Leave a comment

ሕዝባችን እንደተዋረደና: አንገቱን እንደ ደፋ አይቀርም!!!


ያኔ የነበረዉ ጀግንነትና ወኔ የት ገባ?

ካፋ;- እነ ግራዝማች ጳዉሎስንና የትግል አጋሮቻቸዉን እነ ደቀራሻ ማሞንና ባራምባራስ ካርሎን ማለራሾ ወ/ጊዮርግስን የመሳሰሉትን የፈጠረ ምድር፣ ደርግን በህይወታቸዉ ሙሉ የተዋጉትን ዎተራሻ ክፍሌን ያበቀለ ምድር፣ ከሰሜን የመጣ በሃገሬ ባላባት መሆን አይችልም ብለዉ አፄ ሃይለ ስላሴን ሞግተዉ አሸንፈዉ ባላባትነትን በሃገሬዉ እጅ ያቆዩትን እንደ ደቀራሻ ዳምጤን ያበቀለ ምድር፣ ሌሎችንም እነ ደቀራሻ አደሎን፣ እነ ዱበራሻ (ደቀራሻ) አሚን እነ ገብረፃድቅ ሻዎን የመሳሰሉትን ጎበዝ የወለደ ሃገር ምነዉ ዛሬ አንድም መሪ አልወጣ አለዉ? አንዴት ዛሬ ደርሶ በዎሮበላ ይገዛል?

ሸካ:- ህገወጥ ሰፈራን በመቃወም ሃያሉን የደርግ ጦር ያንቀጠቀጠዉን ጀግናዉን የሸካን ሕዝብ የፈጠረ ምድር ዛሬ ደርሶ ምን ነካዉ? አንዴት ዛሬ ደርሶ በዎሮበላ ይገዛል?

ቤንች:- ደርግን እስከመጨረሻዉ የተዋጋዉን እነ ሓብቴ አድሴን የወለደዉ ቤንች፣ እነ ባርጅናንስን፣ ዳኬራሻን፣ ኮምቲ ካስንና፣ ለሚኒሊክ ናና እደፋሃለሁ የሚል መልእክት ጥቁር በሬና ሚጥሚጣ የላከዉን እንደ ማራ ፋይኒኮምስን ያበቀለ ቤንች አንዴት ዛሬ ደርሶ በዎሮበላ ይገዛል?

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ለሃገራቸዉና ለሕዝባቸዉ ክብር ሞተዋል። የዛሬዎቹ መሪ ነን ባዮች የገዛ ሕዝባቸዉን፣ ቤተሰባቸዉን አሳልፈዉ ለዉሸትና ለገንዘብ ይሸጣሉ። ሕሊናቸዉን ለባሪነት ሽጠዉ የገዛ ሃገራቸዉንና ሕዝባቸዉን አዋርደዋል፣ የማያዉቀዉን ባሪነት እንድሸከም አድርገዉታል። እንዴት ሰዉ የገዛ እናቱን አባቱን ወንድሙንና እህቱን ለሆዱ ሲል ይሸጣል? እንዴትስ አዕምሯቸዉ ዉሸትን ተቀበሎ በሰላም ተኝተዉ ያድራሉ? ምን አይነት ህሊና ቢኖራቸዉ ነዉ?

እነዚህ መሪ ተብየዎች ሕዝቡን አዋረዱ፣ አስደፈሩ። ጭራሽ ሕዝቡ በሃገሪቱ ዉስጥ እንደሌለ ተቆጠረ፣ ከሃገሪቱ ካርታም ተሰረዘ። መሬቱ ሃብቱ ሁሉ አይኑ እያየ ተዘረፈ፣ አርቃኑን ቀረ። የኛ ሕዝብ ከመጠን በላይ ደግ ነዉ። ደግነቱም እንደ ሞኝ አስቆጠረዉ። ሃገሩ: መሬቱ እንደ ባለቤት አልባ ተቆጠረ። የማንም መጫወቻ ሆነ። ማንም እየመጣ ያለ ማንም ጠያቅነት መሬቱንና ሃብቱን ይነጥቀዋል። ጫካዉ ያለ ማንም ከልካይ ተመነጠረ፣ መሬቱ ተቸበችበ፣ ለምና ምርታማ መሬቱ በሰፈራ ስም ተዘረፈ። ሌላዉ ለልጅ ልጆቹ የሚያወርሰዉን ንግድና ፎቅ እየገነባ ነዉ። የኛ ሕዝብ ያለ ጫካዉና መሬቱ በስተቀር ሌላ ምንም የለዉም። ታድያ ምኑን ነዉ ለልጅ ልጁ የሚያወርሰዉ? ሕዝባችን ያለዉን ሁሉ ተነጠቅ፣ እርቃኑን ቀረ። አሁን እንዴት አድርገን ነው ሕባችንን ከዚህ መዐት የምናወጣዉ? የሚገርመዉ ነገር ሕዝቡ ተቸግሮ የመጣዉን ሁሉ እንደ እናቱ ልጅ ነዉ የሚቀበለዉ። ውለታዉ ግን ትንሽ ቆይቶ “ይህ ምን አባቱ” ነዉ። የተቀበለዉ እንግዳ በ”ምን አባቱ” ብቻ አያበቃም። በአንድ አንድ ቦታ እንደታየዉ አልፎለት ክላሽ ገዝቶ የሃግሬዉ ሰዉ ከብቱን በገዛ ሜዳዉ ሳር እንዳያስግጥ እንኳን ይከለክለዋል። የኸን ያህል ነው ሕዝባችን የተዋረደዉና አንገቱን የደፋዉ። የሄ ሁሉ የሆነዉ በገዛ ልጆቹ ጥፋት ነዉ። የገዛ ወንድሙን ሳያከብር፣ ሳይጠቅም ሌላኛዉን በጭንቅላቱ ይሸከማል:: ለሌላኛዉ ታማኝ ተላላኪ ይሆናል። ግን እስከ መች ይህ ግፍ ይቀጥላል? ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ማንም መጥቶ ሕዝባችንን የሚታደግ የለም። እኛዉ ራሳችን መላ ልንል ይገባል። መፍትሄዉም በእጃችን ነዉ። እንደ ቀደምት አባቶቻችን ዎኔንና ብልህነትን መታጠቅ ይኖርብናል።

አንድ ማስተዋል የሚገባን ጉዳይ ቢኖር የኛ ሕዝብ ለኢትዮጵያውነቱ ሟች ነዉ። ነገር ግን ለገዢዎች የኛ አካባቢ ሕዝብ ኢትዮጵያው የሚሆነዉ ሃገር ሲወረር ወታደር ሆኖ እንዲዋጋ ብቻ ነው። አከባቢውም ኢትዮጵያ የሚሆነው ሃብቱን ለመዝረፍ ሲፈልጉ ብቻ ነዉ። ከዚያ በተቀረ ሕዝቡም ሃገሩም የለም፣ ከቁጥርም አይገባም። አሁን ይባስ ብሎ አማራና ኦሮሞ ብቻ በሃገሪቱ እንዳሉ፣ ሌሎቹ እንድሌሉና ቢኖሩም ለምንም አይፈይዱም እይተባለ ነጋሪት ሲጎሰም የጆሯችን ታምቡር እስኪቀደድ እየሰማን ነው። ለዚህ ግፍ ሁሉ ምስክር መጥራት አያስፈልግም። ምስክር ያ ሁሉ የዚያ አከባቢ ሕዝብ ሃብት ሌላኛውን የኢትዮጵያን ክፍል ሲገነባ ያ አከባቢ የረባ ት/ቤት የለውም። መንገድ ሆስፕታል መብራት ውሃ የማይታሰብና የማይታለም ነዉ። ሕዝቡ ሆን ተብሎ በተንኮል እንዳያውቅ: እንዳይነቃ ተደርጎ በጨላማ ውስጥ የተወረወረ ዕቃ ነው የሆነው። ለምሳሌ ትንሿ ትግራይ ፋብሪካ በፋብሪካ ስትጥለቀለቅ እንድሁም አንድ የአለም አቀፍና ስድስት የሃገር ውስጥ በረራ አይሮፕላን ማረፊያ ሲኖራት የእኛ አከባቢ እንኳን ፋብሪካ ይቅርና በደርግ ጊዜ የነበረውን የሚዛን አማንን ኤርፖርት፣ የቴፒን ኤርፖርትና የማጂን ኤርፖርት አጥቷል። ዛሬ አንድም ኤርፖርት በአከባቢው የለም። ታዲያ ይሄ ነው ኢትዮጵያውነት? በእውነት እኛ እኩል የአንድ ሃገር ዜጎች ነን? መልሱን ለሁላችሁ ትቸዋለሁ።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: