Leave a comment

ጋኪ ሻሮቺ በካፋ ህዝብ አጅግ አዘኑ የተከበረዉን የዙፋን ቀለበታቸዉን በጎጀብ ወንዝ ወረወሩ::


ጋኪ ሻሮቺ በካፋ ህዝብ አጅግ አዘኑ የተከበረዉን የዙፋን ቀለበታቸዉን በጎጀብ ወንዝ ወረወሩ።

ከአኔ ጭምር ሁላችንም የካፋ ልጆች ስለጋኪ ሻሮቺ ማውራት የምንፈልገዉ ስለ አርሳቸዉ ጀግንነትና ማንነት ስለብልህና አስተዋይ መሪነታቸዉ፣ ለሶስተኛ ጊዜ በተቃጣ በምኒሊክ ወረራ እስኪሸነፉ ድረስ ሁለቴ የሚንልክን ጦር መክተዉ የመለሱ ጀግና መሪ አንደነበሩ፣ ከፍተኛ የሀገር ጉዳዮች ላይ ዉሳኔአቸዉን የሚወስዱት ከሁሉም የካፋ አካባቢ የተዉጣጡ የፓርላማ አባላትን (ወይም ምክረቾን) በማማከር ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም በቀጥታና በተዘዋዋሪ በዎቅቱ በነበረዉ የመግባቢያ ዘዴ፣በቀረርቶና በእንጉርጉሮ (ግራሮና፣ ሾሾና) መልክ የሚቀርቡላቸዉን አስተያየቶች ተቀብለዉ በማገናዘብ አንደሆነ፣ ንጉሥ አንደመሆናቸዉ ስልጣናቸዉ አምባገነንነትንና የአንድ ሰዉን ዉሳኔ የሚፈቅድ ቢሆንም ወደ ደሞክራሲ የተጠጋ የህዝብን ድምፅ ያማከለ ስርዓትን የመረጡ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍርካ ታርክም አጅግ ልዩ ሥፍራ የሚገባቸዉ መሪ መሆናቸዉን አንጂ የገጠማቸዉን የክህደት ስራ አይደለም።

ታድያ ለምን የቀለበት ውወራዉ ጉዳይ ተነሳ ሳትሉኝ አይቀርም። ፈረንጆች በምሳሌያዊ አነጋገር “እቤት ዉስጥ ስላለዉ ዝሆን አናውራ” (lets talk about the elephant in the house) አንደሚሉት የጋኪ ሻሮቺን ጀግንነት ብቻ አዉርተን ስለሃዘናቸዉና፣ ስለልባቸዉ መሰበር ሳናነሳ ብናልፍ ከታሪክ የሚቀርብን ጠንካራ ትምህርት ስላለ ነዉ። አንድን ሃገርና ህዝብ ለማቃናትና ገናናነቱን ለመመለስ የአንድን ሃገርና ሕዝብ ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል። በአንድ ወቅት ላይ የቻይና መሪ የነበሩት ቼርማን ማኦ ዘዶንግ ስለ ሶሺአልዝም ብዙ መፃፍ የፃፉ በመሆናቸዉ አንድ ጋዜጠኛ የርስዎን የሶሻሊዝም መፃፍት በዓለም ዙርያ ብዙ ሰዉ ያነባል፣ አርስዎስ ምን አይነት መፃፍ ነዉ የሚያነቡት ብሎ ቢጠይቃቸዉ፣ አኔ ሁሌም የማነበዉ የቻይናን የታርክ መፃፎች ነው። ሀገሪቱን ለማስተዳደር የምያስችለኝ ሁሉ ነገር በታሪካችን ዉስጥ ይገኛል ብለዉ አንደነበር ይነገራል። በታርክ የተሰሩ ስህተቶችና መሰናክሎች አንዳይደገሙ ለማድረግ ታሪክን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቃል። አዉነቱ ይነሳ ከተባለ ለአንድ ሕበረተሰብ ገናናነትም ሆነ ዉድቀት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ከታሪክ ዉስጥ ማየት ይቻላል።

ቤት ዉስጥ ወዳለዉ ዝሆን ልመለስና፣ ፈረንጆች በዝሆን ያስመሰሉት፣ ጉዳይ ሁሉ ሰዉ የሚያውቀዉ፣ ግን ለማንሳትና ለመነጋገር ብዙ የማይፈልገዉን ጉዳይ ነዉ። አኛም የካፋ ልጆች ለማንሳት የማንጏጏዉ የጋኪ ሻሮቺን ልብ ሰብሮ ቀለበታቸዉን ወደ ጎጀብወንዝ አንዲወረዉሩ ያበቃቸዉን የታሪካችንን ጥቁር ነጥብ ነዉ። ከአባቶች ትረካ አንደሰማነዉ ጋኪ ሻሮቺ አጅግ ብልህና አስተዋይ በመሆናቸዉ ለሶስተኛ ጊዜ ከምኒልክ ጋር ስለሚገጥሙት ጦርነት ልባቸዉ አልተነሳም ነበረ። አዉነታዉን ጠንቅቀዉ ያውቃሉ።አንዱ አስደናቂዉ የጋኪ ሻሮቺ ጥበብ በድንበራቸዉ የተወሰኑ ሳይሆኑ በዙርያቸዉ በመላ ኢትዮጵያና በዓለምም አካባቢ በወቅቱ አየተከሰቱ ያሉትን አዉነታወች ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ነበሩ። በአድዋ ጦርነት አፄሚንልክ ጣልያንን ድል አድርገዉ መመለሳቸዉን ጠንቅቀዉ ያውቃሉ። የአድዋ ድል ዉጤት ዘመናዊ መሳርያንና ድፍረትን ለምኒልክ አንደሚሰጥ ያገናዝቡም ነበር። ስለዚህም አንደበፊቱ ለዚህ ለሶስተኛዉ ጊዜ ከምኒልክ ጋር ሊደረግ ስለታሰበዉ ጦርነት ብዙም አልጏጉም፣ በልባቸዉ አንድያውም ሌላ አማራጭ ቢገኝ ይመርጡ ነበር። ሆኖም የአማካሪዎቻቸዉን አስተያየት የሚያከብሩ መሪ በመሆናቸዉ ምክረቾን ሰብስበዉ በቀጥታ ለመጠየቅ ህዝቡን ደግሞ በተዘዋዋሪ ለማማከር ወሰኑ።

የሃይማኖት መሪዎች የነበሩትን አላሞዎችን ጭምር አማክረው አንደነበረ የአባቶች አፈታሪክ ይነግረናል። በዚህም መሰረት ንጉሡ ምክረቾን ሰብስበዉ አስተያየት አንዲሰጡ ጠየቁ። ከምክረቾ መሃል ጥቂት በቂም በቀል ስሜትና በስልጣን ጥማት የታወሩ ከሃዲ ይሁዳዎች ስለነበሩ አነርሱ በፍጥነት መልሱ መዋጋት አንደሆነ ተናገሩ። በርግጥ አብዛኛዉ ምክረቾ ለንጉሡ ያደረና ታማኝ ነበረ።

ከሀድዎቹ እንዋጋ ብለዉ ቀድመዉ ለንጉሡ መልስ ሲሰጡ ሌሎች ጦርነቱን በልባቸዉ ያልተቀበሉት አብዛኞቹ የምክረቾ አባላት ደካማ ሆኖ ላለመታየት ሲሉ እንዋጋ ብለዉ አብረዉ አንደተስማሙ አባቶች ይተርካሉ። አላሞዎችም ምክራቸዉን ሲጠየቁ የኛ ‘ኤቆ’ በንብ አስነድፎ በጉንዳን አስነክሶ፣ በሴት ልጆቻችን በጥፊ አስመትቶ የሚንሊክን ጦር መመለስ ይችላልና እንዋጋ የሚል መልስ ነበር የሰጡት።
ከሕዝቡ መሃል ግን በግጥም አድርገዉ ጦርነቱን መዋጋት ትልቅ አደጋ ሊያስከትል አንደሚችልና ከዚህ በፊት ጦርነቱን ብናሸንፍም የብዙ ሰው ህይወት ተከፍሎበት አንደሆነ አሁን ላይ የሚያዋጣዉ ከምኒልክ ጋር ተደራድሮ ሰላም መፍጠር አንደሆነ የመከሩ ጥቂት ደፋር ሴቶችና ወንዶችም አንደነበሩ ይነገራል።

አፈታሪክ አንደምያስተምረን ከከሀድዎቹ የምክረቾ አባላት መሃል አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት የንጉሱን ትእዛዝ አጉድለዉ በመገኘታቸዉ አስከፊ ቂጣት የተቀጡና በቂም በቀል ስሜት የተቃጠሉ አንደነበር፣ ሊሎቹ ደግሞ ለምኒልክ ጦር መረጃ አቀብለዉ የንጉሱን ዉድቀት ብያመቻቹ ምኒልክ በተራ ንጉሥ አድርጎ ይሾመናል በሚል የተሳሳተ የስልጣን ጥማትና ምኞት ለክህደት የተዘጋጁ ግለሰቦች አንደነበሩ የአባቶች አፈታሪክ ያስረዳናል።
በመጨረሻም በከሃዲ የምክረቾ አባላት አነሳሽነት አብዛኞቹ የምክረቾ አባላት ልባቸዉ በሙሉ ሳይቀበል ደካማ ሆነዉ ላለመታየት ሲሉ የተስማሙበት፣ አላሞዎች አኛ ተፈጥሮን አስነስተን አንዋጋለን በማለት ያደፋፈሩት፣ ነገር ግን ጥቂት ደፋር ሴትና ወንድ የካፋ ልጆች የተቃወሙት ጦርነት በድንገት ተጀመረ።

የሚኒልክ ጦር ከአድዋ የማረከዉን የጣልያን ጦር መሳርያ ይዞ የበላይነቱን ብያረጋግጥም ዉግያዉን ለማሳጠር ስል ከካፋ ዉስጥም ከሃድዎችም የመረጃ ትብብር አግኝቶም ስለነበረ ሳይታሰብ በድንገት ሌሊት ህዝቡ በአንቅልፍ በተዋጠበት ሰዓት ላይ ጦርነቱን በሁሉም አቅጣጫ ቤቶችን በማቃጠል ከፈተ። ይሄም ጦርነት የአትዮጵያን ግዛት ለማስፋፋት ከተደረጉት ጦርነትቶች ሁሉ የላቀ በጭካኔዉ ወደር የማይገኝለት ጦርነት አንደነበረ አዛዉንት አባቶችና የተለያዩ አውሮዊያን የታሪክ ፀሐፊዎች ዘግበዋል ። ከካፋ ህዝብም ከግማሽ በላይ የሆነዉ በጦርነቱ አንዳለቀ ይነገራል። ጦርነቱ ባይኖር በዛሬዉ እለት የህዝባችን ቁጥር ከ 5 – 10 ሚልዮን ሊደርስ አንደሚችል ይገመታል።
ሕዝቡም በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመነሳሳት በድንገት የተከፈተበትን ጦርነት ተያያዘ። ህዝቡ አገሩን ለመከላከልና ንጉሱን ለመጠበቅ አራሱን የሰጠ ቢሆንም የዘመናዊ መሳሪያን ኃይል መቋቋም ባለመቻሉ የማይቀረዉ አስከፊ እድል አየታየዉ መጣ። በዚህም መሃል ንጉሱን ለመጠበቅና በንጉሡ ዙርያ ጠላትን ለመከላከል በፍቃደኝነት ተሰልፈዉ የነበሩት ከሃዲ የምክረቾ አባላት ንጉሱን፣ የምኒልክ ጦር አየገፋ ስለመጣ በጌሻ በኩል አናሺሾት ብለዉ በማሳመን ይዘዋቸዉ ጉዞ ጀመሩ። ንጉሱን ይዘዉ ስጏዙ ከቆዩ በሗላ ወደጌሻ ሲቃረቡ ንጉሡ ይሄ አካሄድ ነፍሳቸዉን የማዳን ሳይሆን አሳልፎ የመስጠት አይነት ሊሆን አንደሚችል በአካባቢዉ ከነበረዉ የጠላት ወታደር እንቅስቃሴ ገመቱ። ብዙም ሳይቆይ ከተዘጋጀላቸዉ ወጥመድ ወደቁ። ዞር ብለዉም ከሃዲዎች ወንድሞቻቸዉን በሀዘንና በንዴት ተመለከቱ። ጠላትም ይዟቸዉ ጉዞ ጀመረ። የንዴት የሃዘንና በገዛ አማካሪ ወንድሞች የደረሰባቸዉ የክህደት ስሜት ሲፈራረቅባቸዉ የነበሩት ጋኪ ሻሮቺ፣ ከጎጀብ ወንዝ ሲደርሱ ካፋን ለአንዴና ለመጨረሽ ጊዜ አየተሰናበቱ አንደሆነ በሃዘን የተሰበረዉ ልባቸዉ አስታወሳቸዉ።

በዚህም ሰዓት፣ በገዛ ወንድሞቻቸዉ አሳልፎ የመሰጠታቸዉን ሃዘንና ንዴት፣ የጣታቸዉን የዙፋን ቀለበት በማውለቅ ሁሉንም በቀለበቱ አጠቃለዉ አባታዊ የሀዘንና፣ የእርግማኔ ቃላቶች ካዘነቡ በኃላ ወደ ጎጀብወንዝ ቀለበቱን ወረወሩት።
በነዚህ የታቶ ጋኪ ሻሮቺን ልብ ባቆሰሉት ከሃዲዎች የተጀመረዉ የክህደት ስራ አስከ ዛሬ በህዝባችን ላይ በተለያዩ መንግሥታትና ዘመን ስያንሰራፋ ቆይቷል። የካፋ መንግስት በሚኒሊክ አጅ ከወደቀበት 1897 ዓ፣ም ጀምሮ ህዝቡ የካፋን ገናናነት ለማንሳት አንደገና ሊያስብ ይችላል በማለት በህዝቡ ዉስጥ አንድቆዩ የተደረጉት ነፍጠኞችና ነጭ ለባሾች ህዝቡን ስበዘብዙና አንቅስቃሴዉን ተከታትለዉ ሲያፍኑ፣ በዉሸት ሲወነጅሉት ቆይተዋል።

የህዝቡ ልጆች ስለህዝባቸዉና አከባቢያቸዉ ተቆጭተዉ ማሰብና መወያየት በጀመሩ ቁጥር ያልተሰራና ያልተነገረዉን በማዉራት የካፋ ልጆች ካፋን ልያስገነጥሉ ነዉ። የፖለቲካ ስራ አየሰሩ ነው ብለዉ በሚያሳብቁ ከመሃሉ በወጡ ከሃዲዎች ልጆቻችን ሲወነጀሉ ቆይተዉ ወደቸልተኝነትና ግድ የለሽነት አያዘነበሉ በመሄዳቸዉ በህዝቡ ላይ ላለፉት 27 አመታት ሲደርስ ስለቆየዉ በደልና ዘረፋ ለለዉጡ መምጣት ከታገሉት በሰሜና በምዕራብ ከተነሱት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብረዉ አንድም ድምፅ ሳያሰሙ ወኔያቸዉን ተገፈዉ ቆይተዋል።

በአሁኑ የይቅርታና የምህረት ዘመን፣ ሞራላችንን ከፍ አድርገን ለህዝባችን መስራት በሚያስፈልገን ሰዓት ይህን ጥቁር ነጥብና አሳዛኝ ታሪክ መተረክ ለምን አስፈለገህ የምትሉኝ አንደምትኖሩ አገምታለሁ። አዉነት ነዉ ዘመኑ የይቅርታና የምህረት መሆን አለበት። የሞኝነትና የየዋህነት ግን ሊሆን ጨርሶ አይገባዉም። ይህንን ለመናገር የሚቀፍ አሳዛኝ ታሪክ ያቀረብኩት ዋንኛ ምክንያት ከታሪካችን አንድኒማር ብቻ ነዉ። የቂም አስተሳሰብ አንድኖረንም አይደለም። ከታርክ መማር አንጂ በታሪክ ቂም መያዝ ጅልነት ነዉ። አሁንም አንደ ፈረንጆች ምሳሌያው አነጋገር የመጣበትን የማያዉቅ የሚሄድበትን ልያዉቅ አይችልም (he who does not know where he came from does not know where
he is going). ከታሪካችን ተምረን የዎደፍት ጉዞአችንን በብልሀት አንድናቅድ ነው። በዛሬዉም ዘመን ያሉትን የህዝባችንን ይሁዳዎች ለይተን አንድናውቅና ትከሻችንን ገጥመን ከመሃላችን ገብተዉ አንዳይከፋፍሉን አንድኒከላከልና ለሁለተኛ ጊዜ አንዳኒካድ ለማሳሰብ ነዉ። አሁንም የፈረንጆችን ምሳሌያው አነጋገር በመጠቀም፣ “አንዴ ብታሞኘኝ ዉርደት በአንተ ላይ ይሁን፣ ሁለቴ ብታሞኘኝ ግን ዉርደት በኔ ላይ ይሁን” (if you fool me once shame on you, if you fool me twice shame on me) አንደሚሉት ካለፈዉ ሳይማሩ ቀርቶ ሁለቴ መሞኘት ጅልነት ነዉ።

አንዳይክዱንና ዛሬም በቂምና በቁጭት፣ በራስ ዎዳድነትና በስልጣን ጥማት ሕዝባችንን ከፋፍለዉ አሁን የመጣዉን የለውጥና የነፃነት ዎጋገን አጨልመዉ ዎደኃላ ልያስቀሩ የሚጥሩ ኃይሎች አንዳሉ በመገመት ነዉ። በተለይ ዎጣቱ ትዉልዳችን የግለሰቦችንና የቡድናትን አካሄድ በጥያቄ ምልክት ዉስጥ በማስገባት የህዝባችንን ህልዉና የሚያስከብር አካሄድ መሆን አለመሆኑን ጠንቅቆ በመረዳት ለግል የፖለትካ ትርፍ የሚደረጉትን የራስ ዎዳዶች ተግባር መዋጋት አለበት። ከአሁን በኅላ የሚገዛን የገንዘብ፣ ጥቅም፣ ዎይም የስልጣን ጥማት ስይሆን የህዝባችን ህልዉና መከበር ብቻ መሆን አለበት። ይሄንን ለማሳካት በዋንኛ አላማችን በሆነዉ የህዝባችንን ህልዉና የማስከበር ጥረት ላይ አተኩረን የግል ስሜታችንን በመቆጣጠር በህብረት መስራትና በትግስት መደማመጥን ይጠይቃል።

የካፋ ልጆች ስለህዝባቸዉ ማሰብና የፖለትካ ድርጅት መስርቶ ለህዝባቸዉ ህልዉና መታገል ከአሁን ጀምሮ መብታቸዉ ነዉ። ነገር አመላላሾች፣ ነጭ ለባሾችና ከፋፋዮች ከስራቸዉ የሚዎገዱበት ዘመን ስለሆነ ሌላ ስራ ይፈልጉ፣ የመከፋፈል መረባቸዉን አቃጥለዉ ለአካባብያቸዉ ተግተዉ መስራት ይጀምሩ።
ከአሁን በኃላ ጥላችንን የምኒጠራጠርበትና የምንፈራበት ጊዜ አይደለም። ፈሪ ያልዎለደን የጀግኖች ልጆችም ነን። አንደጀግናዉ ጋኪ ሻሮቺና የርሱ ሰራዊት ቂንነትና አዉነትን ተላብሰን ለህዝባችን ህልዉና መከበር በድፍረትና በግልፅ በአደባባይ የምንሰራበትና የምኒጋፈጥበት ዘመን አሁን ነዉ። የተፈጥሮ ሕግ በመሆኑ የተዎለደዉ ሁሉ ማደጉ በአንድ ዎቅት ላይ በህመም ዎይም በእድሜ መሞቱ አይቀርም። ከአአሳፋሪ ሞት አግዛብሔር ይሰዉለን። አሳፋርዉ ሞት የህዝባችንን ስቃይ በቸልተኘነት ኢያየን አንድም ነገር ሳናደርግ መሞት ነዉ። ፣ በአልባሌ ስፍራ አልባሌ ተግባር ስፈፅሙ፣ የክህደትና የመከፋፈል ስራ አየሰሩ መሞት ነው። አባቶቻችን አንዳሳዩን የህዝቡን ህልዉና ሲያስከብሩና ለህዝቡ ሲጋፈጡ መሞት፣ ሞት ሳይሆን በታሪክና በትዉልድ ሕያው መዝገብ መመዝገብ ነው።

በሚቀጥለዉ ጊዜ – “ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ የምንጠይቀዉ በምን መልክ መሆን አለበት” በሚል ጽሑፍ አስኪኒገናኝ መልካም ጊዜ።
ከአማኑእል ካርሎ ጋኖ
ለካፋ ሚዲያ – Kafa Media

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: