Leave a comment

ከመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ውጭ ሕዝባችን ሌላ አይሻም!


ከመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ውጭ ሕዝባችን ሌላ አይሻም!
ከአናሞ

ሰሞኑን በአገራችን የሆነውና እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ እውነታ ሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቅንበት የትግል አካሄድ በመጠንም ይሁን በይዘት ወደ ላቀና ጨርሶ ወደ ኋላ በማይመለስበት ደረጃ መሸጋገሩን ብዙ ማብራሪያ ሳያስፈልገው ራሱን ግልፅና ግልፅ አድርጎ እያሳየን ስለመሆኑ ለመረዳት ብዙ የሚያከራክረን ባለመሆኑ የወያኔ ካድሬዎች ራሳቸው በውል የማያውቁት አብዮታው ዴሞክራስ ውል ዛሬም ተጠምቀናል ብሉም ለውጡን አይመልሰውም ። ሕዝባችን ኮትኩቶና ተንከባክብው ያጠነከረውን የለውጥ ችግኝ መልሰን ሳናባላሸው በረጅሙ የፖለቲካ ታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እምንመሠርተው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበረሰብ ከሚያሸጋግረን ድልድይ የመጨረሻ ጫፍ ላይ እንገኛለን።
ይህን የትግል ምዕራፍ በስኬት የማጠናቀቁ ሥራ ከመቸውም በላይ በአብሮነት፣ በፅእኑ ቁርጠኝነትና አስፈላጊውን መስዋትነትም ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ በመገኘት ላይ የሚወሰን መሆኑን ከልብ አመኖና ተቀብሎ መራመድን የግድ ይላል። ያለዚያ ግን የድል ዋዜማ አምባ ላይ የወጣውን ህዝባዊ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ አምባገነኑ ገዥ ቡድን የለመደውን የጭካኔ በትሩንና የማዘናጊያ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ተውኔቱን እያቀላቀለ በመጠቀም ከአምባው ላይ በማውረድ በመሬት ላይ እንደሚጎትተው ግልፅ መሆን አለበት ። ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የመጣንበት ተሞክሮ ይህ ሊሆን የሚችል ስለመሆኑ መሪር ትምህርት ሆኖን በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ልቀን ካልተገኘን የሩብ ምዕተ ዓመቱ መከራና ውርደት ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት የማይራዘምበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም።

ህወሃቶች/ኢህአዴጎች የአገርና የወገን መከራና ውርደት አብቅቶ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት፣ የጋራ ብልፅግና እና ዘላቂ ሰላም በሰፈነባት አገር እንኑር ብለው የዜግነታቸውን ድርሻ ለመወጣት ከመንቀሳቀስ ውጭ ሌላ ጥፋት የሌለባቸውን ዜጎች በህዝብ የተቃውሞ ማእበል አስገዳጅነት ከየጠባብ እስር ቤቱ ከለቀቁ ገና ቀናት ሳይቆጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (መንግሥታዊ የሽብር አዋጅ) በማወጅ የያንዳዱን ዜጋ ቤት እስር ቤት አድርገው የአፈና እና የዘረፋ መንበረ ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት መወራጨት የሚያስከትለው የጥፋት አስከፊነትን መገመት አያስቸግርም ። ይህን የእንተላለቅ የፖለቲካ እብደት በጥሞና ለሚታዘብ ሰው ገዥዎቻችን እየረገጡና እየገደሉ በመግዛት ጭራቃዊ ራስ ወዳድነት ህሊናቸው ጨርሶ ስለታወረ የህዝብን በቃኝ ባይነትን ቆም ብለው ለማየት የሚችሉ ሆነው አልተገኙም ።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ህዝብን የማዘናጊያ (የማታለያ) ፖለቲካዊ ተውኔታቸውን በህወሃት ዋና አዘጋጅነትና ዳይሬክተርነት ሃያ ሰባት አመታት በመተወን ላይ ይገኛሉ ። የትወናው ትረካ ማጠንጠኛውም “ልማት ” የሚል ተረት ተረት ሲሆን የሚጀምረውም የዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ የማይችሉ ሚሊየኖች ባሉባትና ከደሃም ደሃ በሆነች አገር ለወራትና ለሳምንታት በተካሄዱና ገንዘብ ፣ የሰው ኀይል፣ ጊዜና በአጠቃላይ የአገር አንጡራ ሃብት (resource) በባከነባቸው የሴራ ጉባኤዎች/ስብሰባዎች ማሟሟቂያነት ነው ። የተውኔቶቹን ስኬታማነት ሪፖርቶችና መግለጫዎችን በጥሞና ለሚያነብ (ለሚሰማ) እና የሩብ ምዕተ ዓመቱን የፖለቲካ መሪር እውነታ ከምር ለተከታተለ የአገሬ ሰው እነዚህ ገዥዎቻችን የህዝብን የማሰብና የማገናዘብ እቅም(ችሎታ)ምን ያህል ከደመነፍስ እንስሳ ጋር አውርደው እንደገመቱት ለመረዳት የሚቸገር አይመስለኝም ።ለነገሩ በእነሱ ብቻ የመፍረዱ ነገር በራሱ የእኛን ጥንካሬና ስኬታማነት ጨርሶ አያመለክትም ። የዚህ ሴረኛና መሰሪ የገዥዎች የሥልጣን አድን ተውኔት አጀንዳ ሰለባ የሆነውንና በተለይም ተማርኩ የሚለውን የአገሬን ሰው ቁጥር ቤቱ ይቁጠረው ። ገዥዎችን ደንቆሮ እያሉ የድንቁርናቸው ተውኔት ታዳሚ ከመሆን የባሰ ድንቁርና የሚኖር አይመስለኝም ።
ህወሃት እረፍት እየወሰደና የሦስቱን ቀጥተኛ ሎሌዎቹን (ፈጥሮ ያሳደጋቸውን የግንባሩ አባል ድርጅቶች ) የልብ ትርታና ዝንባሌ እየለካ የሴራ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ በኢህአዴግ ስም በዝግ አዳራሽ ሰብስቦ “ከወደቅን ተያያዘን ስለምንወድቅ ሁላችንም ከዚህ የሚታደጉን ስልቶች የሚከተሉት ናቸውና ተመካክረን ለህዝብ የምሥራች እንበለው”በማለት ያቀረባቸውና እየተተገበሩ ያሉ እጅግ መሰሪ ስልቶች : ሀ) ህዝብና ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚጮኸውን ጬኸት ለማስታገስና ሊያስከትል የሚችለውን የሥልጣን ማጣት አደጋ ለማስቀረት የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ ቁጥሩ የማይናቅ እስረኛ መፍታት ለ) የተሃድሶውን ተውኔት ከራሱ ከህወሃት ጀምሮ በእያንዳንዱ ታዛዥ የግንባሩ አባል ድርጅት ውስጥ በመተወንና ቤተ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር) ድረስ በመዝለቅ የተነሳውን የህዝብ የለውጥ ማዕበል ፍጥነቱንና ስፋቱን እንዲቀንስ ለማድረግና ቀስ በቀስም ተውኔቱን አጠናክሮ በመቀጠል ማዕበሉን ማስቆም በሚቻልበት አጀንዳ ላይ መክሮ ተግባራዊ ማድረግ ሐ) ) አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያመጣው ነፃነትና እድገት/ብልፅግና ዓለምን ሳይቀር ያስደመመ ስለመሆኑ እና መልካም አስተዳደርን የበለጠ ለማጠናከር በሚደረግ ሂደት ውስጥ ግን የተመዘገበውን “አንፀባራኪ ድል” ፈተና ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ያጋጠሙ በመሆኑ ዙሪያ ተመካክሮ “ስለጥልቅ ተሃድሶው ግንዛቤየሚጎለውን” ህዝብ ማስተማርና ማጥመቅ መ)ለተፈጠረው ቀውስ ( እነሱ ቀውስ አይሉትም ) ኅላፊነትን መውሰድና ስለመበስበስም ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ አድናቆትን ማግኘት ሐ) የመበስበሱ ጉዳይ “በጥልቅ ተሃድሶ”እንደሚቀረፍ ለህዝቦች ፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች ማብሰር (በነገራችን ላይ ይኸ የመበስበስና የመታደስ መዝሙር አሁን በህይወት የሌለው ታላቁ መሪያቸው አቶ መለስ ዜናዊ መንበረ ሥልጣኑን የሚያሰጋ ነገር በተሰማው ቁጥር ይዘመረው የነበረ መዝሙር ነው ። ይህም ለጋሲ ሆኖባቸው ነው መሰል አሁንም መዝሙረ መበስበስና መታደስ አድርገው ይዘምሩታል) ሠ) በተፈጠረው ህዝባዊ አመፅ ( እነሱ ሁከት ይሉታል) በንቃት የተሳተፉትን (ልብ በሉ የገደሉትንና በጅምላ ሰቆቃ የፈፀሙትን ጨካኝ ኀይሎቻቸውን ጨርሶ አይጠቅሱም ) “ለህግ
አቅርቦ” አይቀጡ ቅጣት ማስቀጣት (መቅጣት) እና ረ) አፈናውን አጠናክሮ መቀጠል (እነሆ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ / መንግሥታዊ የሽብር አዋጁ እውን ሆኗል ። )
ወደ ግራም እንውሰደው ወደ ቀኝ ፣ ወደ ላይም እናዉጣው ወደ ታች እናውርደው ፣ ይዋጥልንም ወይም ያስመልሰን በመሬት ላይ ያለውና ተዘርግቶ ፀሐይ የሚሞቀው የገዥዎቻችን አደገኛ የቅዠት ፖለቲካዊ ድርሰታቸው (እየበሰበሱ ታደስን የሚሉት ትራጀዲያቸው) ይኸው ነው ። የኦህዴድም ይሁን የብአዴን እና የደህዴን ባለሥልጣናትና ካድሬዎች የፖለቲካ ሰብእናቸው ፈጣሪ ከሆነውና በግንባር (ኢህአዴግ) ስም ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ በደም የቆሸሸውን የፖለቲካ አጀንዳውን አስፈፃሚ ካደረጋቸው የትግራይ ነፃ አውጭ ፈልቀቀው ለመውጣት ከአሁኑ የተሻለ እድል ወይም አጋጣሚ የላቸምም ። ወኔው ከድቷቸው ወይም በአድር ባይነት ክፉ አባዜ ተጠርንፈው የአፈና መሳሪያንና የማታለያ (ማዘናጊያ) ፖለቲካዊ ተውኔትን እያቀላቀለ ከሚነጉደው መንኮራኩር ወርደው ወደ ህዝብ የነፃነትና ፍትህ መርከብ እስከ አልተቀላቀሉ ድረስ አልፎ አልፎ በየአጋጣሚው የሚያሰሙት ህዝባዊ የሚመስል ዲስኩራቸው (populist rhetoric) የትም የሚያደርስ አይደለም ። ይባስ ተብሎ ደግሞ በዚህ ሰሞን የጠቅላይ ሚኒስተርነቱ ወንበር “ለድርጅታችንና ለእኛ ሰዎች ቢሰጥ ተሃድሶውን ለማሳካት ተአምር እንሠራበታለን” የሚል የተውኔቱን የሴራ ጡዘት ከፍ የሚያደርግ ሁኔታ እየታዘበን ነው። በእጅጉ የሚሳስበው ግን የዚህ “ድንቅ ፖለቲካዊ ተውኔት” ሰለባዎች ለመሆን የሚከጅለን ብዙ የመሆናችን ጉዳይ ነው ። ከልብም ልብ ይስጠን!
• ይህ የሰሞኑ የትግል እመርታ በፍፁም መባከን የሌለበት ወርቃማ የድል ዋዜማ መሆኑን ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚከተሉት መልዕከት እናስተላለፋለን ።

• ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ እና በተለይ ደግሞ ከ1997ቱ የህዝብ ድምፅ ቅሚያ (ንጥቂያ) በኋላ ውድ ልጆቹን እያስገደለና ወደ ማሰቃያ ማዕከላትና ወህኒ ቤቶች እየሸኘ አርፎ መቀመጥ የእግር እሳት የሆነበት የአገራችን ህዝብ ካለፉት ሁለት/ሶስት ዓመታት ወዲህ ፍርሃት ሲበዛ በቁም መሞት መሆኑን ከምር ተረድቶ መከራና ውርደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቁ ዘንድ በቃ ብሎ መነሳቱን በማያሻማ መንገድ ግልፅ አድርጓል ። ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ወጣቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ የአደባባይ ተቃውሞና ለብዙ ቀናት ማነኛውንም እንቅስቃሴ የማቆም አድማ የመቱት ፣ እና በተቃውሞው የአርበኝነት ጎራ የቆሙ ወገኖች ፋና ወጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ከፊታችን ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቁ ፈታኝ ጉዳዮች የመኖራቸው እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የጋራ እጣ ፈንታን በጋራ ለመወሰን በቁርጠኝነት መንፈስ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ትግል እያንዳንችን ነፃነትና ፍትህ ወዳድ ዜጎች እና ከምር ለሕዝባችንና ለወገን ቁመናል የሚሉ ባለድርሻ አካላትን (የፖለቲካና የሲቪክ
ድርጅቶችን) ከምር የመደማመጥንና በአብሮነት በአብሮነት እንድንቆም እንጠይቃለን። ይህን ሁኔታ ወደ እሚጨበጥ ውጤት ለማሸጋገር የሚታየው ተነሳሽነትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጥልቀትና ስፋት እያገኘ በሄደ ቁጥር የመከራና የውርደት ሰለባ የሆንበት የፖለቲካ ሥርዓት የሚያከትምበትን ጊዜ ከአሁን በኋላ ወራትንና አመታትን እየቆጠርን የምንታገሰው አለመሆኑም ይበልጥ ግልፅ እንዲሆን እንፈልጋለን። ። • የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ በባለጌዎችና በግፈኞች እጅ ወድቀው የሰቆቃ አይነት መፈተኛ ከሆኑት ልጆቹ መካከል የተወሰኑትንና ለህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እውን መሆን ግንባር ቀደም ሚና ያላቸውን ልጆችህን ደግፍ፡፡ ይኸው ነው የአሁኑ የደምኢሕሕ የምርና የማይታጠፍ መልክት ። የሚሰማ ሰምቶ ራሱንም ያድናል ፥ የአገርንና የወገንን የመስዋእትነት ዋጋም ከመጠን እንዳያልፍ እና የመከራውና የውርደቱ ጊዜም እንዳይረዝም ያግዛል ። የማይሰማ ካለ ደግሞ ድንቁርናውና እኩይ ባህሪው የሚያስከትልበትን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት ። ያለንበት ገሃዱ ሁኔታ የሚያሳየንና የሚነግረን ይህንኑ የማያወላዳ ሃቅ ብቻ ነው ። ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው።በተለይ ግን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የአገርን ክብር ክፉኛ ያረከሱት እና የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ህይወት ምስቅቅሉን ያወጡት የገዥው ቡድን ባለጌ ባለስልጣናትና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው አሁን ያሉበት ሁኔታ እስከአሁን የተጠቀሙበትን ታደስን እያሉ የባሰ የመበስበስ ፖለቲካዊ ጨዋታ ጨርሶ የሚያስተናግድ ወይም የሚሸከም አለመሆኑን ተቀብለው ምርጫቸውን ለእነሱም ለአገርም በሚጠቅም አኳኋን ማስኬድ ግድ ይላቸዋል ።
• በአጠቃላይ አምባገነን ገዥዎች በተለይ ደግሞ የእኛዎቹ ከሚጠቀሙባቸው አይነተኛ ረግጦ የመግዛት ዘዴዎች መካከል የኢንፎርሜሽን ነፃነት የሌለው ህዝብ ያለበትን የፖለቲካ ምንነትንና ለማንነት የመረዳት ዉሱንነትን ፣ የገንዘብና የማተሪያል እጥረትን እና የመሰባሰብና የመደራጀት አስቸጋሪነትን በመጠቀም እድሉን ከማማረር አልፎ አልገዛም እንዳይል ማረጋገጥ ነው። ህዝብ ከእንዲህ አይነቱ ችግር ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል የሚመሩና የሚያስተባብሩ ዜጎችን ወይ ዝም ማሰኘት የለዚያ በየምክንያቱ ማዋከብ ፣ ማሰቃየት ፣ በህግ ስም በሃሰት ወንጅሎ ወህኒ ማጎርና በጎዳና ወይም በአደባባ ላይ ተኩሶ መግደል ነው የአምባገነኖች በሥልጣን ላይ የመቆያ ስልታቸው። በአጭር አገላለፅ ” የህዝባዊ ንቅናቄ አስተባባሪ ወይም ለተሻለ ሥርዓት የሚሠራ ድርጅት መሪ ነኝ የሚለውን ሁሉ ከተቻለ ጨርሶ እንዳይኖር ካልሆነ ደግሞ በሚገባ አንዲኮላሽ ከተደረገ ህዝብ ችግሩንና መከራውን ወደ ውስጥ እያስታመመ ከመኖር አያልፍም” የሚል መቀበል ቀርቶ ማሰብ የሚከብድ እርኩስ (እኩይ) የፖለቲካ መሰሪነት ነው የዛሬዎቹን ዘረኛ አምባገነን ገዥዎች የተጠናወታቸው ።
እናም ለዚህ ነው ከአሁን በኋላ ከዘመናት የመከራና የውርደት መውጫ ብቸኛው መንገድ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እና ግንባታ የመሆኑ ጉዳይ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ግልፀና የማያሻማ
ሆኗል ማለት እውነት የሚሆነው። ይህን የሚጠራጠርና የአርበኝነቱን የመጨረሻ የፍልሚያ ጎራ ለመቀላቀል የሚቸገር አይጠፋምና ቆም ብሎና ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ራሱን እንዲጠይቅ ማስገንዘቡ አይከፋም። ።
ለሩብ ምዕተ ዓመት አብዝተን እንደመናገራችንና እንደመነጋገራችን ከውድቀታችን እየተማርን ይበልጥ ጠንክረን በመነሳት የመከራና የውርደትን አድሜ ማሳጠር የተሳነን በሚያስማሙን ጉዳዮቻችን እየተስማማን፣ የምንለያይባቸውን ደግሞ በሂደት እየፈታን ፣ ማህበረሰብ የእያንዳችን ባህሪና ፍላጎት ስብስብ እንደመሆኑ ከዚህ ተፈጥሯዊና ማህበረሰባዊ እውነታ የሚመነጩትንና ማስወገድ የማንቻለውን ጉዳዮች ደግሞ እንደአመጣጣቸው ለማስተናገድ በሚያስችለን የጋራ ዣንጥላ (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ሥር መሰባሰብ ስለአልቻልን ነው። ወደ ድል የተጠጋው የነፃነትና የፍትህ ትግል ግቡን ይመታ ዘንድ ተመሳሳይ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን የባለጌና ጨቃኝ ገዥ ቡድን ሰለባዎች እንዳንሆን ከመሪሩ ተሞክሯችን ( the bitter expereince) መማር የግድ ይለናል ። ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የጎጠኛና ዘረኛ አምባገነን ገዥዎች መፈንጫ ሆነን የዘለቅነው ማነኛውም ለነፃነትና ለፍትህ የሚደረግ ትግል የሚያጋጥመው መውደቅና መነሳት ስለአጋጠመን ሳይሆን ከውድቀት ባለመማራችንና ከመጠን በላይ ደጋግመን በመውደቃችን ነውና የአሁኑ በቃኝ ባይነት ለእውነተኛ ትንሳኤ (ተመልሶ ያለመሞት) መሆን አለበት ። የዚህ ዋስትናው (ብቸኛውና አስተማማኝ መንገድ) እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ እንጅ አምባገነኖች የአገዛዛቸውን እድሜ ለማራዘም የሚሸርቡት የሴራ ተውኔት ከቶ ሊሆን አይችልም

Leave a comment