Leave a comment

ለካፋ ወጣቶች ወቅታዊ ጥሪና መልዕክት


ለካፋ ወጣቶች ወቅታዊ ጥሪና መልዕክት

 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ክልል ሥር በተካለሉት ምዕራባዊ ዞኖች በደረሰዉ የተቀነባበረ ተፅዕኖና፣ ሥር በሰደደ መዋቅር አማካይነት ባለፉት 27 ዓመታት የደረሰዉ የአስተዳደር በደል፣ ግፍና የተፈፀመዉ ወንጀል፣ በርካታ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአካባቢ ባለሥልጣናት፣ የደቡብ ገዢና፣ ያሰማራቸዉ ወያኔ ትኩረቱ ሁሉ ዝርፊያ ስለነበረ፣ ስለህዝቡና ስለአካባቢዉ ልማት የሚታሰብበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ህዝቡ ሲቆረቁዝና፣ አካባቢዉ ወደሁዋላ ሲጓዝ፣ የወያኔ አባላትና ተላላኪዎቻቸዉ ግን በራሳቸዉ፣ በቤተሰቦቻቸዉና በታማኞቻቸዉ ሥም የዘረፉት፣ አካባቢያዊና የአገር ሃብት ሰፊ፣ የደረሰዉ ጠባሳም የማይሽር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህዝቡ ፈረጀ-ብዙዉን ዘረፋና፣ አፈና ችሎ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ምሬቱ ሲበቃዉ መብቱን በአደባባይ መጠየቅ ጀምሯል፡፡ አሁን የተጀመረዉ ያልተለመደ፣ በግልፅና በአደባባይ የመጠየቅ ጅማሮ፣ የሚበረታታ ነዉ፡፡

 

ሆኖም ይህ እየታየ ያለዉ፣ የመጠየቅ ሂደትና ሁሉም እንቅስቃሴዎች፣ ህግን መሰረት በማድረግ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም የህዝብን ሰላም፣ እንቅስቃሴና፣ የዕለት ተዕለት ተግባር በማወክ፣ እንዲሁም የአካባቢዉንና የሃገርን ሃብት በማዉደም ሊሆን አይገባም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ መቀጠል ያለበት ሆኖ፣ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ዉስጥ፣ በለዉጥ ሃይሎች የተጀመረዉን ሂደት በቅርበት መከታተል፣ ለተሻለ ተስፋና ዉጤት መደገፍና ማበረታታት ጠቃሚ ሲሆን፣ ህግ ዉጭ፣ ሰላማዊ ያልሆነ ተግባር፣ የአደናቃፊዉ ቡድን ማሣሪያ መሆን፣ ወዲያዉም ግፉና በደሉ እንዲቀጥል አስተዋፅኦ ማድረግ ይሆናል፡፡ ለዚህም የመብት ጥያቄዉን በተረጋጋ፣ በአስተዋይነትና በብልሃት፣ ማካሄድ፣ ከየአቅጣጫዉ የሚመነጩ ወጣቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ ቅስቀሣዎችን፣ ምንጫቸዉን፣ ዓላማና ግብ በትክክል መረዳት፣ ዉጤቱ ለማን የሚጠቅም እንደሆነ መመርመር ተገቢ ነዉ፡፡ የደረሰዉን ግፍ የፈፀሙና፣ የመሩ ብልጣ ብልጦች፣ የተጀመሩ የህዝብ ጥያቄዎችን አቅጣጫ እንዳያስቀይሩ መጠንቀቅ፣ እርምጃዉ ሁሉ በአርቆ አስተዋይነትና፣ በሃላፊነት ስሜት መቀጠል እንዲችል መረጋጋት አስፈላጊ ነዉ፡፡

 

ለዚህ ፅሑፍ ያነሳሳኝ፣ ሰሞኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በተለይም በወጣቶች እየተካሄደ ያለዉ ተግባር አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ነዉ፡፡ ወጣቱ በየትኛዉም እንቅስቃሴ ከመሳተፉ በፊት፣ ዓላማዉን፣ የሃሳቦቹን ጠንሳሾች ማንነት መመርመር፣ ከሚወሰደዉ እርምጃ የሚገኘዉ ዉጤት ምን እንደሆነ፣ ዘላቂነቱን፣ ከዚህ ዋናዉ ተጠቃሚዉ ማን እንደሚሆን፣ በጥልቀት መተንተን አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቴ ነዉ፡፡

 

የህዝቡ ጥያቄ፣ በተለይም ለአፈ-ጉባኤ ሙፌሪያት ካሚል የቀረበዉ አቤቱታ ጥሩ ጅማሮ ነዉ፡፡ በዚህ ዓይነት በሁሉም ችግሮቻችን ላይ መብት መጠየቅ ተገቢና የሚበረታታ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን የነበረዉ ዉይይት አጭር፣ ዋናዎቹን ተጎጂዎች ማለትም፣ ገበሬዎችና ወጣቶችን በበቂ ደረጃ ያሳተፈ ባይሆንም፣ ከተሳታፊዎቹ የቀረበዉ ጅማሮ የሚበረታታ ነዉ፡፡ ተሳታፊዎች ጉልህ ጉዳዮችን በድፍረት ያነሱ ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ከዚህ ባላፈ በርካታ ጥልቅ ዉይይትና በተደራጀ መንገድ መነሳት ያለባቸዉ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህም በተደራጀ መንገድ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ መድረኮችና መንገዶች፣ በድፍረት፣ ሰላማዊና፣ አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መንገድ ሊቀጥል ይገባል፡፡

 

ከሰሞኑ፣ የካፋ ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ባደራጀዉ ስብሰባ ላይ፣ ስለክልል ጉዳይ በምሁራን የተደረገዉ ዉይይትም ጠቃሚ፣ አስተባባሪዎቹም ሊመሰገኑ፣ ተመሳሳይ ሂደትም በስፋጥ ሊቀጥል የሚገባዉ መሰረታዊ ጉዳይ ነዉ፡፡

የአካባቢዉ ህዝብ ጫንቃዉ ከሚችለዉ ባለይ ብዙ በደል ተሸክሞ ቆይቷል፡፡ ይህ ያንገበገባቸዉ በርካታ ወጣቶች ብዙ እንደሆኑ፣ አሁን በሚታየዉ የተቃዉሞ ሂደት ዉስጥ ሲሳተፉ፣ አብዛኛዎቹ ህዝባዊ ዓላማ አንግበዉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መሰረታዊዉ ጥያቄያቸዉም ተገቢና ምላሽ ሊሰጠዉ የሚገባዉ ነዉ፡፡

 

በዚህ ሂደት፣ ህዝቡ ለመብቱ እንዲቆም መታገልና፣ መፍትሄ እስኪሰጠዉ ድረስ፣ በጋራ መቆም ትክክል ነዉ፡፡

በስሰባዉ የተነሳዉ የህዝቡ ጥያቄና፣ የሰሞኑ የምሁራን ዉይይትም፣ መንግሥት ራሱ በፈጠረዉ መዋቅራዊ ስህተት ያደረሰዉን፣ በደልና ጫና መንግሥት ራሱ በህጋዊ መንገድ እንዲያሰተካክለዉ ነዉ፡፡ ከአፈ-ጉባኤ ጋር በተደረገዉ ዉይይትም ሆነ፣ በምሁራን የተደረገዉ ሰላማዊና፣ ህጋዊ ዉይይትና ጥያቄ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለዉ መገንዘብ ይገባል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት የሚጠበቀዉ፣ በአስተዋይነት፣ ለመብትና፣ ለተሻለ ህይወት፣ ለአገሪቱም ደጋፊ እንቅስቃሴና፣ ጥያቄ መቀጠል ይገባል፡፡

 

ሆኖም አልፎ አልፎ የሚታየዉ የሃይል እርምጃ፣ የህዝቡን መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ፣ ለሌሎች የሚጠቅም ዉጤት ስለሚኖረዉ፣ ከግርግሩ የሚጠቀሙ ሌሎች ሃይሎች እጅ እንዳይኖርበት መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ለወጣቱ ስሜታዊነት ምክንቱ የታወቀ ነዉ፡፡ ገና ያልተነገረና በአደባባይ ያልወጣ ብዙ ጥያቄ፣ መፍትሄ የሚያሻዉ የአስተዳደር በደልና ግፍ ተፈፅሟል፡፡ በአንዳንድ ስሜታዊ እርምጃዎች መብትና ጥቅምን ማረጋገጥ የሚቻል አይደለም፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት፣ ተገጂዉ የአካባቢዉ ህዝብ ጭምር ደስተኛ እንደማይሆን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከየትኛዉም ወገን ቢሆን፣ ሰዉ በመሞቱ የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ከየትኛዉም ወገን ዛሬ የሚጠፋ ህይወት፣ ወደ ቂምና በቀል አዙሪት እንዳያስገባን ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ በሃይል ንብረት መቆጣጠርም ሆነ ማዉደም ቢቻልም፣ የሚወድመዉ ንብረት ለወጣቱም ሆነ ለህዝቡ ጥቅም አይሰጥም፡፡

 

መሬትና፣ ደንም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ ሃብቶችን መያዝ ቢቻልም፣ ህጋዊ እስካልተደረገ ድረስ በዘላቂነት የራስ ይዞታ አይሆንም፡፡ ከዚህ ይልቅ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ መሬት የሌላቸዉ በርካታ የአካባቢዉ ዜጎች ስላሉ፣ በህጋዊ መንገድ መሬት መጠየቅና መያዝ፣ ለመቋቋሚያም እንደማንኛዉም ዜጋ፣ ከመንግሥት ተገቢዉን ድጋፍ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ መታወቅ ያለበት፣ በራሱ በገዢዉ ድርጅት፣ በኢህአዴግ ዉስጥና፣ በአካባቢያችንም ጭምር በመንግሥት ዉስጥ፣ የለዉጡ መንፈስ ሙሉ በሙሉ እንዳልሰረገ፣ አልፎ አልፎም በግልፅና፣ በሥዉር በአፍራሽ ጎዳና ላይ የቆሙ፣ አደናቃፊ አካላት፣መኖራቸዉና በዚህ ተግባር መጠመዳቸዉን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ የበለጠ ማስረጃ የለም፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ አቅጣጫ፣ በመላ ሀገሪቱ፣ ህዝቡ የተከመሩበትን በደሎች አያነሳ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ አንዳንዴም አመፅ የተሞላበት፣ የህይወትና፣ የንብረት ዉድመት ያደረሰ እንቅስቃሴ እየታየ ነዉ፡፡ ይህም በተበደሉና ለመብታቸዉ በተነሱ፣ በምሬት የተሞሉ ወገኖች ብቻ ሳይሆን፣ አልፎ አልፎ አጋጣሚዉን ተጠቅመዉ ህዝብን ተጠቅመዉ በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጭምር የተቀናበረ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከተለመደዉ በተለየ ሁኔታ፣ መንግሥት ከሃይል ይልቅ ወደ ዉይይት ማድላቱ በበጎ ጎኑ ሊታይ፣ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባዉ ይሆናል፡፡

 

በወቅቱ የሚታየዉ ያልተደራጀ፣ በስሜት ላይ የተመሰረተ የወጣቱ ተግባር በዋናነት ጉዳቱ ለራስ፣ ለአካባቢዉ ህዝብና፣ በጋራ ጥቅማች ላይ ነዉ፡፡ አስተዋይነት በጎደለዉና፣ በስሜታዊነት የሚወሰድ እርምጃ፣ ባለፉት ዘመናት በአካባቢዉ ለደረሰዉ በደል፣ ግፍና፣ ሁዋለ ቀርነት መፍትሄ አይሆንም፡፡ መፍትሄዉ ህጋዊ፣ ሰላማዊና፣ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ተከታታይና፣ በተለያዩ መንገዶች የሚቀርብ ጥያቄ ብቻ ነዉ፡፡ የተጀመረዉ አገራዊ ሂደት ወደ ሁዋላ እንደማይመለስ ተስፋ አለንና፣ ሁሉንም በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ፣ ህጋዊና የተደራጀ መስመር መከተል፣ ትዕግሥትናአስተዋይነት ያዋጣል፡፡

 

ሆኖም አንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች ዓላመዉን መዛባት እንደሚችሉ ማሰብ ተገቢ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ፣ በደቡብ ምዕራብ ህዝቦችና፣ አካባቢ ላይ ለደረሰዉ ዝርፊያዉና አፈና፣ በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂዎቹ፣ በየደረጃዉና፣ በየሴክተር መ/ቤቶች እየተመራረጡ የተሰገሰጉ ለጥቅማቸዉና፣ ለሥልጣናቸዉ ብቻ የተሰለፉ፣ ኢህአዴግን ራሱን ሲሸረሽሩ የነበሩና፣ አሁንም ከማደናቀፍ የማይቦዝኑ፣ አባላት ናቸዉ፡፡ ዋናዎቹ ተዋናዮችና ፈፃሚዎች፣ ህዝቡ ራሱ ተግባራቸዉን፣ ማንነታቸዉን፣ መነሻና መድረሻቸዉን አብጠርጥሮ የሚያዉቃቸዉ፣ እነዚህ የአካባቢዉ ምልምል ባለሥልጣናት ናቸዉ፡፡ እነዚህን የመለመለዉ፣ ያደራጀዉ፣ በዋናነት፣ የካፋን፣ በአጠቃላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ሃብት የዘረፈዉ፣ ለዚህ እንዲመቸዉ፣ የአካባቢዉን ካድሬዎች ተንከባክቦ ያሳደገዉ፣ የቀረፀዉና፣ ሥልጣን የሰጣቸዉ፣ የአፈናዉ ሁሉ ዋናዉ ተጠቃሚ፣ ወያኔ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

በሰንሰለቱ ዉስጥ ለዋናዉ ገዢ በቅርበት ሆነዉ፣ ጉዳይ ያስፈፀሙ፣ ህዝቡን በግልፅ የናቁና፣ በሁሉም ረገድ የደፈጠጡት፣ ደግሞ የደቡብ ክልል ባለሥልጣናት ናቸዉ፡፡ የተጀመረዉ የለዉጥ ሂደት ደግሞ በዋናነት የሚያሰጋዉ፣ እነዚህን ሁሉ ሲሆን፣ ለዉጡ ከተሳካና ዉጤታማ ከሆነም፣ ጥቅማቸዉን፣ ሥልጣንና፣ ኑሮአቸዉን እንደሚያናጋባቸዉ ግልፅ ነዉ፡፡ እነዚህ አካላት ሰንሰለታቸዉን ተጠቅመዉ ህዝቡን ከራሱ መሰረታዊ ጉዳይ ማዘናጋት፣ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት፣ የጥያቄዉን አቅጣጫ፣ ትኩረትና ይዘት ማዛባት፣ ለህገ- ወጥ ተግባር ማመቻቸትና ማነሳሳት እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛዎቹ የሚተዳደሩበትን ሃላፊነታቸዉን ከመወጣትና ህዝቡን ከማረጋጋት ይልቅ፣ ቸልተኝነት፣ ብሎም ዉስጥ ለዉስጥ ቅስቀሳ ማድረግ ላይ ቢሆኑ አይገርምም፡፡ በዉጤቱም ባሉበት የመንግሥት ሥልጣን ላይ መሰንበት፣ የለዉጡ ሂደት ሲሳካም፣ ቆዳቸዉን አዉልቀዉ በተለመደዉ ቦታቸዉ መቀጠል እንደሚሞክሩ ሊታሰብ ይገባል፡፡

 

እንደሚታወቀዉና፣ ብዙዎቹ ወጣቶች በዋናነት በድረ-ገፅ እንደዘገቡት፣ ዋናዉ ፈጣሪያቸዉ በፌስ ቡክ መርዘኛ አሉባልታ እየረጨ፣ የዋሁን ወጣት ማነሳሳት ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በአጠቃላይ ይህንን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ብዙ ጊዜና፣ ጥረት ይጠይቃል፣ አስታዋይነትና ብልህነትን ይጠይቃል፡፡

ህዘቡ፣ በተለይም ወጣቱ ብዙ ብሶት ማወቅ ያለበት፣ የህዝቡን እንቅስቃሴ ተጠቅመዉ ዓላማቸዉን ማሳካት የሚፈልጉ በርካታዎች ናቸዉ፡፡ ከካድሬዎች ሌላ ከህዝብ ሥር እየተሽሎከሎኩ፣ ከመጣዉ ጋር ሆነዉ ጥቅማቸዉን ሲያካብቱ የቆዩ በርካት ሲሆኑ፣ የአፈናዉ አባላት አቅም፣ ልምድና ሰንሰለቱ ያካበተዉ ብቃት፣ ሊፈጥሩ የሚችሉትንም ተፅዕኖም በቀላሉ መገመትና፣ መዘናጋት አይገባም፡፡ ብዙ ልምድ ያካበቱና፣ በሴራ የተካኑ በመሆናቸዉ፣ ህዝቡን የእነርሱ መሣሪያ እንዲሆን ከማድረግ አይመለሱም፡፡

 

ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ካነሳቸዉ የመብት ጥያቄዎች ይልቅ፣ ጎልተዉ የተነገሩት ግን ለህዝቡ መብት መከበር ምንም የማይጠቅሙ፣ በግልፅ ጎጂ የሆኑት ናቸዉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የሃይል እርምጃዎች፣ ለማንም ምንም ጠቀሜታ የሌላቸዉ፣ በተለይም ለለዉጡ ሂደት ጎጂ ናቸዉ፡፡ አንዳዶቹን ለመጥቀስ ያክል፡-

➢ በቅርቡ በቴፒና አካባቢዉ የደረሰዉ ብሄር ተኮር ግጭት መነሻዉና ዉጤቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ነዉ፡፡ ማንም ማንንም ዉጣ፣ ግባ ማለት፣ በብሄር ደረጃም ባህርዩን መፈረጅ አይችልም፣ እንደዚህ የሚባል ዕዉነታ የለምና፡፡ ክፉና፣ ደካማ ባህርይ ከሁሉም አገር ዜጎች፣ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና፣ ግለሰቦች ላይ ሊታይ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እጅግ የተመሰገኑ ግለሰቦች ከየትኛዉም ወገን ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ይህንን ባላገናዘበ መንገድ፣ የሃይል እርምጃ መዉሰድ፣ የቂምና፣ የበቀል አዙሪት ከመፍጠር ያለፈ ትርፍ የለዉም፡፡

 

➢ እንዲሁም በገዋታ ወረዳ ለዘመናት አብሮ በኖረዉ፣ በንግድ፣ በጋብቻና በብዙ ጉዳዮች የተሳሰረዉን ህዝብ ለማጋጨት መቀስቀስ ተሞክሯል፡፡ አስተዋይ ዜጋ ሊረዳዉ የሚገባዉ፣ በሌላዉ ሰፊ የኦሮሚያ ክልል እንኳን ቢሆን፣ በኦነግ ሥም ያልታወቁ ሰዎች ህገ-ወጥ ተግባር ማድረጋቸዉ ታዉቋል፡፡ ይህ ቅስቀሳና፣ ተግባር፣ ድርጅቱ፣ ኦነግ ከመንግሥት ጋር አብሮ እንዳይሰራ ለማደናቀፍና፣ ህዝቡን ለማደናገር የሚደረግ እኩይ ሴራና ሙከራ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አደናቃፊዎች ደግሞ አሁን ደርሰዉ ለህዝብ አሳቢ መስለዉ፣ ግጭት በመቀስቀስ፣ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር መሞከራቸዉ የሚጠበቅ ነዉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዳይ በማስተዋል፣ በብልህነትና በጥልቀት መታየት የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

➢ አሁን ደግሞ ወጣቱ መሬትና ደን በራሱ መንገድ ተቆጣጥሮ መከፋፈል መጀመሩ በየቦታዉ ይሰማል፡፡ ኢንቨስተር ተብለዉ የገቡ ገዢዎቻቸን ያወደሙት የተፈጥሮ ደን፣ የዘረፉትና እየጫኑት ያለዉ ግንድና ጣዉላ ሊቆጨዉ የሚገባዉ የአካባቢዉ ወጣት በራሱ ተመሳሳይ ተግባር ላይ መሰማራቱ የሚያሳዝን ነዉ፡፡ ለዘመናት ትዉልዱ ጠብቆ ያቆየዉ ደን በዘራፊዎች ወድሞ፣ ግንድና ጣዉላ ሲነግዱ፣ ህዝቡ ማዉገዝ ሲገባዉ፣ ራሱ ተመሳሳይ ሂደት ጀምሯል ማለት፣ ለሌሎች ዘራፊዎች ከለላ ከመሆን የሚያልፍ ዉጤት አይኖረዉም፡፡ በገዢዎቻችን የተፈፀመዉ፣ የደን ወረራ፣ የወደመዉ እድሜ-ጠገብ ዛፍ፣ የጠፋዉ ንብ፣ ኮሮሪማ፣ ጥምዝና ሌላዉ የህዝቡ የጋራ ሃበት ሊተካ አይችልም፡፡ ከዚህ አልፎ የቀረዉን ደን መከፋፈል ማለት፣ ከሁዋላዉ ያለዉን ሃይልና ዓላማ መርዳት ብቻ ነዉ፡፡

 

ዋናዉ መፈተሽ ያለበት ግን፣ ከአካባቢዉ ሁኔታ አኳያ በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ ጉዳዮች ስላሉ፣ አቅጣጫ ለማስቀየር ካልሆነ በስተቀር ይህ ለምን ተደረገ፣ ይህንን ሁሉ ማን አደራጀዉ፣ ዓላማዉና ግቡስ ምንድነዉ፣ ከዚህ የሚጠቀመዉስ ማነዉ? የሚለዉ ነዉ፡፡ የለዉጡ ሃይልም ተጠናክሮ፣ መንግሥትም እየገባ ያለዉን ቃል መፈፀም ሲጀምር፣ ዋናዎቹን በዘረፋ፣ በአፈናና በህገ- ወጥ ተግባር የተሳተፉ አካላት ጨምሮ፣ ሁሉም ዜጋ በየግሉ ተጠያቂ መሆኑ የማይቀር ነዉ፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴዎች፣ በእርጋታ፣ በአስተዋይነት፣ በተረጋገጠ መረጃ መመስረት፣ በብልህነትና በአርቆ አስተዋይነት ቢሆኑ ተገቢ ይሆናል፡፡ ህዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ ሊያተኮርባቸዉ ከሚገባቸዉ ወቅታዊ ጉዳዮች የሚቀጥሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

1. የደረሰዉን ግፍና በደል፣ በተረጋጋና በሰላማዊ መዉገዝና፣ የመብት ጥያቄ መቀጠል፡፡

የደረሰዉ በደል ብዙ፣ አፈፃፀሙም ሆነ መፍትሄዉ ብዙዎችን የሚመለከት ነዉ፡፡ ገዢ ድርጅቱን ራሱን ለማስተካከል በሚያደርገዉ ሂደት፣ ህዝቡ በተለያየና ባገኘዉ መንገድ ሁሉ ድምፁን ማሰማት መቀጠል አለበት፡፡ ይህም በሰላማዊና፣ ህጋዊ መንገድ እንዲሆን ይገባል፡፡ በተለይ ወጣቱ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚተላለፈዉን፣ በጥልቀት እየመረመረ መርጦ መቀበል አለበት፡፡ስሜቱንም በተገቢዉና፣ ዘላቁዉን ግብ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ሊገልፅ ይገባዋል፡፡ ምሁራን ከመመራትና ከዝምታ መዉጣት መጀመር አለባቸዉ፡፡ በሰከነ መንገድ፣ በየሙያቸዉ መረጃዎችን መተንተንና፣ ማስተማር፤ ሰሞኑን የተጀመረዉን የመብት ጉዳይና ዉይይት ማስፋትና መቀጠል ይገባል፡፡

 

2. የአደናቃፊ ሃይሎችን ሚናና ተፅዕኖ መቋቋም፡፡

አሁን ባለዉ አያያዝ፣ ኢህአዴግ ራሱ በመርህ ደረጃ ቢፈልገዉና ተስፋ ብናደርግም፣ ለዓመታት ህዝቡን ካቆረቆዙት የአካባቢዉ

የኢህዴግ አባላት እንቅፋት አይገጥመዉም ተብሎ አየጠበቅም፣ የኢህአዴግን የራሱን የለዉጥ ሂደት እንደሚያደናቅፉና፣ ማደናቀፍ እንደጀመሩ እየታየ ነዉና፡፡ በመሆኑም ለነዚህ ሃይሎችና ለሚያደራጁት እንቅፋት መዘጋጀትና፣ መመከት በተለይም ከወጣቱና ከምሁራን የሚጠበቅ የቅድሚያ ተግባር ነዉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በአብዛኛዉ ምንም ዓይነት ህዝባዊም ሆነ፣ ፖለቲካዊ መርህ የሌላቸዉ፣ ለጥቅማቸዉ ብቻ እንጂ ለኢህአዴግ ለራሱ ዓላማ የተሰለፉ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የለመዱትን ከፍተኛ ኑሮ እና ሥልጣን ጠብቀዉ ለመቆየት መሞከራቸዉ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም የበላዮቻቸዉ ለዉጥ ቢፈልጉ እንኳን፣ እነዚህ ሰዎች ግን የቻሉትን ሁሉ በማድረግ የሚመጣዉን ለዉጥ ማደናቀፋቸዉ ስለሚጠበቅ፣ ወጣቱ ለእነዚህ ቅስቀሳና፣ አፋኞች ቆዳቸዉን ለዉጠዉ እንዳይቀጥሉ በጥንቃቄ መከታተልና መታግል ይገባዋል፡፡

 

3. ቆስቋሾች ሴራና፣ ከሚፈጠር ግጭት መራቅና መከላከል፡፡

በዚህ የዝግጅትና የለዉጥ ሂደት በተለይም ልዩ ትኩረትና አርቆ አስተዋይነት ለደረግበት ከሚገባቸዉ ጉዳዮች፣ አንዱ የህዝቡን ትኩረት ወደሌላ አቅጣጫ በማዞር በተለይም ግጭት መፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች፣ ራሳቸዉ ዘንግተዉ የቆዩትን፣ ሲያስዘርፉና፣ ሲዘርፉ፣ ሲጨቁኑትና ሲያፍኑት የቆዩትን ህዝብ፣ አሁን ደርሶ ተቆርቋሪ፣ ወገናዊና፣ ባለቤት መስለዉ በመቅረብ ሊቀሰቅሱት ይችላሉ፡፡ አንዳንዶችም ጥቃቅን የግል ጉዳዮችን ወቅቱን ተጠቅመዉ ህዝባዊ መልክ ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ እነዚህና ተመሳሳይ ሴረኞችና፣ ስሜታዊ ግለሰቦች፣ ወቅቱን ተጠቅመዉ ወጣቱን ሊጠቀሙበትና፣ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ይችላሉ፡፡

 

የዚህ ጭምጭምታ እየታየ ሲሆን፣ ከዚህ በፊትም ጠባሣ ጥሎ ያለፈ ሥልት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ አርቆ አስተዋይ ሆኖ፣ ማን፣ ለምን እንደሚቀሰቅሰዉ፣ ለይቶ ማሰብ አለበት፡፡ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የገዚነትና የብዝበዛ ዘመናቸዉን ለማርዘም በቆሙ ካድሬዎች ቅስቀሳ የተነሳ የደረሰዉን አቅጣጫ የማስቀየሪያ ሥልት፣ የደረሰዉን ጉዳትም ማስተዋልና፣ ተመሳሳይ ሙከራ፣ በአካባቢያችንም ሊተገበር ስለሚችል፣ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ነባሩም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ በአካባቢዉ ኑሮዉን የመሰረተዉ ዜጋ፣ እኩል የተጎዳና፣ ለተመሳሳይ ግብ የሚታገል በመሆኑ፣ በብሄር መነሻ ሥጋት እንዳይፈጠር፣ በአጋርነት መቆምና፣ ይልቁንም የሌቦች መሣሪያ እንዳይሆን መጠንቀቅና፣ በአስመሳዮች ቅስቀሳ የተነሳ ከመናቆር በመራቅ በዋናዉ የጋራ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባል፡፡

 

መሰረታዊዉ ጉዳይ ህዝባችን በኢትዮጵያ ዉሥጥ ራሱን አስተዳድሮ፣ መሪዎቹን በራሱ መርጦ፣ ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖሊስ፣ ስትራቴጅና ደንብ በማዉጣት፣ በህጉ መሰረት አካባቢዉንና አገሩን ማልማት፣ አብሮ ማደግ መበልፀግና፣ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤ በአገሪቱም ዉስጥ ሁለ-ገብና፣ እኩልነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ፣ አስተዋፅኦ ማድረግና፣ ተከባብሮ መኖር፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ አንድ ጉልህ አካል መሆን ነዉ፡፡

 

ይህ ሲሆን ግን ወቅቱን ጠብቆ የሚፈታ ብዙ የመብት ጥያቄ እንደተጠበቀ፣ ወጣጡን በተመለከተ መንግሥት ሊፈታዉ የሚገባዉ አፋጣኝ ጥያቄ መጠቆም ተገቢ ይሆናል፡፡ ታሪኩ ብዙ ሲሆን፣ የተደረጉ ጥረቶችንና ዉጤቱን በመተረክ ጊዜ መፍጀት አያስፈልግም፡፡ ለቀድሞዉ ጠ/ሚ/ር ሃይለማሪያምና ለክልሉ አካላት በተደጋጋሚ ቀርቦ ችላ የተባለ፣ ብዙ ተመክሮ የተደናቀፈ፣ መፈታት ያለበት ወሳኝ የወጣቱ ጥያቄ ስለሆነ እንደሚከተለዉ በአጭሩ ቀርቧል፡፡

 

ማሳሰቢያ፣ ለመንግሥት ሃላፊዎች

 

በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ዞኖች፣ ሰፊ ለም መሬት እያለ፣ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በርካታ ገበሬዎችም ጭምር፣ መሬት እንደሌላቸዉ ለረጅም ጊዜ፣ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ካፋ ዉስጥ ይህ ጉዳይ፣ በ1998 ዓ.ም. ለቀድሞዉ ጠ/ሚ/ (በወቅቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚ/ር) እና የክልሉ ድርጅት መሪ ለነበሩት አቶ ሃይለማሪያም የቀረበ ሲሆን፣ በየጊዜዉ ለመጡ የክልሉ ሃላፊዎች የቀረበ ቢሆነም ተገቢዉን ምላሽ ግን አላገኘም፡፡

 

ማንም የሚያዉቀዉ በአገሪቱ ባለፉት አሥር ዓመታት የተደረገዉ የሰፈራ ፕሮግራም፣ በመንግሥት ታቅዶ፣ በየክልሉም በአባል ድርጅቶችና በክልል መንግሥታት መተግበሩ ይታወቃል፡፡ መንግሥትም ዕቅዱን ለአጋሮች ጭምር አሳዉቆ ድጋፍ ማግኘቱ የታወቃል፡፡ በደቡብ ክልል የታቀደዉ ሰፈራ ደግሞ ከዞን ወደ ሌላ ዞንና፣ ሰፋሪዎች በያሉበት ዞን ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሆን፣ የሚሰፍረዉ የቤተሰብ ብዛት ጭምር በመንግሥት ግልፅ ተደርጎ ነበር፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ለዓለም ጭምር ያሳወቀዉ ጉዳይ፣ አድሏዊ በሆነ መንገድ ከየዞኑ የሚደረገዉን ሰፈራ ዞኖች ራሳቸዉ እንዲደግፉት የደቡብ ክልል ትቷል፡፡ ሰፈራዉ በሙሉ የሚደረገዉ በምዕራብ ዞኖች ዉስጥ በመሆኑ፣ የተደረገዉ አድልኦም የተለመደ በመሆኑ፣ የሚገርም አይደለም፡፡

 

በዚህም መሰረት ሁሉም ተሟልቶላቸዉ፣ ከደቡብ ዞኖች ብዙ ኪ.ሜ. ርቀዉ ተጉዘዉ ሰፈራ ተደርጓል፡፡ ለእነዚህ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቀዉ ለሰፈሩት ወገኖች፣ መሰረተ-ልማት ተሟልቶ፣ የእርሻ ግብዓት ተሟልቶ፣ ፀጥታዉ ተጠብቆ፣ ከፍተኛ እንከባክቤ ተደርጎ ነዉ፡፡ በሂደቱ ተቀባይ አካባቢዎች በራሳቸዉ ወጪ ክትትልና ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የአካባቢዉ ህዝብ ግን፣ቀዬዉ በሰፈራና፣ በኢንቨስትመንት ስም ሲሸነሸንና፣ ሲዘረፍ፣ እያየ ህግ በማክበር ብቻ የበይ-ተመልካች ሆኖ ቆይቷል፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር፣ መሰረተ-ልማትና ሌላ ድገፍ ማድረግ ያልቻሉ ዞኖችም በአጎራባች ወረዳዎች ከማስፈር ይልቅ፣ የተወሰኑ ወጣቶችን በያሉበት አካባቢ አደራጅተዉ፣ ለዘመናት ህዝቡ በወል ጠብቆ ይዞት የነበረዉን የግጦሽ መሬት በማከፋፈል፣ የግብር ይዉጣ ሥራ ሰርተዋል፡፡

 

በዚህ የተወሰኑ ወጣቶችን ዝም ማድረግ የተሞከረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን መላ ህዝቡ ከስምንት ዓመታት ወዲህ የወተት የግጦሽ ቦታ በማጣት፣ ላምና ጥጃዋን ቀርቶ፣ ለቀለቡ የሚያርስበትን አንድ በሬ እንኳን መንከባከብ ስላቃተዉ ያለዉን ሁሉ ሽጦ ወደ ባሰ ድህነት ዕየወረደ ነዉ፡፡ የተወሰኑት ልጆቻቸዉን ከትምህርት አስቅርተዉ ላማስጠበቅ ሲመክሩ፣ ልጅ የሌላቸዉ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ደግሞ ከአቅማቸዉ በላይ የከብት እረኛ መሆን መፐክረዋል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ህዝቡ፣ ከመቶ ዓመት በፊት እንደሆነዉ፣ ወተት ቀርቶ፣ እበት እንኳን መናፈቅ ጀምሯል፡፡ የመሬት ጥበት ባለባቸዉ የአገሪቱ አከባቢዎች እንኳን፣ እስካሁን የተንጣለለ የጋራ የግጦሽ መሬት ተከልሎ፣ እንስሳት ይርመሰመሳሉ፡፡ በተቃራኒዉ፣ ከዞን ዉጪ ለሚደረግ ሰፈራና ለኢንቨስትመንት መሬት እየተመደበ ባለበት አካባቢ፣ ለዉስጥ ሰፈራ ድጋፍ አይደረግም በማለት፣ ጥቂት ወጣቶችን በግጦሽ መሬት እንዲሰፍር ማድረግ፤ ህዝቡንም ከብቶችህን በየጓሮህና፣ በማሳህ ዉስጥ ጠብቅ፣ ካልሆነም ሽጥ ማለት፣ በዚህም ህፃናትን ያለ ወተት፣ ገበሬዉን ያለበሬ ማስቀረት ለህዝብ ከቆመ መንግሥት የማይጠበቅ፣ ሌላዉ ታሪክ ይቅር የማይለዉ ግፍ፡ ሲሆን ዉጤቱም አስከፊ ነዉ፡፡

 

አሁን ደግሞ ወጣቱ መሬት ሲጠይቆ ቆይቶ፣ ተስፋ ሲቆርጥ፣ ከተለመደዉ አካሄድ ዉጭ፣ በራሱ መንገድ ከኢንቨስተሮች የተረፈዉን ደን መከፋፈል ጀምሯል፡፡ በመሰረቱ ወጣቱ በዚህ መንገድ ደኑን መዉረሩ አይደገፍም፡፡ ጥያቄዉ ግን ሰርቶ ማደግ ከሆነ በአግባቡ ሊፈታለት ይገባል፡፡ የወጣቱ የመሬት ጥያቄ ሰርቶ ለመልማት ከሆነ፣ እንደሌሎች ወጣቶች፣ በተገቢዉ መንገድ ሊደገፍ ይገባል፡፡ በመሆኑም የነበረዉ አመራር ቢያበላሸዉም፣ አሁን ያለዉ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ፣ አድሎዉን እንዲቀለብስ፣ በቃሉ መሰረትም፤ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ ደኖችን በማይነካ መንገድ፣ ለመሬት አልባ ወገኖች በሙሉና፣ በተለይም ለወጣቶች፣ በህጋዊ መንገድ፣ የመሬት ዕደላ እንዲያደርግ ይገባል፡፡ ለሌሎች ሰፋሪዎች እንደተደረገዉም፣ የክልሉ መንግሥት፣ በጀት መድቦ፣ ድጋፍ ማድረግ፣ መሰረተ-ልማት ማሟላት፣ ዘር፣ መሳሪያና ሌሎች ለመቋቋም አስፈላጊ ነገሮችን መደጎም፣ በሰፈራዉም አካባቢ ፀጥታዉን ማስጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡

 

ይህ ካልሆነ ግን ግልፅ የሆነ ማግለል፣ ንቀትና፣ ጥላቻ እንደቀጠለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአግባቡ ባልተመራ ሁኔታ፣ ወጣቱ በዙሪያዉ ያለችዉን የቀረችዉን ደን ካወደመ፣ ጉዳቱ የአገርና የዓለም ሁሉ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል፡፡ እየታየ ያለዉ ግጭት፣ የንብረት ዉድመትና፣ አሁን ደግሞ ከጫፍ እስከ ጫፍ ደን ላይ መስፈር ትክክላኛ መንገድ አይደለም፡፡ ሥራ ያጣ፣ ኑሮዉ በመንገድ ላይ የሆነ፣ ወጣት ግን ከሁዋላዉ የሚገፋፋዉ ሃይል ካለ፣ ሊገነፍል ይችላል፡፡ መንግሥት ህዝቡን ማወያየትና ማደራጀት፣ ለቁልፍ ችግሮች ፍትሃዊ መፍትሄ መስጠት፣ ህግና ሥርዓት ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

ከG.C

ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: