Leave a comment

“እኔ በአገሬ ጉዳይ ተስፋ አልቆርጥም”


5e0e419b4e9850f9724f18befdbd8b6c_XLለሁለት አስርት ዓመታት በተቃውሞ የፖለቲካ ጎራ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በተለያዩ ጊዜያት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እየመሰረቱ መርተዋል፡፡ ከስድስት ዓመታት ወዲህ መድረክን የተቀላቀሉት ፕሮፌሰሩ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፖለቲካው ንፍቀ ክበብ ጠፍተው ከርመዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ እቁባይ፤ ፕሮፌሰሩ የት ጠፍተው እንደከረሙ፣ ስለተቃዋሚ ፓርቲዎችና ኢህአዴግ ወቅታዊ እንቅስቃሴ፣ ስለመጪው ምርጫና ሌሎች ተያያዥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አነጋግራቸዋለች፡፡ የፕሮፌሰር በየነ፤ የት እንደጠፉ በመመለስ ይጀምራሉ፡-

ትንሹንም ትልቁንም ማሰር ለምን እንዳስፈለገ እኔ አላውቅም
አገራችሁ የጋዜጠኞች እስር ቤት ነው መባል አያስከብርም
መንግስትን እንወያይ ብለን ከጠየቅን ዓመት ሆኖናል

ሁለት አመት የተባለው በዝቷል፡፡ ለአንድ ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ሳባቲካል ሊቭ” (ለጥናትና ምርምር እረፍት መውሰድ ማለት ነው) ወስጄ አሜሪካን አገር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳስተምርና ምርምር ሳደርግ ቆይቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ያ ማለት ግን ከፖለቲካው እንቅስቃሴ ውጪ ሆኛለሁ ማለት አይደለም፡፡ ውጪም ሆኜ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እገናኝ ነበር፡፡ ምናልባት ደጋግሜ አገር ውስጥ በሚታተሙ የግል ጋዜጦች ላይ አለመታየቴ ይሆናል እንጂ የያዝነውን አጀንዳ ለማራመድ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅደው ደረጃ እየተንቀሳቀስኩ ነኝ፡፡

በእርግጥ እዩኝ እዩኝ የሚል አካሄድ የለኝም፡፡ ድሮውንም በተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባሁት በድንገት ወይም በግርግር አልነበረም፡፡ ኢህአዴግን ስለምጠላም አይደለም፡፡ የመርህ ልዩነት ስላለኝ ነው፡፡ እኔ በሌለሁ ጊዜ ታዲያ ትግሉን ሌሎች ያራምዱታል፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እየተከታተሉ የቆዩኝ ታጋዮች አሉ፡፡ በተረፈ ይሄው አለሁ፤ መጥቻለሁ፡፡
እንደዚያ ከሆነ እስቲ የወቅቱን የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ይግለፁልኝ …
እኔ መናገር የምችለው ስለመድረክ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተሰባስበን ፕሮግራማችንን በዝርዝር አስቀምጠን መንቀሳቀስ ከጀመርን አመታት አልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲባል ዝም ብሎ ኢህአዴግን ከመጥላት ወይም በጣም ስላናደደን፣ አሊያም ስለበደለ (እንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ጨምሮ) … የፖለቲካ ድርጅቶች አቋቁሞ “ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች” ዓይነት በቂ አይደለም፡፡ ብዙ የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ዝም ብለው ተቃዋሚ ነን ብለው እንደሚቀመጡ አወቃለሁ፡፡ እኔ ባለፉት ሀያ ዓመታት በተቃዋሚው አካባቢ ስንቀሳቀስ ያለኝ ግንዛቤ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚባሉት የተለያየ አላማ ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ኢህአዴግ ይጠቅሙኛል፣ ከኔ ፈቃድ ውጪ አይንቀሳቀሱም ብሎ የሚረዳቸው መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ በተለያየ ደረጃና በተለያየ አላማ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደቁጥራቸው የተለያዩ፣ በሚያግባባቸው መለስተኛ ፕሮግራም ዙሪያ እንኳን መሰባሰብ የማይችሉ ናቸው፡፡
በቁጥር የበዙ ቡድኖች ናቸው ያሉት፡፡ መድረክ ባስቀመጠው ራዕይ ዙሪያ ዲሞክራት ከሆኑ፣ አማራጭ አጀንዳ ካላቸው፣ ከኢህአዴግ ጋር የተደራጁ ፓርቲዎችን ጭምር አሰባስቦ የመጓዝ ፍላጐት አለን፡፡ እስከአሁን ባለው ሁኔታ ግን በመድረክ ዙሪያ ከተሰበሰቡት ወጣ ያሉቱ የጋራችን የሚሉት መለስተኛ ፕሮግራም ቀርጸው መንቀሳቀስ ያልቻሉ እንደሆኑ እውነታው ያሳያል፡፡ እርግጥ ነው ሙከራዎች ይደረጋሉ፤ ነገር ግን በሙጫ እንኳን ያልተጣበቀ ስብስብ ይሆንና ውዝግቡና መበታተኑ ይመጣል፡፡ እስካሁን ያለው የተቃዋሚው አካሄድ ወጥ አይደለም፡፡
መድረክስ ጤናው እንዴት ነው? በአንድ በኩል የ“አንድነት” እግድ አለ፤ ሰሞኑን ደግሞ “አረና” አቶ አስገደ ገ/ስላሴን ጨምሮ ያገዳቸው አባላት አሉ…
ከ“አንድነት” ፓርቲ በቀር የመድረክ አባላት አካባቢ ምንም ችግር አይታየኝም፡፡ አረና ውስጥ የተፈጠረው የሀሳብ አለመግባባት ነው፡፡ የሃሳቦች ልዩነት፡፡ ያንንም የአረና አመራር አጥርቶት አልፏል፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴው ተሰብስቦ የተወሰኑቱ በድርጅቱ ደንብና ስርአት መሰረት ራሳቸውን የማያርሙ ስለሆኑ እንዲገለሉ ተደርጓል፤ የተወሰኑት ደግሞ እንደታገዱ ታውቋል፡፡ የታገዱት አቋማቸውን አስተካክለው፣ የእገዳ ጊዜያቸውን ጨርሰው፣ ቆመንለታል ላሉት አላማ በጋራ መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ በማዕከላዊ ምክር ቤቱ ታገዱ የተባሉት የትግል ተመክሮ የሚያንሳቸው አይደሉም፤ በትግል ያደጉ ናቸው፡፡ መገለላቸውን የምንወደውና የምንፈልገው አይደለም፡፡ ነገር ግን አዙረው አይተው፣ ወዳቋቋሙት ፓርቲያቸውና ወደ ትግሉ ይመለሳሉ የሚል ምኞት አለኝ፡፡ ከዚያ ውጭ ከአረና ጋር የተያያዘ ችግር መድረክ ውስጥ የለም፡፡
“አንድነት” ከመኢአድ ጋር የውህደት ሂደት ላይ ነው፡፡ ይህ ከመድረክ ጋር ካለው ግንኙነት አንፃር እንዴት ይታያል?
ይሄ ፈጽሞ የማይጣጣም ነገር ነው፡፡ የ“አንድነት” የእገዳ ጊዜ አልፏል፤ ነገር ግን አንድነት በዚህ መሀል ማሟላት ያለበትን ማሟላት እንዳልቻለ ተግባሩ ያሳያል፡፡ ልዋሀድ የሚለው አካል መኢአድ፣ ወደ መድረኩ ገብቶ እንዲጣመር በጠየቅነው ወቅት፣ “በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላችሁን አቋም በፅሁፍ ግለፁልን” የሚል የትምክህትና የትእቢት ደብዳቤ የፃፈ ቡድን ነው፡፡ ያ አካል ከመድረክ ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም፡፡ ለእኛ የኢትዮጵያዊነት ሰጪና ከልካይነት፣ የትምክህት አስተሳሰብ ያለው ነውረኛ ደብዳቤ የሰጠ ድርጅት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ቁምነገር ከሌለው ቡድን ጋር ጊዜያችንን አናባክንም ብለን ትተነዋል፡፡ በእኔ ግምገማ፣ አንድነት ከመኢአድ ጋር እዋሃዳለሁ ማለቱ፣ ከመድረክ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳበቃ ነው የሚያሳየው፡፡ መድረክን ከሚኮንን ወገን ጋር መዋሃድ ማለት ምን ማለት ነው? መድረክን መኮነን ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ያደርስብናል ከሚሉት ጫና ባልተናነሰ በእርስ በርስ ሽኩቻ ይበልጥ እየተዳከሙ ነው… የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አንደኛ፤ ይሄ ተቃዋሚ የሚባለው አንድ አይነት መለስተኛ ፕሮግራም ኖሮት እስካልሰራ ድረስ እንደው ዝም ብሎ ተቃዋሚ ስለተባለ ብቻ እነሱ መሀል አንድነት አለ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ ምናልባት መድረክ ከኢህአዴግ ጋር ካለው ልዩነት የበለጠ ልዩነት ያለው የተቃዋሚ ድርጅት ሊኖር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ማዕከላዊ ስርአት ይቋቋም፤ ፌደራሊዝም ይፈራርስ የሚል ፓርቲ ቢመጣ፣ ምን ያህል ከኢህአዴግ ይሻላል በማለት መለየት አለብን፡፡ ልክ ከኢህአዴግ ጋር የምንታገለውን ያህል ከሌላም ህዝባዊ አጀንዳ የላቸውም ከምንላቸውም ጋር እንታገላለን፡፡
ተቃዋሚ ብሎ ራሱን በዚያ ፈርጅ ላይ ስላስቀመጠ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” ብለን አብረን አንቆምም፡፡ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ፣ አገሪቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ቢኖር እንቃወመዋለን፡፡ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ አይሆንም፡፡ ሁላችንንም ቀፍድዶ ስልጣን ላይ እንዳንወጣ ያደረገንን ኢህአዴግን ተረባርበን መጣል ብቻውን መልስ አይሆንም፡፡ ይሄ ዓይነቱ ሽኩቻ ግን ያለ ነው፡፡ ባይኖር ነበር የሚገርመኝ፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ ላይ ባለ አገር የሚኖር ተፈጥሮአዊ ጉዞ ነው፡፡
የገዢውን ፓርቲ ወቅታዊ ሁኔታስ እንዴት ይገመግሙታል?
ገዢው ፓርቲ በፖለቲካው ጉዳይ አመራር መስጠት አልቻለም፡፡ የስርአቱ አካሄድ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሙሰኝነት ተንሰራፍቷል፡፡ የሀገሪቷና የህዝቡ ንብረት ተበዝብዞ ካለቀ በኋላ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አይነት ነገር ነው የሚሯሯጠው፡፡ አንድ ሰሞን ግርግር ይጀምርና ወዲያው ይተወዋል፡፡ ይሄን ህዝብ እየታዘበው ነው፡፡ ካድሬዎቻቸው ህዝብ ላይ ምን ያህል እንደሚባልጉ፣ ምን አይነት ተንኮል እንደሚፈጥሩ፣ እያንዳንዱን ቡድንና ግለሰቦችን እንዴት እያሰቃዩ ወደ ጥላቻ እንደሚገፉ የታወቀ ነው፡፡ ህዝቡ “ሆድ ይፍጀው” እያለ በከፍተኛ ምሬት ውስጥ ነው ያለው፡፡
የውጪ መንግስታት በተለይ ለጋሾቹ፣ “መንግስት የፖለቲካ አያያዙ ጥሩ አይደለም፤ በኢኮኖሚው ግን ደህና ነው” ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ መቼም ዝም ብሎ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡፡ ልማት ተብላ የምትታየው ብቻ ሳትሆን ለአንድ አገር ቋሚ የሆነ ዋስትናው ፖለቲካው ላይ መስማማት ሲኖር ነው፡፡ ስልጣን እንዴት ይሸጋገራል የሚለው ላይ አሁንም ስምምነት የለም፡፡ የዚህ ስምምነት ያለመኖር በብሶት ላይ ብሶት እየጨመረ፣ የአገራችን መፃኢ ዕድል ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል የሚል ስጋት አለን፤ እኔም በግሌ በእጅጉ ያሰጋኛል፡፡
በእርስዎ አተያይ አገሪቱ ያለችበት አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ያለነው የሚነድ ፍም ያለበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ እሳተ-ጎመራ ቆይቶ ይፈነዳል አይደል? የታመቀ ፍም እሳት አለ ማለት ነው፡፡ በግልም በቡድንም የማገኛቸው ሰዎች ይህን ነው የሚሉት፡፡ አሜሪካ ደውለው ምነው መላ ጠፋ? የሚሉኝ ነበሩ፡፡ ከመጣሁ ጀምሮ ብዙ ጥሪዎችን እቀበላለሁ፡፡ ሌሊት ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሱኝ አሉ፡፡ መምጣቴን እንደትልቅ ነገር ቆጥረው፣ “ምን ይዘህ መጣህ?” ሲሉኝ “እስቲ እንግዲህ አንድ ላይ እናያለን” እላለሁ፡፡ ድምፃቸውን ሰጥተው የመረጡኝ ህዝቦች፤ “የምንችለውን ሰጠን፣ ነገር ግን ለውጥ አልመጣም፤ ከዚህ በላይ ምን እንስጥ?” ይሉኛል፡፡ የኔ መልስ “በአገር ጉዳይ ተስፋ አይቆረጥም” ነው፡፡ ባለፈው ካልሆነልን አሁን ደግሞ እንሞክራለን እላለሁ፡፡ ምርጫ ምርጫ እያላችሁ በየጊዜው ሰውን መማገድ ነው፤ መብት ማስከበር ካልቻልክ፣ ምርጫ ውስጥ ተሳተፉ፣ ለምን ትላለህ እባላለሁ፡፡ እኔ ግን ለዚህ ሁሉ የምለው፤ እኔ በአገሬ ጉዳይ ተስፋ አልቆርጥም ነው፡፡ ኢህአዴጎችም ሰብአዊ ፍጡር ናቸው፤ ይህንን ሁኔታ ወጥረው ይዘው ከመኖር መለስ ቢሉ መልካም ነው፡፡ እነሱ ከሚያስቡበት ክብ ውስጥ መውጣት ባለመቻላቸው አገሪቱ ችግር ላይ ናት፡፡ ህዝባችን ተረባርቦ በሚያሳየው ጥረት አንዳንድ እድገቶችና ለውጦች እናያለን፤ ይሄም ትንሽ ከፈት ስለተደረገ ነው፡፡ ሌላውን ተፅዕኖም ቢያነሱት ይህ አገር ምን ያህል ተንቀሳቅሶ፣ ምን ያህል የህዝቡ ህይወት ይቀየር እንደነበር መገመት እችላለሁ፡፡ አሁን እኮ ከበርቴው ሁሉ “እያበላሁ ነው የምንቀሳቀሰው” ነው የሚለኝ፤ ይሄ ቢወገድ ውጤቱ ምን ያህል ይሆን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ናት፤ ኢህአዴጎች “በዚህ አይነት መንገድ አርባ ስልሳ ዓመት እንመራለን” ከሚለው ስነልቦና መውጣት አለባቸው፡፡
በሩቅ ምስራቅ ወጥ የሆነ ህዝብ ላይ ተግባራዊ የሆነ ሞዴል፣ ስብጥሩ በበዛ ህዝብ ላይ መሞከሩን ቢተውት ጥሩ ነው፡፡ ገና ህገመንግስቱን ያልተቀበሉ ቡድኖች ያሉበት አገር ላይ ይሄ አያዋጣም፡፡ እኛ ፓርላማ በነበርን ጊዜ ህዝቡ ማለት የሚፈልገውን ስለምንናገርለት ተንፈስ ይል ነበረ፤ ያንንም ዕድል አሁን ዘጉት፡፡ በመድረክ ግምገማ መሰረት፤ አሁን ወደ 1983 ዓ.ም መልሰውናል፡፡ ኢሰፓ ብቸኛ ፓርቲ ወደ ነበረበት ዘመን ማለት ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል በሮች በመዘጋታቸው ወደ ሌላ የትግል ስልት ለመሄድ የሚያደፋፍር፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ “እናንተ በሰላማዊ፣ ፓርላሜንታዊ ሂደት ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብላችሁ የትግል መንፈሳችንን ገደላችሁት” ብለው የሚኮንኑን በርካታ ወገኖች አሉ፡፡
ከመንግስት ጋር ችግሮችን ተቀራርቦ በውይይት የመፍታት ዕድል አለ ብለው ያስባሉ?
እኔ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በሽግግር ወቅትም አብሬያቸው ሰርቻለሁ፡፡ ስነልቦናቸውን አውቀዋለሁ፡፡ ከጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ማለፍ በኋላ አልፎ አልፎ የነበረው የመነጋገር ዕድል ከእነ አካቴው የተዘጋ ይመስለኛል፤ እስከአሁን ምልክት አላየንም፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ በተቻለ አቅም ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን፣ ተገናኝተን እንወያይ፤ በምርጫው ያሸነፈ ወገንን “እንኳን ደስ አለህ” ብሎ የመለያየት ባህል እንጀምር ብለን የሚያዳምጠን አጣን፡፡
መንግስትን ለውይይት ጠይቃችሁት ነበር?
የሚያከብሩት ለጋሽ አገሮቹን ነው፤ በእነሱ በኩል ብዙ ጥረት አድርገናል፤ የሚሠጠን ምላሽ ግን የአገሪቱ ህግ አካል የሆነውን የስነምግባር ደንብ አልፈረሙም ነው፡፡ ይሄ “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” ነው፡፡ እኛ ደግሞ “ፓርላማ ወስዳችሁ ህግ አድርጋችሁታል፤ ፓርላማ በሚያወጣው ህግ ላይ አንፈርምም፤ የአገሪቱ ህግ ስለሆነ በሱ እንገዛለን” አልን፡፡ እኛ የምንለውን በግድ ተቀብላችሁ ካላንበረከክናችሁ ከሆነ ስህተት ነው፡፡
ዋናው ነገር መነጋገር አለብን፤ ዘግተን ከተቀመጥን ያው ጠላትነት ብቻ ነው ትርፉ፡፡ የምርጫ ስነምግባሩም ሶስት ነጥቦች አሉት፤ በምርጫ ወቅት እንዴት እንወዳደራለን፣ የምርጫ አስተዳደር እና የምርጫ ታዛቢዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ከሶስቱ የመጀመሪያው ላይ ብቻ ነው የሚያተኩሩት፡፡ ሁሉንም ለምን አናይም በሚል ጥያቄ ነው የተፋረስነው፡፡ እንነጋገር ብለን ከጠየቅን አመት አልፎናል፤ እስከአሁን መልስ አልሰጡም፡፡
3 ጋዜጠኞችና 6 ጦማሪዎች በሽብርተኝነት ተከሰው በእስር ላይ ናቸው፡፡ 6 ያህል የግል መፅሄቶችና ጋዜጣ ክስ ተመስርቶባቸው፣ አሳታሚዎችና ጋዜጠኞችም ከአገር ወጥተዋል፡፡ በእዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ይሄንን ለምን እንዳደረገው የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው፡፡ ትንሹንም ትልቁንም ማሰር ለምን እንዳስፈለገ እኔ አላውቅም፡፡ አንድ ቤት ውስጥ አጥፊ ልጅ ካለ ተገቢ ዲሲፕሊን እንዲኖረው የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ግን አገራዊ ሃላፊነት የሌለበት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በአለም አቀፍ ድርጅቶችና በአንዳንድ መንግስታት የምንታይበት አይን ጥሩ አይደለም፡፡ በዚህ ድርጊት ማናችንም አንከበርም፤ አገራችሁ የጋዜጠኞች እስር ቤት ነው መባል አያስከብርም፡፡ ኢህአዴግ ለነገሮች የተጋነነ ምላሽ ይሰጣል፡፡ አንዳንዴ የሚደነግጡበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ የዋህ ቡድን አይደለም፤ መሠሪ ነው፡፡ መክሰስ ከፈለገ ቀደም ብሎ ነው የሚያቅደው፡፡ ጋዜጠኛ ልኮ መረጃ ሰብስቦ ኬዝ ይሠራል፡፡ የህጉ ፍትሀዊነትና ተገቢነት ብዙ ጥያቄ ያለበት ነው፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተወሰደ ነው ይላል፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካን አገር ያለው የሽብርተኛ ትርጉምና እዚህ ያለው በጣም ይለያያል፡፡ እዚህ የወጡ ህጐች ተለክተው የተሠፉ ስለሆኑ፣ የታሠሩ ልጆች በጥንቃቄ ጉድለት በዚያ ወጥመድ የወደቁበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ይሆናል፤ ዝርዝር ክሱን አላየሁም፤ ነገር ግን ኢህአዴግ ቀደም ብሎ ህግ ያወጣል፤ ከዚያ ኬዝ ይሠራል፡፡ ይህ ስርአት በሌላ እስከሚተካ ድረስ አንቀፆቹን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ አንቀጽ ተጠቅሶ ስለሚከሰስ፣ ህዝባዊና አገራዊ ጥቅም የሌላቸውን ህጐች እስከምናሳርም ድረስ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ነገር ሊሠሩ የሚችሉ ልጆች እንደማይሠሩ ሆነው በየእስር ቤቶቹ መታጨቃቸው ያሳዝነኛል፡፡
ሌላው ጉልህ የአገሪቱ ችግር ሆኖ የዘለቀው የ “ሙስሊሞች ጉዳይ” ነው … በየጊዜው በሚነሳ ተቃውሞ ጉዳት ይደርሳል፣ ሰዎች ይታሰራሉ፡፡ መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?
ጥያቄያቸው መንግስትና ሃይማኖት ይለያዩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከቻርተሩ ጀምሮ ህገመንግስታዊ መብት ነው፡፡ መንግስት የራሱን አመራር ለመምረጥ ሲሞክር የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ኢህአዴግ የተጠናወተው የመቆጣጠር አባዜ ውጤት ነው፡፡ ሁሉንም በሱ ቁጥጥር ስር እስካላደረገ ድረስ አያርፍም፡፡ ይህ አባዜ እኮ ነው ለችግሮቹ ሁሉ መንስኤ የሆነው፡፡
ከመጪው ምርጫ ምን ይጠብቃሉ?
ህዝቡ እንዲያውቅ የምፈልገው የ92ቱ ምርጫ በተወሰነ አካባቢ በተለይ በሀዲያ ዞን እኔን ጨምሮ የሌሎችን ቁርጠኝነት ህዝቡ ተቀብሎ፣ ለውጥ ይመጣል ብሎ ውጤት መገኘቱ፣ ኢህአዴግንም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚዎችን አቅንቷል፡፡ ለ97 መሠረት የሆነው የ92 ምርጫ ነው፡፡ የሚወራው ስለ 97 ምርጫ ነው፡፡ እንግዲህ “አፍ ያለው ጤፍ ይቆላል” ነው፡፡ የ97ቱ ምርጫ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት፣ ከኢህአዴግ ጋር ቁጭ ብሎ የምርጫውን ሜዳ፣ የምርጫውን ህግ መደራደሩን ተከትሎ የመጣ ውጤት ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉም ህጐች ተለውጠዋል፡፡ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል፡፡ የ97ቱ ምርጫ ኢህአዴግንም አስደነገጠ፤ ተቃዋሚዎችንም መድረስ እንችላለን ካሉት በላይ ስሜት ውስጥ ከተታቸው፡፡ ያኔ የውጪ ታዛቢዎች ነበሩ፤ የሲቪል ማህበራት እንደ አሸን የፈሉበት ወቅት ነው፤ ታች ድረስ ወርደው እያንዳንዱን ነጥብ ያዩበት ጊዜ ነበር፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ “ይህቺ እንደገና አትደገምም” ብሎ እኛ እዚያው ፓርላማ ተቀምጠን የተደራደርንባቸውን ነገሮች ከልሶታል፡፡ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደገና ቁጭ ብለን እንነጋገር እያልን ነው፡፡ ኢህአዴግ ተቀምጦ ወደ መደራደር መግባት አለበት፤ የምርጫው ምህዳር ላይ እንስማማበት እያልን ነው፡፡ ይሄ ለአገሪቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በየቦታው ያለው የብሶት ስሜት አስቸጋሪ ነገር እየወለደ ነው፡፡ አንዳንዱ ደፋር ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ፣ እኛን “የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው” ለማለት ሁሉ ይዳዳዋል፡፡
አንዳንድ ወገኖች እርስዎን በለዘብተኛነት ይፈርጅዎታል…
ለአላማዬ ጽኑ ነኝ፡፡ የአቋም ለዘብተኛ አይደለሁም፡፡ ሰው መዝለፍ ላይ ግን የለሁበትም፡፡ የሰውን ሃሳብ አጥላላለሁ እንጂ ግለሰብን አላጥላላም፡፡ ሰብዕና መንካት፣ መሳደብ አልወድም፡፡ ብዙ ጭብጨባ ፈላጊም አይደለሁም፡፡ የቴሌቪዥን ክርክር ላይ ስድብ ምናም ሲመጣ፣ ተቃዋሚንም ኢህአዴግንም አደብ ግዙ ብዬ አውቃለሁ፡፡
በ2007 አገራዊ ምርጫ ይወዳደራሉ?
ድርጅቴ መወዳደር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እነማን የት ጣቢያ ይወዳደሩ የሚለው ድርጅታዊ ውሳኔ ነው፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ድርጅቴን አወዳድራለሁ ማለት ግን ተገቢ እወጃ አይደለም፡፡ ድርጅቴ እንዲወዳደር ቀዳዳ ፍለጋ ላይ ነኝ፡፡
ድርጅትዎ እጩ ቢያደርግዎትስ …?
እሱንም አሁን መናገሩ ተገቢ አይደለም፡፡ የምናሠማራቸው አባሎች እንዲመረጡ አቅሜ የቻለውን ዕገዛ አደርጋለሁ፡፡ እኔ በግሌ ገባሁ አልገባሁ ልዩነት አያመጣም፡፡ የህዝብን አላማ በብቃት ሊያቀርቡ የሚችሉ ወገኖች ምርጫ ውስጥ ገብተው የህዝብ ይሁንታ እንዲያገኙ ለማብቃት ግን ጉልበቴን አልቆጥብም፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ምን አይነት አስተማሪ ናቸው?
ሄደሽ ተማሪዎቼን ጠይቂያቸው፡፡
ውጤት ሲሰጡ “ኤ ለእግዚአብሔር”፣ “ቢ ለአስተማሪ”፣ “ሲ ለተማሪ” የሚሉ ዓይነትነዎት?
(ረጅም ሳቅ) እኔ ራሴን የምቆጥረው የተማሪዎች አገልጋይ አድርጌ ነው፡፡ ምክንያቱም ቀጣሪዎቼ ተማሪዎቼ ናቸው፤ ሁሌም ተማሪዎቼን “አለቆቼ ናችሁ” ነው የምለው፡፡ እኔ የምኖረው ተማሪዎቼ እስካሉ ድረስ ነው፡፡ የአስተዳደር ሰራተኛ ከመሆኔ በፊት ሥራዬ ምርምር መስራትና ማስተማር ነበር፡፡ ከተማሪዎቼ ጋር ውድድር የለብኝም፡፡ ፈተና ሳወጣም ከተማሪዎቼ ጋር ውድድር ውስጥ አልገባም፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ ሊያገኙት አይችሉም በሚል ፈተና አላወጣም፡፡ የማወጣው ጥያቄ ተማሪ አስቦ እንዲመልስ የሚያደርግ ነው፡፡ በፈተና ዜሮ የማያገኙበት አማራጭ ያለው ጥያቄ ነው የማወጣው፡፡
ምን አይነት የፈተና አወጣጥ ይጠቀማሉ?
በመምህርነት ባሳለፍኩባቸው ከ30 አመታት በላይ ጊዜ ውስጥ “ምርጫ” እና “አዛምድ” የሚሉትን የፈተና ዓይነቶች አውጥቼ አላውቅም፡፡ “እውነት ወይም ውሸት” አይነት ጥያቄ ካወጣሁ፣ ተማሪዎቼ እውነት ካሉ ለምን እንዳሉ፤ ውሸት ካሉም እንደዚያው ምክንያት እንዲያስቀምጡ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ተማሪ ማስታወሻ ያዘ አልያዘ አያስጨንቀኝም፡፡ ማዳመጥ እንዳለባቸው ግን እነግራቸዋለሁ፡፡
ተማሪ ክፍል መጣ አልመጣ የሚለውንስ ይቆጣጠራሉ?
ተማሪ ለራሱ እጠቀማለሁ ሲል ይመጣል የሚል እምነት ስላለኝ አቴንዳንስ አልወስድም፡፡ ግን ክፍሌ ባዶ ሆኖ አያውቅም፡፡ ብትመጡ ይመከራል እላለሁ:: አሜሪካን ኢሊያኖስ ውስጥ ያስተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ “ገቨርናንስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ” ይባላል፡፡ የትምህርት ቤቱ ህግ አቴንዳንስ ግዴታ (Compulsory) ነው ይላል፡፡ እኔ ግን አቴንዳንስ ይመከራል (Advised) እያልኩ ነው ያስተማርኩት፡፡
ከመጣችሁ ትጠቀማላችሁ እላለሁ፡፡ ካልመጣችሁ ኤፍ ታገኛላችሁ ግን አልልም፡፡ የቀረ ተማሪ ውጤቱን በራሱ መንገድ ያገኘዋል፡፡

http://addisadmassnews.com

Posted by: Kumilachew Gebremeskel Ambo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: