Leave a comment

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሊቀ መንበርና፣ አፈ-ጉባኤዋ የቀረበ ጥያቄ


ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሊቀ መንበርና፣ አፈ-ጉባኤዋ የቀረበ ጥያቄ

ከሰሞኑ የደቡብ ህ/ዴ/ን ሊቀመንበርና የኢፌዲሪ ህ/ተ/ም/ቤት አፈ-ጉባኤ፣ ወ/ሮ ሙፌሪያት ካሚል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ጎብኝተዉ ተመልሰዋል፡፡ ከቀናት በሁዋላም ጠ/ሚንስትሩ የቦንጋን የጫካ ቡና ጎብኝተዋል፡፡

ስለጠ/ሚንስትር ጉብኝት ብዙ የተባለ ባይኖርም፣ ከደቡብ/ህ/ዴ/ን ሊ/መንበር ጋር የተደረገዉ ስብሰባ ግልፅነትና፣ ቁርጠኝነት የተሞላበት ነበር፡፡ እርሳቸዉም የሚችሉትን ያህል ቢመልሱም፣ ለአብዛኛዉ ጥያቄ መልሱን በይደር አለፈዉ፣ ግን ደግሞ ካጠኑና ካጣሩ በሁዋላ ተመልሰዉ ሌላ መድረክ እንደሚያዘጋጁ በሦስቱም ቦታዎች ቃል ገብተዋል፡፡

በርግጥ ይህንን አካባቢ ኢህአዴግ ራሱ በስማ በለዉና በምስለኔዎች ሪፖርት ብቻ እንደሚያዉቅና በዝርዝር ማጥናትና ማጥራት እንደሚገባዉ በሚያሳብቅ መልኩ፣ የጥሩ ፖለቲከኛ መልስ ሰጥተዋል፡፡
ከልምድ የሚታወቀዉ ከበላይ ከሚመጡ ሃላፊዎች ጋር ለሚደረግ ስብሰባ ተሰብሳቢዎቹን የሚመርጡት ራሳቸዉ በሌብነት የጎለበቱ፣ አካባቢዉን ለዓመታት ሲደፍቁ የነበሩት በሥልጣን ላይ ያሉ ምስለኔ ካድሬዎችና ሰንሰለታቸዉ እንደነበር ስለሚታወቅ አዲስ ነገር ይነሳል ብለን አልጠበቀንም፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ዓይነት ስብሰባ የሚገኙት የተለመዱ ተሰብሳቢዎች አወዳሽ፣ አድናቂ፣ ያለዉ እንዲቀጥል ድጋፍ የሚሰጡ፣ ለቀጣዩም ለበጎ አስተዋፅኦ ቃል የሚገቡ ነበሩ፡፡

ሆኖም በሰሞኑ ስብሰባዎችም የተለመደዉ ቅንብር እንደተደረገ ቢታመንም፣ ከታዳሚዉ የቀረበዉ ብሶትና አቤቱታ፣ የበደል ዝርዝርና፣ ወሳኝ የመፍትሄ ጥቆማ ግን ቁርጠኝነት የታየበት ነበር፡፡ ይህ አንድ ምልክት ነዉ፣ ህዝቡ በቃኝ ማለት ጀምሯል፣ መፍትሄ ካልተሰጠዉ ወደየት እንደሚያመራ በግልፅ መናገር አይቻልም፡፡ ከቦንጋ እስከ ቴፒ፣ ከማጂ እስከ ሚዛንና አስከ ማሻ ከተሳታፊዎቹ፣ ተመሳሳይ ብሶት የቀረበበት ስብስባ ነበር፡፡

ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ

• አካባቢዉ በሁሉም ረገድ በልማት መዘንጋቱ፣
• ህዝቡ በዞኖቹ ባሉ ካድሬዎችና ሃላፊዎች በሚደርስ የአስተዳደር በደል መማረራቸዉ፣
• ከአካባቢዉ የሚወጣዉና ኤክስፖርት የሚደረግ የሃብት መጠን ከፍተኛ ሆኖ ሳለ፣ በአካባቢዉ ላይ መንግሥት በሁሉም ረገድ የሰጠዉ ትኩረት አለመኖር ወይም አለመጣጣም፣
• በሁሉም ቦታዎች “ኢንቨስተር” ተብለዉ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ወስደዉ፣ ደን ጨፍጭፈዉ ግንድና ጣዉላ ነግደዉ ስለከበሩ ሰዎች፣
• መሬቱን ደጋግመዉ በመሸጥና ከተለያዩ ባንኮች መሬቱን አስይዘዉ ብድር ወስደዉ ሃብት አካብተዉ ስለተሰወሩ ሰዎች፣
• በእነዚህ ሰዎች ስም ከቀረጥ ነፃ የገቡ ከፍተኛ ማሽኖች በአካባቢዉ አለመገኘት፣
• የአካባቢዉ ባለሥልጣናት ከነዚህ የዘረፋ ቡድኖች ጋር መመሳጠርና በጥቅም መገዛት፣
• በኢንቨስትመንት ሰበብ የአካባቢዉ የተፈጥሮ ሃብት የጥባቃ ባህል አለመከበርና መቃወስ፣
• በዚህም መሰረት፣ ሃላፊነት በጎደለዉ መንገድ የተፈጥሮ ሃብቱን ስለሚያወድሙት ቡድኖችና ማንነታቸዉን ጭምር በመጥቀስ ህዝቡ ምሬቱን አቅርቧል፡፡
• በዚህም ሂደት፣ ለሚነሳ ጥያቄ የአካባቢዉ ባለሥልጣናት ተፅዕኖና፣ ለመሸፋፈን የሚያደርጉት ተሳትፎና የጥቅም መጋራት፣
• በዞኖቹና በየወረዳዉ ቃል የተገቡ መሰረተ-ልማቶች የዉሃ ሽታ ሆኖ መቅረት፣
• የተሰሩትም ፕሮጀክቶችም የጥራት ጉድለት፣ በሁሉም ላይ ግድየለሽነትና፣ ባለቤትነት አለመኖር፣
• የተጀመሩም ሆነ ያለቁ ፕሮጀክቶች ለአካባቢዉ ህዝብ በማይጠቅም ሁኔታ መተግበር፣ የጥራት ማነስ ወይም የሚያደርሱት ጉዳት መበራከት፣
• ወጣቶች፣ መሬት በማጣትና የመሥሪያ ድጋፍ በማጣት፣ ሥራ አጥ መሆናቸዉን፣
• ከክልሉ መጥተዉ ለሰፈሩ ሰዎች ክልሉ በጀት እየመደበ፣ ከዞኑ ተደራጅተዉ ለሰፈሩት ግን ድጋፍ አለማድረጉ፣
• የማጂ ዞን አሁን ግን አካባቢዉ ወደ ወረዳ በመዉረዱና ትኩረት በማጣቱ በሁሉም ዘርፍ ተዘንግቷል፡፡
• ከሁሉም በጣም የሚያሳምመዉ የማጂ ዞን ተሳታፊዎች ጥያቄ ነበር፡፡ ማጂ የጠረፍ አካባቢ ሆኖ ሳለ፣ ከነገሥታቱ ጀምሮ ድንበሩ ለዘመናት በማዕከላዊ መንግሥት የሚጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የሽፍቶች የወረራ አካባቢ ሆኖ፣ ህዝብ እየተሰቃይና፣ እያለቀ መሆኑ ፡፡
• እስካሁን የሁሉም አካባቢዎቹ ወጣቶች ያልረበሹትን ሲገልፁ፣ የነበረዉ ብሶት አነስተኛ ሆኖ፣ ወይም ባለዉ ሁኔታ ረክተዉ ሳይሆን፣ ምሬታቸዉን ችለዉ፣ ግን ደግሞ የለዉጡን ጅማሮ ላለመረበሽና፣ በተስፋ ብቻ መሆኑን በመግለፅ በጨዋነት ሃሳባቸዉን ገልፀዋል፡፡
• ከሁሉም በላይ ሰብሳቢዋ በደምሳሰዉ ያለፉትና በተጨባጭ ምክንያት በሁሉም ከተሞች በብዙ ተሳታፊዎች የቀረበዉ ጥያቄ የክልል ጥያቄ ነበር፡፡

የክልል ጥያቄ የረጅም ጊዜ የምሬት ምንጭ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ጥያቄ በዋሽንግተን፣ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ዉስን፣ አጭርና፣ ዉይይት ላይ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ አንድነት ተወካይ በተሰጠዉ አጭር ጊዜ የቀረቡት ሁለት ጥያቄዎች የኸዉ የክልል ጥያቄና የደን ዉድመት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እንዲሁም ለእኒሁ የደቡብ ድርጅት ሊ/መንበርና፣ አፈ-ጉባኤም ከዚሁ ድርጅት ደብዳቤ በቅርቡ የተፃፈ ስለነበረ፣ ለጥያቄዉ ሳይዘጋጁ ነበር ማለት አይቻልም፡፡

በመሆኑም፣ እርሳቸዉም በተለመደዉ የፖሊቲከኛ አመላለስ፣ ለዚህ ጥያቄ በተለይ የሰጡት መልስ የተድበሰበሳና፣ ቁርጠኛ አቅጣጫ የሚጠቁም አልነበረም፡፡ ሆኖም ማንም ፖለቲከኛ ይህንን ጥያቄ በቀላሉ እንደማያይ ይታሰባል፡፡ በተለይም ከተሰብሳቢዎቹም ለጥያቄዉ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶች በዝርዝር በመቅረባቸዉ ለዉሳኔ ሌላ ማረጋገጫ አይጠይቅም፡፡ እርሳቸዉም፣ ኢህአዴግ ሁሌም እንደሚለዉ ምናልባትም በራሱ መንገድ ሲከታተል እንደነበረዉና፣ አሁን ደግሞ እየበረታ ለመጣዉ የህዝብ ጥያቄ እንደማስታገሻ ያህል እንደሚናገረዉ፣ መንግሥትና ድርጅቱ ራሱን አስተካክሎ፣ የህዝቡን ጥያቄ እንደሚመልስ፣ ሁሉም ነገር ግን በሽግግር ላይ እንዳለ በመግለፅ ህዙቡ ለሁሉም ጥያቄ መልሱን በትዕግሥት እንዲጠብቅ በመጥቀስ አልፈዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ በሙስናና በህዝብ ላይ በሚደርስ በደል ላይ በተነሳዉ ጉዳይም፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ መፍትሄ እንደሚሰጥ፣ ትዕግሥት፣ ፋታና፣ ጊዜ ጠይቀዋል፡፡ የህዝብ ጉዳይ ዉስብስብ ነዉ፡፡ በስብሰባዉ ጉዳዮቹ መነሳታቸዉና በሂደት መልስ እንደሚሰጥ መገለፁ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ በጥቂት ቀናት ዉስጥ ቴፒ የደረሰዉ ክስተት ግን አሳሳቢና ተስፋ አስቆራጭ ይመስላል፡፡ ከህዝቡ ይልቅ የራሱ የኢህአዴግ ካድሬዎች እጅ እንዳለበት ይወራልና ድርጅቱ ራሱን በፍጥነት መለወጥ ካልቻለ አደጋዉ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ግን ራሳቸዉ ሁሉንም ያበላሹ፣ አካባቢዉን ያቀጨጩ፣ አፈ-ጉባኤዋን አጅበዉ፣ ከክልል፣ ከተለያየ ቦታዎችና ከየዞኑ የመጡትን አምባገነን የመንግሥትና የድርጅት መሪዎች፣ እነርሱ ራሳቸዉ የመለመሉትና፣ ያደራጁትን፣ በየደረጃዉ ሰግስገዉ አካባቢዉን እንደራሳቸዉ ንብረት ሲጋልቡ የነበሩ ግለሰቦችን፣ ኢህአዴግ አስተካክሎ የአካባቢዉን ችግር በመሰረታዊነት መለወጥ ይችላል ተብሎ እንደማይታመን ግልፅ ነዉ፡፡

በአጭሩ ህዝቡ በየቦታዉ የተናገረዉ፣ የለዉጥ አስታሰቡ ደጋፊ መሆኑን፣ ሆኖም ግን ባለዉ የክልልና አካባቢ አመራርና አሰራር አካባቢዉን መለወጥ እንደማይቻል፣ ሁሉንም በማፅዳት፣ በአዲስ ሃይል መሞከር እንደሚገባ ነዉ፡፡ እንዲያዉም በሂደት እነዚህ በየደራጃዉ የተሰገሰጉ ህዝቡን የበደሉ፣ በራሳቸዉም ሆነ “ኢንቨስተር” ከሚሏቸዉ የዘረፋ ቡድኖች ጋር ተደራጅተዉ ከፍተኛ የሃገር ሃብት የዘረፉ ግለሰቦች ጉዳይ ተጣርቶ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንደሚፈልግ ነዉ፡፡ ይህንን አለመስማትና አለመመለስ ደግሞ የህዝቡን አቅም መዘንጋት፣ ታጋሽነትና አስተዋይነቱን መናቅ፣ በመጨረሻም ከደጋፊነት ወደ ተቃራኒነት መግፋት ይሆናል፡፡

የነበረዉ አጋጣሚ፣ አፈ-ጉባኤና ሊቀ መንበሯ ዝርዝር መረጃ ሊወስዱ የሚችሉበት በቂ መድረክ ስላልነበረ ትክክለኛዉን ገፅታ አይተዉታል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም በገቡት ቃል መሰረት፣ የተነሱ ጉዳዮችን ተከታትለዉ የሚወስዱትን እርምጃ እስክናይ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
ስብሰባዉን የዘገበዉ የደቡብ ቴሌቪዥን ፕሮግራምም፣ አልፎ አልፎ ቢቆራረጥም ከተለመደዉ ዉጪ፣ አብዛኛዎቹን ጥያቄዎች አቅርቧል፡፡
ከኬቶ ጋዎ
ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: