Leave a comment

ለካፋ: ለሸካና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ያለ ምርጫችሁ ወደ ሌላ ክልል የተካተታችሁ


ለካፋ: ለሸካና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ያለ ምርጫችሁ ወደ ሌላ ክልል የተካተታችሁ የጅማ የኣንፊሎ እንዲሁም በኢሉባቦር ሲዳማ የምትኖሩ በታሪክ ኣጋጣሚ ራቅ ብላችሁ ጎጃም መተከል ውስጥ የሰፈራችሁ የቦሮ ሽናሻዎችና እንዲሁም እስከ ሩዋንዳ ድረስ ያላችሁ እንዲሁም ባጠቃላይ በ1897 ዓ.ም በሚኒሊክ የግዛት ማስፋፋት ጦርነት ምክንያት የትውልድ ቀያችሁን ለቃችሁ በየአቅጣጫው የተሰደዳችሁ::

ንጉሠ ነገሥት ጋኪ ሸሮቾን ኣጅባችሁ ወደ መሀል ሀገር ከገባችሁ በኃላ በደረሰባችሁ ግፍና በደል ምክንያት በኣዲስ ኣበባና ኣካባቢው የተሰደዳችሁ በተለያየ ምክንያት ከሀገር ተሰዳችሁ በመላው ኣለም የምትኖሩ የጎንጋ ማህበረሰብ ትውልድ የሆናችሁ ወደ ኣንድ እንድትመጡና ህዝባችሁን ከዚያም ኢትዮጵያ ሀገራችሁን ወደ ተሻለ የእድገት ዱረጃ እንድታሸጋግሩ በያላችሁበት ይህን መልክት ላልሰማ እንድታሰሙ::

የጎንጋ ህዝቦች እነማናቸው?? ለዚህ ጥያቄ በቀለ ወ/ማርያም ኣዴሎ የካፋ ህዝቦችና መንግሥታት ኣጭር ታሪክ 2004 ገፅ 4-5

የጎንጋ ህዝቦች የሚባሉት የዛሬዎቹ የካፋ የሸካ የሂናሮ የኣንፊሎ/ቡሻሾ ቦሮ ሽናሻ የቦሾ/የጋሮ ህዝቦችን ያካትታል:: የቦሻና የኣንፊሎ ህዝቦች ከቦሮ ሽናሻ ጋር ቅርበት ያላቸው ሲሆን በኣሁኑ ሰኣት (እንደ በቀለ ወ/ማርያም መረጃ ) በተለያዩ ጊዜ በተደረጉ የኦሮሞ ግዛት መስፋፋት ወረራዎች ግፊት ግማሾቹ ሲበታተኑ ግማሾቹ በኦሮሞ በመዋጣቸው በኣብዛኛው ያለፍላጎታችው የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ ለመሆን ተገደዋል ሌሎችም ከስመዋል:: ሰፊ ግንዛቤ ለማግኘት መፅሐፉን ማንበብ ይመከራል መረጃ ሙሉ ሰው ያደርጋልና::

ወደ ተነሳሁበት ኣላማ ልመለስ:: የፅሑፌ ኣላማ በዋነኝንት የጎንጋ ዝርያዎች በያላችሁበት እንኳን ለ2011 ዓ.ም ዋዜማ ኣደረሳችሁ ኣደረሰን የሚል የመልካም ምኞት ማስተላለፍ ሲሆን እኔም በ1897 ዓ.ም ሰለባ በመሆን የተወለዱበትን ቀየ ለቆ በስደት ከተበነ ነገር ግን ካልከሰመ የጎንጋ ዝርያ የተገኘሁ የካፋ ወይም የጎንጋ ዝርያ ነኝ:: በወቅቱ የመጣው የለውጥ ጭላንጭል በሰጠኝ ተስፋ የሰው ልጅ የሚኖሩው በተስፋ ስለሆነ ኣንድ ቀን እንሰባሰባለን የሚል ተስፋ ስለፈነጠቀብኝ ይህን ተስፋ ብዙዎቻችሁ ትጋሩኛላችሁ ብየ በመተማመን መሆኑን ከወዲሁ እገልፃለሁ:: ይህን ለማለት ያስደፈረኝ በ2006/2007 ዓም ካፋ ቦንጋ ላይ ሽናሻ መተከል ወንበራ ላይ በመቀጠል ሸካ ላይ (በኣጋጣሚ ሁለቱን ስብሰባዎች በኣካል ተገኝቼ ተካፍያለሁ የሸካውን ግን ከሀገር ውጭ ስለነበርኩ ኣልተሳተፍኩም:: ከላይ የዘረዘርኳቸው የጎንጋን ህዝቦች በቋንቋም ሆነ በባህል ተመሳሳይነት ስላላቸው ወደ ኣንድ ቢመጡ ጠቀሜታ እንዳለው ኣምነውበት እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር :: ይህን ኣስተሳሰብ የሚደግፍ የለውጥ እንቅስቃሴ በመከሰቱ ኣንድነታችንን በማጠናከር ለጋራ ብልፅግና መንገድ ይከፍታል የሚል እምነት ኣለኝ:: ኣንድ ህዝብ ነበርን ኣንድ እንሆናለን::

ጊዜና ዘመን የማይለውጠው ዘላለማዊ ኣምላክ ይህን እድል ስለሰጠኝ ድምፄን ከፍ ኣድርጌ ኣምላኬን ላመሰግን እወዳለሁ:: ለምን ብትሉ ይህችን መልእክት በዚህ ኣዲስ ኣመት ዋዜማ ለናንተ ለወግኖቼ እንዳስተላልፍና ብሥራት እንዳበሥር ስለፈቀደልኝ::

እንኳን ለ2011 ዓ.ም የፍትህ የዕኩልነት የዴሞክራሲ የኣንድነት የእድገትና የብልፅግና ብሎም የኣዲሲቱን ኢትዮጵያ ምዕራፍ መጀመሪያ ዘመን ላይ ኣደረሰን ኣደረሳችሁ::

በመቀጠል በቅርቡ ዩ ትዩብ ላይ የተለቀቀ የቦሮ ሽናሻ የሽማግሌዎች ግጭት ኣፈታት ባህል በጣም ኣስደመመኝና እነዚህ ሽማግሌዎች ሸካ መጥተው ሰሞኑን ቴፒ ውስጥ ተቀስቅሶ ህዝብን ከህዝብ ወንድምን ከወንድም ብሔርን ከብሔር እንዲያጋጭ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው ኣንዱ ብሔር ሌላውን ለቀህ ውጣ በሚል ኣሳፋሪ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል:: ይህ ሴራ ምንም እንኳን የጠንሳሾቹን ምኞትና ኣላማ ግብ ባያደርስም ጥቂት የማይባል ንብረት ሲወድምና መተኪያ የሌለው የሰው ህይወትም ሲያልፍ መጥተው ቢሸመግሉና ቢያስታርቁ ብየ ኣሰብኩ:: የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በቀላሉ ችግሩ ይፈታ ነበር በሽማግሌ::

ይህ ችግር በቴፒ ከበድ ይበል እንጂ በሽሽንዳና በጨና: በጋዋታ በቦንጋና ኣካባቢው በተለያዩ ቦታዎች ብልጭ ድርግም እያለ የህዝቡን ስላማዊ እንቅስቃሴ እየተፈታተነው ይገኛል:: የሚገርመው ነገር የህዝብ ለህዝብ ማጋጨት በህዝቡ ኣስተዋይነት ረገብ ቢልም በዚህ ያልተደሰቱት ወገኖች በካፋና ሸካ መካከል ችግር በመፍጠር ወንድማማቾቹን ለማቃቃር ሸካን ኣማራ ውጣ ሲል ካፋ ኣማራን ወግኖ ሸከቾን ኣግሏል ከሸክቾ ጎን ኣልቆመም ከዚህም በላይ የካፋ ባለሥልጣናት ላለፈው 27 ዓመት ሥልጣኑን ለካፋ መጠቀሚያ ኣድርገው የሸካን ህዝብ በድለዋል የሚል ቅሬታ ከሸክቾ በኩል ይንሸራሸራል:: ይህ የሸክቾ አመለካከት ኣይመስለኝም:: በሌላ በኩል ደግሞ ሸከቾወች በአንድነት ቢያምኑ ካፋና ሸካ የተለያየ ሕዝብ ነው ባይሉ ሁሌም እንደ ባዳ ለብቻ መሆንን ባይፈልጉ ኖሮ ካፋና ሸካ ተባብሮ ትልቅ ሕዝብ መሆን በቻለ ነበር:: በሸካ አክራሪ አስተሳሰብ ወደ ሗላ ቀረን በወያኔ ተረገጥን ይላሉ:: ይህም ይካፋ አመለካከት አይመስለኝም:: ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ህዝቡን ኣጨፋጭፈው የራሳቸውን ተልኮ ለማሳካት በውስጡ የተሰገሰጉ ኣዛኝ ቅቤ ኣንጏች ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ስለማይታጡ ነገሮች ወደ ኣላስፈላጊ ኣቅጣጫ እንዳይሄዱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል:: ውሻ በቀደደው ጅብ እንዳይገባና የለውጡ ኣቅጣጫ እንዳይቀለበስ:: ታስሮ የተፈታ ጥጃና ተጨቁኖ ግፍና በደል ያንገሸገሸው ህዝብ ሁለት ሞት መጣ ቢሉት ኣዱን ግባ ማለቱ ኣይቀሬ ነው::

ኣዲሱ ዘመን የኣንድነት የፍቅር የመተሳሰብ የጤና የፍትህና የእኩልነት የእድገትና ብልፅግና እንዲሆንልንና ኣላማችን እንዲሳካ ህዝባችን ከድህነት እንዲላቀቅ በያለንበት እንፀልይ::

ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘላለም ትኑር!!!
ቸር ይግጠመን::
ከፋንታዬ መኮ
ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a comment