Leave a comment

የካፋና ምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ፤


የካፋና ምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ፤

የጥቂቶች አይደለም፣ ታሪካዊ መሰረትና ተጨባጭ ምክንያት ያለዉ፣ ምላሽ የሚገባዉ ነዉ፡፡

 

I. መግቢያ

በታሪክ እንደሚታወቀዉ፣ አገሮች በወረራና በተመሳሳይ መንገዶች መመሥረታቸዉና፣መስፋፋታቸዉ ይታወቃል፡፡ ገዢዎች የራሳቸዉ ማብራሪያ ቢኖራቸዉም፣ የትም ቢሆን ወረራ በዋናነት የሚካሄደዉ፣ ሃብት ለመቆጣጠር፣ ግዛት ለማስፋፋትና፣ የራስን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ሆኖም በሂደት ሁኔታዎች ሲሻሻሉና፣ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ተገዢዎች ክብራቸዉ ተጠብቆ፣ የአገራቱ እኩለ ዜጋ ሆነዉ ሲቀጥሉ፣ በዘር የተገለሉት ሁሉ ሳይቀሩ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸዉ ሲረጋገጥና፣ የመሪነት ሥልጣን ሲይዙ ጭምር ታይቷል፡፡ አንዳንድ አገሮች ግን እስካሁንም ድረስ የተወሰኑ ማህበረሰቦችን እኩል ባለማስተናገዳቸዉ፣ በሚቀሰቀሱ የመብት ጥያቆችና እንቅስቃሴዎቸ የተነሳ፣ ሰላም ሲደፈርስና፣ ሰብዓዊ ጉዳት ሲደርስ ይታያል፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን የተወረሩም ሆኑ፣ በባርነት ሥር የነበሩ ህዝቦችን እኩል የማያዩ መንግሥታት ቁጥር አነስተኛ ነዉ፡፡

 

ጥንታዊዉ፣ በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ቀደምትና ጉልህ ታሪክ ከነበራቸዉ አንዱና፣ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ነፃነቱን ጠብቆ የቆየዉ፣ የካፋ መንግሥትና ሥርዓቱ በወታደራዊ ድርጅትና በመሣሪያ ኃይል ተበልጦ በ1889 ዓ ም ህልውናወን አጥቷል:: ይህ እልህ አስጨራሽና አዉዳሚ ጦርነት፣ ቀጥሎም፣ ንጉሱና ቅርሶቹ ተማርከዉ ወደ አዲስ አበባ ሲወሰዱ፣ ከዚያ በሁዋላ በካፋ ላይ የተፈራረቁበት ገዢዎችም ሃብቱን ዘረፉ፣ ነፃነቱን፣ ስብዕናዉንና ክብሩን በሙሉ አጠፉት፡፡ ካፋ፣ ከሌሎች ህዝቦች፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተገልሎ፣ ማህበራዊ እና እኮኖሚያዊ ልማትም ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የራሱን የውስጥ ጉዳይ ጭምር በራሱ ለማስተዳደር እንዳይችል፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚመደቡ ሹመኞች እየተገዛ፣ ሲገብር ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ አሳልፏል፡፡ ሹመኞቹም የመንግሥት ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን፣ መሬቱን፣ሕዝቡንከቀዬዉ በማፈናቀልና፣ እንዲሰደድ አድርገዉ፣ በቦታዉ ሰፋሪ በማስፈር፣ ሀብቱንና ንብረቱን በመቆጣጠር፣ ህልዉናዉን አጠፉት፡፡

 

የካፋ ህዝብ ህልዉናዉን ለማስጠበቅ ጥረት ከማድረገ የተዘናጋበት ጊዜ ባይኖርም በአብዛኛዉ የተሳካ አልነበረም፡፡ ከወረራዉ በሁዋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት፣ በሌላ ንግሥ አማካይነት ካፋን መልሶ ለማቋቋም፣ ዘዉዱንና ቅርሶችን ወደ ካፋ ለመመለስ ጥረት ተደሮ አልተሳካም፡፡ ይልቁንም፣ ይህ ሙከራ አፄ ምኒልክንም፣ ሆነ ተከታታይ ገዢዎች፣ የበለጠ አፋኝ እንዲሆኑ አደረገ፡፡ በመሆኑም ቅርሶቹን ወደ አዉሮፓ ከመላክ ጀምሮ፣ ስለካፋ ታሪክ የተፃፉ መፅሐፍት እንኳን ከዉጭ እንዳይገቡ በመከልከል ማንነቱ እንዲረሳ ተደረገ፡፡ የህዝቡን እንቅስቀሴም በሰፋሪዎችና በነጭ-ለባሾች አማካይነት በአይነ ቁራኛ በመከታተል፣ የተለየ የመሬት ሥሪትና፣ አፋኝ አገዛዝ በመመስረት፣ ህዝቡ መልሶ እንዳይቆም አደረጉ፡፡ የካፋን ሥርዓት፣ ብልፅግናና ለዚህ ሲባል ስለተካሄደዉ ጦርነትም ሆነ ስለደረሰዉ ተከታታይና ሰፊ ግፍና አፈና በዚህ ፅሑፍ ለዝርዝር አይቻልም፡፡

 

ሆኖም ህዝቡ ጥረቱን ያቆመበት ጊዜ እንዳልነበረና፣ አፈናዉም እንደቀጠለ፣ ዉጤቱም እንደቀጠለ መጠቆም ተገቢ ይሆናል፡፡ ዓላማዉ ከላይ ከተጠቀሰዉ የዓለም ታሪክ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ደግሞ ህልዉናዉን ማሳጣት፣ የፅሑፉም ርዕሥ ይኸዉ በመሆኑ ታሪኩን በአጭሩ ማቅረብ ተገቢ ነዉ፡፡ ከ1889 ጀምሮ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ በነበረዉ 43 ዓመታት፣ ካፋ ለማዕከላዊዉ የኢትዮጵያ ን/ነ/ መንግሥት ተጠሪ ከነበሩት 12 ግዛቶች አንዱ ነበር፡፡ በ1933 ዓ ም ግን፣ ካፋ በጅማ ጠቅላይ ግዛት ሥር አንድ አውራጃ እንዲሆን፣ ተወስኖሥያሜዉም ከታሪክ በመፋቁ ሌላ የመረረ ትግል ተነሳ፡፡ በመሆኑም በ1935 ዓ.ም. እንደገና ጠቅላይ ግዛቱ፣ ጅማ መባሉ ቀርቶ፣ ከፋ ጠ/ግዛት እንዲባል፣ ዋና ከተማዉ ግን ጅማ እንዲሆንና፣ ካፋ ደግሞ በጠ/ግዘቱ ከተዋቁ ስድስት አዉራጃዎች አንዱ ሆነ ካፋ አዉራጃ እንዲባል ተወስኗል፡፡

 

በወታደራዊ መንግሥት መመጀመሪያም፣ ምሁራን ተጠራርተዉ ወደ ካፋ ገብተዉ አካባቢያቸዉን ለማልማትና፣ ህዝቡን ለማንቃት ቢሞክሩም፣ በንጉሳዊዉ ዘመን በተደራጀዉ ጥንስስ የስለላና የአፈና መዋቅር ቅሪቶች ሴራ፣ “የካፋ ነፃ አዉጪ ተመሰረተ፣ ካፋ ከኤርትራ ቀጥሎ ነፃ ሊሆን ነዉ” የሚል ዜና ለደርግ በመድረሱ፣ ከዚህ በሁዋላ ሁሉም ነገር ህቡእ ሆነ፡፡ ይህ የረጅም ዘመናት የነጭ ለባሽና፣ የአፈና መዋቅርና ቀጣይ ተፅዕኖዉ ዛሬም በሥራ ላይ አለመሆኑን በአሳማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

 

በወታደራሪዉ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት፣ በብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ጥናት መሰረት፣ በመልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር፣ ኢኮኖሚዊ ትስስር፣ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና፣ ሥነ-ልቦና መቀራረብ መሰረት፣ የካፋ አስተዳደር አካባቢ የተመሰረተ ሲሆን፣ በኢህአዴግም የሽግግር ወቅትም ቀጥሎ ነበር፡፡ ደርግ መርሁ እኩልነትና አንድነት ቢሆንም ዉስጥ ለዉሥጥ ግን የተለመደዉ ጫና እንደነበረ፣ በወቅቱ የተሳተፉ ይናገራሉ፡፡

 

ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ተረጋግቶ በራሱ ቅኝት በአካባቢዉ ካድሬዎቹን ካዘጋጀ፣ በሁዋላ የራሱን ካድሬዎችም ሆነ፣ በደቡብ የተመሰረቱ ተቃዋሚዎችን አደናግሮ ወደ አንድነት በማጠቃለል፣ ክልሉን ጨፍልቆ በደቡብ ሥር አደረገ፡፡ በዚህም ካፋ እና አጎራባች ህዝቦች ከሺህ ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘዉ ደቡብን ተቀላቀሉ፣ አዋሳንም ተላመዱት፡፡ ይህ ካፋንና አጎራባች አካባቢዎች፣ በደቡብ ሥር የመጠቅለል ሴራ፣ ለቀጣዩ አፈናና ዝርፊያ ዝግጅት መሆኑ አሁን ግልፅ ሆኗል፡፡

 

ካፋም ሆነ አጎራባች ህዝቦች፣ ከአዋሳ ካላቸዉ ርቀትም በላይ፣ በዕድገት ደረጃቸዉና በሌሎች ብዙ ጉዳዮች የተነሳ በደቡብ ክልል ሥር ሆነዉ፣ የሚመጥናቸዉንና የሚስማማቸዉን እንዳያስቡ፣ የራሳቸዉን ፖሊሲና አመራር እንዳያቋቁሙ፣ የደቡብ ክልል አንድ አካል የመሆን መንፈስ፣ አስተሳሰብና ትዕዛዝ ፈፃሚዎች ተደርገዉ፡ ለክልሉ ባለሥልጣናት አጎብድደዉ፣ ተለማምጠዉ ማደርን ተላመዱት፡፡ ህዝቡና አካባቢዉም ከነበረበት ወደ ባሰ ደረጃ ቆርቁዞ፣ ገዢዎችም እንዳለሙት የአካባቢዉንና የአገርን ሃብት መዝረፍ ቀጠሉ፡፡ ይህ ሁሉ የተፈፀመዉ፣ አካባቢዉን በደቡብ ክልል ሥር በማድረግ፣ ለራሱ የሚመጥን ፖሊሲና ህግ ስትራቴጂና ደንብ እንዳያወጣ፣ የደቡብ ተገዢ፣ ታዛዥና ፖሊሲ ፈፃሚ፣ በማድረግ፣ ለዚህም ጥቂት ምስለኔዎችን በማዕከል፣ በክልልና በየደረጃዉ ከፍተኛ ሥልጣንና ጥቅም በመስጠት፣ ህዝቡንና ሃብቱን በመቆጣጠር ነዉ፡፡ ህዝቡ በደቡብ ሥር በመሆኑ አሁንም ሰቆቃዉ ቀጥሏል፡፡

 

ይህንን ጫና መሸከም የከበደዉ ህዝብ፣ ባገኘዉ የመጀመሪዉ መድረክ፣ ለአፈ-ጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል የክልል ጥያቄን ጨምሮ፣ የደረሰበትን በደል በምሬት አቅርቧል፡፡ አፈ- ጉባኤዋ ግን፣ በደቡብ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ “የምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ የጥቂቶች እንጂ መሰረት የሌለዉ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እዉነቱ ግን የካፋና የሌሎች የምዕራብ ዞኖች የክልልና ራስን የማስተዳደር ጥያቄ፣ የጥቂቶች ጉዳይ ሳይሆን፣ ታሪካዊና አሳማኝ ተጨባጭ መሰረት ያለዉ፣ በሁሉም አዕምሮ ሲጉላላ የነበረ ነዉ፡፡ ካፋ አስከ ዛሬም ከአገሪቱ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ልማት፣ከፖለቲካም መገለሉ በመቀጠሉ፣ የዛሬዉ ትዉልድ ወቅቱን የሚመጥኑ ጥያቄዎች ማቅረብና፣ የህዝቡን መብቶች በህጋዊ መንገድ ማስከበር ተራዉ ይሆናል፡፡ መንግሥትም እንደሌሎች የሰለጠኑ ሥርዓቶች ተገቢዉን ምላሽ በመስጠት፣ የጋራ አገሩን በእኩልነት እንዲያለማ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

 

II. በደቡብ ክልል ሥር በመሆን ገዢዎች የተጠቀሙትና ህዝቡ የደረሰበት ጉዳት::

 

ልክ ካፋ ራሱን የማስተዳደር መብት በማጣቱ የደረሰበት ጉዳት፣ አሁንም በደቡብ ክልል ሥር በመሆኑ የተነሳ ገዢዎች እንዳቀዱት ከፍተኛ የሃብት ዘረፋ ሲያደርጉ፣ አካባቢዉም ሊያገኝ የሚገባዉ በርካታ ጥቅም መቅረቱ ቀጥሏል፡፡ ይህንን ጉዳትና፣ ገዢዎቹ ያቀዱትና ተግባራዊ ያደረጉትን ሁሉ፣ ለማካካስ ዘመናትን የሚፈልግ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ብቻ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡

 

II.1. የራስን አስተዳዳሪ አለመምረጥና አለመቆጣጠር፣ በምስለኔዎች መገዛት፡፡

 

​​የካፋ ህዝብ መሪዎቹን የመምርጥ፤ የመገምገም፤ የመቆጣተር፣ የመገሰፅ፤ ብሎም የማዉረድና፣ በአጠቃላይ ራሱን በራሱ የመምራት የደረጀ የረጅም ዘመናት ልምድና ባህል ባለቤት የነበረ መሆኑን ሁሉም ያዉቃል። ንጉሥ እስከማዉረድ የሚችል በጠቅላይ ምኒስተር የሚመራ የተለያ ዘርፎችን የሚመራ ምኒስትሮች ምክር ቤት (ምክረቾ) የሚመራ ሥርዓት ነበረዉ፡፡ በአገር መከላከል ጊዜ ወታደር ከማንቀሳቀስና ማስተባበር፣ በምክር ቤት አባል የሚመራ የመንገድና ድልድይ ሥራ ካልሆነ በስተቀር በክልላቸዉ ግብር የሚሰበስቡ፣ ወሳኝ የክፍለ ሃገር ገዢዎች፣ በየደረጃዉም የራሳቸዉ ሃላፊነት ያላቸዉ ባለሥልጣናት የሚታደደር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ላለፈዉ ምዕተ-ዓመትና፣ እየባሰ ሲመታም ላለፉት 27 ዓመታትም፣ በአብዛኛዉ የአካባቢና የወረዳ አስተዳደሪ መርጦም ሆነ አዉርዶ አያዉቅም፡፡

 

የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች በክልል ባለስልጣናት ሲሾሙ፣ ሌሎችም ሃላፊዎች በክልልና፣ የክልሉ ምስለኔ በሆኑ ፈላጭ ቆራች ገዢዎች ሲመደቡና፣ ህዝቡ በማያዉቀዉ ምክንያት ከኃላፊነት ሲወገዱ፣ የህዝብ አቤቱታ የበዛባቸዉ ደግሞ ዕድገት ሲሰጣቸዉ፣ በየቀበሌዉም ሥራ አሥኪያጅ የሚባሉ የመንግሥት ደሞዝተኞች ሳይቀሩ በሃላፊዎች ሲመደቡበት ሰላማዊ ታዛዥና ተገዢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ መነሻ የባለስልጣናቱ ተግባር፣ የሚመድቡአቸዉንና የሚያወርዱአቸዉን የክልል ኃላፊዎችና፣ ምስለኔዎቻቸዉን ማስደስት፣ ትዕዛዝ ማስፈፀምና መፈፀም ላይ በማተኮሩ፣ ከህዝቡ የራቁና የማይታወቁ ናቸዉ፡፡ አብዛኛዎቹም ራሳቸዉ ጨቋኝ፣ አስኪወርዱ ሃበት ማግበስበስ፣ የተጠሉ ቢሆኑም ከአለቆቻቸዉ በስተቀር ማንም አይጠይቃቸዉም፡፡ ህዝቡ በብቃታቸዉ የተሻሉትንና የሚያምንባቸዉን አስተዳዳሪዎች የሚመርጥበት ዴሞክራሲያዊ መብቱን ከተቀማ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በአካባቢዉ በሁሉም ደረጃ፣ የህዝቡን ጉዳዮች የሚወስነዉ የማይመለከተዉ የደቡብ ባለስልጣን ሲሆን፣ የሚተላለፈዉን ዉሳኔዎችም፣ በየደረጃዉ ያሉ ሃላፊዎች ቢፈልጉም ባይፈልጉም ተቀብለዉ መፈጸምና ማስፈጸም አለባቸዉ፡፡ ምክንያቱም የሚያስቀምጣቸዉም ሆነ የሚያነሳቸዉ የደቡብ ባለስልጣን እንጂ፣ የሚመለከተዉ የአካባቢዉ ህዝብ አይደለም ፡፡ ይህም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ሁኔታዎች ለማመቻቸት ወሳኙ ሂደት በመሆኑ በገዢዎቻችን ታስቦበት የተደረገ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

 

II.2. ከአካባቢዉ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና ደንብ ማዉጣትና፣ መልማት ያለመቻል፡፡

 

በህጉ መሰረት ማዕከላዊ መንግሥት ያወጣዉን ህግና ፖሊሲ፣ የክልል መንግሥት ወደራሱ ሁኔታ አጣጥሞ፣ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በታች ያሉት መዋቅሮች ሁሉ ፈፃሚና አስፈፃሚ ብቻ ናቸዉ፡፡ በደቡብ ክልል የምዕራብ ዞኖችን ባላማከለ መልኩ ማዕከሉ አዋሳ በመደረጉ፣ ክልሉ ደግሞ ፖሊሲዎችና ደንቦችን የሚያወጣዉ፣ ከማዕከሉ በቅርበት ያሉ፣ አብዛኛዉን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ባለሥልጣናትና ተወካዮቻቸዉ የመጡበትን፣ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ ማዕከላዊ የደቡብ አካባቢዎች ታሳቢ አድርጎ ነዉ፡፡ የምዕራብ ዞኖች ተግባር ደግሞ የራሳቸዉን የአስተዳደር ልምድ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ ሀብትና፣ የኢኮኖሚ መሠረት፣ ማህበረ-ኤኮኖሚያዊ መስተጋብር፣ ስነ-ልቦና፣ ታሪክና የደረሰባቸዉን ጭቆና፤ ዉጤቱንና፣ የዕድገት ደረጃቸዉን ታሳቢ ያላደረገ፣ በኮታና በጫና የሚመደብ ዕቅድ መፈፀም ነዉ፡፡ ለምሳሌ፡-የክልሉ የማዳበሪያ አጠቃቀም ፖሊሲና ሥርዓት የምዕራብ ዞኖችን አፈር፣ ለምነትና የማዳበሪያ ፍላጎት ከግመት የማያስገባ፣ በኮታ፣ በግዴታ የሚታደል፣ ዕዳዉም የህዝቡን ጥሪት በግዳጅ በማሸጥ የሚከፈል፣ የድህነት ምንጭ ሆኗል፡፡

 

ህዝቡን ሳያማክሩ በመሬቱ በተደረገ ሰፈራ የመስፋፊ መሬቱ ሲወረስ፣ በተመሳሳይ ፖሊሲ ወደሰፈራ የተጓዙ የዞኖቹ ተወላጆች የሰፈሩበት ቦታ ግን፣ መሰረተ-ልማት ያልተማላበት፣ ይልቁንም የፀጥታ ችግር ባለባቸዉ አካባቢዎች በመሆኑ ለጥቃት ሲዳረጉ፣ ቦታዉን እየለቀቁ ተመልሰዉ ሥራ-ፈት፣ የቤተሰብ ጥገኛ ያደረገ ነዉ፡፡ ይባስ ተብሎ የህዝቡን የግጦሽ መሬትም ያሳጣ ነዉ፡፡ የአካባቢዉ ልማት፣ በደንና ደን ዉጤቶች፣ ከአፈሩና ባህሉ የተጣጣመ እርሻና እንስሳት እርባታ፣ ከዚህ ጋር የተገናኘ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና፣ኢኮ-ቱሪዝም መሆኑን ብዙዎች ይመክራሉ፡፡ ይህ ሊሆን ቢገባም፣ ምዕራብ ዞኖች ግን፣ የክልሉን ኮፒ እየፈፀሙ ባሉበት ቆመዋል፣ ወይም ወደ ሁዋላ እየተጓዙ ነዉ፡፡ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶችም በጥራትና፣ በጊዜ ባለመፈፀም፣ አንዳንዴም ጉዳት በማድረስ የታወቁ፤ ዝርፊያ፣ የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉድለት፣ ጌቶቹን ለማስደሰት በቆመ ባለሥልጣን የተሞላ ነዉ፡፡

 

II.3. የገዢዎችን ዓላማ ማሳካት፣ ጠያቂ የሌለዉ የመሬት ወረራ፣ የህዝብ ኑሮ መናጋትና፣ የተፈጥሮ ሃብት ዉድመት

 

የምዕራብ ዞኖች በደቡብ ክልል ሥር መዋቀር ዋናዉ ሚስጥር ግን፣ ራሱን ባለማስተዳደሩና፣ የራሱን ፖሊሲ ባለማዉጣቱ፣ የሃበቱን መሰረት በማጣቱ ተረጋግጧል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ልማትና ኢኮኖሚ የተመሰረተዉ በተፈጥሮ ሃብትና ተጓዳኝ ዘርፎች መሆኑ ከላይ ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢዉ በአጭር ጊዜ፣ ታይቶ በማያዉቅ ፍጥነት የመሬት ወረራ (Land Grabing) ተፈፅሟል፡፡ ይህም የተፈፀመዉ በዋናነት በገዚዎቻችን የቀድሞ የድርጅት አባላት ስም፣ ምንም ሃብት ባልነበራቸዉ የከተማ ሰዎች፣ በዘመዶቻቸዉና፣ በአጋሮቻቸዉ ስም ነዉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ መሃል ያሉት የደቡብ ገዢዎች በዘመዶቻቸዉ ተመሳሳይ አድርገዋል፡፡ በካፋ½ በቤንች ማጂና½ ሸካ ዞኖች በርካታ ተደፍረዉ የማያዉቁ ደኖች እየተከለሉ ሰፋፊ የቡና፣ ሻይና ሌሎች እርሻዎች በሚል ተዘርፈዋል፡፡ ይህ የሆነዉ በተጠናና በየደረጃዉ ለዚህና፣ ለሌላ አፈና ማስፈፀሚያ፣ ተመርጠዉ በየደረጃዉ በተቀመጡ ሹመኞችና፣ ቅጥረኞች አስፈፃሚነት ነዉ፡፡ ለዚህም ክልል ማጠፍና ህጋዊ ሥልጠን ማሳጣት፣ ባለሥልታናትንም በክልል የመመደብ ሥርኣት በመፍጠር ሁሉም ተመቻቸ፡፡ በዚህ የተቀናበረ፣ ወረራ፣ “ጥብቅ የደን ክልል” ተብለዉ፣ ማንም እንዳይደርስባቸዉ ተጠብቀዉ የቆዩ፣ በእድሜ-ጠገብ ዛፎች የተሞሉ ጥቅጥቅ ደኖች ያለገደብ ወደሙ፡፡

 

እነዚህ ግለሰቦች፣ በተቋማዊ ደረጃ ልዩ እንክብካቤና፣ ድጋፍተደርጎላቸዉ፣ ከባንኮች በመመሪያ፣ በመንግሥት ዋስትና ደግሞ ከዉጭ ባንኮች ብድር፣ ከቀረጥ ነፃ በርካታ ማሽኖችና፣ ተሽከርካሪዎች ተገዝተዋል፡፡ ብድሩን ለከተማ ኢንቨስትመንት ሲያዞሩት፣ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን አየር በአየር ሽጠዉ፣ መሬቶቹን በብዙ ሚሊዮን ብር ደጋግመዉ እየሸጡ ከምንም ተነስተዉ፣ እዉነተኛ ባለሃብት ሆነዋል፡፡ በዚህም ከደኑና፣ የተፈጥሮ ሃብቱ ዉድመት ሌላ፤ ህዝቡ ከደኑ ያገኝ የነበረዉ ጥቅምና በደን ላይ የተመሰረተዉ ኑሮዉ ተናጋ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሩቅ አካባቢያቸዉ ተራ ሰራተኛ አመጡ እንጂ ሥራ አልፈጠሩም፡፡ አንዳንዶቹም ከህግ በላይ ሆነዉ የሚያስሩበትና የሚያሰቃዩበት፣የራሳቸዉ እስር ቤት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ከዚህ ሌላ፣ በግፍና በአድሎአዊነት የወሰዱትን መሬት ካላሙት ይልቅ፣ እድሜ ጠገብ ዛፎችን ያለምንም ርህራሄና ይሉኝታ በመጨፍጨፍ፣ እስካሁንም እያጓጓዙ ያለዉ ግንድና፣ ጣዉላ የላቀ መሆኑ ነዉÝÝ አካባቢዉ ክልል ቢሆን ኖሮ፣ ተጠቃሚዉም አካባቢዉ ይሆን የነበር ሲሆን፣ ተግባሩም ህገ-ወጥ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሆነዉ፡- 1) በዉሉ መሰረት፣ በሥፍራዉ የሚገኝን የተፈጥሮ ሃብት ሁሉ መጠቀም የሚችለዉ የአካባቢዉ መንግሥት መሆኑ እታወቀ 2) በክልሉ የደን ህግ መሰረት፣ ዛፍ መቁረጥ ክልክል መሆኑ፣ ገበሬዉ እንኳን በጓሮዉ ተንከባክቦ ያሳደገዉን ዛፍ ቆርጦ ለመጠቀም የሚከለከል በሆነበት ሁኔታ ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ህዝቡ አቅም በማጣት፣ ባለሥልጣናቱ በጥቅም በመገዛትና፣ በማስፈራሪያ ነዉ፡፡

 

በመሰረቱ የአካባቢዉ ደን ዝም ብሎ ጫካ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ህዝቡ ወደ ዕምነት በሚጠጋ ትኩረትና ጥበቃ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ያቆየዉ፣ በባህልም፣ በቤተሰብና በቡድን ተከፋፍሎ፣ የሚጠብቀዉና የሚንከባከበዉ፣ የአየር ንብረት ጠባቂ ነዉ፡፡ ህዝቡ ለዘመናት የጫካ ቡና፣ ማር፣ ኮሮሪማ፣ ጥምዝና የመሳሰሉ የቅመማ ቅመም ምርት የሚያገኝበት nwu:: በዉስጡ ተዘርዝሮ የማያልቅ፣ ዕፅዋት፣ እንስሳትና፣ አዕዋፋት፣ ከምግብነት እስከ መዲሃኒትነት የሚያያገለግሉ የአገሪቱ የብዝሃ-ህይወት መሰረቶችም የያዘ ነዉ፡፡ ለአገሪቱና ለዓለም የአየር ንብረት ጥበቃ፤ በሽታን የሚቋቋም የቡና ዝሪያን ጨምሮ የበርካታ የብዝሀ-ህይወት መጠበቂያም ነዉ፡፡ ይህንን ሁሉ ይዞ፣አካባቢዉ፣ ባለቤት- አልባ፣ በራሱ ጉዳይ የማይወስን፣ በልማትም ሁዋላ-ቀር ሲሆን የራሱ ገዢ ባለመሆኑ የተፈጥረ ነዉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግባር በካፋና ሌሎች ምእራባዊ ዞኖች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ታዳጊ አካባቢዎች እንደተፈፀመ የሚታወቅ፣ የመንግሥት የቤት ሥራ ነዉ፡፡

 

II.4. ከኋላ ቀርነቱ ጋር ተመጣጣኝ ትኩረትና ድጋፍ ያለማግኘት፡፡

 

አካባቢዉ በአንፃራዊነት ከለማዉ የደቡብ ክልል ሥር በመሆኑ፣ከማዕከላዊ መንግሥትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለታዳጊ አከባቢዎች የሚደረገዉ ድጋፍ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ በደቡብ ክልልም በጋራ በጀት የአስፋልት መንገዶች፣ ስታዲየሞች፣ ቢሮዎችና ሌሎች ህንፃዎች፣ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ኮንዶሚኒየም፣ አዳራሾችና ሌሎች ተቋማት በማዕከላዊ ከተሞች ሲገነቡ፣ ለምዕራቡ ዞኖች ግን ከማዕከልም ሆነ ከክልሉ አንድም ድጋፍ አልተደረገም፡፡ ቢሆንማ፣ አካባቢዉና ህዝቡ፣ ታሪኩና ማንነቱ የጠፋ፣ ስነ-ልቡናዊ፤ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ዉድመት ለዘመናት የደረሰበት በመሆኑ ልዩ ጥኩረት በተሰጠዉ ነበር፡፡ አካባቢዉ በክልል ደረጃ ቢዋቀር ኖሮ ይህ ሁሉ አይሆንም ነበር፡፡

II.5. የመንግስትና የግለሰቦች ሃብት በጉዞ ማለቅ፣ ተጉዞም መፍትሄ አለማግኘት፡፡

 

ከሁዋላ ቀርነቱና፣ ከርቀቱ የተነሳ በበጀት ሊደጎም ሲገባዉ፣ የሚመደበዉ ትንሽ በጀት ወደ ኣዋሳ ለሚደረገዉ ምልልስ በአበል፤ በነዳጅና በመኪና ጥገና በማለቁ ዋናዉን የልማት ክፍተት ከማስፋቱም በላይ በወቅታዊና አዳዲስ ፍላጎቶች ጭምር አካባቢዉ የባሰ ወደሚባል ደረጃ እየተንሸራተተ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ አዋሳና ሌሎች ለስብሰባ ወደሚመቹ ከተሞች በሚደረግ ጉዞ የተነሳ፣ ባለስልጣናት በስራ ቦታቸው ባለመገኘታቸዉና ዉሳኔ ስለማይሰጡ፣ በዞኖቹም ዉስጥ ቢሆን ጉዳይ ማስፈፀም አልተቻለም፡፡ በዚህም አቤቱታዎች ለወራት ባለሥልጣን እየጠበቀ ሲቆዩ፣ ማህበረሰቡ በልማትና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት አየቃተተ ይገኛል፡፡ ከቢሮ ርቀዉ ስለሚቆዩም፣ ባለሥልጣናቱ ከደራሽ ሥራ በስተቀር በዕቅድ የማይመሩ፣ ጉዳያቸዉ ከክልል የተሰጠ ኮታ መተግበር ሆነ፡፡ህዝቡም ለፍትህ፣ ለንግድ ፈቃድ፣ ለግብር ጉዳዮች ወደ ክልሉ ማዕከል ሲሄዱ ብዙ ዕንግልትና ወጪ ይደርስባቸዋል፡፡ በነዚህ ጉዞዎች ዕንግልት፣ ገንዘብ፤ ጊዜ፤ አካላዊ ድካም፣ ማህበረሰቡን ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡

 

በዚህም የተነሳ አካባቢያቸዉን ለማልማት የመጡ ምሁራንና አሁን ደግሞ፣ ሲታትሩ የነበሩ ነጋዴዎች ዞኖቹን እየጣሉ መሄድ ጀምረዋል፡፡ ሌላዉ በክልሉ ቢሮዎች ጉዳዮች ለማስፈፀም፣ ባለጉዳዩ ከመጣበት አካባቢ የወጣ ሃላፊ ወይም ባለሙያ ከሌለ፣ በግልፅ በተቀመጠ መመሪያ መሰረት እንኳን ጉዳይ ማስፈፀም ሰሊሚከብድ ሌላዉ ህዝቡን ለምሬት የዳረገ ጉዳይ ሆኗል፡:

 

II.6. በየደረጃዉ ዉክልናና ተከራከሪ ማጣት፡፡

 

አጠቃላይ መዘንጋት፣ ተደማጭነትና ትኩረትና፣ ዉክልና ማጣት የመዋጡ አንዱ ዉጤት ነዉ፡፡ በክልሉ ምሥረታ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት፣ ጥቂት ንቁ ተወካዮች ከአካባቢዉ ተወክለዉ ነበር፡፡ እነዚህ በጊዜዉ ተመልምለዉ ወደ ክልል ሥልጣን የገቡ ሰዎች፣ ባደረጉት ጥረት ጥቂት ጭላንጭል ታይቶ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን ይህ ሁሉ ቀርቷል፡፡ ክልሉ፣ ምዕራባዊ ዞኖችን እንደክልሉ አካል አለማየቱን፣ አካባቢዉም ተከራካሪና፣ ባለቤት የሌለዉ መሆኑን ለማሳየት አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይጠቅማል፡፡ ይኸዉም የኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር ፅ/ቤትና ቀርቦ በመንግሥት በተወሰነዉ መሰረት፣ ካፋና ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኑን ዕዉቅና የሰጠ ዉሳኔ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በ1999 ዓ.ም. በፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መሰረቱ ተጥሎ ቦንጋ ላይ፣ ብሄራዊ የቡና መዚየም ግንባታ ተጀምሮ ዓመታት ፈጅቶ ነበር፡፡

 

የሚሊኒየም ፅ/ቤቱ ስለተዘጋና በጀቱም ስላለቀ፣ ግራ የገባቸዉ የዞኑ ባለሥልጣናት እንደተለመደዉ አፈ-ሙዛቸዉን ወደ ዞኑ ህዝብ አዙረዉ ገቢ በማሰባሰብ፣ ሲጨርሱት፣ የክልሉ መንግሥት ግን አንዲትም ሳንቲም አስተዋፅኦ አላደረገም፡፡ ይባስ ብሎ ግንባታዉ ሲጠናቀቅ የክልሉ ገዢ ድርጅት ሊ/መንበርና የወቅቱ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ሃይለማሪያም መርቀዉ፣ በዚያዉም የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዉ ቢመለሱም፣ በመጨረሻም ሥራ ባለመጀመሩ፣ ህንፃዉ ሲፈራርስ ፌደራል መንግሥትም፣ ሆነ ክልሉ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ይልቁንም የክልሉ ሃላፊዎች “የታሪክ ሽሚያ አለ፣ የፌደራል አካላት መልስ አልሰጡም፣ ወዘተ” እያሉ ጉዳዩ እንደማይመለከታቸዉ በተደጋጋሚ በክልል ም/ቤት ስብሰባ ጭምር የለበጣ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡም የማዕካለዊ መንግሥት አንድ ሃላፊ በሃገሪቱ ቲሌቪዥን ቀርቦ ከእዉነታዉ ዉጪ በዞኑ ተነሳሽነት የተሰራ ነዉ ብሎ አረፈዉ፡፡

 

በአጠቃላይ አካባቢዉና ህዝቡ እንደሌላዉ የኢትዮጵያ ያልተወከለ፣ የተዘነጋ፣ ተከራካሪ የሌለዉ፣ ከልማትና ከዲሞክራሲ የተገለለ፣ ለሀገር ግንባታ ሊያበረክት የሚችለዉን ዕድል የተነፈገ ነዉ። ሁሉም በክልል ይሁንታና ዝንባሌ የሚወሰን፣ በእርዳታና በማዕከላዊ መንግሥት የሚላኩ ቴክኖሎጂዎችና ፕሮጀክቶች ሁሉ ወደ ማዕከላዋዊዉ የክልሉ አካባቢዎች ያደላበት፣ በመሆኑ ምዕራቡ የተገለለ፣ በሁሉም አመልካች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሆነ። ብዙ ሊጠቀሱ የሚገባቸዉ የአካባቢዉ የመዘንጋትና የኋሊት ጉዞን የሚያሳዩ ምሳሌዎች አሉ፡፡ እንኳን አዲስ ድጋፍ ይቅርና፣ ለምሳሌ ቦንጋ ዉስጥ፣ በአገሪቱ ከመጀመሪያዎቹ ኤክስፖት ካምፓኒዎች የነበረዉ የቡና ፕሮሰሲንግና ኤክስፖት ካምፓኒ ተመስርቶ የነበረበና በሂደት የጠፋበትን፤ በ1920 ዓ ም ቦንጋ ዉስጥ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል የነበረበትንና አሁን ግን የተዘጋበትን ሁኔታ ጨምሮ በሂደት የከሰሙና የአካባቢዉን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩ በርካታ ጉዳዮችን በዝርዝርና በመረጃ ማስድግፍ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ በራሱ የሚወስን የህዝቡ ክልል ቢኖር አይደረግም ነበር፡፡

 

II.7. ባህልና ቋንቋ ማጎልበትና ማሳደግ አለመቻል፡፡

 

አካባቢዉ የበርካታ ነባር ብሄር፣ በሄረ ሰቦችና አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ብሄረሰቦች የሚገኙበት ነዉ፡፡ ህዝቡ ቋንቋዉንና ባህሉን እንዲዘነጋና ማንነቱ እንዳይታወቅ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ጫና ነበረበት፡፡ ባህሉ በተቀናጀና በተቀነባበረ ሁኔታ እንዲጠፋ ብዙ ተጥሯል፡፡ የህዝቡ ቅርሶች ወደባህር ማዶ ጭምር ተወስደዉ ተሰዉረዋል፡፡ ቋሚ መረጃ ሊሆኑ የሚችሉት ንጉሳዊ ቤተ መንግስት፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፤ የጥበብ መሠረቶች እንዲወድሙ ተደርጓል፡፡ የአሁኑ ትዉልድ እነዚህን ሁሉ አያዉቅም፡፡ በአካባቢዉ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦችና ቅርሶችና፣ የኢኮ- ቱሪዝም ሃብቶች ቢኖሩም፣ በመጠኑም ቢሆን የሚያስተዋዉቁት አገር አቀፍ ሚዲያና፣ የዉጭ ዜጎች እንጂ የክልል ሚዲያ አይደለም፡፡ ባህልና ታሪክ ለማሳደግና ለማዳበር፣ የተደረጉ ጅማሮዎች በባለሥልጣናት፣ በረቀቀ መንገድ እንዲቆም፣ እንዲዛቡና፣ እንዲዳፈን ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡና በተለይም አዲሱ ትዉልድ ባህሉን ታሪኩንና ማንነቱን እንዲያዉቅና ስነ-ልቦናዉ እንዳያንሰራራ በርካታ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ መፅሐፍትና፣ የባህል ሥራ ዉቴቶችን ከማደናቀፍ ጀመር ለምሳሌ በካፋ ዞን ዋና ከተማ በፕሬዝዳንት ነጋሦ ጊዳዳ የመሰረት ድነጋይ የተጣለለት፣ የሠማዕታት ኃዉልትና፣ የባህል ሙዝየም እነዲዳፈን የተደረገበት ይጠቀሳል፡፡ በአጠቃላይ የአካባቢዉን ህዝብ በርካታ ዝክረ-ታሪኮችና ዉጥኖችን በማደብዘዝና በማደናቀፍ፣ የሥነ-ልቦና ዘመቻ ተደርጓል፡፡

 

III. የአፈናዉ ማስፈፀሚያ ሥልት

 

በቀደሙት ዘመናት በተከታታይ በመጡ መንግሥታት የተፈፀሙ የአፈና፣ የዘረፋ ሥልቶችና ዉጤቶች ለመዘርዘር ራሱን የቻለ አጋጣሚና መድረክ የሚየስፈልግ ሲሆን ወቅታዊዉ ጉዳይ ላይ ማተከሩ፣ አሁን ያለዉን ስለሚገልፅና ወደ ወቅታዊ መፍትሄ ለማምራት ስለሚረዳ ካፋ በደቡብ ሥር ከወደቀ በሁዋላ ተግባራዊ እየሆነ ያለዉን የአፈናዉና ዘረፋ ሥልት በአጭሩ መጥቀስ ጠቃኒ ነዉ፡፡ ሥልቱ በአጭሩ ይህ ነዉ፡፡

III.1. በምስለኔ መግዛት፤ ሁሉንም አፈና የሚያቀናብሩት በሴረኝነታቸዉና ብቃታቸዉ ከየዞኑ የተመረጡ፣ ለክልሉና ለዋናዎቹ አለቆቻቸዉ እንደተፈለገዉ የሚታዘዙና፣

እነርሱም በተራቸዉ በየዞኑ ህዝባ ላይ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ እነዚህ በክልል ወይም በማዕከል፣ ከፍተኛ ቦታና ጥቅም ተስጥቷቸዉ በየመጡበት አካባቢ ላይ ባለሙሉ ሥልጣን፣ ተቆጣጠሪና፣ ገዢ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ተግባራቸዉ የአለቆቻቸዉን ትዕዛዝ መፈፀምና ሃብት ማካበት ብቻ ነዉ፡፡

 

III.2. በየደረጃዉ ታዛዥና ታማኝ አስፈፃሚዎች መመደብ፤ ከላይ በተጠቀሱት ምስለኔዎ መሪነትና እዉቀት በየደረጃዉ፣ ተመሳሳይ ሚናና ጥቅማ ጥቅም

የሚሰጣቸዉ አስፈፃሚዎች ይመደባሉ፡፡ እነዚህ ወደ ህዝቡ በቀረበ እርከን ላይ የሚመደቡ ሰዎች፣ የህዝቡን ስሜት መከታተልና ማፈን፣ ለገዢዎቻቸዉ ሁሉንም ማመቻቸትና ማስፈፀምና መፈፀም ሆኖ ቆይቷል፡፡ አልፎ አልፎ ህሊናቸዉ የቆረቆራቸዉ ተሿሚዎች ቢኖሩ እንኳን፣ ለራሳቸዉ ስለሚሰጉ ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ የሚሰታቸዉን ትዕዛዝ ላለመፈፀም ያንገራገሩ ወይም ያፈነገጡ ሲያጋጥሙ ምክንያት ተፈልጎ፣ ምክንያት ከቦታዉ ገለል ይደረጋሉ፣ ወይም ወደ እሥር ቤት Yወረወራሉ፡፡ በመሰረቱ ከእንደዚህ ዓይነቶቹ በስተቀር፣ ኢህአዴግ የሚመለምላቸዉ አብዛኛዎቹ ፣ ሆነ ብሎ ለዚህ የተመቹ ነበሩ፡፡ ጥቂቶችም በጊዜ ገብቷቸዉ ከመድረክ ሲጠፉ፣ ሌሎቹ ፀባቸያዉን አሳምረዉ መስለዉ ማደር ይቀጥላሉ ፡፡

 

III.3. አጠራጣሪ ካድሬዎች፣ ወደ መድረክ እንዳይመጡ ማድረግ፤

 

አንዱ ሥልት ደግሞ ገዢዎች የሚፈልጉትን ጉዳይ በቀላሉ፣ በሥልክ ትዕዛዝ ብቻ ጭምር

ለመፈፀም የማይመቹ አባላት እየታዩ ይወገዳሉ፡፡

አልፎ አልፎ ተመድበዉ ከነበሩትም፣ መጠየቅና፣ መከራከር የጀምሩት በፍጥነት ይወገዳሉ፡፡ በዋናነት ግን ከመጀመሪያዉ ለአካባቢዉ መብትና ጥቅም ተቆርቋሪና፣ ተወዳጅ የሆኑ ካድሬዎች ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ ይደረጋል፡፡ በስህተት ሚስጥር ያወቁ ካሉም ተሸማቅቀዉ ጥጋቸዉን ይዘዉ ዝም እንዲሉ፣ የዉስጡን ሥርዓትና አሰራር ስለሚያዉቁም፣ አፋቸዉን ዘግተዉ፣ ራሳቸዉን ያገላሉ፣ ክትትልም ይደረግባቸዋል፣ አሊም በርግገዉ እንዲጠፉ ሴራ ይነደፋል፡፡

 

III.4. ንቁ ወጣቶችና ምሁራንን አስበርግጎ ማባረር፤

 

ሌላዉ የማስፈፀሚያ መንገድ ወጣት ምሩቃንን አስበርግጎ መባረር ነዉ፡፡ ሁሉም ዜጋ አካባቢዉን

ማገልገሉን የሚደግፍ መስሏቸዉ፣ ከኮሌጅ ሲመረቁ በጉጉትና በወኔ ወደ አካባቢያቸዉ የጎረፉትን ወጣቶች፣ መጀመሪያ ላለመቅጠር ማንገላታት፣ ከተቀጠሩም በየምክንያቱ ተስፋ በማስቆረጥ አካባቢዉን ለቀዉ እንዲሄዱ በማድረግ፣ በራሱ በአካባቢዉና በመንግሥት እንዳይተማመን በማድረግ ወገናዊነትና ብቃት ያለዉ፣ ጠያቂ ሰራተኛ እንዳይኖር ማድረግ መሰረታዊ ሥልት ነዉ፡፡ በዚህም የተነሳ በጉጉት ወደአካባቢዉ በመሄድ ሥራ ይዘዉ የነበሩ በርካታ ወጣት ምሩቃን መሃንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የሂሳብ ባላሙያዎች፣ የዉሃና የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያዎች፣ የኮምፒዩተርና ቴክኖሎጂ ባላሙያዎች፣ ተማርረዉ አካባቢዉን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ በዚህም፣ ወጣት ምሁራኑ፣ የሚከናወነዉን ዝርፊያና በደሎችን እያዩ ማለፍም ሆነ ታዘዉ ለመፈፀም ስለማይመቹ ይባረራሉ፡፡ ዘራፊዎቹና፣ ፍርፋሪ ለቃሚ አገልጋዮቹም እንደልብ፣ ያለ ብቁ ተመልካች፣ ያለተከራካሪና፣ ያለታዛቢ እንዲፈነጩ ተመቻችቷልÝÝ ከነዚህ ወጣት ምሁራን መካከል፣ ቁርጠኛ የሆኑ፣ ከሙያዊ አገልግሎት ባለፈ፣ የድርጅት አባል በመሆን ለዉጥ ለማምጣት ቢሞክሩም፣ ሙሰኞቹ በተለመደዉ ድርጅታዊና ቡድናዊ ሰንሰለት፣ ጠልፈዉ በመጣል፣ በመፈታተንና በማስጨነቅ እንደሌሎቹ ያባርራሉ፣ ወይም በማሸማቀቅ ዝም ያሰኛሉ፡፡

 

III.5. በአካባቢዉ የተወለዱ የሌላነት ስሜት ላቸዉ ጥቅመኞችን መጠቀም፤

 

ሌላዉ መንገድ በአካባቢዉ ተወልድዉ ያደጉ፣ ራሳቸዉን ባይተዋር አድርገዉና፣ ደብቀዉና ስሜታቸዉን ቀብረዉ የቆዩ፣ ወቅቱን የሚጠብቁትን ሰዎች መጠቀም ነዉ፡፡ እነዚህ ለግል ጥቅምና ዕድገት ሲሉ ራሳቸዉን ለክልሉ ገዢዎች አገልግሎት የመደቡ፣ በተለይም በቀጭን የደም ቆጠራ፣ የሌላ በሄረሰብ ደም እንዳላቸዉ የሚያምኑ አካባቢዉን የካዱ፣ ጥቂት ግለሰቦችን መጠቀም የተለመደ ነዉ፡፡ እነዚህ ስለአካባቢዉ ባላቸዉ እዉቀትና ባላቸዉ፣ ወይም በተደረገዉ ቅስቀሳ የሌላነት ስሜት የሰረፀባቸዉ ግለሰቦች በሚስጥር ተመዝዘዉ፣ የመረጃ ምንጭ በመሆንና፣ መስመር በመዘርጋት የገዢዎችን ተግባር ያገለግላሉ፡፡ ከነዚህ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ገዢዎች አካባበቀጥታ መቆጣጠር ችለዋል፡፡

 

III.6. ከአካባቢዎቹ ጋር በዝምድና የሚገናኙ በሌላ አካባቢ ያደጉት መጠቀም፤

 

ከወቅቱ የደቡብ ባለሥልጣናት ጋር ትዉዉቅና ቀረቤታ ያላቸዉና ከመሃል የደቡብ ክልል አካባቢዎች የተገኙ፣ ባላቸዉ ዝምድና ጭምር ስለአካባቢዉ የሚያዉቁ ግለሰቦችን በቁልፍ የሃላፊነትቦታ መመደብ ሌላዉ ሥልት ነዉ፡፡ እነዚህ ዘመድ ቢኖራቸዉም በአካባቢዉ ባለማደጋቸዉ ባይተዋር የሆኑ፣ በአካባቢዉ ማህረሰብ የማይታወቁ፣ ምናልባትም ሲመለመሉ ጀምሮ ባይተዋር እንዲሆኑ ተደርገዉ የተቀረፁ፣ ክትትልና ልዩ እንክብካቤ፣ የሚደረግላቸዉ ግለሰቦች ዋናዉ ተግባራቸዉና ትኩረታቸዉ ሁሉ እስከወዲያኛዉ አካባቢዉን መድፈቅ፣ ምሁራንን ማሳደድ፣ የአካባቢዉን ጥቃቅን ነጋዴዎችና ጀማሪ ባለሃብቶች ማቆርቆዝ፣ የአካባቢዉን የተፈጥሮ ሃብትም አሳልፎ መስጠትና ራሳቸዉ ቸብችበዉ ኢኮኖሚያቸዉን መገንባት ነዉ፡፡

III.7. ከሌላ አካባቢ ሰዉ መመደብ፤ የመጨረሻዉ መንገድ ከዚያዉ አካባቢ የሚመች ከጠፋ፣ ወይም በዉጪ ሰዉ ቢሰራ የሚሻል ጉዳይ ሲኖር ከደቡብ ማዕከላዊ አካባቢዎች ሃላፊዎችን አምጥቶ በግልፅም ሆነ በሥዉር መመደብ ከተጀመረ ሰነባበተ፡፡

 

የመጨረሻዉን ይህን አማራጭ ለመትግበር እንዲመች ጥያቄ እንዳይነሳ በመጀመሪያና በቅድሚያ፣ የአካባቢዉን ልጆች በማሸማቀቅ፣ በየአጋጣሚዉ “ጠባብ፣ ጎጠኛ ወዘተ” በሚባሉ አነጋገሮች ማዉገዝና የመስፈራራት ሥራ ይሰራል፡፡

 

ማጠቃለያ

 

የራስ አስተዳደር ማጣት ከመጀመሪያዉ እስከዛሬ ዉጤቱ፤ በገዢዎች ረገድ አንድ ዓላማ፣ (ሃብት መቆጣጠር)፣ በተገዢዎች ረገድ ደግሞ መታፈን፣ ሞትና ስደት፣ መደህየት፣ በራስ አለመተማመን፣ ባህል ቋንቋና ማንነትን ማጣት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ መግቢያዉ ላይ በአጭሩ የተነገሩ በደሎች በዝርዘር ቢቀርቡ፣ በጣም አስከፊና ቀስቃሽ እንደሚሆኑ ስለሚታወቅ አጠር ብሎ ቀርቧል፡፡ በአጠቃላይ ምስለኔዎችና ሁሉም አስፈፃሚ የገዢዎችን ትዕዛዝና ጉዳይ ከማስፈፀም ሌላ፣ በተራቸዉ ዓይን ባወጣ መልኩ፣ ሥልጣናቸዉና ሰንሰለታቸዉ በፈቀደዉ መሰረት ሰዎችን በየቦታዉ በመመደብ መረባቸዉን በማጠናከር ዝርፊያና አፈና ማድረግ ነዉ፡፡ ለነዚህ አስፈፃሚዎች ደግሞ ክልሉና የበላዮቻቸዉ ከላላና ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፡፡ ካፋ ራሱን ማስተዳደር እስኪጀምር፣ በኢትዮጵያ ዉሥጥ በአግባቡ የሚመራዉና የሚያስተዳድረዉ፣ ተጠሪነቱና፣ ተጠያቂነቱ ለራሱ ለህዝቡ የሆኑ፣ መሪዎቹን መምረጥ አይችልም፡፡ ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖሊስ፣ ስትራቴጂና ደንብ ማዉጣት፣ የአካባቢዉንና የአገር ሃብት መጠበቅ፣ ማልማትና መጠቀም፣ አብሮ ማደግና መበልፀግ፣ አይችልም፡፡ ራሱን አስተዳድሮ፣ እንደዜጋ እኩል መታየት፣ ሰብአዊ መብቱን ማስከበርና፣ እኩልነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ አስተዋፅኦና ተሳትፎ ማድረግ፣ ተከባብሮና ተማምኖ መኖር አይችልም፡፡ ለአገሪቱም ተገቢዉን ሚና መጫወትና፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ አንድ ጉልህ አካል ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡

 

አሁን በተደረሰበት ደረጃ ግን በአግባቡ ራሱን ማስተዳደር ካልቻለ፣ እየተካሄደ ያለዉን ዝርፊያና አፈናእያወቀ፣ ዝም ብሎ መቀጠል አይችልም፡፡ በመሆኑም አሁን የተጀመረዉ የህዝብ ጥያቄ ወደ አልተገባ አቅጣጫ እንዳያመራ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል፡፡ የካፋና ምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ፣ መሰረት የሌለዉ የጥቂቶች ጉዳይ አይይደለም፤ የቆየ ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ቀጣይ ሂደት፣ በታሪካዊ መሰረት የተደገፈ፣ አሳማኝና ተጨባጭ መሰረት ያለዉ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ካፋ አስከ ዛሬም ድረስ ከማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ልማት፣ እንዲሁም ከፖለቲካ መገለሉ በመቀጠሉ፣ የዛሬዉ ትዉልድና መንግሥት ወቅቱን የሚመጥን፣ መፍትሄ በመስጠት የህዝቡን መብቶች፣ ጥቅምና ክብር በህጋዊ መንገድ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

ከG.C.

ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: