እናስተዉል!!
የካፋ አከባቢ ሕብረተሰብ በአንድ ወቅት ገናና እና ጠንካራ አስተዳደራዊ መዋቅር የነበረ ሆኖ፤ በየአካባቢዉ እስከ 19ኛው ክ/ዘመን የዘለቀ የራሱ የሆነ የዘውድ አገዛዝና ጠንካራ አስተዳደር እንደነበረዉ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያሰረዳል።  በኢትዮዽያ ማዕከላዊ መንግስት ሥር መዉደቅ የጀመረዉ በሚኒልክ ዘመነ መንግሥት ነዉ:: የሚኒልክ ሠራዊት ይህንን አከባቢ ለመቆጣጠር  እንዲሁ ከሸዋ ጀምሮ ያገኘዉን እየገደለ ማጂ አልደረሰም። አካባቢዉ በአብዛኛዉ በደን የተሸፈነና እጅግ የታዎቁ ጦረኞች  ሀገር  ስለነበር  የተላያዬ የአከባቢዉን ኃይል የማነጣጠል ዜዴዎችን ተጠቅመዋል ። ከነሱ አንዱና መሠረታዊዉ ግን በታሪክ እምብዛም ያልተነገረዉን እዚህ ላይ ላንሳ።
የካፋ አካባቢ ህዝቦች የረጅም ጊዜ የመደጋገፍ ባህል ያለዉ ህዝብ ነዉ። በግጭቶችና ጦርነቶች ጊዜ
ቤንች ያለዉ ንጉስ ለካፋ፣ ሌላዉም እንዲሁ የሰዉ ሀይል ድጋፍ በመስጠት በጋራ አካባቢአቸዉን
ጠብቀዉ አቆይተዋል።  በተለይ የኦሮሞ ተስፋፊዎች በካፋ ንጉስ ላይ ያደርስ የነበረዉን ተፀዕኖ በጋራ ተባብሮ ይመክቱ ነበር። ለዚህ ትብብራቸዉ መሠረቱ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓታቸዉ ነበር።
ከመስከረም ወር እስከ የካቲት ወር ባለዉ ጊዜ ከአንድ እስከ አምስት አመት ልዩነት የሚደረግ የድግስና የምስጋና  ሥርዓት ነበር።የማንኛዉም ንጉሥ ኃያልነት መለኪያዉ አጋሮቹና በቂ ሀብት መያዝ ስለነበር የካፋ ንጉስም ኃያልነቱን ለወዳጅ ለጠላት ያሳይ የነበረዉ ይህ ከአንድ ወር በላይ የሚቆየዉን የምስጋና ድግስ በማዘጋጀት ነበር።
በድግሱ ላይ በዙሪያ ካሉ የየአካባቢዉ ንጉሥ ፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ኃይማኖታዊ ተልዕኮ ያላቸዉ ግለሰቦች ከጊሚራ፣ ከሻካ፣ ከዳዉሮ ፣ ከጂማ እና ከለሎችም አካባቢዎች ይገኙ እንደነበር የአፈ ታሪክ መረጃዎች ያሳያል። የድግሱ ተጋባዞች ወርቅን ፣ የዝሆን ጥርስን፣ የቀንድ ከብትን፣ማርንና ለሎችን በስጦታ መልክ ያበረክቱ ነበር።ሴት ልጅና ወጣት ወንድንም  አንዱ ንጉስ ለሌላዉ ያበረክት እንደነበር እስከዛሬም አሻራዉ በጉልህ ይገኛል።
ይህ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነሥርዓት ፍፁም ሠላማዊ፤ የተቀያየሙ ድግሱን ለመቅመስ ፍጹም ልባዊ ይቅር የሚባባሉበት ፤ የበደለዉ ካለ ተበዳዩን ከልቡ የሚክስበት ፤ዉሸት መምስከር ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ለመዓት ይዳሪጋል ተብሎ የሚታምንበት፤ሁሉም ያለበትን ኃጢአት ተናዘዉ በንጹህ ልብ ብቻ ምስጋና በማቅረብ ከአምላኩ በረከት የሚለምንበት ፍጹም ሠላማዊ ሥነሥርዓት ነበር።
ይህንን ፍጹም ሠላማዊ ሥነሥርዓትን ነበር ሚኒልክ  ለራሱ ዓላማ ሲል ለበደል የተጠቀመዉ።የሚኒልክ መልዕክተኞች ወደ ካፋ ንጉስ (ጋኪ ሻረቾ) ጋ  በተዳጋጋሚ ይላኩ ነበር።አካባቢዉ እጅግ ደናማ በመሆኑ ጦር ብቻ መላክ ከባድ እንደሚሆን የሚኒልክ መልዕክተኞች በጉዞኣቸዉ ተረድቶ ስለነበሩ የካፋ ንጉሥ የሚያዘጋጀዉን የምስጋና ድግስ ቀን ለመጠቀም ወሰኑ። በዚህ መሠረት ንጉስ ጋኪ ሻረቾም የተለመደዉን ድግስ በማዘጋጀት በጊሚራና በሻካ ያሉትን ንገሶች ፣ተዋቂ ሰዎችና ባላበቶች እንዲገኙ አደረገ።ተዳሚዎቹ ተጠቃሎ ሲገቡ የሚኒልክ ጦር አከባቢዉን ተቆጣጠረ። ያገኙትን በሙሉ ረሸኑ። ንጉስ ጋኪ ሻረቾም ሌላ ቤት ሰለነበር አምልጦ ጫካ ገባ።ከጥቂት ጊዜ በኃላ እሱም ተይዞ አንኮበር እስር ቤት ተወሰደ። በእስር  ላይ ሆኖ ማቅቆ እንዲሞት ተደረገ።
የሚኒልክ ሠራዊት በእንዲህ ሁኔታ ህዝቡን መሪ አልባ በማድረግ ከአንድራቻ እስከ ማጂ ያለዉን
ተቆጣጠረ። ቀጣይ ትዉልድ ማንነቱን እንዳይጠይቅ የማንነቱ መሠረት የሆኑት ኃይማኖታዊና
አስተዳደራዊ ተቋማቶች እንዲወድሙ፣እንዲጠፉ ተደረጉ። ህዝቡ በራሱ መሬት ሌላ ንጉስ ከሸዋ ተሹሞ መሬቱን ተነጥቆ በራሱ መሬት ላይ ጭሰኛ ተባለ። በጉልበቱ ደክሞ አርሶ ስሶና ምልጃ ለዘመናት ከፈለ።
ለተሿሚዉ እንዳሸዉ የሚያዘዉ፣ የሚጠቀመዉ ንብረት ሆነ። መሬቱ በተፈለገ ጊዜም ከቄየዉ ያለአንዳች ጥቅም ለዘመናት ሲፈናቀል ኖረ። መሬቱ ሲወሰድ አዲስ አበባ  መጥተዉ ንጉሱ ፊት ወድቆ የራሱን መሬት ለመለመን ስንቱ አዲስ አበባ ገብቶ መመለሻ በማጣት እዛዉ ቀርቷል። ይሄዉ በደልና ግፍ ፣ ሕዝቡን በራሱ መሬት ላይ ባይተዋር ማድሬግ ለረጅም ጊዜ ዘልቆ የ1966ቱ አብዮት ዋና ምክንያት ሆነዋል።
ጭቁኑም አርሶ አደር የራሱን መሬት ከረጅም ከተማሪዎችና ከተረማጆች ትግል ቦኃላ መስከረም 02፣ 1967 ዓም መሬትን ለአራሹ (Land to the Tiller) ባደረገዉ አዋጅ የመሬት ባለበትነትን አረጋግጠዋል። ይህ ታዲያ ግልጽ የሆነ ዋና የኢኮኖሚ አዉታር የሆነዉን መሬትን ከመላዉ ህዝብ የነጠቀ ሥርዓት ነበር።
በመሆኑም ተማሪዉ፣ተራማጁ፣ ወታደሩ፣ወዘተ የመረረ ትግል በማድረጋቸዉ የአምላክ ሥርዓት ተደርጎ ከኢትዮዽያ ዉጭ ሳይቀር ታምኖ የነበረዉ  የኢትዮዽያ  ንጉሰነገስታዊ ሥርዓት በወጣቱ ደም ዋጋ ዳግም ላይመለስ ፈርሰዋል።
ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በመደረግ ላይ ያለዉ ደግሞ ሕቡዕ የመሬት ነጠቃ ነዉ። የስዉር ደባ። የሕብረተሰቡን የልማት ፍላጎት መሣሪያ በማድረግ ልማት እያመጣን ነዉ በማለት መሬት ነጠቃ ላይ ናቸዉ። በመሠረቱ ልማት ከሌላ ቦታ በሌላ ሰዉ ሊመጣ አይችልም።ልማት ሊመጣ የሚችለዉ ህዝቡ ራሱ የለማ ሲሆን ብቻ ነዉ። የለማ ህዝብ ማለት በዕዉቀቱና በአመለካከቱ የበለጸገ፣የሚኖሪበትን አከባቢ ምንነት የተረዳና ለራሱ በሚመች ሁኔታ ቀይሮ መጠቀም የሚችል፣ ነፃ አመለካከትና ፍትሓዊነትን ያዳበረ፣ ሰዉ ሠራሽና ተፈጥሮኣዊ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ብሎም ለመቆጣጠር በቂ ማህበራዊ ትስስርና ተቋማት ያለዉ ነወ።ይህ ዕዉን ሊሆን ከሆነ ደግሞ ህዝቡን ማፋናቀልና የባሰ ደሃ ማድረግ  ሳይሆን የድህነት መሠረት የሆኑትን ዕዉቀት ማጣትን፣ኢፍትሓዊነትንና፣ኢደሞክራሲያዊነትን ማስወገድ ከሁሉም በፍት መቅደም ነበረባቸዉ። እነኝህ እየሆኑ አይደሉም።የኑሮ ዉድነት፣ ተስፋ ዕጦት፣ኢፍትሓዊነትና ምሬት ይባስ ብሎ እጅግ ጨምሮኣል።
የስዉር የመሬት ነጠቃዉ ግን ተጠናክሮ ቀጥለዋል። በካፋ፣ በሻካና በቤንች-ማጂ ያሉት እጅግ ሰፋፊ የደን መሬቶች በቋሚ ሰብሎች በጣም ጥቂት የሕወሃት ካደሬዎች በእንቬስተርነት ስም ተይዘዋል።ጥቂቶችን ለማንሳት ያክል ግሪን ኮፊ፣ በበቃ ቡና ልማት፣ዉሽዉሽ ሻይ፣ገማድሮ ሻይ ልማት ወዘተ በቂ ማሳያ ናቸዉ። እነኝህ እርሻዎች ለባለቤቱ የገንዘብ ምንጭ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ሊኖራኣቸዉ አይችልም።
ምክንያቱም በህብረተሰቡ ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጨባጭና በጎ ተፅዕኖ የላቸዉም። ሊኖራቸዉም አይችልም።ለዚህ ሳይንሳዊ መረጃ መጥቀስ አያስፈልግም። እነኝህ እርሻዎች አከባቢ ያሉትን ሕብረተሰብ ኑሮ ብቻ ማስተዋል በቂ ነዉ።የመሬቱ ባለቤት የነበረዉ ህዝብ አሁን በእርሻዉ ላይ የየዕለት ምግብ እንኳን መሸፈን በማይችል ገንዘብ ተቀጣሪ ጭሰኞች ናቸዉ። ያዉም ዕድለኞች ከሆኑ። በኑሮኣቸዉ ላይ ክፋት እንጂ በጎ ለዉጥ አልተከሰተም። የሚያርሱበትን መሬት ፣ ቀፎ የሚሰቅሉበትን ዛፍ፣ሚጥሚጣና ኮሬሪማ የሚለቅሙበት ደን፣ ለቤት ግንባታና ለማገዶ  የሚያፈልጋቸዉን ከደናቸዉ ያግኙ የነበረዉን አጡ እንጂ በኑሮኣቸዉ ላይ አንዳችም በጎ ለዉጥ አልተከሰተላቸዉም። እነኝህ እርሻዎች በተፈጥሮኣቸዉ ሰፊ መሬትን የሚሸፍኑ ኢኮኖሚያዊ የልማት አዉታሮች ናቸዉ።ለባለቤቶቻቸዉ ኢኮኖሚያዉ ፋይዳቸዉ የጎላ ነዉ።
ለአከባቢዉ ሕብረተሰብ ግን መሬትን በማሳነስ የበለጠ ከመጉዳት ዉጭ ሊያለማቸዉ፣ ሊያበለፅጋቸዉ የሚያስችል ተፈጥሮኣዊ ባህሪም የላቸዉም። የበበቃ ቡና ከሃምሣ አመት በላይ በቤንችና በሸኮ መሃል ቆየ። መሬቱ ላይ የነበሩት ሸኮዎች፣ ቤንቾችና ለሎችም ለስደት ተዳረጉ እንጂ በዙሪያዉ የበለፀገ ሕብረተሰብ አልተፈጠረም።ስለዚህ በልማት ስም ለም መሬት ከሕብረተሰቡ በአሳዛኝ ሁኔታ እየተነጠቀ እንደሆነ በተለይ የሕዝቡ መሪዎች ነን የምንል  ሰዎች ልብ እንበል!፣ እናስተዉል።የነገ ታሪክ ተወቃሾች እንዳንሆን ዛሬ ኃላፊነታችንን በማስተወል እንወጣ።
እጅግ የተዛባ የሀብት ሥርጭት በገነነበት፣ፍትሕና ደሞክራሲ በሌለበትና የኢኮኖሚ ሽግግር ተስፋ
በማይታይበት እንደ ኢትዮዽያ ባሉ ሀገሮች መሬትን የመሰለዉን  ቁልፍ አዉታር ከብዙሃኑ ነጥቆ
ለጥቂቶች መስጠት ተዛብቶ ያለዉን የበለጠ እንዲዛባ ማድረግ ነወ። ስለዚህ አሁን በልማት ስም እየተካሄደ ያለዉ ስዉር የመሬት ነጠቃዉ በዚሁ ፍጥነት  ከቀጠለ ከበፊቱም እጅግ የባሰ፣ በጣም ጥቂቶቹ ባለመሬት፣ ሰፊዉ ሕዝብ ጭሰኛ የሆነበት አፓርታዳዊ ሥርዓት እንደሚመጣ አልጠራጠሪም። አሁንም ላስተዋለ ሰዉ ጋሃድ ስለሆነ እስቲ የሆነዉንና እየሆነ ያለዉን ሐቅ ደግመን ደጋግመን እናስተዉል።
ዳግም በሌላ ማስታወሻ እስከሚንገናኝ ድረስ በማስተወል ያቆየን፣ መልካም ጊዜ ይሁን!!
ከአሳዬ ሚዛን

source http://kaffamedia.com/

Posted by Kumilachew Ambo