Leave a comment

የሰቆቃ ኑሮ የምትገፋ ታሪካዊቷን ካፋ፡ እንዴት እንታደጋት?


የሰቆቃ ኑሮ የምትገፋ ታሪካዊቷን ካፋ፡ እንዴት እንታደጋት?
የራሷ መንግስታዊ አስተዳደር የነበራትና የዓለም ሕዝብ በአፉ ፉት ካሚለው ተወዳጅ ቡና
ጋር አብሮ በየዕለቱ የምያወሳት የቡና መገኛ ምድር ፤ ሕዝቧም ለአገርና ለሕዝብ ቅድምያ
ሰጥተው ሌት ተቀን ይዋደቁላት የነበረች፤ ድንበርና ባህር አቋርጠው እየተጓዙና ከተለያዮ
አካባቢዎች ለሚመጡም ትልቅ የገበያ ማዕከል በመሆን ጭምር የቡና፣ የወርቅ፣ የማር ፣የጥርኝ
ዝባድ፣ የቅመማ ቅመምና የመሳሰሉ ምርቶችን በመገበያየት ጠንካራ የምጣኔ ሃብት መሠረት
የነበራት፣ በነፍስ ወከፍ በሺዎች የሚቆጠር የቀንድ ከብት ያፈሩ የነበሩባት፣ ልጆቿም ከ10
ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ አገራዊ አገልግሎት መስጠት ይጀምሩ የነበሩባት፤ ጠንካራ የነቃና
የተደራጀ ሕዝብ፣ ወታደራዊና የደህንነት ተቋም የነበራትና ብዙ ሊባልላት የምትችል በተፈትሮ
ሃብት የታደለች ውብ በአሁኑ የደቡብ ክልል በደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኝ
‘ክልል’ ወይም ዞን ነች።
ዛሬ ግን ሕዝቦቿ እጅግ የሚያሳዝንና የምያንገበግብ የሰቆቃ ሕይወት እየገፉ ይገኛል።
ለዘመናት የዘለቀውን የካፋ ሕዝብ ሰቆቃ፥ በተለይ ደግሞ አሁን ባለው ሥርዓት እየተከሰተ
ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግርና ጭቆና ሁሉ በዚህ አጭር ፅሁፍ መግለፅ ስለማይቻል፤ ለዚህ ጊዜ
ሊሰጠው የማይገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ሁላችንም ድርሻችንን እንድንወጣ ያክል ጥቂት ችግሮችን
እና መፍትሔ ይሆናሉ የምላቸውን ሃሳቦች ላጋራ እወዳለሁ።
‘በክልሉ’ እየተከሰቱ ያሉ ጭቆናዎችና ችግሮች፥
1. የመሬት ንጥቅያና ዘረፋ፥
ለካፋ ሕዝብ መሬቱ የኑሮው መሠረታዊ ዋስትናና ለመጭው ትውልድ የሚያስረክበው አንጡራ
ሃብቱ ነው። ሃብቱን የተነጠቀ ሕዝብ ደግሞ ከጨቋኞቹ ምፅዋት ሰብሳቢ፣ የራሱን ተቋማት
መስርቶ በራሱ የማይተዳደር አቅም የሌለው፣ ከብሩን የተነጠቀና የተዋረደ እንደሚሆን
በዓለምላይ ያሉ ተመሳሳይ እጣ የደረሰባቸው ሕዝቦች ታሪክ ያስተምረናል።
በአሁኑ ሰዓት የካፋ ሕዝብ ወደዝያው እያመራ እንደሆነ መሬት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት
ያሳያሉ። ይህንን በየእለቱ የምናየውንና የምንሰማውን ግፍ አንድ Ines Possemyer የተባለ
ፀሐፊ ከገለፀው ውስጥ አንዱ አንቀፅ እንዲህ ይነበባል፥
“***•••ኢንቬስተሮች የሚያደርጉት የመጀመርያው ነገር በመሣሪያ የሚጠበቅ ኬላ እና እስር
ቤት ማበጀት ነው። ከከብቶቻቸው [የመሬቱ ባለቤት የሆነው ነዋሪዎች] ጋር የሚመጡ
የአካባቢው ሰዎች በኬላው ለማለፍ ክፍያ መክፈል አለባቸው። በተጨማሪም ቀድሞ ያደርጉ
እንደነበረ ሁሉ ከከብቶቻቸው ውስጥ አንዱ እንኳ ደን ውስጥ ቢገባ፣ ለእርሻ የሚሆን ሞፈርና
ቀንበር ለመስራትም ሆነ ለጎጇቸዉ መቀለሻ የሚሆን አንዲት እንጨት ቢውስዱ
[በኢንቬስተሮቹ] ይቀጣሉ ይታሠራሉ።
በተለይ በአካቢው ትልቁ የቡና አምራች የሆነው “የግሪን ኮፍ” ኢንቬስተር የአካባቢውን
ገበሬዎች ሦስት ሺህ (3000) የንብ ቀፎውች እራሱ እንኳን ፈቃድ ካላገኘባቸው መሬቶች
ሳይቀር ጭምር አስነስቶና አውድሞ ገበሬዎቹ አስራ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ዩሮ(13,500.00
euro) የሚደርስ ኪሳራ አድርሶባቸዋል። “
በተመሳሳይ የማኪራን የደን ቡና የወሰዱትን የሼህ አላሙዲንን ሁኔታ እንዲሁ ያመለክታል፥
በበለጠ የፀሐፊውን ፅሑፍ የሚቀጥለውን መስፈንጠሪያ በመከተል ያንብቡ፥

Click to access wild-coffee.pdf


በዋናነት ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ጭምር የአየር ንብረት ሚዛንን በመጠበቅ ረግድ ጉልህ
አስተዋፅኦ በማበርከት ያለውን በሕዝቦች አንክብካቤ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ
ሲወራረስ የዘለቀውን ጥቅጥቅ ደን ያለማንም ከልካይ ለምንም ደንታ የሌላቸው አልሚ
(Investor) ተብዬዎች እያወደሙት ይገኛል።
ከዚህ የባሰ ጥፋት ሳይደርስ በፊት ይህንን የማን አለብኝነት ግብታዊ አሰራር ለማስቆም
ከመላው ፍትህ ናፋቂ የኢትዮጵያ ወገናችን ጋር በመሆን የምንነሳበት ጊዜው አሁን ነው!!!
2. የተማረው ማህበረሰብ ኃይል መገፋት
ለአንድ ማህበረሰብ ዕድገት ማህበረሰቡ ነገ ህይውታችንን ይቀይሩልናል እነሱም ከእኛ የተሻለ
ሕይውት ይኖራቸዋል በሚል ተስፋ ሃብቱን፣ ጊዜውንና፣ ጉልበቱን ሳይሰስት በማበርከት
የሚያስተምራቸው የልጅቹ ሚና እጅግ ጉልህ ነው። ለተማሩት ለልጆቹም ቢሆን የወላጆቹንና
የወገኖቹን ሕይወት ከመቀየርና ለመጭው ትውልድ የተሻለ ነባራዊ ሁኔታ ፈጥሮ ከማለፍ
የበለጥ የሚያረካና የሚያኮራ ነገር አይኖርም፤ የመማራቸውን ውጤትም ቢሆን የሚመዝኑበት
ከዚህ የተ ሻለ መመዘኛ አይኖርም።
ሆኖም በካፋ ‘ክልል’ ወይም ዞን እየተደረገ ያለው ግን ሕዝቡ በሁለት እግሩ እንዳይቆምና
ብሎም እንዳያድግ ሆን ተብሎ እየተደረገ ያለ ሴራ ነው።
በየጊዜው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀው በከፍተኛ ስሜትና ወኔ
የአካባቢያቸውንና የወገናቸውን ሕይወት ለመለወጥ ተስፋ ሰንቀው የሚመለሱ ምሁራንን፥
ገሚሶቹን ጭራሽ አካባቢው ውስጥ እንዳይሰሩ፥ ገሚሶቹን ደግሞ ስራ መስራት ከጀመሩ በኋላ
የሕዝቡን በደል በየስብሰባ መድረኮች ስለምያነሱና ኢፍትሃዊ ድርጊቶች እንዲስተካከሉ
በሚያነሷቸው ጠንካራ አቋሞች የተነሳ ብዙዎቹ ከአካባቢው እንዲገለሉ ተደርገዋል
እየተደረጉም ነው።
እንደምንም ታግለው የቀሩትም ቢሆኑ የአካባቢውንና የማህበረሰቡን ፍላጎትና ተጨባጭ ሁኔታ
ያገናዘበ የልማት ዕቅድ ነድፈው ለውጥ የሚያመጣ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ የስርዓቱን
ጨቋኝና በዝባዥ መመሪያዎች እንድያስፈፅሙ ሆነው በባርነት ቀንበር ሥር ይኖራሉ። በተለይ
መምህራኖችና የግብርና ሰራተ ኞች እያሳለፉት ያለው ስቃይ ለመሽከም ቀርቶ ለማውራት
የሚከብድ ነው። ብዙሃኑ ለሕዝባቸውና ለአካባቢያቸው የሚቆረቆሩ የዞኑ የኢሕአዴግ አባላት
እና የአስተዳደር ሰራተኞችም ሁኔታ ከዚህ የሚብስ ነው።
ደግነቱ ግን ይህ የባርነት ቀንበር በኛው ብልሃትና ጥበብ ከጫንቃችን የሚወርድበት ጊዜ እሩቅ
አይሆንም!!!
3. አስተዳደራዊ በደል እና የመስረተ ልማት እጦት
የተረጋጋ አስተዳደራዊ ስርዓትና የስልጣን ሽግግር መኖር፣ በጉዳዮች ላይ ሙሉ የመወሰን መብት
ያላቸውን ከህዝቡ ለህዝቡና በህዝቡ የተወከሉ ባለስጣናት የመምረጥ፣ ሃሳብን የመግለፅ
መብት መጠበቅ፣ ፍትህን በአቅራቢያና ያለምንም መጉላላት ማግኘት መቻል፣ በነፃነት
የመደራጀትና ለአካባቢና ለወገን ዕድገት አስተዋፅኦ ማበርከትን የመሳሰሉ ተፈጥሮዓዊና
ሰብዓዊ መብቶቹን በእጁ ያልጨበጠና ከሌሎች ይሁኝታ እንዲጠብቅ የተደረገ ሕዝብ እሱ
ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የባርነትና የሰቆቃ ቀንበር ውስጥ መውደቁ አይቀሬ ነው።
የካፋ ሕዝብ እስከዛሬ ድረስ መብቱንና ክብሩን ለማስጠበቅ የልፈፀመው ገድል የለም፥
እየፈፀመም ይገኛል፥ ያውም በላቀ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ስብእና እና ከአገርና ሕዝብ ወዳድነት
መለያ ባህሪያት ጭምር።
ሆኖም እስከዛሬ ይህንን ገናና ማንነት እና የሕዝቡን እምቅ ጥበብና ክህሎት አደራጅቶ ለግብ
የሚያበቃ ሕዝባዊ ተቋም (በየጊዜው በሚመጡ የማዕከላዊው መንግሥት ኃይሎች
እየተበታተነ) ባለመኖሩ ምክንያት እየተሰቃየ ይገኛል።
አሁን ግን ሕዝቡ ይህንን ታሪካዊ ቀውስ ለመቅረፍና ብሎም ለመጭው ትውልድ የተሻለ
ታሪክና ስርዓት ገንብቶ ለማለፍ በቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላቀ እየተጋ ይገኛል።
ከነዚህ ተግዳሮቶች መሃከል በጥቂቱ፥
3.1. የአስተዳዳሪዎች በየጊዜው መቀያየር፦በዚህ ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ የዞኑ
አስተዳደርና የከተማው ከንቲባ በየዓመቱ ለማለት በሚቻል ሁኔታ ተቀያይረዋል።
የምያሳዝነው ነገር ደግሞ ከነዚህ ከሚቀየሩት መካከል አብዛኞቹ ከቦታቸው
የሚነሱት ገና ዕቅድ ነድፈው ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው ለውጥ አምጪ
እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሲጀምሩ መሆኑ ነው።
3.2. የፍትህ እጦትና እንግልት፦የካፋ ሕዝብ ያለፍላጎቱ የቦታ እርቀትና በሃብቱ፣
በጉልበቱና በጊዜው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ብክነት ከግምት ባላስገባ መልኩ
ፍትህን ፍለጋ እስከ ሐዋሳ ድረስ እንዲጓዝ በመደረጉ ምክንያት እጅግ ብዙዎች
ለጉዞው አቅም ከማጣታቸው የተነሳ ፍትህን ሳያገኙ ፊታቸውን በእንባ አርሰው
በቤታቸው እየቀሩ ይገኛል። በተጨማሪም ለአካባቢው ልማት መዋል የሚገባው
በጀት ሠራተኞች ወደ ሐዋሳ በምያደርጉት አላስፈላጊ ጉዞ እየባከነ ይገኛል።
እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችና አንዳንድ በአካባቢው ለመስራት የሚመጡ
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስተዳደራዊ አገልግሎት ለማግኘት እንግልት
አየደረሰባቸው ይገኛል።
3.3. የልማት መሬት ለአካቢው ተወላጆች መከልከል፡ ከውጭና ከሌላ አካባቢ የመጡ
የስርዓቱ ጥቅመኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሬት እንደፈለጉ ሲያገኙ የአካባቢው
ተወላጅ ግን የራሱን መሬት ጠይቆ የማኘት መብት ተነፍጎታል።
3.4. በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከቦታቸው ለተፈናቀሉ ወግኖች እገዛ መነፈግ፡
ለምሳሌ እንደ ኢ.አ በ1998ቹ አካባቢ በቦንጋ ከተማ ውስጥ በተከሰተው የመሬት ናዳ
ምክንያት ለፍተውና ጥሪታቸውን አሟጠው ከሰሩበት ቤት እና ካለሙት
አካባቢ(በተለይ ነተለምዶ “ዘጠኝ ሰማንያ” ከሚባለው ሰፈር) ያለምንም በቂ እገዛ
ከቦታቸው የተነሱ ወገኖች ታሪክ እስከዛሬ ድረስ ዞኑ ለነማንና በነማነው
የሚተዳደረው የሚለውን ጥያቄ በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ እንዲያጭር አድርጓል።
ይህንን የሕዝቡን ጥያቄ በይበልጥ ያጠናከረው በተመሳሳይ ወቅት በድሬዳዋ
በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ዞኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ብር እርዳታ መላኩ
ነው። በእርግጥ እርዳታው ለድሬዳዋ ወገኖቻችን ተገቢና አስፈላጊ የነበር ቢሆንም፥
ፍቅር ከቤት ይጀምራል እንደሚባለው ለራሱ ነዋሪዎች ቅድምያ መድረስ ነበረበት
ለማለት ነው።
3.5. ለአካባቢው ዕድገት አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚመጡ ግለሰቦችንና ወገኖችን
ከፖለቲካ ትርፍና ጉዳት አንፃር እየመዘኑ የማራቅ አካባቢውን ከመጠን በላይ
እየጎዳ ይገኛል።
3.6. በተፈጥሮ ሃብቱ እራሱን መቻል የነበረበት አካባቢና ሕዝብ በህክምና ማዕከላት፣
በቁሳቁስ የተደራጁ ት/ቤቶች፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የንባብ ማዕከል (Library)፣
የመብራት አገልግሎት፣ መንገድ፣ የሕዝብ ማዕከላት፣ ደረጃውን የጠበቀ እስፖርት
ማዘውተሪያና እስታዲዬም ወዘተ በመሳሰሉ አገልግሎቶች እጥረት ሰሚ አጥቶ
እየተሰቃዬ ይገኛል።
3.7. የአካባቢው ንብረት መዘረፍ፦ ኢሕአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ ጥቂት ዓመታት
ውስጥ ከዚህ በመሰረተልማት ግንባታ ደሃ ከሆነ አካባቢ ንብረቶች ተዘርፈዋል።
በተለይ ለዘመናት ለአካባቢው ሕዝብ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውና በአገራችን
ውስጥ በደርግ ጊዜ ከተተከሉ ጥቂት ዘመናዊ የከብት ማረጃ ማሽኖች አብዱ
የሆነው የቦንጋ ከተማ ማሽን ለአብነት የሚጠቀስ ነው። የስርቆቱ ዱካ እስከዛሬ
ድረስ አለመገኘቱና በወቅቱ ሌቦቹ ሊሻገሩበት የሚችሉባት አንዲት መንገት ያለችው
በጊዜው ፖሊስ ጣቢያ በነበረው አሁን ኮፊ ላንድ ሆቴል በሆነው አጠገብ መሆኑ
ዘራፊዎቹ ማን እንደሆኑ ጥያቄ ያስጭራል። ከሁሉም በላይ እስከዛሬ ድረስ ሕዝቡን
እጅግ እያስቆጨ ያለው፥ መከላከል ሲገባው ምራቁን በመምጠጥ ብቻ ያሳለፈው
ጉዳይ ቢኖር ነገሩን ለማድበስበስ ተብሎ የቄራው ጥበቃ ሠራተኛ የነበሩት አንድ
ግለሰብ ሌቦችን አጋልጥ እየተባሉ ሌትና ቀን በግርፋት ይሰቃዩ የነበሩት የታሪካችን
የቅርብ ጊዜ ጠባሳ ነው።ከአሁን በኋላ እንዲህ አይነቱ ፀያፍ ነገር በአንዱም ወገናችን
ላይ እንዳይደርስ በጋራ መቆም አለብን።
በተጨማሪም ደርግ መውደቅያው አካባቢ ለቦንጋ ከተማና አካባቢዋ አስመጥቶ ወደ
አካባቢው አስኪጓጓዝ ድረስ በአዲስ አበባ የኢትዮጵ መብራት ኃይል ባለስልጣ ግቢ
አስቀምጦት የነበረው ግዙፍ የመብራት ጀነሬተር አና በበቃ ቡና ለዘመናት የቆዬ
ዘመናዊና ተጣጣፊ ድልድይ ወደ ትግራይ መኼዳቸው ይጠቀሳል።
መፍትሔዎች፦
1. እንደቀድሞው ሁሉ በሁለንተናዊ የኑሮ ደረጃዎች ሁሉ ከምንም በፊት የሕዝባችንና
የአካባቢያችንን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ
2. ለወገኔና ለአካባቢዬ ምን አስተዋፅኦ ላበርክት በሚል የጋለ ውስጣዊ ስሜት ተነሳስተን
በየለንበት እራሳችንን በማደራጀት አቅማችንን የሚያጎለብቱና ለትውልድ የሚሸጋገሩ
ተቋማትን መገንባት
3. የመሬታችንና የሃብታችን ሙሉ ባለቤት መሆናችንን ማረጋገጥ፤ መልማት የሚገባቸው
መሬቶቻችንንና የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በደንብ በአግናቡ በመጠቀም የሃብት
አቅማችንን ማበልፀግ
4. እርስ በርሳችን እየተመካከርን፣ እየተማማርንና እየተጋገዝን በራሳችን እግሮች
መቆማችንን ማረጋገጥና ከአጎራባች ክልሎችና የመላው የአገራችን ሕዝቦች ጋር ያለንን
የመተባበርና የአብሮነት ተግባር በይበለጥ አጠናክሮ መቀጠል
5. በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወገናቸውን በሚጎዳ ተልዕኮ የተሰማሩ ግለሰቦችን
ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ከማያልፈው ወገናቸው ጋር ዘብ የመቆም ክብር ምንነትን
እንድያዩ መርዳት
6. ለእውነትና ለሕዝብ ጥቅም በመቆማቸው ምክንያት ስደት፣ እስርና እንግልት
ከሚደርስባቸው ወገኖቻችን ጎን በመሆን እነሱንና ቤተሰቦቻቸውን በሁለንተናዊ ረገድ
ሁሉ መከላከል፣ መርዳትና ማገዝ
7. በአካባቢያችን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት በመከታተልና መረጃ በመለዋወጥ
ችግሮች ከተከሰቱ ባፋጣኝ መፍትሄ መፈለግ
8. በማናቸውም ማህበራዊ እንቅስቃሴቆች ውስጥ ወጣቶች እያድደረጉት ያሉትን ሚና
ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ሁለንተናዊ እገዛ ማድረግ
9. ገበሬዎቻችን እንደማዳበርያ ካሉ የአካባቢውን የመሬት ለምነት ከግምት ያላስገቡና
የጭቆናና የብዝበዛ መሳሪያ ከሆኑ ተፅኖዎች ነፃ ሆነው የልማት ሥራዎቻቸውን
እንዲሠሩ ማስቻል
10. የመንግሥት ሠራተኞች ያለማንምና ያለምንም ተፅዕኖ በሙያቸው ሕዝባዊ
አገልግሎታቸውን የሚወጡበትን ሥርዓት ማበጀት።
ምንም ዓይነት ኃይል ወይም አጥር ሳያግደንና ሳይገድበን እራሳችን የራሳችን የማህበራዊ፣
ምጣኔ ሃብታዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት የምያስችለን አቅምና
አደረጃጀት የመገንባት ሂደታችንን አፋፍመን መቀጠል ታሪካዊ ግዴታችን ብቻ ሳይሆን
የህልውናችን ማስጠበቅያ ቁልፍ ተግባር ጭምር ነው!!!
ፀሐፊው፦ ኖኔ ኖች
የካቲት 13 2009 ዓ.ም
noonenooch@outlook.com

http://kaffamedia.com

Posted by, Kumilachew Ambo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: