Leave a comment

የካፋ ሕዝብ ታሪክ የማይካድ እውነታ፥ ይድረስ ለኦሮሞ ወገናችን ሊህቃኖች


    ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት ተብትቦ በዘለቀው••• በተለይ  በአሁኑ ስርዓት ምክንያት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃና መከራ ለመታደግና ብሎም በሕዝቦች መፈቃቀድና መተማመን ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባቱ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም።

የዚህንም ዓላማ ስኬታማነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዓላማዎች ማዕቀፍ ስር የተደራጁና እየተደራጁ ያሉ አካላት የቀውሱን መንሳኣኤዎች፣ ለቀውሱ መፍቻ መላ ምቶችንና ወደፊት የምትመሰረተዋ ኢትዮጵያ በምን መልኩ መገንባት አለባት የሚሉ ግለሰባዊና ምሁራዊ መፍትሄዎችን ከየአቅጣጫው እያነሱና እየሰነዘሩ ይገኛሉ።

     ከዛም አልፎ እነ / ብርሃኑ ነጋን የመሳሰሉ የአገራችን ምሁራንና ወገኖች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ልንታደግ የምንችለው በሁለገብ የትግል ስልት ነው በማለት ያላቸውን ክብርና ዝና የተንደላቀቀ የኑሮ ደረጃ ትተው ክቡር ሕይወታቸውን ለመሰዋት ጭምር በረሃ ከወረዱ ጊዜያት ተቆጥረዋል። አቶ አንዳርጋቸውም ስለሁላችን ነፃነት ሲሉ እስር ቤት የህሊና እስረኛ ሆነው እየማቀቁ ይገኛል።

     ሂደቱን እንደሚከታተልና የተሻለ ስርዓት ለዛች አገር እና ሕዝቦች እንደሚናፍቅ እንደ አንድ ተራ ግለሰብ ብዕሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ Ethiomedia ላይ ያነበብኩት The Oromo Leadership Convention and the Future of Ethiopia: A Reply to Tedla Woldeyohanes’s Plea for Clarity በሚል ርዕስ Oct. 20, 2016 በፕ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳ የቀረበው ፅሑፍ ነው።

ዶ/ር ተድላ አትላንታ ሊደረግ ከታቀደው የኦሮሞ ምሁራንና መሪዎች ጉባኤ በፊት ሊመለሱ ይገባል ብሎ ካነሱት  ጥያቄዎች ውስጥ ትኩሬቴን የሳበው ፕ/ር ሕዝቅኤል ለሁለተኛው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ነው።

ጥያቄውም፥ ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ግዛት የሚባል ነበር ወይ? በካርታ ላይ የትኛው ቦታ ላይ ይገኛል? የሚለው ሲሆን፤

ፕ/ር ሕዝቅኤል ሲመልሱም፥ ፈረንሳዊ ተጓዥ Antoine d’Abbadi እንደፈረንጆች አቆጣጠር በ1840ቹ ውስጥ ክልሉ (የኦሮምያ) ከምፅዋ እስከ ካፋ መሽፈኑን በ1902 Oromo as “a great African nation” በሚል ርዕስ ባሳተመው ፅሑፍ ውስጥ መግለፁንና አባይን አቐርጦ ወደ ደቡብ በዘለቀበት ወቅትም የገዳ ሥርዓትን የምያራምዱ አምስት የሕዝብ መንግሥታት (Republic)፥ ሊሙ፣ ጌራ፣ ጎማ፣ ጉማና ጅማን መመልከቱን እንደማጣቃሻ ተጠቅመው፥ የመጪውም የኦሮምያ ክልል የአሁኑን የካርታ ቅርፅ ይዞ የአሁኑ የይስሙላ የራስ አስስተዳደር የወደፊቱ እውነተኛ የራስ አስስተዳደር ይሆናል ሲሉ ይገልፃሉ።

ከጉዳዩ እይታዬ  በፊት ፕ/ር ሕዝቄልን በየግዜው በምያነሷቸው ገንቢ የሆኑ አገራዊ ጭብጦችና በእውነትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ማህበራዊና አገራዊ አንድነት ይገነባ ዘንድ በምያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸው የማከብራቸው ግለሰብና ምሁር መሆናቸውን ሳልገልፅ ማለፍ አልፈልግም።

ሆኖም በዚህ የኦሮሚያ ካርታ ላይ ያነሱት አስተያት ብያንስ የታሪኩ ባለቤት የሆንኩት እኔንና ብሎም በሚሊዬን የሚቆጠር የካፋ ሕዝብንና በካፋ ግዛት በአንድ መንግሥታዊ መዋቅር ስር ሆነው ህልውናቸው ተጠብቆ በራሳቸው ነገስታት ይተዳደሩ የነበሩ ሕዝቦችን ታሪክ፣ ማንነትና ህልውና ያገለለ ትንታኔ ነው።

ለዚህም እማኝ ደግሞ ከታሪኩ ባለቤቶች ባሻገር እንደ ታሪክ ተመራማሪ ፕ/ር ሕዝቅኤልን ከመሳሰሉ ሰዎች የተሻለ ለእውነታው ቅርብ የሆነ አለ ብዬ አልገምትም።

እኔ እዚህ የማቀርበው እይታ እንደ አንድ ዜጋ እንጅ ምሁራዊ ትንታኔ ስላልሆነ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ የሚያውቁትን እውነት ለአገራችን ሕዝቦች በማቅረብ መታረምና መስተካከል ያሉባቸውን ሃቆች አስተካክለን ለሕዝቦቻችንና አገራችን በሚጠቅም መልኩ እንድንጓዝ እንዲረዱን ስል በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የካፋ ግዛት (Kingdom) በፀሐፊዎች እይታ

  1. Herbert Lewis, “Jimma Abba Jifar, An Oromo Monarchy: Ethiopia, 1830-1932”, (201), p.35

” The people of Jimma calim that their predecessors in this area were the Kafa.”

የጅማ ሰዎች እዚህ ቦታ የነበሩ ቀደምት ወላጆቻቸው ካፋዎች እንደነበሩ ይገልፃሉ ካለን በኋላ ፥በአካባቢው የኦሮሞዎች አሰፋፈር  ሲገልፅ፥ እንደ አፈታሪክ አገላለፅ ኦሮሞዎች በአንዲት መሬት ስትረግጥ ምድሪቱን በምታንቀጠቅጥ ማካሆሬ (Makahore) በተባለች ንግስት መሪነት አማካኝነት አካባቢውን ሲወሩ ካፋዎች ከጎጀብ ማዶ ሸሹ ይልና፥

ሁሉም ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ሸሹ ወይም ሞቱ ተብሎ አይገመትም። ምክንያቱም በኦሮሞ ባህል መሠረት አንድ ኦሮሞ ያልሆነ ግለሰብ ወድያውኑ የኦሮሞ ሥም ተሰቶት እንደማህበረሰቡ አካል በደል ሳይሰርስበት ይኖራልና።

ነባራዊ ሃቅ፥ ኦሮሞ ወደ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ መስፋፋት የጀመረው በ18ኛው መቶ ክ/ዘ ሲሆን የካፋ ንጉሳዊ አስተዳደር ግን ከመካከለኛው እስከ 19ኛው መቶ ክ/ዘ ድረስ በአካባቢው (የግቤ እናርያን ጠቅልሎ ማለት ነው) ገናና እና ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር ኖሮት የዘለቀ ነው።

ከግቤ መለስ ያሉ አካባቢዎች በካፋ ዘውዳዊ ግዛት ሥር ነው ስንል ከምርምር ከተገኙት የታሪክ ማስረጃዎች በተጨማሪ የቦታዎች ስያሜና በውስጡ የሚገኙት ሕዝቦች የጎሳ መጠሪያዎች ለምሳሌ፥ ቦሾ፣ ጊቤ (ጊቤ ወንዝ)፣ በደሌ፣ ጎሬ ወዘተ እና ሌሎች ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።

አንፍሎ በወለጋ፣ ሻካ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ፥ ሽናሻ ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣

በአማራ እና በኦሮሞ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የካፋ (ጎንጋ)ሕዝብ አካል ናቸው።

  1. Amnon Orent “Refocusing on the history of Kafa prior to 1897: A discussion of political process” በሚል ርዕስ ባሳተመው ፅሑፍ የካፋ ግዛት ከጅማም አልፎ እስከ ካንባታና ወላይታ ይዘልቅ እንደነበር፣ በወቅቱ ያሁኗ ጅማ እና እናርያ (Enaria) ሕዝቦች ግዛት የካፋ ንጉሳዊ አስተዳደር ሥር  እንደነበርና ቛንቛቸውም ተመሳሳይ እንደነበር ያብራራል፡

በተጨመሪም የግዛቱን ስፋት ሲያብራራ፥•••በካፋው ንጉሥ በሆቲ ሼሮቺ የአገዛዝ ዘመን (1798-1821) ካፋ በደጋማው የኢትዮጵያ አካባቢ ከነበሩት መንግሥታት ሁሉ የላቀ ሃያል ነበር። በመሆኑም አርባ ነገስታትና ባላባቶች ለካፋ ንጉሳዊ አስተዳደር ግብር ይከፍሉ ነበረ።••• በወቅቱም በሆቲ ሼሮቺ አመራር ካፋ ግዛቱን አስፋፍቶ ወሊሶ ከሚገኝ አንድ ልዩ ዛፍ ሦር ተቀምጠው ከመከሩ በኋላ ወደ ሸዋ ላለመቀጠል ወሰኑ•••” ኦሬንት 197፣277 ላንጌ 1982፣2223 ከአቶ በቀለ ወ/ማርያም የካፋ ሕዝቦችና አጭር ታርክ ገፅ 95 ።

     ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቡና የተገኘው በአሁኑ ካርታ በደቡብ ክልል ካፋ ዞን ማኪራ ቀበሌ

ውስጥ መሆኑ በዓለምና አገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቶት የካፋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ቦንጋ ውስጥ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ተገንብቶ ይገኛል።

     ሆኖም የካፋ ስያሜ ለቡና ምንጭ ባለቤትነት ማረጋገጫ ያለው ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚታወቅ ብቻ ፥ በኦሮምያ ከልላዊ መንግሥት አማካኝነት ቡና የተገኘው ጅማ ነው እየተባለ በመንሥት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የሚደረገው ታሪክ ማዛባቱ ሂደት መቆም ያለበትና አሳዛኝ ድርጊት ነው። ምንም እንኳን ጅማ የካፋ አካል መሆኑ ቢታወቅም።

     ስለሆነም ሁላችንም መብታችንን ለማስከበር በምናደርገው እንቅስቃሴ ሂደት የሌሎችንም መብትና ህልውና ማክበራችንን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል እያልኩ፥ ለዘላቂ ህልውናችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የጋራ ቤታችንን የመገንባቱን ጥረት እንድንቀጥል ስል በዚህ አጋጣሚ መልእክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ።

ያሮን ቆጭቶ ከካሊፎርንያ

Nov., 2016

Posted by Kumilachew Ambo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: