Leave a comment

‹‹ባለሥልጣናት መሬቴን ከነኩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ያገኙታል››


interview

ሳይ ራማክሪሽና ካሩቱሪ፣ የካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር

መንግሥት በኢትዮጵያ የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ በትልቁ ይጠቅሳቸው ከነበሩ ትልልቅ ኩባንያዎች ዋናው የህንዱ ካሩቱሪ ግሎባል ነው፡፡ የኩባንያው መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳይ ራማክሪሽና ካሩቱሪ እዚህ አገር ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያን በመመሥረት፣ በጋምቤላ ክልል ሰፊ መሬት ወስደው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ግን በውዝግብ የተሞላ ሒደት ያሳለፉት ራም ካሩቱሪ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፋጠዋል፡፡ ባንኩ ለሁለተኛ ጊዜ ሐራጅ አውጥቶባቸዋል፡፡ በቅርቡ ታኅሳስ 12 ቀንም በ55.8 ሚሊዮን ብር ዕዳ ምክንያት ባንኩ ለጨረታ ያቀረበው የእርሻ መሬት በፍርድ ቤት ዕግድ ምክንያት ከመሸጥ አምልጧል፡፡ ሆኖም ከባንኩ ጋር ያላቸው ጠብ በብድር ዕዳ እንዳልጀመረ ይናገራሉ፡፡ በአገሪቱ የእርሻ ሥራቸው መዳከም ሳቢያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚቀርብባቸውን ወቀሳም ይኮንናሉ፡፡ ይብሱን ለውድቀቴ የሚተጉ የሚሏቸውን በስም እየጠቀሱ ያብጠለጥላሉ፡፡ በጋምቤላ ክልል የተሰጣቸው 300 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደነበር፣ እሳቸው የጠየቁትን ግን 10 ሺሕ ሔክታር ብቻ እንደነበር፣ የተሰጣቸው መሬትም በጎርፍ የሚጥለቀለቅ፣ በዛፍ የተሞላና ለምንጠራ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ እንደነበር በመጥቀስ በርካታ ቅሬታዎችን አሰምተዋል፡፡ ንግድ ባንክ ያወጣውን የሐራጅ ጨረታ መነሻ በማድረግ ብርሃኑ ፈቃደ ራም ካሩቱሪን አነጋግሯቸዋል፡፡

 ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ የሐራጅ ማስታወቂያ በእርስዎ ኩባንያ ላይ አውጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ዘመን ባንክም ከእርስዎ ጋር በብድር ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ 

ራም ካሩቱሪ፡- በዚህ አገር ብዙ ኢንቨስት አድርገናል፡፡ እዚህ ኢንቨስት ያደረግሁት የራሴን ገንዘብ ነው፡፡ እርግጥ ነው ባንኮች የተወሰነ ብድር ሰጥተውናል፡፡ አዎ ዘመን ባንክ 70 ወይም 80 ሚሊዮን ብር አበድሮን ነበር፡፡ ከንግድ ባንክም ተበድረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳሸን ባንክም አበድሯችሁ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ራም ካሩቱሪ፡- ዳሸን ባንክ አበድሮን የነበረው 10 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2006 ያበደረንን ብድር በዓመቱ መልሰናል፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት የዳሸን ባንክ ብድር የለብንም፡፡ ዕዳ ያለብን የዘመን ባንክና የንግድ ባንክ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዘመን ባንክ መክፈል ያለብን 26 ሚሊዮን ብር ሲሆን ይህንን ለመክፈል በምንችለበት አቋም ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዘመን ባንክ ብድር አልተከፈለኝም በማለት ፍርድ ቤት ጉዳይዎን ወስዶትም ነበር፡፡

ራም ካሩቱሪ፡- ኢትዮጵያ የራሷ ሕጎች፣ ባህልና ውርስ ያላት አገር ነች፡፡ ከዚህ አገር ባህል ጋር ተጣጥሞ ለመሥራት ካስፈለገ ሕጎችና ደንቦችን ማክበር ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚመራባቸው መመርያዎች አሉት፡፡ ባንኮች የሚጠየቁት ብድር አጠራጣሪ ከመሰላቸው ከብድሩ መቶ እጥፍ በላይ ሀብት ቢኖርህ እንኳ አያበድሩህም፡፡ የተበላሸ ብድር እንዳይሆንም ይከታተላሉ፡፡ ይህ ሆኖ ሲገኝም ጨረታ ያወጣሉ፡፡ ምክንያቱም ገንዘባቸውን እንዳያጡ ስለሚፈሩ ነው፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብዬ አልጠይቅም፡፡ ሆኖም ግን ይህን እንዲደረግ የምትፈቅደው አገርና ሕጎቿ መልሰው ለተበዳሪዎች ማገገሚያ ሥርዓትን ስለሚፈቅዱ፣ ብድራቸውን መክፈል እስከቻሉና ለብድሩ ማስያዣ ንብረት እንስካላቸው ድረስ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያጵያዊም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር ማሟላት የሚገባውን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሟላ ድረስ፣ ሕጉ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ጉዳዩን እንዲያቀርብና ከብሔራዊ ባንኩ ገዳቢ ሕጎች አኳያ ለሚመጣበት ጫና ማስታረቂያ መፍትሔ ይሰጠዋል፡፡ በመሆኑም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ በኋላ የዘመን ባንክን ብድር በሦስት ቀናት ውስጥ መልሰናል፡፡ ምክንያቱም ገንዘባችን እየመጣ የነበረ ቢሆንም፣ እነሱ ግን ሊታገሱ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለባቸውን አደረጉ፡፡ እኛ ግን ገንዘቡ እየመጣልን ስለነበር እንደምንከፍላቸው እናውቅ ነበር፡፡ በሕጉ ገዳቢነት ሳቢያ ባንክ ሆነህ ስታየው እንዲህ ያለውን ነገር በማመን ለመሥራት ትቸገር ይሆናል፡፡ ይሁንና ዘመን ባንክ የፍርድ ቤት ሒደቱን አቋርጠዋል፡፡

እኔ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ፡፡ እዚህ የመጣሁት አገሪቱን ስለምወድ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት አድርጌያለሁ፡፡ መንግሥት አምኖኝ እንዳለማ በጋምቤላ መሬት ሰጥቶኛል፡፡ ይህንን ማሳካት ነው ዓላማዬ፡፡ እኔ የዓለም የአበባ ንግድ ንጉሥ ነኝ፡፡ ይህንን ለማንም መንገር አይጠበቅብኝም፡፡ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የዓለምን አሥር በመቶ የገበያ ድርሻ ይዣለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በዚህ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ሥልጣን ከነበራቸው ከአንድ ትልቅ ሰው ጋር ተገናኘሁ፡፡ ከእሳቸው ጋር ቀጠሮ ስለነበረኝ ቢሯቸው እንግዳ መቀበያ ቁጭ ባልኩበት ጋዜጣ ላይ የተጻፈ ነገር አነበብሁ፡፡ ኢትዮጵያ 70 ሺሕ ቶን ስንዴ ከደቡብ አፍሪካ ታስመጣለች ይላል፡፡ ከሰውየው ጋር የነበረኝን ጉዳይ ከጨረስኩ በኋላ ግን 80 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር፣ 100 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ባለው አገር፣ ከበቂ በላይ ዝናብና ፀሐይ በሚገኝበት አገር ውስጥ ምግብ ከደቡብ አፍሪካ ማስመጣት ያሳምመኛል አልኳቸው፡፡ ለዚህ አገር እኔ ምንም ነኝ፡፡ የዓለም ባንክም አይደለሁም፡፡ ግን ነገርየው ያሳምማል፡፡ ታላቁ መሪ ግብርና ላይ ኢንቨስት እንዳደርግ ጠየቁኝ፡፡ እኔ ግን ሐሳቡም አልነበረኝም፡፡ እኔ ስለአበባ ብቻ ነው የማውቀው፡፡ ሆኖም ባኮ ላይ መሬት ተሰጠኝ፡፡ እዚያ ማልማት ጀመርኩ፡፡ ከዚያ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ ሰማሁ፡፡ ኤምባሲያቸው የት ነው ብዬ ነበር የጠቅሁት፡፡ ጋምቤላ ሌላ አገር እንጂ ክልል አልመሰለኝም ነበር፡፡ ላለማወቄ አትታዘቡኝ፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በግዮን ሆቴል ስንነጋገር በጋምቤላ መሬት እንደሚሰጠኝ ገለጹልኝ፡፡ በፕሬዚዳንቱና በጋምቤላ ክልል መንግሥት ግብዣ ቦታውን ለማየት ሄድን፡፡ እኛ የጠየቅነው 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ 10 ሺሕ ሔክታር ጠየቅሁ ቢሉም እኛ የምናውቀው ግን 300 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደተቀበሉ ነው፡፡ ይህ እውነት አይደለም እንዴ?

ራም ካሪቱሪ፡- የተመዘገበና በየትኛውም ፍርድ ቤት ላረጋግጠው የምችለው ሀቅ አለኝ፡፡ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ካቢኔ በሙሉ ስብሰባ ከተቀመጠ በኋላ 10 ሺሕ ብቻማ አንሰጥህም አሉኝ፡፡ እኔ ግን አቅሜ ይኸው ብቻ እንደሆነ ገልጬላቸዋለሁ፡፡ ከስብሰባቸው በኋላ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚሰጡኝ ይልቁንም እኔ በማምንበት ዋጋ እንድከፍል፣ ከዚያ ያነሰ መሬት ግን እንደማይሰጡኝ አስታወቁ፡፡ ምርጫ አልነበረኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለእርስዎ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት ለምን እንደተሰጠ ሚዲያው ሁልጊዜ መንግሥትን ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- እኔ አልወሰድኩም፡፡ አንተ በአንዴ መብላት የምትችለው አንድ እንጀራ ነው፡፡ አምስት እንጀራ በግድ ብላ ብዬ እሰጥሃለሁ፡፡ ከሆነ ጊዜ በኋላ ስመለስ ለምን አልጨረስከውም ብዬ የምወቅስህ ከሆነ እንዲህ ያለው ነገር አመክንዮው ምንድነው? በወቅቱ የውጭ ኢንቨስተር ለማግኘት በጣም ትፈልጉ ነበር …

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ኃላፊዎች ለምንድነው አንድ ጊዜ ተሳስተው እንኳ እርስዎ ጠይቀው የነበረው 10 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደነበር የማይናገሩት? መንግሥት በይፋ ሲናገር የቆየው 100 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደተሰጠዎ ነው፡፡ ሆኖም በተግባር የተሰጠዎ ግን 300 ሺሕ ሔክታር ነው፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- ስምምነቱ በተረቀቀበት ወቅት 300 ሺሕ ሔክታር ብለው እንዳያሰፍሩ ተማጽኛቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን በግድ ይሁን ብለው 300 ሺሕ ሔክታር አደረጉት፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ቢክደውም ለእርስዎ የተሰጠዎ መሬት ስፋት 300 ሺሕ ሔክታር እንደሆነ የሚያሳይ የስምምነታችሁ ሰነድ ቅጅ እኛም አለን፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- ሊኖራችሁ የሚችለው በወቅቱ ግብርና ሚኒስቴር (የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስተር) ያወጣው ሰነድ ቅጅ ነው፡፡ ዋናው ሰነድ እሱ አይደለም፡፡ ዋናው ሰነድ ከጋምቤላ ክልል ጋር የተስማማንበት ነው፡፡ ይህ ስምምነት የ300 ሺሕ ሔክታር መሬት ነው፡፡ በኋላ ግን አዲስ ስምምነት ተደርጎ 100 ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲሰጠኝና እንዳለማ ቀሪው 200 ሺሕ ወደፊት ስፈልግና የተሰጠኝን ካለማሁ በኋላ የሚጨመር ተደርጐ በታሳቢነት የተያዘ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ያስከተለው የእኔ ምርጫ ነው ወይስ የእናንተ ኢንቨስተር ለማግኘት የነበራችሁ ፍላጐት? በዚህ አገር ሰፋፊ እርሻን ያስተዋወቅሁና የፈጠርሁ እኔ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ እኔ በራሴ አንደበት የተናገርኩት ሳይሆን የዚህ አገር ሰዎች የሚሉት ነው፡፡ መንግሥት የአበባ እርሻ በመፍጠሩ፣ የሥጋ ኤክስፖርት በመጀመሩ ደስተኛ ሆኖ ነበር፡፡ በውጭ አልሚዎች የሚንቀሳቀስ የሰፋፊ እርሻ ሥራ ግን አልነበረም፡፡ ኢንቨስተሮችም አቅሙ እንዳለ አላሰቡም ነበር፡፡ በመሆኑም ካሩቱሪ ጀማሪ በመሆን አስፋፋው፡፡

ሪፖርተር፡-  በመንግሥት ደካማ ከተባለው ውስጥ የሚመደብ ቢሆንም ሳዑዲ ስታር መሰለኝ ቀደምት የሰፋፊ እርሻ ሥራ ጀማሪ?

ራም ካሪቱሪ፡- ስለሼክ መሐመድ አል አሙዲ ማውራት ተገቢ አይሆንም፡፡ እሳቸው ራሳቸውን የቻሉ መንግሥት ማለት ናቸውና፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ዓለም አቀፍ ዕውቅና የመጣው፡፡ የተወሰኑት የሰፋፊ እርሻን ሲደግፉ የተወሰኑት ተቃወሙት፡፡ በመሀሉ በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም በመምጣቱ ነገሩን ይበልጥ አወሳሰበው፡፡ ፕሮግራሙ የነዋሪዎችን መሬት በመውሰድ ለሰፋፊ እርሻዎች ለመስጠት የመጣ ነው ብለው የተቃወሙም ነበሩ፡፡ እንዲህ ያሉት መግለጫዎች በፍጥነት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተራግበዋል፡፡ ሚዲያው ስለአፍሪካ መጥፎውን እንጂ ጥሩውን አይዘግብም፡፡ በህንድም እንዲህ ያለው ነገር አጋጥሞን ያውቃል፡፡ በወቅቱ መንግሥት ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ሔክታር የሚገመት መሬት ለሰፋፊ እርሻዎች ሰጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታር ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ ሌላ ሦስተኛ ኩባንያ ስለመኖሩ ልትጠራልኝ አትችልም፡፡ ሁሉም ጥለው ሄደዋል፡፡ እኔም እንድሄድ ትፈለጋላችሁ እንዴ?

ሪፖርተር፡- ግን ምን ያህል ጊዜ መፍጀት አለበት? በስድስት ዓመታት ውስጥ ምንም ነገር ካልተገኘ ስንት ዓመት መጠበቅ ሊያስፈልግ ነው?

ራም ካሪቱሪ፡- አላውቅም፡፡ 60 ዓመትም ሊፈጅ ይችላል፡፡ በግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ያልታሰበ ፍልውኃ ሲገኝ፣ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ምን ያህል ጊዜ እንደሚጠይቅ ልትነግረኝ ትችላለህ? ለሁለት ዓመት ያህል በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ላገኝ ባለመቻሌ እቤቴ በጄኔሬተር ለመጠቀም ተገድጃለሁ፡፡ ሙቅ ውኃ በግድቡ ቦይ በኩል በመምጣቱ የማን ስህተት ነው? ይህ የእግዜር ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሐራጁ ጉዳይ እንመለስ፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- እንደ እኔ ከሆነ ሐራጅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ካለም ሄደህ ስለ እሱ መጻፍ ትችላለህ፡፡ አንድ የዚህ አገር ኩባንያ (ስሙን ጠቅሰዋል ማረጋገጫ አላገኘንለትም) ሊከፍለኝ የሚገባው 100 ሚሊዮን ብር ዕዳ አለበት፡፡ ከገበያው የሚሰበሰብ 350 ሚሊዮን ብር አለኝ፡፡ ሆኖም በንግድ ባንክ የሚፈለግብኝ ዕዳ 55 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ባንኩ በሕግ መጽሐፍ ብቻ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ቅሬታም ፀፀትም የለኝም፡፡ ሥራቸውንም አከብራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት በስልክ እንደነገሩኝ ከነበረብዎት የ65 ሚሊዮን ብር ዕዳ 25 በመቶ ከፍለው ቀሪውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም በባንኩ የሚፈለግብዎን ዕዳ አልከፈሉም፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- አዎ፡፡ ግን እነሱ እንቢ ስላሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንቢ ስላሉ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

ራም ካሪቱሪ፡- በተለያዩ ቴክኒካዊ ምክንያቶች ነው፡፡ ይህ ሁሌም የሚሆን ነው፡፡ አንዳንዴ የቴክኒካዊ ጉዳዮች …

ሪፖርተር፡- የቴክኒክ ጉዳይ ከምን አኳያ?

ራም ካሪቱሪ፡- ይህንን ለመረዳት ውስብስብ ነገር ነው፡፡ የብድሩ መክፈያ ጊዜ መራዘም ነበረበት፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ የተነሳ ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ ሕጉ 25 በመቶ የብድሩ መጠን መከፈል አለበት ይላል፡፡ እኛም ያንኑ ከፍለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ብድሩን ሙሉ በሙሉ ለመክፈል ፈልጋችሁ ያገዳችሁ የቴክኒክ ምክንያት ሊታየኝ አልቻለም፡፡ በየትኛውም ጊዜ መክፈል ከቻላችሁ ምንድነው ችግሩ?

ራም ካሪቱሪ፡- 25 ከመቶውን ከፍለናል፡፡ ማስረጃም አለን፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ ቀሪው ብድር የሚከፈልበት ጊዜ መራዘም አለበት ቢልም እነሱ ግን ይህንን አላደረጉም፡፡ በንግድ ባንክ ቦታ ገብቼ መመለስ አልችልም፡፡ ተጨማሪ እንድከፍል ጠየቁኝ፣ ከፈልኩ፡፡ ባለፈው ወር አራት ሚሊዮን ብር ከፍያለሁ፡፡ ገበያው አያፈናፍንም፡፡ የንግድ ባንክ ሰዎች እኔን በመወትወት ከህንድ ቼክ አምጥቼ እንድከፍላቸው ያስባሉ፡፡ ይህንን ማድረግ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን አላደርገውም፡፡ ክብሬን የማውቅ ሰው ነኝ፡፡ በዚህ አገር የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዕዳ የለብኝም፡፡ የትኛውንም ሕግ አልጣስኩም፡፡ በየትኛውም ፍርድ ቤት አልተቀጣሁም፡፡ ለሁሉም አክብሮት አለኝ፡፡ ወደ ጋምቤላ የሄድኩ አንበሳ ነኝ፡፡ ቆስዬ ይሆናል ግን አሁንም አንበሳ ነኝ፡፡ ለጉራ ወይም ለመኮፈስ አይደለም፡፡ ስንቱ ነው ጋምቤላ ሄዶ የሚያውቅ? ኢትዮጵያዊ ጓደኞቼ ወደ ጋምቤላ መሄዴን እንደ ዕብደት ቆጥረውት ነበር፡፡ ስላሰቡልኝ አመስግኜ ምንም እንደማልሆን ነግሬያቸው ሄጃለሁ፡፡ ወደ ጋምቤላ የሄድኩት የአገሪቱን የምግብ ምርት ለመጨመር በማሰብ ነው፡፡ ይኼ ከመቼ ጀምሮ ወንጀል እንደሆነ አላውቅም፡፡ ገንዘቤን አውጥቼ ነው እርሻ እያለማሁ ያለሁት፡፡ እዚህ አንድ ኪሎ ሩዝ 60 ብር ወይም ሦስት ዶላር ይሸጣል፡፡ በዓለም ገበያ የሩዝ ዋጋ በቶን 350 ዶላር ነው፡፡ ለጂቡቲ መንግሥት በቶን 350 ዶላር ሒሳብ ሩዝ እያቀረብሁ ነው፡፡ እዚህ ግን ለአንድ ቶን ሩዝ 3,000 ዶላር እያወጣችሁ ነው፡፡ ለምን ይህንን ሁሉ ገንዘብ ታወጣላችሁ? ስለድሆቻችሁስ ምን ታስባላችሁ? የምግብ አቅርቦትን ለመጨመር እየሞከርኩ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምን እንደ ወንጀለኛ ይቆጥረኛል? መንግሥትና ሚዲያውስ ለምን ወንጀለኛ እንደሆንኩ ለሚያስቡኝ አሳልፈው ይሰጡኛል? ለምን ከዚህ አገር እንድሄድ ይገፉኛል?

ሪፖርተር፡- ከፕሬስ አኳያ ስህተት ሲፈጸም መጠየቅ ተገቢነት ያለው ነገር አይደለም እንዴ?

ራም ካሪቱሪ፡- ይኼ ተገቢነቱ እንዴት ነው? ህንድ እያለሁ ባለፈው ጊዜ ደውለህልኝ ሐሳቤን ገልጬልህ ጽፈሃል፡፡ የእኔን ሐሳብ የሚቃረን ነገርም ጽፈሃል፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ስለእኔ የሰጠውን ትልቅ የተዛባ መግለጫም ጽፈሃል፡፡  ስለተጻፈው ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጬ ጽፌላቸዋለሁ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ስለሆኑ ብቻ ሰድበውኛል ብዬ ጽፌያለሁ፡፡ ማንም ይሁን የሰዎችን ታማኝነት የሚያጥላላና ጥላሸት የሚቀባ ነገር እንዲያደርግ ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ ይሁንና ሐራጅ የተባለው ይካሄድ እንደሆነ የምናየው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ፕሬስ የሰዎችን አመለካከቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አቅርበናል፡፡ እርስዎን እንዳነጋገርነው ሁሉ የመንግሥት ኃላፊዎችንም ስለጉዳዩ ጠይቀናል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ነበር ማድረግ የሚገባን?

ራም ካሪቱሪ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን አነጋግሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ትላልቅ ባለሥልጣናት ካሩቱሪ ለኢትዮጵያ ሰፋፊ እርሻ ትልቅ ተስፋ ቢጣልበትም ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፣ ደካማ ነው እያሉ ስለእርስዎ እየተናገሩ እኮ ነው?

ራም ካሪቱሪ፡- አፈጻጸማችን የሚያበሳጭ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን መሄድ አይገባም፡፡ እምነት የማይጣልበት ተብዬ በመንግሥት ባለሥልጣን ልገለጽ አይገባም ነበር፡፡ መሬታችንን እንደሚወስዱ መናገር አይችሉም፡፡ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መሬቴ በንግድ ባንክ ሥር በዕዳ ምክንያት ያለ ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም ቢሆን ማለት ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው መሬቱ የሚወሰደው? በንግድ ባንክ ያለብኝን ዕዳ ይከፍላሉ ማለት ነው? እንዲህ ባለው ነገር ላይ ስንከራከር ብስለት ሊኖረን ይገባል፡፡ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ባለሥልጣናት አያስፈራሩኝም፡፡ ጋምቤላ ሄጄ ሁሉን ያየሁ ሰው ነኝ፡፡ በድንኳን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት የኖርኩ፣ ከዘንዶውም፣ ከእባቡም፣ ከአንበሳውና ከሚሊዮን ጐሽ ጋር የተጋፈጥኩ ነኝ፡፡ እኔን የምታስፈራሩ ይመስልሃል? ይኼን ሌላ ቦታ ሄዶ መሞከር ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ያለኝን መብት ያልተጠቀምኩ፣ ሆኖም በአንዳንድ ቀልደኞች ቸል የተባልኩ ይመስለኛል፡፡ በህንድና በኢትዮጵያ መካከል የኢንቨስትመንት ከለላ የሁለትዮሽ ስምምነት ስላለ ይኼም እኔን ይከላከልልኛል፡፡ መሬቴን ንኩና የህንድን ኃያልነት ታያላችሁ፡፡ ይኼ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ የእስካሁኑ የሚበቃ መሰለኝ፡፡ ራሴን መከላከል አያስፈልገኝም፡፡ ባለሥልጣናት መሬቴን ከነኩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ያገኙታል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ኃላፊዎች ተግባራቸውን እየተወጡ እንደሆነ አይገነዘቡም ማለት ነው?

ራም ካሪቱሪ፡- የሕይወቴን አሥር ዓመት እዚህ አሳልፌያለሁ፡፡ አገሪቱን አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ አላውቃትም፡፡ በዚህ አገር አስገራሚ የመንግሥት አወቃቀር አለ፡፡ ከላይ ያለው ከፍተኛው የመንግሥት መዋቅር በአብዛኛው በታማኝ፣ ለሚሠሩት ሥራ ቦታ በሚሰጡና በብልህ አመራሮች የተዋቀረ ነው፡፡ ተግባራዊም ባይሆን ከመልካም እሳቤ በመነሳት የሚመሩ ሰዎች ያሉበት ነው፡፡ ሆኖም መካከለኛው ላይ ሥርወ መንግሥት አለ፡፡ በፓርቲ አባልነት የተነሳ ከኃላፊነት ገሸሸ ሊደረጉ የማይችሉ ነገር ግን ለብዙዎች ችግር የሆኑ ኃላፊዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ የፖለቲካ ክርክር እንዲካሄድ በሙሉ ልብ እሞግታለሁ፡፡ ይሁንና ማለት ከሚገባኝ በላይ መናገር አልችልም፡፡ ኢትዮጵያዊ ስላልሆንኩኝ፡፡ ለአገሩ እንግዳ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አፈጻጸምዎ መንግሥት በሚጠብቀው ልክ ካልሆነ እኮ …?

ራም ካሪቱሪ፡- መንግሥት ማነው? የሚጠብቀውስ ምንድነው? መንግሥትን እየጠየቅሁ ነው፡፡ አባቴ የሰጠኝን ገንዘብ ነው ጋምቤላ ላይ ያዋልኩት፡፡ ምን አድርጋችሁልኛል? መንግሥት ምንድነው የሰጠኝ?

ሪፖርተር፡- ለመጥቀስ ካስፈለገ ቢያንስ ለም መሬት ሰጥቶዎታል፡፡

ራም ካሪቱሪ፡- ቡል … ይህንን ቃል አትመው፡፡ የተሰጠኝ መሬት ዘጠኝ ወራት ሙሉ  ጐርፍ የሚተኛበት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ነው የግብርና መሬት ለመፍጠር እየሞከርኩ ያለሁት፡፡ ይህንን የምትሞግት ከሆነ በቂ አኃዝ አለልህ፡፡ የባሮ ወንዝ ጐርፍ የሚማተኛበት ቦታ ስለሆነ ውኃው ሱዳን ደርሶ ሲመለስ እርሻውን ያጥለቀልቀዋል፡፡ ይኼንን መሬት ነው የሰጣችሁኝ፡፡ ምንም ዋጋ የሌለው ነው፡፡ የተሰጠኝ መሬት ከውኃ ወጥቶ የግብርና መሬት እስኪሆን ድረስ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን ለመንቀፍ ባይሆንም፣ ሁሉም ኢንቨስተር ከመንግሥት የተሰጠው መሬት ዋጋ ቢስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋ ቢስ ነው ማለት ግን ከባድ ውንጀላ አይሆንም?

ራም ካሪቱሪ፡- አዎ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሁላችንንም ወደዚህ እንድንመጣ ጋበዛችሁን፡፡ በወቅቱ ይኼ መንግሥት ብልህ ነው ብዬ ነበር፡፡ መሬት በሔክታር 135 ብር እያስከፈሉ ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን ከተማ በሆነው ሆለታ አካባቢ ከጋምቤላ ይልቅ ውድ የሆነ መሬት አለ፡፡ የጋምቤላ መሬት ከ10 እስከ 12 በመቶው ተዳፋትና በባህር ዛፍ የተሞላ ነው፡፡ መሬቱን መንጥሮ ለማስተካከል በሔክታር አንድ ሺሕ ዶላር ይጠይቃል፡፡ በዚያ ላይ ለ50 ዓመታት ነው የተሰጠኝ፡፡

ሪፖርተር፡-  ስለመሬቱ አስቸጋሪነትና ለማስተካከል ስለሚጠይቀው ወጪ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል?

ራም ካሪቱሪ፡- አዎን፡፡ የውጭ ኢንቨስተር ገንዘቡን ይዞ ከመምጣቱ በፊት የሚሰጠው ዋጋና ገንዘቡን ካመጣ በኋላ ያለው ዋጋ አንድ አይደለም፡፡ ይኼ የትም ዓለም ላይ ያለ እውነታ ነው፡፡ በወቅቱ የአበባ እርሻን ያስተዳድሩ ለነበሩት ከፍተኛ ሚኒስትር ጉዳዩን ገልጬላቸው ነበር፡፡ የተሰጠኝ መሬት ጥሩ ባለመሆኑ ለጥ ያለ ሜዳማ መሬት እንደምፈልግ ነገርኳቸው፡፡ ከ20 ሔክታር በላይ አንሰጥም አሉ፡፡ እኔ የምፈልገው ግን ከ100 ሔክታር በላይ ነበር፡፡ ትቼ ስሄድ ግን ከገበሬዎች መግዛት ትችላለህ አሉኝ፡፡ ይኼን ማድረግ እንደሚቻል አላውቅም ነበር፡፡ ከገበሬዎች በቀጥታ መኮናተር እንደሚቻል ተገነዘብኩ፡፡ ከሆለታ ገበሬዎች ጋር ተደራድሬ በዚህ አገር የመጀመሪያውን ኢንቨስትመንት በሆለታ አካሄድኩ፡፡ በሔክታር 30 ሺሕ ብር ከፍዬ መሬት በሊዝ ገዛኋቸው፡፡ የሆለታ እርሻዬ ከብድርም ሆነ ከመንግሥት የተገኘ አይደለም፡፡ ገበሬዎች የሰጡኝ ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ነው መሬት ወራሪ፣ ተቀራማች የሚያሰኘኝ? መንግሥት በሔክታር 135 ብር እስከከፈልኩ ድረስ ሊሰጠኝ ፈቃደኛ ነበር፡፡ እኔ ግን አመስግኜ በሔክታር 30 ሺሕ ብር ከፍዬ ወደምገዛበት ሄድኩኝ፡፡ ይህንን በማድረጌ ደደብ ነኝ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ግን በዚህ ተገርሞ ወሊሶ ላይ የተንጣለለ መሬት ሊሰጠኝ ተገዷል፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ባንክ ዕዳዬ ይከፈለኝ እያለ ነው፡፡ ሌሎችም ባንኮች እንዲሁ፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎችም ደስተኛ አይደለንም ብለዋል፡፡ ታዲያ የእርስዎ መጨረሻ ምንድነው?

ራም ካሪቱሪ፡- ነገዬን መተንበይ አልችልም፡፡ ነገን ግን መፍጠር እችላለሁ፡፡ ለምንድን ነው ግን ሁሉም ውድቀቴን የሚፈልገው? ሞቴን ለማየት ለምን ይቸኩላሉ? ሁሉን ነገር ዘጋግቼ ባዶ የምቀር እመስላለሁ እንዴ? ይህ ከሆነ ሐሳባችሁ የተሳሳተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተስፋ መቁረጥዎን እያሳዩኝ ነው?

ራም ካሪቱሪ፡- በአሥር ዓመት የኢትዮጵያ ኑሮዬ አንድ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ አትሞክር፣ ከሞከርክ ግን ማሳካት አለብህ፡፡ ከወደቅህ ትሰቀላለህ፡፡ ማናችሁ እኔን የምትሰቅሉ? እዚህ አገር ውድቀት ቦታ የለውም፡፡ በአሜሪካ ሲሊከን ቫሊ ውስጥ ግን ውድቀት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በአፍሪካ የወደቀ ያበቃለታል፡፡ ስትወድቅ ጥንብ አንሳው ሁሉ ተሰብስቦ ሊበላህ ሞትህን ይጠባበቃል፡፡ መንግሥትንም ሆነ የባንክ ሰዎችን ዕርዳታ እየጠየቅሁ ወይም እስኪሻለኝ ተንከባከቡኝ እያልኩ አይደለም፡፡ ዕርዳታ አልጠየቅሁም፡፡ ማንንም አላስቸገርኩም፡፡ ለማድረግ እየጣርኩ ያለሁት የተከበረ ተግባር ነው፡፡ ምግብ ማምረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በግብርና ኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር ያለው የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ነው ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደናንተ ያሉትን እርሻዎች የሚከታተለው፡፡ በመሆኑም የኤጀንሲውን ኃላፊዎች መሞገቱም ሆነ ሚናቸውን ማጣጣሉ ምንም ነጥብ ያለው አይመስልም፡፡

ራም ካሩቱሪ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ሰፋፊ እርሻዎችን እንዲከታተል ነው የተቋቋመው፡፡ እስከዚህ ባለው ሒደት ምንም ቅራኔ የለኝም፡፡ ሆኖም ካሩቱሪ በዚህ ኤጀንሲ ሥር ነው ወይም ኤጀንሲውም ሆነ ኃላፊዎች እኛን ይቆጣጠራሉ ወይ ከተባለ መልሱ በጭራሽ አይደለም ነው፡፡ ካሩቱሪ ክትትል የሚደረግበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ለምን ብለህ አትጠይቀኝ ይኼው ነው የሆነው፡፡ ስለዚህ ለግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ተጠሪ አይደለንም፡፡ በእኛ ላይ ሥልጣን ስለሌላቸው ገለል በሉ እላቸዋለሁ፡፡ ከእኛ ፕሮጀክት ጋር ለሚያያዝ ማንኛውም ነገር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ማነጋገር ትችላለህ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ፕሮጀክት ቢሳካ ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ቢሰናከል ግን ማንንም ሳይሆን ካሩቱሪን ነው የሚጎዳው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካፒታሌን ለማሳደግ እንዲረዳኝ የአክሲዮን ድርሻ እንድሸጥ ነግረውኝ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ገንዘብ እንዳለኝ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ አክሲዮን ለመሸጥ ወደ ገበያ መምጣት አላስፈለገኝም፡፡ በጊዜው የአክሲዮን ገበያው እንዳሁኑ ቁጥጥር አልተደረገበትም ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክም መሄድ አላስፈለገኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ሆኖም ከንግድ ባንክ ለሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ተበድረዋል፡፡

ራም ካሩቱሪ፡- ይህ እውነት አይደለም፡፡ ከንግድ ባንክ ጋር ያለን ጠብ በአንድ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ለማልማት 180 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማምጣት እየሠራሁ ነበር፡፡ ብሔራዊ ባንክ ገንዘቡን ማምጣት የምችልበት ፈቃድ እንዲሰጠኝ አመልክቼ ነበር፡፡ ገንዘቡ በብድር የሚመጣ በመሆኑም መልሼ ማስወጣት እንድችልም ነበር የጠየቅሁት፡፡ ብሔራዊ ባንክ በገንዘቡ መምጣት ላይ መወሰን አልቻለም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማክሬ ገንዘቡን ለውጭ የምታመጣው ከሆነ ምንም ችግር የለውም ስላሉ፣ በኋላም ገዥው ባንክ ስለፈቀደ የውጭ አበዳሪዎቼ ከህንድ በመምጣት 180 ሚሊዮን ዶላሩን ሊሰጡን ዝግጁ ነበሩ፡፡ ይሁንና ጠበቆች ምን ሲደረግ በአገር ውስጥ ፈቃድ የሌለው ባንክ እንዴት ንብረት አስይዞ ይበደራል? ሕጉ አይፈቅድም አሉ፡፡ ስለዚህ እዚህ ያለኝን ንብረት በዋስትና በማስያዝ መበደር አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከአገር ውስጥ ባንኮች አነስተኛ ገንዘብ በመበደርና እነሱን አጋር በማድረግ በሚጽፉልን የዋስትና ሰነድ ብድሩን ልናገኝበት የምንችልበት ዕድል እንዳለ ምክር ስላገኘን ለንግድ ባንክ የብድር ጥያቄ አቀረብን፡፡ ከመነሻው 25 ሺሕ ሔክታር በማስያዝ ነበር ብድር የጠየቅነው፡፡ ሆኖም የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ስለንብረት ሲጠየቅ 100 ሺሕ ሔክታር ነው በማለት ሙሉውን መሬት ለማስያዣነት ሰጣቸው፡፡ ከዚሁ ሁሉ በኋላም ንግድ ባንክ የዋስትና ሰነዱን ይሰጠናል ብለን በተስፋ ብንጠብቅም ለአምስት ዓመታት ያህል ቆይቶም አልተሰጠንም፡፡ ይህንን ላደረጉበት በርካታ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ሒደት አበዳሪዎቼ ፍላጎት በማጣት ሄደዋል፡፡ የ180 ሚሊዮን ዶላሩን ብድር ያጣሁትም በንግድ ባንክ እንቢተኛነት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ የምንፋለምበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ልናገር ከምችልበት ርቀት በላይ መናገር አልችልም፡፡ ነገር ግን ያለኝ ማስረጃ በርካታ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ይህ ግን ለእኔ ምንም አይጠቅመኝም፡፡

Kumilachew Ambo

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: