Leave a comment

ቃለ መጠይቅ ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በ21/1/2ዐዐ5 ዓ.ም.


ቃለ መጠይቅ ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በ21/1/2ዐዐ5 ዓ.ም.ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

ይህ ቃለ መጠይቅ ሰኞ በ21/1/2ዐዐ5 ዓ.ም. በኘሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መኖሪያ አፓርትመንት ውስጥ
በሚገኘው የግል–ቢሮአቸው የተካሄደ ሲሆን በአቶ መለስ ሞት ዙሪያ፣ ትተዋቸው ባለፏቸው —
መታሰቢያዎች(legacy)፣ እንዲሁም በመፃዒ የኢህአዴግ እና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዎች ላይ ያነጋገራቸው የሰማያዊ
ፓርቲ ልሳን የሆነው የ“ሰማያዊ” ሚድያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ነው፡፡ መልካም ንባብ! መልካም ንባብ!
ሰማያዊ፡- በቅድሚያ ለቃለ-መጠይቁ ስለተባበሩን በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ በቀጥታ ወደ ጥያቄው ስገባ፡-
በጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ሞት ምን እንደተሰማዎ ቢገልፁልንና ከዚያ ብንጀምር…..
ኘሮፌሰር መስፍን፡- የአቶ መለስ ሞት ድንገተኛ ነው፤ ድንገተኛ በመሆኑም ያስደነግጣል፡፡ ለማናችንም ቢሆን ሞት
የማይቀር መሆኑንም ብናውቅ፤ እንኳን እንደዚህ በድንገት ሲሆንና ታመውም ቆይተው በሚሞቱበት ጊዜ ማዘን
አይቀርም፡፡ ምንም አይነት ሰው ይሁን! እኔ በመለስ ሞት ያደረብኝ ስሜት፤ ከዚህ በፊት በጠ/ሚኒስትርነቱ ወይም
በኘሬዚዳንትነቱ አሊያም በፈላጭ ቆራጭነቱ ያደረገው ነገር አይደለም፡፡ድንገት በመሆኑ፣ ዕድሜ ለንስሃ ሳያገኝ
መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ …… እና …. መቼም…..እእእ….. የሱ ሞት ለብዙዎቻችን እንደዚሁ እንደማንም እንደሰው የሰው
ባህርይ ሆኖ የመጣ መሆኑን ብንገነዘበውም፤ ለጓደኞቹ ደግሞ እንደዚህ አልነበረም ይመስለኛል፡፡ እነሱ ይበልጥ
የደነገጡ፣ የተደናበሩ፣ ሞትን ለመደበቅ የሞከሩ፣ የማይደበቀውን ለመደበቅ የሞከሩ በመሆናቸው ትንሽ የመለስን
ሞት እእ….. አንድ ያጠላበት አጉል ነገር ነበረና እሱ ያሳዝናል፡፡ እሱም በራሱ በኩል ሆነ፤ ለርሱም የሚቆም ሰው-
የሚመለከተው፣ ለቤተሰቡ ያ ሁኔታ እና ለመደበቅ የተደረገው ሽር-ጉድ (እስካሁንም ድረስ ብዙ ነገር ተደብቋል) ያ
ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል- ከሞቱም ይበልጥ ያሳዝናል-አሟሟቱ! ይኸው ነው፡፡

ሰማያዊ፡- በዚህ ዙሪያ ግን በዚያን ሰሞን በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት
አቶ በረከት ሰምኦን ተጠይቀው፡- “ይሄ በፓርቲያችን የተለመደ ባህል ነው፤አዲስ አይደለም፡ ፡ የአንድ ሰው
መታመም ወይም መሞት ብዙ ስለማያስደንቀን በአደባባይ መግለፁንም ያን ያክል አሳሳቢ አድርገን አናየውም”
ብለው ነበረ፡፡ በዚህ ረገድ ሌሎች ደግሞ፡- “የኢትዮጵያ ህዝብ የማወቅ መብት ነበረው፤ ሊደበቁ የሚገቡ ነገሮች
ብሔራዊ የደህንነት ምስጢሮች ወይም የመከላከያ ምስጢሮች ተብለው ሊያዙ የሚችሉ የመኖራቸውን ያህል ስለአንድ የአገሩ ጠቅላይ-ሚኒስትር ግን ለዚያውም የህዝብ ኃላፊነት ቦታ እና ስልጣን እንደመያዛቸው፤ህዝቡ በይፋ
ማወቅ ይገባው ነበረ” ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጋናውን ኘሬዚዳንት ሞትና ወዲያው ለህዝቡ
በይፋ መገለፁን ብሎም በተገቢው ወቅት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መካሄዱን እንደአብነት ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡
እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ኘሮፌሰር መስፍን፡- እንግዲህ በረከት እኛ ሲል እነማን ናቸው እነሱ? እኛ የሚለው! እንደዚህ ልዩ ባህል ያለው!
የተለየ የሆነው! ከኢትዮጵያ ህዝብ ባህል፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ልማድ ውጭ የቆመ ማን ነው እሱ? ማነው በረከትና
ቡድኑ? ኢህአዴግን እንደሆነ ኢህአዴግ አንድ የፖለቲካ ቡድን ነው፤ግንባር ነው፤ ብዙዎች አሉበት ውስጡ-ሰዎች!
አሁን እንደዚህ ‘መርዶ ባህላችን አይደለም’ ሲሉ ከዚህ በፊትም ሰምቻለሁ በሌላ አጋጣሚ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ
ውስጥ ነው ያሉት እኮ! የኢትዮጵያን ህዝብ ነው የሚያስተዳድሩት፤ ለኢትዮጵያ ህዝብም ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ካልሆነ ይሄ የተለመደው የነሱ ግዴታቸውን ቸል የማለት እና ‘እኛ ነን ሁሉንም ነገር የምንወስነው- ልማድንም
ባህልንም የምንወስነው እኛ ነን፤ ከእኛ በላይ ማንም የለም! ህዝቡም ቢሆን የራሱ ባህል የለውም! የማወቅም
መብት የለውም፤ ማለት ይችላል በረከት ከዚህ በፊት በሌላም ነገር እንዳለው፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅድም እንዳልኩት፡-
በመለስ ሞት ምክንያት ተደናብረው እንጂ በረከት ስቶት አይደለም፡፡ በመሆኑም፡- በድንብርብር ውስጥ ሆነው
አንዴ ‘ታሟል!፣ አንዴ ‘ደህና ነው!፣ አንዴ አሁን ነው!፣ “እንዲህ ነው…. እንዲህ ነው….” እያሉ ቆይተው ስለነበረ፤
በእውነቱ የነሱን መደናበር እና በትክክለኛው አእምሮ ውስጥ እንዳልነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡
ሰማያዊ፡- በአቶ መለስ ሞት ላይ መደናበሩን ምን አመጣው ይላሉ?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ስለራሳቸው ነውኮ እነሱ የሚደናበሩት እንጂ መለስማ ሞቷል፡፡
ሰማያዊ፡- ለማለት የፈለግሁት፡- ‘የፖለቲካ ድርጅት ወይም ቡድን ነን፣ የምንመራበት መስመር አለን የሚሉ
እስከሆኑ ድረስ በቀጣይነት ተተኪው ነገር….
ኘሮፌሰር መስፍን፡- አልተዘጋጁም! ድንገተኛ ነበር ይሄ ነገር፡፡ በእርግጥ እንዲህ ቢሆን እንዲህ እናደርጋለን ብለው፣
ህጉ ግልፅ ሆኖ ፣ የሚፈለግ ሰው ወዲያው የሚተካ ቢሆን፤ አንዳንድ አገር…. ቅድም እንደተናገርከው ጋና እንደዚህ
ሆኗል፡፡ እ… አሜሪካ ኬኔዲ በሞተ ጊዜ ምክትል ኘሬዚዳንቱ ወደዋሽንግተን ሲመለስ አውሮኘላን ላይ ቃለ-መሐላ
ፈፀመና ኘሬዚዳንት ሆነ፡፡ እንደዚህ በቀጥታ ህጉ የሚከበርበት አገር ምንም ችግር የለም፡ ፡ እዚህ ህጉ እኮ እነሱ
በፈለጉት መንገድ እንዲሄድ ነው የሚፈልጉት፡፡ እና አሁንም በህጉ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ይግባ ከተባለ፣ አሁን
ያለው ምክትል ጠ/ሚኒስትር ይግባ ከተባለ እነሱ ያንን የጠ/ሚንስትርነቱን ቦታ እንዲይዝ ይፈልጉታል ወይ? ወይስ
ደግሞ ሌላ ያንን ቦታ የሚፈልግ አለ? ሌላውም ቦታውን በሚፈልጉትና ይህ ሰው እዛ ቦታ ላይ እንዲሆን
በማይፈልጉት መሃከል ፉክክር ይነሳል፡፡ ያ ፉክክር ነው እንግዲህ መደናበር ውስጥ የከተታቸው፡፡ ምን እናድርግ?
ምን እንሁን? እንዴት እናድርገው? እንዴት እንስማማ? በሚሉና በረድ ብለው በሰከነ አይምሮ እስኪወስኑ ድረስ
መጀመሪያው ላይ በጣም ተደናበሩ፡፡ ያ መደናበር ነው ያን ሁሉ ነገር ያመጣው የሚመስለኝ እኔ፡፡

ሰማያዊ፡-ምናልባት ይሄ “ሥልጣን ባህልና እና አገዛዝ” በሚል መጽሐፍዎ ላይ ያነሱት “ሥልጣንን እስሁንም ድረስ
መግራት አልቻልንም-እንደኢትዮጵያውያን!” ብለው ነበር፡፡ እና ከዚያ ጋር የሚያያዝ ነፀብራቅ ይኖረው ይሆን?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ሁልጊዜም አለ እሱ እኮ! እሱ ባህላችን ነው-አገዛዝን ሳንገራ አለን እስካሁን ድረስ፤ ታሪካችን
ነው፡፡ እና….. ውስጣችን ነው እሱ!

ሰማያዊ፡- ኢህአዴግ ግን አሁን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ሥልጣንን በማሸጋገር በገዥነት መቀጠል
እችላለሁ ብሎ በይፋ የሚናገር ድርጅት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ያሉት ነገሮች (ከመጋረጃ ጀርባ ያሉት እንደተጠበቁ
ሆነው) እስካሁን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የተደረገ ያስመስላል፡፡ እና ምናልባት ይሄ ኢህአዴግን ልክ ያሰኘው
ይሆን?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- አልገባኝም!
ሰማያዊ፡- ማለት ብዙዎች ከአቶ መለስ በኋላ የሚመጣው ስርዓት ያልተደላደለ፣ ሰላማዊ የማይሆን፣ ብዙ
የሥልጣን ሽኩቻ የሚኖርበት ሲሉ ተንብየውና ተንትነው ነበር፡፡ በአንፃሩ ግን የሆነው፡- ም/ጠ/ሚ የነበሩት አቶ
ኃ/ማርያም ደሳለኝ ናቸው በቦታው የተተኩት፡፡ እና ይሄ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በዚች አገር አለ ሊያስብል
ይችላል?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ገና ነን እኮ! አሁን ለሁሉም የተመቸ በመሆኑ የኃ/ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትርነት አፀደቁ፡፡
ነገር ግን የኃ/ማርያም አሠራር በሥልጣኑ መጠቀም ሲጀምር ከማን ጋር ይሰለፋል? ከነማን ጋር አይሰለፍም? ማንን
ያስቀይማል? ማንን ይደግፋል? በየትኛው መስመር ይሄዳል? ገና ነው….. ገና አልተጀመረም፤ ይሄ ሁሉ ሆኗል! ደህና
ተረጋግቷል! ሰላም ነው! ምን የሚባል ነገር የለም ለኔ፡፡ ገና ነው! ጊዜ ይፈልጋል ይሄ፡፡
ሰማያዊ፡- አቶ መለስ በጠ/ሚኒስትርነት ዘመናቸው ብቁ አመራር ነበራቸው! የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዓለም-አቀፍ
መድረክም በአገር-አቀፍም አስማሚ ሰው ናቸው! ሁሉንም ከሞላ ጐደል አቻችለው ይሄዱ ነበረ ብለው የሚያምኑ
አሉ፤ የለም እሳቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጥሱ በስልጣናቸው ብቻ ሲያስቡ የኖሩና ለአገር ደግሞ
ብዙም ግድ የሌላቸው ናቸው! የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ መሃል አሁን በተያዘው የኘሮፖጋንዳ ስራ ላይ አቶ መለስን
እንደቅዱስ የሚስሉ ክስተቶች አሉ፡፡ የሁሉ ነገር ባለራዕይ፣ ሃሳብ አመንጪና የልማት ሁሉ አርበኛ እስከማለት
የደረሱ አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ፡- የሰብዓዊ መብትን የደፈጠጡ፣ ብዙዎችን ያሰሩ፣ የኘሬስ ነፃነትን የተጋፉ፣
እንዳሻቸው ህግን በአንድ ዕለት ያወጡ ናቸው ብለው የሚኮንኗቸው አሉ፡፡ የርስዎ አስተያየት በዚህ ላይ
ምንድነው?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ይሄ እኮ ምን….. ለኔ ጥያቄው ባዶ ነው፡፡ ባዶ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው…. መለስን
እየካቡ የሚናገሩት ሰዎች እነማን ናቸው? ሊክቡት የሚገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከሱ ጋራ የተሰለፉ ሰዎች ናቸው፡፡
ከዛ ሌላ ከዛ ውጪ ሊወጡ አይችሉም፡፡ ስለዚህ እነሱ ያንን የተናገሩት ለነሱ እውነት ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ፡-
የለም መለስ ስልጣንን ጨብጦ ለራሱ ብቻ ይዞ ሲጠቀምበት የነበረ ጉልበተኛ ነው፤ አምባገነን ነው የሚሉ ሰዎች የፖለቲካ ቡድኑ የስልጣን ተካፋይ እንሁን ብለው የሞከሩ ያቃታቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የነሱም ልክ ነው፡፡ በነሱ
በኩል ሆነህ ስታየው፡፡
ስለዚህ ይሄንን ልታወዳድረው አትችልም፡፡ ይሄም ከሱ በኩል ሆነህ ስታየው ልክ ነው፤ ያኛውም ከሱ በኩል ሆነህ
ስታየው ልክ ነው፡፡ እንደው በኢትዮጵያዊ ዓይን ብቻ ከፖለቲካዊ የስልጣን ትግሉ ወጣ ብለህ ልመልከተው
ያልከው እንደሆነ ግን፤ መለስ የአርቆ ማስተዋል ችሎታ አለው ብዬ እኔ አልገምትም፡፡ ይሄንን አርቆ ማየት
አለመቻሉን እኮ አሟሟቱ ራሱ ይገልፀዋል፡፡ በደንብ አድርጐ ይገልፀዋል-ለእኔ፡፡ አሟሟቱ፣ የፓርቲው
መርበድበድ፣ መረበሽ ይሄ ሁሉ ቀደም ብሎ ያልታየ ያልታሰበበት ነገር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም
መለስ…. እ…. ኖረ ለማለት እንኳን እኔ በእውነት አልችልም፡፡ በፍርሃት ኖሮ….. ከቤቱ ወጥቶ አውሮኘላን ማረፊያ
እስኪደርስ ድረስ ስንት ወታደር በየመንገዱ ላይ ቆሞ በዚያ ዓይነት ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ የኖረ ሰው ነው፡፡
እ…. ምናልባት ለራሱ ትንሽ ነፃነት ቢሰጥና ያንን ነፃነትም ለሌሎች እንደዚሁ ቢያስተጋባ ምንአልባት ልንገራችሁ
ከማለት ብቻ ወጥቶ የማዳመጥም (የማይፈልገውንም ነገር ቢሆን የማዳመጥ) ችሎታ ቢያዳብር ኖሮ በብዙ ነገር
ችሎታውን ይስልለት ነበር፡፡ እ…. ለኢትዮጵያም ህዝብ….እንደው ከልብ እ…..እንደው ከሱ ኋላ መቆም
የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አያቅተውም ነበር ይመስለኛል፡፡ ግን ሁሉንም እንደጠላት አድርጐ በመገመት
ሊያደርግ የሚችለውን ሊያስማማው የሚችለውን ኢትዮጵያንም ሊለውጣት የሚችለውን የኢትዮጵያን ህዝብም
ሊለውጥ የሚችለውን ነገር ሁሉ አደረገ- ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለማለት አልችልም እኔ፡፡ እ…..እሱ የሚፈልገውን
ነገር፣ እሱ በሚፈልገው መንገድ፣ እሱ ባለው ጊዜ አድርጓል፡፡ ያ ስንት ሰው አስከፍቷል? ስንት ሰውስ ጐድቷል?
ስንት ሰው አስደስቷል? ይሄ እንግዲህ ታሪክ-ፀሐፊዎች ወደፊት የሚናገሩት ነገር ነው፡፡
ሰማያዊ፡-ስለዚህ ምናልባት ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ አለመሆናቸው ኢትዮጵያዊነታቸው ላይ የጥያቄ ምልክት
ያሳርፍ ይሆን?
ኘሮፌሰርመስፍን፡- እኔ ኢትዮጵያዊነቱ ላይ የጥያቄ ምልክት አላስቀምጥም፡፡ ኢትዮጵያዊነቱ ሌላ ነገር ነው፡፡
በተፈጥሮው ያገኘው ነገር ነው-ማንም ሊወስደው አይችልም፤ እሱ ራሱ እኔ አይደለሁም ካላለ በቀር እንደኢሳይያስ
አፈወርቂ! ይሄ ሲወለድ ያገኘው ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ አይደለህም ሊለው አይችልም፡፡ ማንም ሌላውን ሰው
አንተ ከእኔ ያነስክ ኢትዮጵያዊ ነህ በኢትዮጵያዊነት ብሎ ማለት የሚችል የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሚዛን በእጁ
የጨበጠ አንድም ሰው የለም፡፡ ሁላችንም እኩል ነን፡፡ ሁላችንም እንደታየን፣ እንደተሰማን፣ እንዳስተዳደጋችን፣
እንደትምህርታችን” ኢትዮጵያን ሀገራችን ኢትዮጵያውያንን ወገናችን ብለን እንሰየማለን፡፡ ነገር ግን አንተ ያነስክ
ኢትዮጵያዊ ነህ፤ አንተ የተሻልክ ኢትዮጵያዊ ነህ ማለት የሚቻልበት መንገድ ምንም የለም፡፡ ስለዚህም፡- መለስ
ከማናችንም የማያንስ ከማናችንም የማይበልጥ ነው- በኢትዮጵያዊነቱ፡፡ ያንን እሱ ራሱ እንደፈተለው ነው
የሚሸመነው፡፡
ሰማያዊ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች የሚያነሱት፡- ከ97 ወዲህ ምርጫውን ተከትሎ ነው ኢህአዴግ
የኢትዮጵያን ህዝብ የልብ ትርታ እየገመተ ከተቃዋሚ ጐራውም ቢሆን አጀንዳዎችን ኮርጆ የባንዲራ ቀን
እስከማክበር፣ ብሔር-ብሔረሰቦችን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር እስከማቀፍና ብሔራዊ አጀንዳ የሚባሉ ነጥቦችን
ማንሳት ያጐላው ብለው የሚያዩ አሉ፡፡ እና በዚህ ረገድ አቶ መለስም በታሪክ ትተው ለማለፍ የፈለጉት ነገር ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ሲሆን ይህን ሃሳባቸውን ሳያሳኩት በአጭር ባይቀጩ ኖሮ ብዙ ህልም ነበራቸው የሚሉ
አሉ፡፡ ከክልላዊ ማዕቀፍ ይልቅ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን የሚያጐሉ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደነበርም
በቁጭት ያነሳሉ፡፡ በህይወት ኖረው ቢቀጥሉ ኖሮ የብሔር ፖለቲካውንና በዚሁ ላይ የቆመውን አወቃቀር
እያሻሻሉት በሂደት እየቀየሩት ይሄዱ ነበር ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ እዚህ ላይስ የርስዎ አስተያየት?’
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ምን እላለሁ በዚህ ላይ? ምን አውቃለሁ? እነዛ የሚያውቁ ሰዎች የሚያውቁትን ነገር ሲነግሩን
ምናልባት እንነጋገር ይሆናል፡፡ እኔ ምንም አላውቅም፤ ስለዚህ የሰማሁት ነገር የለም፡፡ እኔ መለስ በሚያደርጋቸው
ነገሮች በሚናገራቸው ነገሮች ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ ብዙ ብያለሁ፣ ፅፌያለሁ፣ ተናግሬያለው፡፡ እና አሁን
መለስ የለም! መለስ ከሞተ በኋላ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ብዬ እሱን ለመውቀስ አልፈልግም፡፡ እኔ ከወደቀ እና
ከሞተ ጋር መታገል አልወድም፡፡ ከመንግሥቱ ኃ/ማርያምም ጋር ከኃይለ ሥላሴም ጋራ! አንድ ጊዜ ከሄዱ በኋላ
ከነሱ ጋር መታገል አያሻም፡፡ መታገል ኃይል ካለው፤ ሊያናግርህ ሊያነጋግርህ ከሚችል ኃይል ጋር ነው፡፡ ከሌለ
ኃይል ጋራ ስለሱ ስላለፈው ነገር ማውራቱ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ተናግሬዋለሁ ደግሞ! ያልተናገርኩት ነገር
የለም፡፡ መለስ ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፤ በተናገራቸው ነገሮች ሁሉ እሱ ባለበት ጊዜ ተናግሬዋለሁ፡፡ እና አሁን
ትርፍ ነው፡፡ እንደ ስብሐት ነጋ አልሆንም! ማለት…. ማንትሴ ሞተ ማንትሴ ሞተ መለስም ሞተ! የሚባለው ነገር….
እኔ እንደዛ ዓይነት ድረስ አላወርደውም፡፡ እ…. ግን….የለም አሁን፡፡ በሌለበት ይሄን አደረገ- ይሄን አደረገ- ይሄን
አደረገ ብለን መነጋገሩ ለኔ ለህሊናዬ ምንም ዋጋ የለውም፡፡
ሰማያዊ፡-ከአቶ መለስ ሞት በኋላስ የኢህአዴግና የኢትዮጵያ ዕጣ – ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ይሄ….. በምን?…. እኔ….አላውቀውም በውነቱ፤ ጠንቋይ አይደለሁም! ነገሩ….. ሰዎች ሁላችንም
በጐ መንፈስ ካደረብን ብዙ ነገር ካለፉት 21 ዓመታት ልንማራቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመለስ ሞት ራሱ
ያስተምረናል-ሁላችንንም! የኢህአዴግም ሌሎቹንም ያሉትን ባለሥልጣኖች ይሄ ሊያስተምራቸው ይገባል፡፡ የአቡነ
ጳውሎስ አለመኖር ሊያስተምር ይገባል- ሌሎቹን ጳጳሳት፤ ሌሉቹን መንፈሳዊ መሪዎች! እና እንዲህ ነው፡፡
ዕድሜያችን በጉልበትም እንኳን በሃይለኞችም እንኳን ባይቀጭ፤ ኃይለኞችም ብንሆን ጉልበተኞችም ብንሆን፤ ከላይ
ደሞ የሚመጣ ያንኑ ህይወት የሚቀጨው ሞት አለ-ሁልጊዜ፡፡ በተፈጥሯችን ሰው በመሆናችን ያለ ነገር ነው፡፡
ስለዚህ በጐ መንፈስ በላያችን እንዲያድር ብናደርግ፣ መርዝ ለመንዛት ባንጥር! ምሳሌ፡- የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን
ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተመልክቶ ስብሐት ነጋ ይሄ ሆነ ብለን ያደረግነው እና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር
ከኦርቶዶክስ እና ከአማራ እንዲወጣ ለማድረግ ያደረግነው ነው አለ፡፡ ይሄ አባባል መርዝ ነው፡፡ መርዝነቱ እንዴት
ነው…. ኃ/ማርያም ደሳለኝ ማነው ብለው ለማያውቁ ሰዎች ኃ/ማርያም ደሳለኝ አማራ አይደለም፤ ኃ/ማርያም
ደሳለኝ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አይደለም ብሎ ለማወጅ ነው ስብሐት ነጋ የፈለገው፡፡ እነዚህን ሁለት አስፈላጊ
ያልሆኑ ነገሮች ለማወጅ ደግሞ አማራን እዛ ውስጥ አስገብቶ ይጨፈልቀዋል፡፡ ያንን ጥላቻውን ያመጣል፡፡ ይሄ
መርዝ ነው- ሁለቱም! ኃ/ማርያም ኦርቶዶክስ ሆነ አልሆነ፤ አማራ ሆነ አልሆነ እኔ እንደሚመስለኝ ለኔ ጉዳዬ
አይደለም፡፡ በፍፁም! ከሚዛን ውስጥ የሚገባ አይደለም ሁለቱም፡፡ ሚዛን ውስጥ የሚገባው እንዴት ነው?
ለምሳሌ፡- ሃይማኖቱ ሚዛን ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በኃ/ማርያም ደሳለኝ በራሱ አንደበት ያነበብኩት እኔ እውነት
ከሆነ፣ እውነት ብሎት እንደሆነ እውነት ተናግሮት እንደሆነ ‘ለእናቴ እፀልያለሁ አልዳነችም’ የሚል ነገር
አንብቤያለሁ ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ይሄ በጣም በጣም አስደንጋጭ ነው! እንኳን ለአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአንድ መደበኛ ፖለቲከኛም እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ እንደዚህ ዓይነት አስተያየት አደገኛ ነው፡፡ እናቱን፣
ኃ/ማርያም ብለው ስም ያወጡለትን ሰው ‘አልዳኑም…. እኔ ድኛለሁ!’ …. በዛ ሂሳብ 99.9 የኢትዮጵያ ህዝብ
አልዳነም- ከኃ/ማርያም ደሳለኝ ጋራ፡፡ ያ አደገኛ ነው፡፡ ይሄ ዳነ አልዳነም አደገኛ ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር
ስም በማይጠራበት ቦታ ላይ እግዚአብሔርን የሚያምን ሰው፣ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለው ሰው እዛ መቀመጡ
ምንም የሚያሰጋ ነገር የለበትም፡፡ የሚያሰጋው ‘እኔ ድኛለው እናንተ አልዳናችሁም! ዳኑ! መዳን አለባችሁ!’ ብሎ
ሊያስገድደን የመጣ ጊዜ ያን ጊዜ ችግር ይፈጠራል፡፡ ፖለቲከኛ መቻቻልን ሁሉንም የሚችል…. ድነሃል አልዳንክም
የሚባል አይደለም፣ ሁላችንም አብረን እንሂድ! አንተም በሃይማኖትህ ድነሃል፣ ይሄም በሃይማኖቱ ድኗል፣ እናቴም
በሃይማኖቷ ድናለች የሚል እንጂ አልዳነችም እፀልይላታለሁ እንድትድን የሚል ለኔ ፀያፍ ነው ይሄ፡፡ እንደዚህ
አይነት አዝማሚያዎች በጊዜው እየታረሙ ካልሄዱ አደገኞች ናቸው፡፡ ከዚህም ከዚያም የሚሰነዘሩ አጉል ሃሳቦች፡፡
ግን በጐ-መንፈስ እንዲያድርብን እግዚአብሔርን እየለመን በሁላችንም ላይ በጐ መንፈስ ካደረብን መነጋገር
መወያየት ጀምረን ከችግራችን የምንወጣበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል፡፡
ሰማያዊ፡-የህዝቡን የሀዘን ስሜት በተመለከተስ? የለቅሶ ሥነ-ሥርዓቱ ለአንድ ሳምንት ያህል የተከናወነ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ መሪውን ለመቅበር ዕድል እንዳለማግኘቱም በአቶ መለስ ሞት ምክንያት የታየው
የለቅሶና የቀብር ክንውንስ ስለህዝቡ ስነ-ልቦና፣ ባህል ወይም ልማድ፣ እና ጠባይ ምን ይናገራል?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- እኔ… ምንም…እ…. እንደው በነገራችን ላይ ይሄ እኮ መለስን የሚመለከት ነገር አይደለም፡፡
መለስ የለም፡፡ ይሄንን አድርጉልኝ አላለም፡፡ ምናልባትም አይፈልግም ይሆናል ይሄንን፡፡ ይሄንን ያደረጉት እነማን
ናቸው? እኔ እውነቱን እና ውሸቱን ለይቶ ለማወቅ አልችልም- በአሁኑ ጊዜ፡፡ ግን ትንሽ ነው ያየሁት፤ ብዙም
አላየሁም፡፡ ካየሁት ያ እውነት የስሜት መግለጫ ከሆነ ያ ሁሉ ሰው ስሜቱን የገለፀው በእውነት ከሆነ መለስ ዜናዊ
የብዙ ሰዎቹን ኑሮ በጥሩ መልኩ ነክቷል፣ አሻሽሏል ማለት…እ…. እንግዲህ ያልታወቀ ስታትስቲክስ ከየት
እንደምናመጣው አላውቅም…እ…. አለ ማለት ነው፡፡ ግን በሌላ በኩል ደግሞ ሲነገር፡- ገንዘብ ተከፍሎ ምን
ተብሎ…. ይሄ ማንን ይጠቅማል? መለስ ዜናዊን አይጠቅመውም፡፡ ቤተሰቡን አይጠቅምም፤ የእሱን ታሪክ
አይጠቅምም፡፡ ከሱ ታሪክ ጋራ ይሄ ሌለው በተፃራሪ የሚባለው ነገር አብሮ ይመጣል፡፡ ስታበዛው….. ስላበዛኸው
ያንን በተፃራሪ መንገድ የሚመለከተው አስታኮ የሚያቀርበው ሃሳብ ሁሉ አፍራሽ ይሆናል፡፡ እና በእውነቱ ለሱ
የሚጠቅመው አይደለም-ለታሪኩም ጭምር፡፡ ለነገሩ ይሄ ማንንም የሚጐዳ አይደለም፡፡ ሰዎቹ ከፈለጉ
ተከፍሏቸውም ይሆን ሳይከፈሉ አለቀሱ፣ እዬዬ አሉ፣ ስሜታቸውን ገለፁ- መልካም! ምንም የሚያመጡት ነገር
የለም፡፡ ምንም የሚለውጡት ነገር የለም፡፡
ሰማያዊ፡- ነገር ግን ኢህአዴጎች ይሄንን ነገር ህዝቡ የአቶ መለስን ፈለግ እንድንከተል እና የያዙትን መንገድ
እንድንገፋበት ድጋፉን እየሰጠን ነው ብለው እንደማስመስከሪያ እየወሰዱት ነው…
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ይሄንን የጊዜውን ሁኔታ አትመልከተው፡፡ አሁን እኮ ገና በትኩሱ ነው፡፡ እያደር እኮ ይሄ ነገር
እውነቱ እየወጣ፣ እውነቱ እየወጣ፣ እውነቱ እየወጣ ሲሄድ፤ ብዙ ነገር ይገለጣል፡፡ አሁንም እየተገለጠ ነው
አንዳንድ ነገር፡፡ ክፍያው ምን ያህል እንደሆነ እንደዚህ አንዳንድ ሰዎች እየተናገሩ ነው በራዲዮ፡፡ እና መዋሸት
ማስዋሸት አይቻልም፡፡ አይጠቅምም፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡ እና እውነቱ ይመጣል፡፡

ሰማያዊ፡- ለኢህዴግስ የሚያስተላልፉት ምን መልዕክት አለ? አሁን ባለበት ወቅት ላይ ይሄን አካሄድ ትቶ ይሄን
አካሄድ ቢከተል ለአገር ይበጃል፤ ሁላችንንም ሊጠቅም ይችላል የሚሉት ሃሳብ ካለ ይሄንን እንደመደምደሚያም
አርገን ይቀራል የሚሉትንም ሃሳብ ጨምረው በዚሁ ቃለ-ምልልሱን ብንቋጭ…..
ኘሮፌሰር መስፍን፡- እኔ በነርሱ በኩል….እ…. ስልጣኑን ወደ ህዝብ ለህዝብ በእውነተኛ መንገድ በትክክለኛ መንገድ
የሚያስተላልፉበት ጊዜ የተቃረበ ይመስለኛል፡፡ ይህንን አውቀው እነሱ መንገዱን ቢጠርጉትና በተቻለ መጠን
የኢትዮጵያን ህዝብ አንገቱን ቀና አድርጐ በኩራት በክብር፣ መብቶቹ ሁሉ ተከብረውለት፣ በህጋዊ ስርዓት ውስጥ
ያለምንም ፍርሃት በሙሉ ነፃነት ኖሮ ወደብልፅግና ወደእኩልነት እና ወደነፃነት እንዲሸጋገር ቢያደርጉ የራሳቸውን
ታሪክ የሚያሳምሩ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያንም ስም ማደስ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ ሳይዘገይ ብዙ ችግር ውስጥ
ሳንገባ በተቻለ መጠን በበጐ መንፈስ ህዝቡን ቢመለከቱትና ቢደግፉት፤ እንዲደግፋቸው ቢያደርጉ ምናልባት
ብርሃን የምናይበት ቀን ይመጣ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ያለው የአፈና ስርዓት ይሄንን ቶሎ ብለው ማስወገድ
አለባቸው፡፡ አሁን የአፈና ስርዓት አለ፡፡
የታሠሩት ሁሉ በሆነ ባልሆነው ነገር፣ ለምን ተናገራችሁ? ለምን ፃፋችሁ? ተብሎ… ዛሬ….መፃፍ ይቻላል መናገር
ይቻላል- ኢትዮጵያ ውስጥ ባይሆን ውጭ ማሳተም ውጭ መናገር ይቻላል፡፡ እንደዛ ሁሉንም ሰው የተናገረውን
ሁሉ የፃፈውን ሁሉ አሸባሪ እያሉ ወህኒ ከተውት አይዘልቁትም፡፡ አያዛልቅም፡፡ እና ይሄንን ይሄንን ማደስ
አለባቸው፤ ማሻሻል አለባቸው፡፡ ከፈት ማድረግ አለባቸው፡፡ ከፍርሃታቸው ትንሽ ድፍረት ማግኘት አለባቸው፡፡
ወኔ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይሄን ሁሉ የሚያመጣው ፍርሃት ነው፡፡ ፍርሃት ጥሩ ስሜት አይደለም፤ ስለዚህ
እግዚሐር ከእዚህ ያውጣቸው ነው፡፡
ሰማያዊ፡- ምናልባት የቀረ የሚሉት ነገር ካለ….
ኘሮፌሰር መስፍን፡- ይኸው እኮ አልኩ! እግዚአብሔር ያውጣቸው ብዬ?! /ፈገግታ/

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s