሙ አሰፋ የሚባሉ ሰዉ «እነ አቶ መለስ ማጅራቱን ከመተቱት ምርጫ ተቃዋሚዎች ለምን እራሳቸዉን አያገሉም ? …ትግሉ የአገሪቷን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለማጎልበትና ሕዝቡን አታግሎ የሕግ የበለያነት የተረጋገጠበት ሥርዓት ለመገንባት ከሆነ በዚህ ምርጫ መሳተፍ ከዚህ ግብ አያደርስም» ሲሉ በምርጫዉ መሳተፍ ለትግሉ ጥቅም እንደማያመጣ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የሚመሩት ሰሞኑን አንዳንድ ድምጾች እያሰማ ያለዉ የዝም አንልሞች ቡድን ደግሞ «እንዴት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ ምርጫ ይገባል?» በማለት በመድረኩ ላይ ጠንካራ ትችት እያቀረበ ነዉ።

የዚህ ጽሁፍ አላማ የማንንም አስተያየት ለማጣጣል አይደለም። ነገር ግን ከስሜት በፀዳ መልኩ ሁኔታዎችን ከሁሉም አቅጣጫዎች ማየት እንድንችልና በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ ቢቻል ሁላችንንም ወደ አንድ አቅጣጫ ሊያመጣ ዉይይት እንድናደርግ ነዉ።

በተቃዋሚ ወገን ያለን ሁላችንም የምንስማማበትና ክርክር የማያስፈልግዉ አንድ ነጥብ አለ። ይህም የ2002 ዓ.ም ምርጫ፣ በምንም መስፈርትና ሚዛን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም። የጠቅላላዉ ምርጫ ሂደት፣ ቅድመ ምርጫን፣ የምርጫ ወቅትንና ድህረ ምርጫን ያካትታል። «አንድ ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነዉ ፤ ወይም አይደለም» ብሎ ለመፍረድ፣ ምርጫ እስኪደረግ የግድ መጠበቅ የለበት። ከምርጫ በፊት ያሉትን ሁኔታዎች በማጥናት የምርጫዉን ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊነት ከወዲሁ ማረጋገጥ ይቻላል።

የቅድመ ምርጫ ወቅት ላይ በመታኮር አሁን በኢትዮጵያ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታዎች ለመቃኘት እንሞክራለን።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የቅንጅት ወራሽ የሆነዉና በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነዉ። በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራዉ የአንድነት ፓርቲ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ መምጣት ሲጀምር፣ ገዢዉ ፓርቲ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የድርጅቱን ሊቀመንበር በግፍና በጭካኔ አሰረ።

ሌላዉ ቢቀር የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ብቻ ምርጫዉን ኢፍትሃዊና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ያደርገዋል። ህዝብን አስተባብራ በዝረራ ልታሸንፍ የምትችለዉን ታላቅ ኢትዮጵያዊት፣ በድምጽና በሃስብ ክርክር እንደማያሸንፏት ሲያዉቁ፣ እነ አቶ መለስ ዜናዊ በጉልበት እርሷን አሳስረዉ «ምርጫ አሸነፍን» ቢሉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይስቅባቸዋል እንጂ በሕዝብ እንደተመረጡ አድርጎ የሚቆጥር አይኖርም።

ይህ ብቻ አይደለም። በዚህ ሁለት ሳምንታት ብቻ ሁለት ጠንካራ የመድረኩ አባላት፣ ርህራሄ በሌለበት ሁኔታ ተደብድበዉ ተገድለዋል። የመጀመሪያው አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ ይባላል። በትግራይ መድረኩን ወክሎ ለተወካዮች ምክር ቤት ሊወዳደር የቀረበ ወንድማችን ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ወጣት ቢያንሳ ዳባ ይባላል። በአምቦ አካባቢ የመድረኩ አደራጅ ነበር። አንድ ማታ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ደህንነት አባላት ወደ ቤቱ መጥተዉ ደበደቡት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከድብደባዉ ማገገም ስላልቻለ ሕይወቱ አለፈች። እነዚህ ስማቸዉ የታወቁ ናቸዉ እንጂ በየቦታዉና በየወረዳዉ መድረኩን ወክለዉ የሚወዳደሩ፣ መድረኩን የሚደግፉ የተገደሉ፣ ከሥራ የተባረሩ፣ የታሰሩ ፣ ወከባና ዛቻ የሚደርስባቸዉ ጥቂት አይደሉም። ሕዝቡ ኢሕአዴግን ካልመረጠ ችግር እንደሚያጋጥመዉ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠዉ ነዉ። ኢሕአዴግን እንደሚመርጡ ዜጎች በመሃላ እንዲፈርሙ እየተደረገ ነዉ። ይህ ሁሉ ምን ያህል ምርጫዉ ቀልድና ጨዋታ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።

እቀጥላለሁ። ወደ አርባ ሰባት ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ምርጫዉን የሚታዘቡ፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚከፈላቸዉ የሕወሃት/ኢሕአዴግን አሸናፊነት የሚያረጋግጡ ታዛቢዎች ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ታዛቢዎች የኢሕአዴግ ሰዎች ናቸዉ ብንል አንሳሳትም። የምርጫዉን ዉጤት የሚወስነዉ ደግሞ ድምጽ ሰጪዉ ሳይሆን ድምጽ ቆጣሪዉ ነዉ። ቆጣሪው ኢሕአዴግ በሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ በምንም መስፈርት ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችለም።

ይህ የ2002 ምርጫ በምንም ተዓምር ኢፍትሃዊና ዴሞርክራሲያዊ ሊባል እንደማይችል ሌላም ሌላም የተጨበጡና የማያከራክሩ መረጃዎችን መዘርዝር ይቻላል። ከላይ እንደተገለጸዉ ብዙም በተቃዋሚዉ ወገን ዘንድ የሚያከራክር ነገር አይደለም።

ክርክሩና አለመስማማቱ የሚመጣዉ «ምርጫዉ ከላይ እንደጠቀስኩት ኢፍትሃዊን ዴሞክራሲያ ሆኖም፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በቀላሉ አጭበብሮ ተመረጥኩኝ ብሎ የሚያዉጅበት ሁኔታ ሰፊ ቢሆንም ፣ ከምርጫዉ እራሳችንን ማግለል ነዉ የሚበጀዉ ወይንስ በምርጫዉ ገፍቶ መሄድ ?» በሚለዉ ላይ ነዉ።

ምርጫዉን አለመሳተፍ ከሚያመጣዉ ጥቅም ይልቅ ብዙ ጉዳት እንደሚኖረዉ በማሳየት ከአንዳንዶች ዘንድ የምንሰማዉ የምርጫ ቦይኮት ዘመቻ ከንዴትና ከስሜት የመነጨ እንጂ ጥቅሙንና ጉዳቱን ያመዛዘነ እንዳልሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ።

ከምርጫዉ ተቃዋሚዎች እራሳችዉን ቢያገሉና ኢሕአዴግ አሸንፊያለሁ ብሎ ቢያወጅ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና አንዳንድ የዉጭ ሜዲያ ጋዜጠኞች ለጥቅት ቀናት ወገዛ ያቀርቡ ይሆናል። ነገር ግን ገንዘቡ በእጃቸዉ የሆነ የምእራባዉያን አገሮች አቶ መለስን ማቀፋቸዉ አይቀርም። በምንም መልኩ ምርጫ ተጭበረበረ ብለዉ አሁን ያለዉን አገዛዝ ከመደገፍ ወደ ኋላ አይሉም። ለእነርሱ ግድ የሚሰጣቸዉ የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን የመረጋጋት ጥያቄ ነዉ። ኢሕአዴግ ደግሞ በሶማሊያ፣ በሱዳን ፣ በኤርትራ ካሉ ገዢዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ለምእራባዉያኑ የተሻለ መንግስት ነዉ። ስለዚህም «አገዛዙ ተቀባይነት እንዳያጣ አስደርገዋለሁ» ብሎ መድረኩ ከምርጫዉ ቢወጣ የሚያገኘዉ አንዳች ፋይዳና ጥቅም አይኖርም። በመሆኑም መድረኩ ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አንድ በሉ።

በምርጫዉ የሚሳተፉ እንደ ኢዴፓ፣ መኢአድ ያሉ ድርጅቶች አሉ። መኢአድና ኤዴፓ በርካታ ወረዳዎች ተወዳዳሪዎች አሰልፈዋል። ስለዚህ ቦይኮቱ ሁሉንም ድርጅቶች ያቀፈ ሊሆን አይችልም። መድረኩ ብቻዉን ቦይኮት ቢያደርግ አቶ መለስ ከኢንጂነር ኃይሉ ሻዉልና ከአቶ ልደቱ ጋር በሸራተን እንደተጨባበጡት፣ መድረኩ ወደ ጎን ተደርጎ፣ ከኢዴፓና ከመኢአድ ጋር በመሆን፣ በኢትዮጵያ ምድበለ -ፓርቲ እንዳለ መለፈፍ ይችላሉ። በሌላ አባባል ኢሕአዴግን የሚያጅቡ ሌሎች ይኖራሉ ማለት ነዉ። ስለዚህ ሁኔታዉ መድረኩን አጣብቂኝ ዉስጥ የሚከት ስለሆነ መድረኩ በምርጫዉ መሳተፍ አለበት። ሁለት በሉ።

የምርጫ ቦይኮት ድርጅታዊ ሥራ ይጠይቃል። ሕዝብን እሰከ ታች ድረስ ማንቀሳቀ፣ ለመምረጥ እንዳይሄድ በየቦታዉ በግልጽ ይሁን በሕብኡ ቅስቀሳ መደረግ አለበት። የደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲ በየቦታው፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ መረብ ነበረዉ። አንድ ሕዝባዊ ጥሪ በተደረገ ጊዜ ሕዝቡ በቀላሉ ተግባራዊ ያደርገዉ ነበር። የቦይኮት ዘመቻዎችም ገዢዉ የአፓርታይድ አገዛዝ ያስጨንቁ ነበር።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየክልሉ በየወረዳዉ ሕዝብን ያደራጀና ጠንካራ መረብ የዘረጋ ድርጅት የለም። መድረኩ ያንን ለማድረግ እየሞከረ ነዉ። ግን አገር አቀፍ ጥሪ አቅርቦ፣ ጥሪዉ በህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ህዝባዊ ንቅናቄ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመዘርጋት ይችል ዘንድ ድርጅታዊ ብቃት ገና የለዉም። ይህ ብቃት ሳይኖር ገዢውን ፓርቲ ፊት ለፊት መጋፈጥ ቅንጅት በ97 የሰራዉን ስህተት መድገም ነዉ። (ቅንጅት በ97 አንጋፋ መሪዎቹ የነበሩት አቶ ልደቱ፣ ኢንጂነር ኅያሉ ሻዉል፣ ዶር ብርሃኑ ነጋና ፕሮፌሰር መስፍን .. በጥንቃቄና በትህትና፣ በመግባባትና የአገርን ጥቅም በማስቀደም የድርጅቱን አንድነት ጠብቀዉ፣ ትግሉን ቀጥለዉ ቢሆን ኖሮ፣ አገዛዙን ማንበርከከ የሚችል ብቃት ያለዉ ድርጅት ይሄን ጊዜ ይኖር ነበር) ህዝባዊ አቅም ሳይገነቡ ከአምባገነኖች ጋር ፊት ለፊት የሚገጥሙ የፖለቲካ ድርጅቶች በስሜት የሚመሩ፣ የትም የማይደርሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸዉ። መድረኩ እንደነዚህ አይነት ድርጅት ሊሆን አይገባም። ማስተዋል ያለዉና የበሰለ ዉሳኔ በመዉሰድ መድረኩ ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ሶስት በሉ።

መድረኩ እራሱን ከምርጫዉ ቢያገል አገዛዙ «ፀረ-ሰላምና ሽብርተኛ ናቸዉ» በማለት የመድረክ አባል ድርጅቶችን ሕጋዊነት ሊነጥቅ እንደሚችል መቼም መገመት አይከብድም። ሕጋዊነት ከሌለ ደግሞ በግልጽ አገሪቷ ዉስጥ መንቀሳቀስ አይቻልም። ስብሰባዎች፣ ሰላማዊ ሰልፎች ማናቸዉም አይነት ዝግጅቶች በመድረኩ ሊዘጋጁ አይችሉም። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጽ/ቤት ይዘጋል። አነሰም በዛም አሁን በአገር ቤት እያየነዉ ያለዉ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ይዳፈናል። ትግሉ የሚመራዉ አካል ያጣል። በሌላ አባባል አንድነት ፓርቲም ሆነ መድረክ የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነዉ።

መድረኩ ሲከስም ደግሞ መድረኩ እያደረገ ያለዉን ትግል ተክቶ ሕዝቡን የሚያደራጅና የሚመራ አካል በቀላሉ ከወዴት ሊመጣ ይችላል? በዉጭ አገር ያሉ ድርጅቶች ሕዝቡን የማደራጀት ሃላፊነት ሊወስዱ ይችላሉን ? አይችሉም። ይኸዉ ለ19 አመታት አላየንም። በመሆኑም መድረኩ ከምርጫዉ በመዉጣት በሕልዉናዉ ላይ አደጋ መጣል ስለሌለበት ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አራት በሉ።

መድረኩ በምርጫ ሂደት መሳተፉ በራሱ ያማጣቸዉ ውጤቶች አሉ። በየክልሎቹ እየሄደ ሕዝብን በማደራጀት ላይ ይገኛል። ሕዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲታገል፤ ከፍርሃት እንዲላቀቀ፣ በራሱን እንዲተማመን፣ ቀንበርና ግፍን በቃኝ እንዲል ቅስቀሳ እየተደረገ ነዉ። ይህ መድረኩ ከምርጫዉ በፊት የሚያደርጋችዉ እንቅስቃሴዎች ምርጫዉም ካለቀ በኋላ እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ነዉ ህዝብ ተደራጅቶ አገዛዙን መጋፈጥ የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር የሚችለዉ። በፊታችን የሚደረገዉን ምርጫ ኢሕአዴግ አሸነፈ ማለት ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ይገዛል ማለት አይደለም። ህዝብ የማደራጀት ሥራ በሚገባ ከተሰራ የሥርዓት ለዉጥ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ማምጣት ይቻላል። ነገር ግን ሕዝብን የሚያደራጅ አካል ከሌለ የዛሬ አምስት አመት ብቻ አይደለም፤ ለሚቀጥሉት ሃያ አመታት ኢሕአደግ መግዛቱ አይቀርም። በመሆኑም መድረኩ ሕጋዊነቱን እንደያዘ ቁልፍ የሆነዉ ሕዝብን የማደራጀት ሥራ ይሰራ ዘንድ የግድ በመሆኑ፣ መድረኩ ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አምስት በሉ።

መድረኩ ከምርጫዉ እራሱን ቢያገል ኢሕአዴግ «አጭበረበረ» ማለት አይቻልም። በፎርፌ አሽንፏል። አጭበረበረ ማለት የሚቻለዉ በምርጫዉ ተሳትፎ በርግጥ መስረቁን በማጋለጥ ነዉ። ምርጫዉ ከተደረገ በኋላ፣ ምርጫዉ እንደተሰረቀ መግለጫ በማወጣት የምርጫዉን ዉጤት ማጣጣል ይቻላል። ከላይ እንደጠቀስኩት የአለም አቀፉ ማህብረሰብ ብዙ ለዲሞክራሲ ጉዳይ ቦታ አይሰጥም። ለዉይይት ያህል ግን፣ ግድ ይሰጣል ብለን ብንቀበል እንኳን፣ ገዢዉን ፓርቲን ማሳጣት የሚቻለዉ በምርጫዉ ባለመሳተፍ ሳይሆን ተሳተፊ ሆኖ ምርጫ መጭበረበሩን በማሳየት ነዉ። በመሆኑ መድረኩ ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ስድስት በሉ።

«ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ እንዴት መድረኩ ምርጫ ይገባል» የሚሉ ወገኖች አሉ። በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ ዉስጥ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ቀዳሚ አጀንዳ አደርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለዉ ብቸኛ ድርጅት የአንድነት ፓርቲ ነዉ። የአንድነት ፓርቲ በሚያደርጋችዉ ህዝባዊ ስበባዎች ሁሉ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ሕገ ወጥ እንደሆነ በመቀስቀስ፣ ሕዝቡ እንድትፈታ እንዲታገል ግፊት እያደረገ ነዉ። በመስቀል አደባባይ የተጠራዉ ሰላማዊ ሰልፍ ቢከለከልም፣ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ የአንድነት አባላት የርሷን ጉዳይ ከማንሳትና ለርሷም ከመሟገት የቦዘኑበት ጊዜ የለም። በቴሌቭዥን በሚደረጉ ክርክሮች የብርቱካን ጉዳይ ይነሳል። የአንድነት ፓርቲ ወጣቶች የብርቱካን ኬኔተራን እየለበሱ ከኔቴራዉን በመሸጥ ታስረዋል። ለብርቱካን የሻማ ማብረት ዝግጅት ላይ ለመካፈል ሁለት ቀናት ሙሉ በእግር ተጉዘዉ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን አሉ። ትላንት «ስለብርቱካን ምንም አይባልም» እያሉ ሲከሱ የነበሩ፣ ዛሬ ደግሞ «የርሷን ስም አሥር ጊዜ እያነሱ መጠቀሚያ እያደርጓት ነዉ» እስኪሉ ድረስ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩ የብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ዋና አጀንዳዉ አደርጎ እየተንቀሳቀሰ ነዉ።

መድረኩ ከምርጫዉ እራሱን ቢያገል በምን ሂሳብ ነዉ ብርቱካን ሚደቅሳ ልትጠቀም የምትችለዉ ? ይልቅስ አንድነት/መድረኩ ሕልዉናዉን ቢያጣ በአገር ዉስጥ የብርቱካን አድቮኬት(ተቆርቋሪ) ሊሆን የሚችል ማን አለ ? የትኛዉ አካል ነዉ በርሷ ጉዳይ ከፈረንጆች ጋር በአገር ቤት የሚነጋገረዉ ? ማነዉ በርሷ ጉዳይ ህዝብን የሚቀሰቅሰዉ? ማን ነዉ፣ አገር ዉስጥ ካሉት፣ የብርቱካንን በግፍ መታሰር የአለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገዉ ? በእዉኑ እንነጋገርና የመድረኩና የአንድነትቱ መኖር ነዉ ወይስ መጥፋት ለብርቱካን መፈታት የሚጠቅመዉ ?

ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ ለምንመለከት መልሱ ቀላል ይመስለኛል። በመሆኑም ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳትረሳ፣ በአገር ዉስጥ የብርቱካን ትፈታ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር መድረኩ መኖር አለበት። በመሆኑ መድረኩ ምርጫዉን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ሰባት በሉ።

ብዙዎቻችን ምርጫዉን እንደቀልድና ጨዋታ ብንወስደዉም ሕዝቡ ዉስጥ የታመቀዉ የነጻነት እሣት ተአምር ሊፈጠር እንደሚችልም መዘንጋት የለብንም። በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች በምርጫ ዘጠና ሰባት እንደታየዉ፣ ህዝቡ በየወረዳዉ በራሱ አነሳሽነት ተነሳስቶ በፊቱ ድምጹ እንዲቆጠር ሊያስገድድ ይችላል። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ምን ያህል የሰፋ እንደሚሆን ለማወቅና ለመተንበይ ይከብዳል። ቢሆንም የሕዝብ ተዓምር የመሥራት እድልንም ስለሚከፍት መድረኩ በምርጫዉ ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ስምንት በሉ።

ዉድ ኢትዮጵያዉያን፡ አንዳንዶቻችን ትግሉን ከምርጫ ጋር ብቻ እናገናኘዋለን። ትግሉ ከዚያ ያለፈ ነዉ። አንዳንዶቻችን ትግሉ የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ እናደርገዋለን። ትግሉ ከግለሰቦች ያለፈ ነዉ። ትግሉ የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱን ነጻነቱ ተከበሮ፤ የአገሩ ባለቤት ሆኖ፣ የሚኖርበትን ሥርዓት ለመገንባት ነዉ። ይህ አይነቱ የነጻነትና የመብት ጥያቄ ደግሞ እስካልተመለሰ ድረስ ትግል አይቆምም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳለችዉ «ሰዉ ያለ ነጻነቱ ምንድን ነዉ ?»

አንድ ተብሎ በመቁጠር ነዉ ወደ ሁለት የሚኬደዉ። እየወደቁ፣ እየዛሉ ነዉ ወደፊት የሚገሰገሰዉ። የአገራችን ጉዳይ ጨዋታ አይደለም። የአገራችን ጉዳይ በግለሰቦች በማዘናችን የምንተወዉ አይደለም። የአገራችን ጉዳይ የሕልዉናችንና የማንነታችን ጉዳይ ነዉ።

መድረኩ ከምርጫዉ እራሱን እንዲያገል ጥሪ እያቀረቡና ግፊት እያደረጉ ያሉ ወገኖች በርግጥ ያሉትን ሁኔታዎች በሙሉ በጥሬዉ ካገናዘቡ ሃሳባቸዉን ይቀይራሉ የሚል እምነት አለኝ።

አይ አሁንም« በምርጫዉ መሳተፍ አይገባም» የሚል አቋም የሚይዙ ወገኖች ካሉ ደግሞ የመከራከሪያ ነጥባቸዉን ለመስማት ዝግጁዎች ነን። አንድ ሁለት ብለዉ የምርጫዉን ቦይኮት ጥቅም ያሰረዱን። ያላቸውን አማራጮች ያቅርቡልን። መከሰስ፣ መተቸት፣ መሳደብ በጣም ቀላል ነዉ። ምፍትሄ ማምጣት ግን ፍጹም የተለየ ነገር ነዉ። ሌሎች ድርጅቶች የሚሰሩትን ማጣጣል አንድ ነገር ነዉ። ሰርቶ ማሳየት ግን ሌላ ነገር ነዉ።

እዚህ ላይ ላይ አቆማለሁ። ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!

http://nazret.com/blog/index.php/2010/05/02/ethiopia_a_4840_a_4938_a_4723_a_4733_a_4_4621?blog=15

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: