Leave a comment

ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ የምርመራ መዝገቡ መዘጋቱ ሕገወጥና አደገኛ መሆኑ ተገለጸ


“አሁን ታስረው የሚገኙበት ሁኔታ ሕገወጥና አደገኛ ነው” ጠበቃ አመሐ መኮንን

zone9 free

በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በክስ ላይ የሚገኙት ሦስት ጋዜጠኞችና ስድስት ጦማርያን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ፖሊስ ‹‹ምርመራዬን ስለጨረስኩ መዝገቡ ይዘጋልኝ›› በማለት መዝገቡ እንዲዘጋ ማድረጉ ሕጉን ያልተከተለና አደገኛ መሆኑን ጠበቃቸው አስታወቁ፡፡

ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪያንና የሕግ መምህር ዘለዓለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃኔ ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሚቀርቡበት ዕለት ነበር፡፡ እንደወትሮው ሁሉ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ጓደኞቻቸውና የተለያዩ የችሎት ታዳሚዎች በጠዋት ማልደው በፍርድ ቤት ግቢ የተገኙ ቢሆንም፣ እስከ ቀኑ 5፡30 ሰዓት ድረስ ፖሊስም ሆነ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ችሎቱ አልመጡም፡፡ ከ5፡30 ሰዓት በኋላ ሌሎች ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎቹና ፖሊስ ችሎት ቆይተው ሲወጡ፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን፣ ደንበኞቻቸው ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረባቸውን ለማጣራት የዕለቱን ተረኛ ዳኛ ለማነጋገር ገቡ፡፡ ጠበቃው ስለደንበኞቻቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ፣ ፖሊስ ምርመራውን መጨረሱን በማሳወቅ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዘጋቱን ሲያስረዳቸው፣ ‹‹እንዴትና በምን ሁኔታ?›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከመዘጋቱ ውጪ ምንም ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

እስረኛ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የምርመራ መዝገቡ ሊዘጋ እንደማይችል የሚናገሩት ጠበቃ አመሐ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ መሆናቸው፣ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ምንም ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ በመሆኑ ድርጊቱ ሕገወጥና አደገኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ ምርመራውን ካጠናቀቀ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ይዞ በመቅረብ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳትና ክስ እስከሚመሠረትባቸው ድረስ በዋስ እንዲቆዩ ወይም የሕግ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ስለሚቆዩበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት እንደነበረበት አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ባልሰጠበት ሁኔታ ተጠርጣሪዎቹ ባሁኑ ወቅት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የሚናገሩት ጠበቃው፣ በወንጀል ሕጉና በሕገ መንግሥቱ በተጠሰው አካልን ነፃ የማውጣት መብት (ሐቢየስ ኮርፐስ) ክስ ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ የተካተቱት ጦማሪያን ማህሌት ፋንታሁን፣ አቤል ዋበላና በፈቃዱ ኃይሉ ደግሞ ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹም ሆኑ መርማሪ ፖሊስ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡

ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች ‹‹የመብት ተሟጋች ነን›› ከሚሉ የውጭ ኃይሎች ጋር በሙሉ ሐሳብና ገንዘብ በመስማማት ሕዝብን የማተራመስ፣ አገርንና መንግሥትን የማፍረስ ዘገባ በኢንተርኔትና በተለያዩ ድረ ገጾች ያልሆነ መረጃ ሲያስተላልፉ ተገኝተዋል በሚል ፖሊስ ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለሁለት ጊዜ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ከተፈቀደለት በኋላ፣ በሦስተኛው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ውስብስብና ድርጊቱም የሽብርተኝነት ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀን እንዲፈቀድለት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ ተፈቅዶለት መመርመር ላይ መሆኑን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 78 ቀናት ሞልቷቸዋል፡፡(ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር ጋዜጣ)

በጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ላይ የተከፈተው የጊዜ ቀጠሮ ፋይል ተዘጋ

“ደንበኞቼ አሁን ያሉበት ሁኔታ ሕገ-ወጥ ነው” ጠበቃ አመሃ መኮንን

ፖሊስ በሽብር ወንጀል ጠርጥሮ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ፤ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች መረጃዎችን ሲለዋወጡና በውጪ ሀገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስልጠና ወስደው፤ ህዝባዊ አመጽ ለመቀስቀስ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተው፤ በሕጋዊ መንገድ ስልጣን የጨበጠውን መንግስት በሕገ-ወጥ መንገድ ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ በሚል ከሁለት ወራት በላይ አስሮ በማዕከላዊ ምርመራ ላይ የቆዩት ዘጠኙ ጋዜጠኞችና የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን በፖሊስ ተከፍቶባቸው የነበረው የጊዜ ቀጠሮ ፋይል ተዘግቶ፤ ወደ ዐቃቤ ሕግ መመራቱን በድንገት ስለመስማታቸው የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አመሃ መኮንን አስታወቁ።zone9 ers

ባሳለፍነው ቅዳሜ እና ሰኞ (ሐምሌ 5 እና 7 ቀን 2006 ዓ.ም) በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት፤ በሁለቱ ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ የነበራቸው ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ባልቀረቡበት፤ የአያያዝ ሁኔታቸውን በግልፅ ለችሎቱ ባላስረዱበትና የዋስትና መብታቸውን ጠይቀው ምላሽ ባልተሰጠበት አኳሃን ጠበቃቸው ሲቀርቡ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ፋይሉን ስለመዝጋቱና በቀጣይ ጉዳዩ ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ደርሶ ክስ ሊመሠረትባቸው መሆኑን ከችሎት መስማታቸውን የሚናገሩት ጠበቃ አመሃ መኮንን፤ በፍርድ ቤቱ ፋይሉ የተዘጋበትን ሁኔታ በተመለከተ “የተለመደ አሠራር ነው” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። ጠበቃው ሒደቱን ስርዓቱን ያልተከተለና የደንበኞቻችንንም ሕጋዊ መብት የጣሰ ነው ሲሉ ይናገራሉ። በተለይም በሰኞው ዕለት (ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም) ቀጠሮ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ቀደም በማለት ተገኝተው እንደነበር ያስታወሱት ጠበቃው፤ ሦስቱም ተከሳሾች ማለትም በዕለቱ የተቀጠሩት ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉና አቤል ዋበላ ባልቀረቡበት፤ እንዲሁም አንድም የመርማሪ ቡድኑ አባል ባልተገኘበት ከመዝገቡ ጋር ተያያዞ በቀረበ ወረቀት አማካኝነት ብቻ መዝገቡ መዘጋቱንና ወደመደበኛ ክስ ለመግባት ዐቃቤ ሕግ ክስ እስኪመሰረት እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

መርማሪ ቡድኑ መዝገቡን አጠናቅሮ ከቀረበለት የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በቀጣዮቹ አስራ አምስት ቀናት ውስጥ ክሱን መስርቶ በፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚኖርበት የአሠራር ሂደት መኖሩን የጠቆሙት ጠበቃ አመሃ መኮንን፤ ደንበኞቻቸው መቼና የት እንደሚቀርቡ አሁን ድረስ አለማወቃቸውን አስረድተዋል። ደንበኞቼን በሙሉ ማግኘት አልቻልኩም። ለዚህም እስረኞቹን ለመጐብኘት ከዕረቡና ከአርብ ቀን ውጪ ክልክል መሆኑና በአንድ ቀን አንድ ሰው አንድ ደንበኛን ብቻ የማግኘት ገደብ መኖሩን እንደመሰናክል በመጥቀስ አሠራሩ ችግር እንዳለበትም አክለው ገልፀዋል።

“ደንበኞቼ አሁን ያሉበት ሁኔታ ሕገ-ወጥ ነው” የሚሉት ጠበቃው፤ ለዚህም የጊዜ ቀጠሮውን ሲሰማ የነበረው ፍርድ ቤት ታስረው ይቆዩ የሚል ትዕዛዝን ባልሰጠበት፤ አልያም ክስ ተመስርቶባቸው ክሱን የሚሰማው ፍርድ ቤት በእስር ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ ባላለበት ሁኔታ ውስጥ ከቅዳሜው 4 ሰዓት እና ከሰኞው 8 ስዓት ጀምሮ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ታስረው የሚቆዩበት ሁኔታ ሕጋዊ መሠረት የለውም” ሲሉ አስረድተዋል። ከዚህ ቀጣይ እርምጃቸው የሚሆነው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ በመመስረት ደንበኞቻችን ነፃ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተዘጋጀን ነው ብለዋል። (አሸናፊ ደምሴ፤ ሰንደቅ ጋዜጣ)

Posted by: Kumilachew Gebremeskel Ambo

Leave a comment