1 Comment

ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ የምንጠይቀዉ በምን መልክ መሆን አለበት?


ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ የምንጠይቀዉ በምን መልክ መሆን አለበት?

 

ባለፈው ስለ ንጉሳችን ጋኪ ሻሮቺ ወይም አዲዮ ጭኒቲ በካፋ ህዝብ ማዘናቸውንና ቀለበታቸውን በሀዘንና በንዴት ወደ ጎጀብ ወንዝ መወርወራቸውን አንስቼ ከህዝቡ አብራክ የወጡ ከፋፋዮችና ከሃዲዎች ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለጥቅማቸዉ ሲሉ በህዝባችን ህይወትና እድገት ላይ ያሳደሩትን ተፅእኖና በደል በማስታወስ አሁን በምንጀምረው አዲስ ጉዞ ከታሪክ ተምረን አንድነታችንን አጠናክረን መጓዝ ግዴታችን እንደሚሆነ ለማሳሰብ ሞክሬ ነበር።

 

በዚያ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ ቃል እንደገባሁት መሠረት ዛሬ ደግሞ .“ንጉሳችን ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ መጠየቅ ያለብን በምን መልኩ መሆን አለበት”?

በሚል ርዕስ ቀጣዩን አቅርቤአለሁ።

 

እንደወትሮው አስተያየታችሁን የድጋፍ ሆነ የማስተካከያ በአድናቆት እቀበላለሁ። የምንዘጋጀዉ ለዴሞክራሲ ስለሆነ በቀና መንፈስ ገንቢ ትችቶችንና አስተያየቶችን መስጠትና መቀበል ባህሪያችን መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

 

የኔ ፅሁፍ ንጉሱን ይቅርታ ስለመጠየቅ የመጀመርያ ሀሳብ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ይልቁንስ ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ የዛሬ 15 ወይም 20 ዓመት ገደማ ቦንጋ ላይ ተደርጉ የነበረ ታላቅ የባህል ትዕይትን ያካተተ የይቅርታ ጥየቃ ስነ ሥርዓት ነው። በቦታው ባልገኝና ጊዜውን በትክክል ባላስታውስም ከስነስርዓቱ የተቀረፁትን አንዳንድ ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች አይቻለሁ። እጅግ የሚያስደስትና በመጥፋት ላይ ያሉትን የተለያዪ ባህሎቻችንን እንድናስታውስ እድል ያገኘንበት ነበር። ባህላችንን ለወጣቱ ትውልድ ለማስታወስና ለማስተላለፍ ሲባል በየዓመቱ ማዘጋጀት ቢከብድ አንኳን እንደ የዓለም ዋንጫ በየአራት አመት የሚደገም ቢሆን ብዙ ጥቅም አለዉ ብዬ አምናለሁ። (የባህል መምሪያ ማስታዎሻ ይያዝልኝ)

 

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ በዚያን ጊዜ የይቅርታ አጠያየቁ በምን መልክ እንደቀረብ ያገኘሁት መረጃ ባይኖርም፣ ይቅርታ ከጠየቅን 15ና 20 ዓመት በኃላ በህዝባችን ህይወት እስካሁን ያየነው ምንም ለውጥ የለም። ይህን በማስታወስ ችግሩ ከይቅርታ አጠያየቃችን ሳይሆን አይቀርም በማለት ነው እንደገና ብንጠይቅ በምን መልኩ ቢሆን የንጉሳችንን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን በሚል የዛሬውን ፅሁፍ ያቀረብኩት.

.

የይቅርታን ጥያቄ ንጉሱን ለመጠየቅ እስኪ በዓይነ ህሊናችሁ ንጉሱን በአካል አግኝተናቸዉ ከንጉሱ ፊት ተንበርክከን ይቅርታ እንደምንለምን አድርጋችሁ አስቡ። እኛም እንዲህ ብለን አዲይ ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ እንለምናቸዋለን። አባታችንና መሪያችን እራስዎን እስከመስጠት ሳይሳሱ የተፋለሙልን አባት፣ ራሳችንን ቀና አድርገን እንድንራመድ ምክንያት የሆኑልን፣ ቀድሞ አንዳንድ አባቶች በክፋትና በስስት ስለከዱዎትና ለግዞት ስለዳረግዎት ከኃላም ደግሞ ህዝቡን እንዲመሩ እድል የተሰጣቸዉ ከህዝቡ አብራክ የወጡ ልጆች ከጥቂቶች በስተቀር የራሳቸዉንና የአለቆቻቸዉን ጥቅም ብቻ በማየትና በማስከበር ህዝቡን በመክዳት እርስዎን ደግመው ስለከዱ ይቅርታ ያደርጉልን ዘንድ ከእግርዎት ስር በመንበርከክ አንጠይቆታለን።

 

ንጉሱም ተነሱ ልጆቼ:: ከተንበረከካችሁበት ተነሱ ብለው እስክንነሳ ከጠበቁ በኃላ እኔ በአካል ከናንተ ጋር ባልሆንም በመንፈስ ከእናንተ ጋር ስለሆንኩ እየሆነ ያለዉን ሁሉንም እመለከታለሁና ከኔ የተደበቀ ነገር የለም። ልጆቼ አባት በልጁ ቢያዝን ቢከፋ አንጀቱ ቢቆስል በስደት ቢማቅቅም እንኳን የልጁን መታረም እንጂ የልጁን ሞት አይመኝም:: ስለዚህ በእርግጥ አዝኛለሁ፣ በርግጥ አምርሬአለሁ ነገር ግን ለጥፋታችሁ ሙቱ፣ ጥፉ አላልኩም፣ እናንተ ግን እንደታረማችሁ አይቼ ይቅር እንዲላችሁ የሚያስችለኝን ነገር ይዛችሁ ስላልመጣችሁም ይቅርታየን ለማግኘት ገና ብዙ ይቀራችኃል። ጥያቄያችሁን በጥያቄ ልመልስና ለናንተ ያሉኝን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሳችሁ ስትመጡ ሙሉ ይቅርታዬን ታገኛላችሁ።

 

1. በእኔ ያየ ይማር ነውና አሁንስ ከመካከላችሁ ከሃዲዎችን አስወግዳችሁ አንድ ሆናችኃል? ወይንስ እኔን አሳልፈው በመስጠታቸው የኔን ዙፋን ጠላት የሚያቀብላቸዉ መስሎ እንደታያቸው ራስ ወዳዶች አሁንም የህዝቤን ህሊውና ሸጠው ለራሳቸው ስልጣንና ዝና ሲሉ ህዝቤን የሚከፋፍሉ በመሃላችሁ ይገኛሉ? ከከሃዲዎች ፀድተን እጅ ለእጅ ተያይዘን ትከሻ ለትከሻ ገጥመን እርስዎ ለሞቱለት ለህዝባችን ህሊውና መከበር ለመሟሟት ተዘጋጅተናል ካላችሁ አንድ የይቅርታ ነጥብ እይዝላችኃለሁ።

 

2. ህዝቤ አሁን የመጣውን መልካም የለውጥ አስተሳሰብ ተሳታፊ እንዲሆንና አንደገና ወደጥግ እንዳይጣል ህዝቡን የማስተማርና የማደራጀት ሥራ ጀምራችኃል? ሥራው መካሄድ ያለበት በከተሞች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች መሆኑን አውቃችኃል? ሥራዎች መሰራት ያለባቸዉ በአዲዮ, ዴቻ, ግንቦ, ጋዋታ, ጨታ, ጨና, ሽሽንዳ, ጌሻ እና በእያንዳንዱ ወረዳ ከሚገኙ ቀበሌዎች በመጀመር መሆን አለበት። በቦንጋና፣ በወረዳ ዋና ከተሞች ሰርታችሁ፣ በእያንዳንዱ የወረዳ ቀበሌ ተስማርታችሁ በአሁኑ ጊዜ በመጣው ለውጥ ራሱን አዘጋጅቶ መሳተፍ ያልቻለ ህዝብ ወደጎን እንደሚጣል አስረድታችሁ ህዝቡ ተወካዮቹን የሚመርጥበት የምርጫ ጊዜ እስኪደርስ ሕዝቡን የሚያደራጁና የሚያዘጋጁ በህዝብ የታመኑ ተወካዮች አዘጋጅታችኃል? ወይስ ሌላ ሰው ከሌላ ክልል መጥቶ የእናንተን ሃላፊነት እንዲወጣላችሁ በመጠበቅ ቀኑን ውላችሁ. ሌሊት በሀሳብ ሳትጨነቁ ጣፋጭ እንቅልፋችሁን አየተኛችሁ ነዉ? እንቅልፍ እየወሰደን አይደለም ህዝባችንን በለውጡ የማሳተፉ ሀሳብ አንቅልፍ አየነሳን ነዉ። በስራ አለም ያለነው የካፋ ልጆች ሳይቀር የአመት ዕረፍታችንንም ቢሆን ወስደን ወደ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ገብተን ህዝቡን ሴት ወንድ ወጣት ሽማግሌ ሳይቀር አሰባስበን በህዝቡ የታመኑ ተወካዮች ይዘን ህዝባችንን በአዲሱ ለውጥ ለማሳተፍ በማደራጀት አሁኑኑ ስራ ጀምረናል ካላችሁኝ ለይቅርታዬ ሁለተኛ ነጥብ እይዝላችኃለሁ።

 

3. ከላይ እንደጠቀስኩት እራሳችሁን አንድ አድርጋችሁ የህዝባችሁን ተወካዮች ካደራጃችሁ በኃላ እንደ አንድ ሰው በመነሳት ከድሮም በችግራችን ተባባሪና ለጥሪያችን ይደርሱልን ከነበሩት ከበስተደቡብ ከሚገኙት ቤንችና ማጂ ህዝብ ዘንድ በመሄድ፣ ከእነርሱ ጋር አንድነታችሁን አረጋግጣችሁ ከእነርሱ ተያይዛችሁ ደግሞ ወደ ምዕራብ ወደ ሻካ በማምራት ሁላችሁም እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ፍትህ ለማግኘት ሁለትና ሶስት ቀን ተጉዞ ወደ ክልል ከተማ የሚሄደዉን ህዝባችሁን ለማሳረፍ በአካባቢዉ የአስተዳደር መንግሥት አንዲቋቋም በጋራ ለመስራትና ማዕከላዊውን መንግስት ለመጠየቅ እና ለማስገደድ ቃል ትገባላችሁ? በዚህም በርትታችሁ ውጤት ካመጣችሁ ሶስተኛ የይቅርታ ነጥብ እይዝላችኃለሁ።

 

4. ህዝቤ እንግዳ ተቀባይ ነው፣ እግዚአብሄርን እንደመቀበል እንግዳውን በሙሉ ደስታ የሚቀበል ህዝብ እንደኔው እንደ ካፋና በአጠቃላይ አንደ ቤንች፣ ማጅና ሻካ ህዝብ የትም አላየሁም። ከዚህም የተነሳ በረሃብ፣ በድርቅና በተለያየ ምክንያት የመጡ እንግዶቹን ስያስተናግድ ቆይቷል። ይህንን ደግነት እንደውለታ ቆጥረው አብረዉ ተባብረዉ የሚኖሩ እንግዶች የነበሩ አሁን ደግሞ ነዋሪዎች የሆኑ ያሉን ስለሆን የህዝቤን ደግነት እንደጅልነት ቆጥረው ለመዳፈር የሚሞክሩ እንዳሉም አውቃለሁ። ካሁን በኃላ የልጅ ልጆቼ ቁጥር እየበዛ መጥቶ ለልጆቼ አንኳ የሚበቃ መሬት የለም። ይሄንን አገናዝባችሁ ሥራ አጥቶ ያለሥራ የተቀመጡትን ወጣት ልጆቼን በማህበር አደራጅታችሁ በቡድን መሬት ሰጥታችሁ የካፒታል (ገንዘብ) ድጋፍ አድርጋችሁ በጋራ ማልማትና ማደግ እንዲችሉ እሁን ያሉ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲያስፈፅሙ ጥያቄ እያቀረባችሁ ነው? ይህ አሁን ባለዉ ሕግ ሙሉ መብቱ የተጠበቀ ጥያቄ ስለሆነ በአስቸኳይ ጠይቃችሁ ስታስፈፅሙ አንድ ትልቅ የይቅርታ ነጥብ እይዝላችኃለሁ።

 

ጥያቄዎቼ ብዙ ናቸዉ። ከላይ የጠየኳችሁ ግን ዋንኛና ወሳኝ ስለሆኑ ለነዚህ ለ4ቱ ጥያቄዎች መልስ ከሰጣችሁኝ ሙሉ ይቅርታየን በአባታዊ ፈገግታና የደስታ ፊት በኩራት አንደምሰጣችሁ አንድታዉቁልኝ አወዳለሁ። ሌሎችም ጥያቄዎች በርግጥ አሉኝ። ከቀሩት መሃል ላሁን 2 ጥያቄዎች እንድታውቋቸውና በተቻላችሁ ሁሉ እንድትሰሩባቸው በማለት አንደሚከተለዉ አጠይቃለሁ።

 

ሀ፣ በየዓመቱ በዞኑ መንግሥት አስተባባሪነት እንግዶች ከየወረዳዉና ከትላልቅ ከተሞች ከጅማ፣ ከአዲሳባ የተጋበዙበት የመስቀል በዓል በታላቅ ድግስ አንደሚከበር መረጃ ደርሶኛል። ለመሆኑ የዚህ በዓል አከባበር ትርግዋሜውና ቁምነገሩ ምንድነዉ? ከጊዜው ጋር ለመሄድ ሞክሩ አንጂ አንዴት ነዉ። ባህል ማክበርና ማስታዎስ አንዳለ ሆኖ በኔ ጊዜ ሳይሆን በራሳችሁ ጊዜ አኮ ነው ያላችሁት። ታዳጊ ህፃናት በትምህርት ቤት አንድ መፃፍ ለሶስት ተጋርተው አየተጠቀሙ እናንተ ሰንጋ ስትጥሉ የህሊና ፀፀት አይሰማችሁም? ወይስ እንደዚህ አይነት ችግር አንዳለ ከነጭራሹም አታውቁትም? ስለዚህ ከአሁን በኃላ ይሄ የመስቀል በዓል የዞኑና የወረዳው የህዝብ መሪዎች ተሰባስበው በዓመት ውስጥ ለህዝቡ ያስጨበጡትን የልማትና የእድገት ሥራዎች በይፋ ለሕዝብ የሚያሳዉቁበትና የሥራቸዉን ዉጤት ከህዝቡ ጋር በጋራ የሚያከብሩበት እንጂ ጥቂት ሰዎች በመስቀል በዓል ስም አግባብ በለሌዉ መንገድ የህዝቡን በጀት የምበትኑበት አንዳይሆን ለማድረግ መታገል አስባችሁ ታውቃላችሁ? ። ከሩቅ ለበዓሉ የሚጋበዙ እንግዶችም ለዚህ አሳፋሪ ተግባር አንደማትሳተፉ ግልፅ አድርጋችሁ የበዓሉ አከባበር ምክንያት በልማትና በህዝብ አገልግሎት ዉጤት ላይ አንዲያተኩር የበኩላችሁን ጫና አድርጉ። ገበሬዉ አንኳን ለፍቶ ያጨደዉን እህል የላቡን ዉጤት ይዞ ነው የመስቀል በዓል የሚያከብረዉ። ትርጉም የሌለዉ ድግስ ትርጉም ባለዉ መተካት አለበት።

 

ለ፣ በኔ ጊዜ የካፋ ምድር አጅግ ዉብ ነበረች። ጫካዋ፣ ሜዳዋ፣ ጋራ ሸንተረሯ፣በዉስጡ የሚመላለሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉ አራዊት ስንቱ ተነግሮ ያልቃል። አሁንማ ሳያት ያ ጥቅጥቅ ያለዉ ጫካ መንምኖ ተራቁቶ፣ እነዚያ የተለያዩ የዱር አራውቷ አልቀዉ ባዶዋን ቀርታለች። በብዙ አራዊት ብዛት ይታወቅ የነበረዉን የጎጀብ ሸለቆን ብመለከት አሁን ከእርሻ ዉጭ ሌላ አይታይም። ዉሽዉሽም ወርጄ የድሮን ጫካ ለማየት ብሞክር ጫካዉ ተራቁቶ ለአይኔ አንግዳ በሆነ እፀዋት ተተክቷል። አፀዋቱ የሻይ ተክል ነዉ አሉኝ። ከድሮም ከካፋና ለተፈጥሮዋ ከካፋ የመነጨና ከደናችን የተገኘዉ፣ ደንን በሙሉ ሳያራቁቱ ማልማት የሚቻለዉ የቡና ተክል ነበረ። ይሄንን ሻይ የተባለዉን ባይተዋር አፀዋት አምጥታችሁ ደኑን ማራቆታችሁ አጅግ አሳዝኖኛል። መቼስ ይህ መሆኑ ካልቀረ ከጎጀቡ አርሻም ሆነ ከዉሽዉሽ ሻይ በሚገኘዉ ገቢ የሕዝቤን ህይወት መቀየር ከተቻለ በጎ ነዉ። ትምህርት ቤቶች ለልጆቼ ከተሰሩ፣ መድሃኒት አዋቂ የሚያክምበት መታከሚያ ሆስፒታል በየቀበሌዉ ከተሰራ፣ ሕዝቤ መገናኛ መንገድ ከተሰራለት፣ ንፁህ ዉሃ ከጠጣ፣ ጨለማዉን ፈካ የምያደርግለት መብራት ከተዘረጋ ለበጎ ነው ብዬ ሳልጨርስ፣ ልማቶቹ የዉሽዉሽም ሆነ የጎጀብ የካፋ ህዝብ አይደሉም አሉኝ። የማን ነው ብዬ በድንጋጤና በመገረም ብጠይቅ ችግሩ ባለቤታቸዉ አይታዎቅም አሉኝ። የህዝቡ ያልሆነ ባለቤቱ የማይታወቅ ልማት በኔ ምድር በካፋ? ቀለበቴን ቀደም ስል በደረሰብኝ ክህደት የተነሳ ባልወረዉር ይሄ በራሱ ቀለበት የሚያስወረዉር ነው። ስለዚህ ሕዝቤ በቀጥታ ባለቤትነቱን አረጋግጦ ወይም በቀጥታ ካልሆነ ደግሞ በተዘዋዋሪ ሕጋዊ ቀረጥ በመሰብሰብ የልማቱ ተጠቃሚ አንዲሆን በህጋዊ መንገድ መፋለም ይጠበቅባችኃል።

 

ሌሎች ያዘንኩባቸዉ የግል ቁጭቶችም አሉኝ። አነርሱን ሌላ ጊዜ አነግራችኃለሁ።

አስከዚያ አደራችሁን በተለይ ከላይ በጠቀስኳቸዉ 4ቱ ነጥቦች ላይ በማተኮር ዉጤት ካገኛችሁና ካኮራችሁኝ ሁሉንም ሃዘኔን ይቅር ብዬ ከግንባራችሁ እንቱፍ ብዬ በራሴ ስም ብቻ ሳይሆን በአባቶቼ በጋሊ ጋፎቺ፣ በጋዬ ነቾቺና ቀድመዉ ባለፉት ነገሥታት ሁሉ ስም መርቄ፣ አርግማኔን በምርቃት ተክቼ ፍፁም በሆነ ልብ ይቅር አንደምላችሁ አትጠራጠሩ። አደራ የምለዉ ግን ጊዜዉ አሁን ነዉ። አዝመራዉን ጠብቆ ያላረሰና ዘሩን ልክ በወቅቱ ያልዘራ ገበሬ አዝመራዉን ጠብቆ በሰዓቱ ከዘራ ገበሬ አኩል ምርት አያገኝም። ስለዚህ ጊዜዉ አሁን ነዉና። በዚህ በአዲሱ ለዉጥ ህዝባቸዉን ለማሳተፍ በየክልሉና በየዞኑ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከዳር አስከዳር አየተሯሯጡ ነው። ካሁኑ ካልተሯሯጣችሁ ህዝባችሁ ከጎን ተጥሎ የበለጠ አንደምታስከፉኝ እወቁ።

 

ችግራችሁንና የህዝቡን በልማት ኋላ መቅረት ካሁን በኋላ በማንም ማሳበብ አትችሉም። ተጠያቂዎቹ አናንተና አናንተ ብቻ ናችሁ። በዉጭ ኃይሎች የማሳበቡ ጊዜ አብቅቷል።

ቀና አስተሳሰብ ካላቸዉ ለእድገቱ ቁጭትና ቅንዓት ካላቸዉ ከልጆቹ የተሻለ የህዝቡን ችግር የሚያውቅም የሚፈታለትም የለምና እራሳችሁን አሳምናችሁ ካሁኑ ሥራ ጀምሩ። አስተማሪዎች የቅዳሜና አሁድ አረፍታችሁን መስዋዕት አድርጉ። በከተማ ያለዉን ህብረተሰብ ካደራጃችሁ በሗላ፣ የቅዳሜና የአሁድ እረፍታችሁን በገጠር የቀበሌዉን ህዝብ በማደራጀት ላይ አሳልፉ። በመንግስትና በግል ኩባንያ ተቀጥራችሁ የምትሰሩ የካፋ ልጆች የዓመት እረፍታችሁን ወስዳችሁ ከገጠር ቀበሌ ህዝቡን በማስተማርና በማደራጀት ላይ አዉሉ። ከባድ አይደለም። የደረሳችሁበት ታውቃላችሁ፣ ለመሰረተ ትምህርት በየቀበሌዉ ዘምታችሗል ። ከናንተ ዉጭ ማንም የራሳችሁን ሥራና ሀላፊነት ሊወጣላችሁ አይችልም።

 

በእርግጥ አንደሚሰማዉ ከሆነ በሀገር ደረጃ የተደራጁ ለሁሉም አትዮጵያዊ አንሰራለን የሚሉ ሃገራዊ ድርጅቶች አሉ። አነዚህ ሃገራዊ ድርጅቶች የካፋን የቤንች የማጂን የሻካን ልዩ ችግር ሊያዉቁ አይችሉም። በኢትዮጵያ ያለዉን 100 ሚልዮን ህዝብ አንወክላለን ካሉ በሌላም ዓለም አንደምናየዉ ጊዜያቸዉን በብዛት የምያዉሉት የህዝብ ብዛት ካለበት ብዙ ድምፅ ከሚያገኙበት አካባቢ አንጂ እናንተ ጋር በ3 እና 4 ሚልዮን ህዝብ ላይ ጊዜአቸዉን አያጠፉም። ለናንተ ጊዜ ቢሰጡ አንኳን ድርጅቶቹ ትልቅ አንደመሆናቸዉ የተነሳ አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመለከት አጠቃላይ አጀንዳ አንጂ የህዝባችሁን ልዩ ብሶትና ጥያቄ አማክለዉ አያራምዱም። ስለዚህ የራሳችሁ የሆነ የህዝብ ድርጅት ኖሯችሁ በድርጅቱ በኩል የናንተን ጥቅም ማስከበርና ጥያቄያችሁን ማስመለስ ትችላላችሁ። ድርጅታችሁም አናንተን በመወከል የናንተን ብሶት ይረዳሉ፣ ጥያቄአችሁን ይመልሳሉ ብሎ ከሚያምናቸዉ ድርጅቶች ጋር አብሮ አንዲሰራ ማድረግ ትችላላችሁ። የህዝባችሁን ድምፅ የሚወክል ያልተከፋፈለ አንድ ጠንካራ ድርጅት ለደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ህዝብ ማለትም ለካፋ፣ ለቤንች፣ ለማጅና ለሸካ መኖሩ ግን አጅግ ወሳኝ ነው። የህዝባችሁን ድምፅ የያዘ የራሳችሁ ድርጅት ሲኖራችሁ ሌሎች አገራዊ ሆነ አከባቢያዊ ድርጅቶች ለህዝቡ ድምፅና ወንበር ሲሉ ድርጅታችሁን ፍለጋ ይመጣሉ። ከእነዚያም መሃል የህዝባችሁን ጥቅም ማስከበር የሚችለዉን ድርጅት መርጣችሁ በመጣመር አብራችሁ መስራት ትችላላችሁ።

 

ለዛሬው ለናንተ ያለኝን ጥያቄና ምክር በዚህ ላብቃ። አናንተም ግዴታችሁን ተወጥታችሁ ወደኔ የምትመለሱበትን ቀን እኔም በአባታዊ ፈገግታና ደስታ ሙሉ ይቅርታዬን የምሰጣችሁን ቀን እግዚአብሔር ያቅርብልን በማለት አዲዮ ጋክ ሻሮቺ ከኛ ተለዩን። አኛም የሃዘን አይሉት የደስታ የተደበላለቀ ስሜት አየተሰማን ወደያለንበት ለመመለስ ጉዞ ጀመርን። በጉዟችንም የንጉሡን ጥያቄዎች ለመፈፀምና ለህዝባችን ህሊውና መከበር የሚያስፈልገዉን ሁሉ አድርገን ከዚያም በኩራት ተመልሰን ያንን ሁሉ ለጋኪ ሻሮቺ ነግረናቸዉ ሙሉ ይቅርታቸዉን አንድንቀበል ቃል ገብተን ሥራ የምንጀምርበትን ቀጠሮ ለሳምንት ይዘን ተመለስን።

 

አንግዲህ ህልም በሉት ምኞት፣ ከቀድሞዉ ንጉሳችን ከጋኪ ሻሮቺ ይቅርታ ያስገኙልናል ብዬ ያሰብኳቸዉን አነዚህን ነጥቦች አቅርቤአለሁ። አይናችሁን ሰጥታችሁ በርዝመቱ ሳትሰላቹ ስላነበባችሁ አጅግ አመሰግናለሁ። በዉስጣችሁ መጠነኛ እሳት አንደተጫረ ተስፋ አደርጋለሁ።

ከአማኑኤል ካርሎ ጋኖ

ካፋ ሚዲያ Kaffamedia

One comment on “ጋኪ ሻሮቺን ይቅርታ የምንጠይቀዉ በምን መልክ መሆን አለበት?

 1. God bless you! This writing puts some radical (new) memorandum in my brain. I am disappointed, when I read your message. I think no one had ever realized what you remembered, the long year’s back event which was a great decline of our hope which has been covered its shadow over the Kafa people’s Internal memory. Please dont be silent because you got the brain of the engine and the driving force. So, continue as you started and we must struggle to get the forgiveness of our King Taatoo Gaakki Sharoch.
  wooho Mishraacha!!! Kafa Will be The Great, As It Was previously!!!!
  Excuse me, I could be grammatically incorrect, would you please correct while you are reading my comment?
  Thank you.
  S
  incerely yours!

  Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: