1 Comment

ማኪራ ወደ እናት ቡና…


10891788_10153031850724587_8516313425612285865_n
(የሔኖክ ስዩም የጉዞ ማስታወሻ …
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ለዛሬ ደግሞ ስለቡና እያወጋን ወደ ቡና መገኛዋ የማንኪራ መንደር ይዞን ተጉዞ አንዲት “እናት ቡና”ን ያስተዋውቀናል… )

ወደ ድንቁ መንደር እየሄድኩ ነው፡፡ ጅማን ተሻገርኳት…ሌላ ጊዜ እንተርካት ብዬ ነው፡፡ አሁን ወደ ተፈጥሮ ምሽግ እያቀናሁ ነው፡፡

ካፋ ዞን…… እውን ሳይሆን ምናብ የሆነ ምድር ነው፤ የካፋ ነገስታትን የተመለከቱ መረጃዎች ከሀገር ውስጥ የታሪክ አዋቂዎች ባሻገር የምዕራቡን ዓለም ጸሐፍት ቀልብ የሳበ እንደ ቢቤር ያሉ ድንቅ የውጭ ጸሐፍት አብዝተው የመሰከሩለት አስደናቂ ምድር ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በ449 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የካፋ ዞን መዲና ቦንጋ የቀድሞ የካፋ ነገስታት መዲና ነበረች፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ ረግጫታለሁ፡፡ ገዢ መሬት ላይ ያረፈችው ቦንጋ በደን የተከበበች ከተማ ናት፡፡ ወደየትም አርቄ መመልከት አልቻልኩም፡፡ የደን ጥሻ ውስጥ የተሸሸገች ጥንታዊ ከተማ…

የካፋ ምድር 70 በመቶ ወይና ደጋማ አየር ንብረት አለው፡፡ አመቱን በሙሉ የማይደርቁት ከ150 በላይ የሚሆኑ ወንዞች ከካፋ ጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ እየተርመሰመሱ ያዜማሉ፡፡ በዩኔስኮ በብዝኃ ህይወት ማእከልነት የተመዘገበው የካፋ ደን በውስጡ አያሌ የእጽዋት ዝርያዎችን ሸሽጎ የያዘ እና ዓለምን ማዳረስ የቻለው የቡና ተክል መገኛ ነው፡፡

ጎጀብን እዩት…ኦሞ እስኪውጠው የሀገሩ አድባር ነው፡፡ ከእድሜ ጠገብ ዛፎች ብስባሽ ወዙን ያደመቀ ወንዝ፡፡ የጥንቱ ጎጀብ እርሻ ልማት ስንቱን ያፈራበት ጎጀብ፡፡

በረጃጅም ዛፎች መሀል እንደጉንዳን ራሳችንን አገኘነው፡፡ ካፍቾው ገበሬ በቆንጨራ መንገድ የሚዘጋ አረም እየጨፈጨፈ ከፊታችን ይሮጣል፡፡ ጉልበታችን ድረስ ውሃ ራስን፤ የካፋ ጤዛ እስከ እኩለ ቀን ይጤሳል፡፡ በጢስ ውስጥ የሚጣደፉ አራት ሰዎች የሆነ ነገር ለማየት ጓጉተዋል፡፡ አንዱ እኔ ነኝ፡፡

በካፋ የተፈጥሮ ደን ውስጥ ከ5ሺ በላይ የቡና ዘረ መሎች ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ ትኩረትን የሳበው አሁን ልንረግጠው የምንሮጥበት አካባቢ ነው፡፡ እኛን ከማንኪራ የለየን ሰው ዋኝቶ የማይሻገረው አንድ ወንዝ ብቻ ነው፡፡ ደረስን፤
መንገድ መሪው አርሶ አደር በያዘው ቆንጨራ አንዲት ግንዷን ሽበት የወረራት፤ ጠመም ያለች ዛፍ መታ፡፡

እነሆ እናት ቡና፤ አሁን ሀገሬ ላይ ካሉት ቡናዎች በእድሜ ትልቋ ይህቺ ናት፡፡ ከጉሚ ወንዝ አጠገብ ነኝ፤ አዋሾ ኦላ ቀበሌ ነው፤ በዚህ ቀበሌ የምትገኛዋ የማንኪራዋ እናት ቡና ታላቅ የሆነች ሌላ እናት ቡና ከደኑ ውስጥ ተገኝታለች፡፡ ለረጅም ጊዜ ያላተገለጸችው ይህች እናት ቡና በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ግን ታዋቂ ነበረች፡፡

የቡናዋ አካባቢ አዛውንቶች ስድስት ትውልድ ቡና ሲለቅም የቆሞች እናት ቡና ናት ይላሉ፡፡

ታዲያ ማንኪራ የት ነው? ዓለም ብዙ ያወራላትን የሆነች ቦታ ለማየት ነገ አጓጓኝ፡፡

በማግስቱ…በጠዋት ተነስተን ወደ ማንኪራ፤ ሌላኛዋ የእናት ቡና መገኛ፤ ቡና በዓለም እውቅ ፍሬ ነው፡፡ ኒውዮርካውያን ከቀሪው የአሜሪካ ከተሞች ነዋሪ በ7 እጥፍ የሚበልጥ ቡና ጠጪዎች ናቸው፡፡

ቀደምት የፈረንሳይ ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው ቡናን እንዲጠጡ ትእዛዝ ይሰጡ ነበር፡፡ ቡና በዚህ ወቅት ለፈረንሳዮች አንድ ግሩም የባህል መድሀኒት ተብሎ ተወድሷል፡፡

ይህ ቡና ዛሬ በዓለም ላይ ጣዕሙ የገነነ ወደር አልባ ልዩ ፍጥረት ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓለምን ያዳረሰው ቡና መነሻው የት ይሆን? ካፋ የሚለው ቃል ኮፊ በሚል በእንግሊዘኛ ለተገለጸው ፍሬ መነሻ ሆኗል፡፡ ካፋ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ዴቻ ወረዳ ነው፡፡ ዴቻ ወረዳ ውስጥ ነኝ፡፡

የምደርስበት ስፍራ ማንኪራ ነው፡፡ እዚሁ ዴቻ ዞን ከሚገኙ ቀበሌዎች አንዷ ስትሆን ከማንኪራ ጥቅጥቅ ደኖች ውስጥ ቡና መገኘቷን አያሌዎች ጽፈዋል፡፡ ቡኒ የተባለችው መንደር በማንኪራ ቀበሌ ትገኛለች፡፡ ቤቤር የተባለው እንግሊዛዊ ጸሐፊ ቡናን በተመለከተ በጻፈው ጽሁፍ ቡኒ የቡና መገኛ መሆኗን መስክሯል፡፡

በሌላ በኩል ማኪራ ዛሬም ድረስ እናት ቡና የሚገኝባት ስፍራ ናት፡፡ በበጋ በደንብ በሚያስገባው መንገድ በመኪና ለተጓዘ ሰው ማኪራ ድረስ መጓዙ አስቸጋሪ አይሆንበትም፡፡ ይህን ጉዞ ስናደርግ ግን በፈረስ ጭምር መጓዙ ግድ ነበር፡፡ ፈረስ ላይ ወጥቼ ማወቄ የጠቀመኝ አሁን ነው፡፡ ከፈረስ አናት ላይ ሆኜ ከዛፎቹ በታች እየተጓዝኩ ነው፡፡

ነፍሴን ለበቅሎዬ አደራ ሰጠኋት…
በማህበር ከተዳራጁት የፈረስ አከራዮች አንዱ የሆነው ወጣት ማኪራ የቡና መገኛ መሆኗን አስረግጦ ነገረኝ፤ እንደ ወጣቱ አባባል “እናት ቡና መገኛዋ ማኪራ ነው፤ በእርግጠኝነት ነው የማምነው በካፋ ባህል በታሪካችን ይነገራል፤ የቡና ዘር ከኛ ምድር መሄዱን ሰምተናል፤ በዚህ ምንም ጥርጣሬ የለኝም፤ እናት ቡና ብትሔድ በደን ተከባ ታያታለህ፤ አሁን 25 ዓመቴ ነው፤ ከዘጠኝ አመቴ ጀምሮ ማኪራ እሄዳለሁ፤”

ይህንን መሰል መከራከሪያዎችን የሚደግፉ የውጭ ጸሀፍት በርካታ ናቸው፡፡ ጀምስ ብሩስ የተባለው የጉዞ ጸሀፊ ካፋ ዋንኛ የቡና አምራችና ላኪ መሆኗን የሚገልጽ ጽሁፍ ከዛሬ 200 ዓመት በፊት ጽፎ ነበር፡፡

የዛሬዋ እናት ቡና የምትገኝበትን ማኪራ በተመለከተ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ቢቢሲ የቡና መገኛን በማስመልከት በሰራው ዘገባ የቡና መገኛ በኢትዮጵያ ደቡበ ምእራብ የምትገኘው ካፋ ብቻ ናት ሲል ማኪራ የቡና መገኛ መሆኗን አስመስክሯል፡፡

ከእነዚህ ጥቅጥቅ ደኖች በአንዱ ስፍራ እንደ ታሪክ ገለጻ ስፍራውም ቡኒ በተባለ መንደር፤ ታሪክ ባላሰፈረው ቀን ካል አዲ የተባለ የፍየል እረኛ የሚጠብቃት ፍየል የቀላ ቡና ቀምሳ ባሳየችው ደስታና ፈንጠዝያ ተመርቶ ያገኛትን ፍሬ ለህዝቡ አስተዋወቀ፡፡

እንደ ቀደምት የታሪክ አዋቂዎች ገለጻም ይህች ቡና የተባለች ፍሬ እዚያው ማንኪራ ቀበሌ አካባቢ በሚገኘው የቲፋ ገበያ አማካኝነት መጀመሪያ አጎራባች ህዝቦችን ቀጥሎም ዓለምን አዳረሰች፡፡

አምኖን ኦሬንት ታዋቂ አሜሪካዊ ጸሀፊ ነው፡፡ ካፋና ደቡብ ምእራብን በዳሰሰበት መጻህፉ ገጽ 42 ላይ ቡና የታላቋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭና መገኛውም ካፋ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የቡና መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗን የሚጠቁሙ የውጭ ሰነዶች አያሌ ናቸው፡፡

ዛሬ ካፋ ይህንን ህያው ለማድረግ የቡና ሙዚየም ሀገር አቀፋዊ ይዘት ባለው መልኩ እየተገነባባት ይገኛል፡፡

በቅሎአችንን አሰርን፡፡ ከዚያም እጅብ ወደ አለው የቡና ደን ውስጥ ገባን፡፡ መንገድ ከሚመራን ገበሬ አንዳች ደስታ ስሜት ከውስጡ ወጥቶ ወደ ቡናው ደን ውስጥ እንደ ጠል ፈሰሰ፤ ቀጭን መንገድ ለእግረኛ የተወው የቡና ደን መፈናፈኛ የለውም፡፡

ብዙ ሳንጓዝ አንድ በዘመናት ሂደት ከቡናነት ይልቅ ዋርካ መሆን የመረጠች የምትመስል ረጅም የቡና ዛፍ ስር ቆምን፡፡ ገበሬው በሙሉ ዓይኑ እንኳን ሊያያት ሳሳ፤ የቡና እናት መሆኗን ነገረን፡፡ ስሯ በተፈጥሮ ረግፈው በተፈጥሮ የፈሉ እልፍ የቡና ዛፎች እና ችግኞች ይርመሰመሳሉ፡፡

ማኪራ ስለመሆኗ የማታውቅ፤ በየጆንያው አብራኳ እንደተጠቀጠቀ ያልሰማች፡፡ በመርከብ ፍሬዋ እንደተሰደደ ያልተነገራት እናት ቡና፡፡ በነገራችን ላይ እናት ቡና ማለት የመጀመሪያዋ የቡና ዛፍ ማለት አይደለም፡፡

አሁኑ በዓለም ላይ ካሉ፤ እዚያ በብራዚል ጥቅጥቅ ደኖች ከፈሰሱ ቡና ዛፎች ሁሉ በእድሜ ወደር የሌላት ማለት ነው፡፡ ትልቋ እድሜ ጠገብ ቡና ዛፍ ማለት፡፡ ገበሬው ሰባት ትውልድ ለቅሞላታል፡፡ አለን፤ ለሽያጭ ሳይሆን ለበረከት…

Posted by: kumilachew Ambo

Advertisements

One comment on “ማኪራ ወደ እናት ቡና…

  1. kume ella taahiyahin, tawo ta beetoocha qiicabeetane

    Liked by 1 person

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: