Leave a comment

ለምን የካፋ ሕዝብ የራሱ ድርጅት አስፈለገው?


ለምን የካፋ ሕዝብ የራሱ ድርጅት አስፈለገው?

 

ቀደምት አባቶች “የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ” ብለው የተረቱት ያለ ምክንያት አይደለም:: የካፋ ሕዝብ ከምንሊክ ወረራ በሗላ የራሴ የሚለው ተቋም ባለመኖሩ ላለፉት መቶ አመታት ሲዘረፍ ኖሯል:: ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕዝባቸውን ለመታደግ የካፋ የቤንች ማጂ እና የሸካ የቁርጥ ልጃች ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረትን በሰሜን አሜሪካ ከመሰረቱ እነሆ ሦስት ዓመት ተቆጥሯል:: በቅርቡ ወደ ሃገራቸው ገብተው ከሕዝባቸው ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት ያደርጋሉ:: ለሕዝባቸውም እንደ ምሰሶ የሚቆም ታላቅና በሕዝባችን ልብ ውስጥ ለዘላለሙ ፀንቶ ያሚቆየውን ድርጅት ይመሰርታሉ:: ከአሁን በሗላ ሕዝባችን በራሱ ድርጅትና ልጆች እንጂ በማንም ድርጅትና ሞግዚትነት አይመራም::

 

የካፋ: ህዝብ: የአመራር: ጥያቄ::

 

I. ችግሩና ታሪካዊ መሰረቱ፤

 

ካፋ ሃብታምና ለምለም አገር ነበር፡፡ ከዉጭ ዜጎች በስተቀር፣ ብዙ የተከበሩ የታሪክ ምሁራን ጭምር ደፍረዉ መፃፍ ወይም መናገር ያልቻሉት እዉነታ፤ ካፋ አስከ 1900 ዎቹ ምዕት-ዓመታት ድረስ በነበረዉ ዘመን፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ ከተካተቱት አካባቢዎችና፣ ህዝቦች፣ በአንፃራዊነት በሰለጠነ አደረጃጀት፣ የመንግሥት አወቃቀርና አመራር የተደራጀ ነበር፡፡ ሆኖም የካፋ ለም መሬትና ሃብት “እንደሌሎቹ ሃብታም አካባቢዎች ሁሉ የጥቃቱ ምንጭ ሆነ”፡፡ ይህ ሃብት እስከ 1889 ዓ.ም. በተደጋጋሚ ለተደረጉና ካፋ በብቃት ለመከታቸዉ ጦርነቶች፣ ምክንያት እንደሆነ በብዙዎች ተፅፏል፡፡ ምንም እንኳን የተሰነዘሩበትን ተደጋጋሚ ጦርነቶች እስከ 1889 ድረስ፤ በብዙ መስዋዕትነት እና ጀግንነት እየመከተ ህልዉናዉን ጠብቆ ቢቆይም፣ በ1889 ግን ይህ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም፣ በተደጋጋሚ ድል እየሆነ የተመለሰዉ ጦር የተለየ ሁኔታ ላይ ደርሶ፣ጊዜዉም ተለዉጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊዉ ጦር በ1888 ዓ. ም. የአድዋ ጦርነት፣ ከጣሊያን ሰራዊት በርካታ ትጥቅ አፍሶ ነበር፡፡ ለራሳቸዉ ዓላማ ሲሉ የተሰባሰቡ፣ አዉሮፓዊያን የጦር ባለሙያዎች ድጋፍም ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ እነዚህ አዉሮፓዊያን ግን ከዓድዋ ጦርነት በፊት፤ የካፋን ንጉሥ በማማለል ምንሊክን በካፋ በኩል ለመዉጋት ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ የካፋ ንጉሥ ግን፣ “ ይህ የወንድማማቾች ጉዳይ ስለሆነ፣ በእኔ በኩል ምንሊክን አትወጉመ……..” ብሎ ሲመልሳቸዉ፣ የሃይል ሚዛኑን አይተዉ፣ ለምኒልክ የጦርነት ሂደት፣ በተለይም በካፋ ወረራ ወቅት ጉልህ ሚና ተጫዉተዉ ነበር፡፡ ስለሆነም የካፋ መንግሥት መዉደቅ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡ ንጉሡም ቢሆኑ ወደዉግያዉ የገቡት በዉስጥ ሴረኞች ተፅዕኖ ነበር፡፡ ዝርዝሩን የሚመለከታቸዉ የፃፉት ስለሆነ፣ ለትምህርት እንዲሆን ምንጮቹን ማየት ይጠቅማል፡፡ ለማንኛዉም ካፋ በአራት አቅጣጫ፣ በዘመናዊ መሣሪያና፣ በአዉሮፓዊያን የጦር መኮንኖች ድጋፍ በተደረገበት ጦርነት ወደመ፡፡ በዚህ እልህ አስጨራሽና አዉዳሚ ጦርነት፣ የታሪካዊዉ የካፋ መንግሥት ህልዉና ሲያከትም፣ የህዝቡም የባርነት ዘመን ጀመረ፡፡ ቀጥሎም ነፃነቱን ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱን፣ ክብሩንና፣ ስብዕናዉን በሙሉ ተገፈፈ፡፡ ከሌሎች በተመሳሳይ መንገድ በማዕካላዊ መንግሥት ከተጠቃለሉ ህዝቦች ሁሉ በተለየ ሁኔታ፣ ከፖለቲካ ተገልሎ፣ ከማህበራዊ እና እኮኖሚያዊ ልማት ከመገለል በላይ ወደ ለየለት አገልጋይነትና ባርነት ወረደ፡፡ መሬቱ፣ ንብረቱ፣ ክብሩ ተነጥቆ ከቀዬዉ በመፈናቀል፣ ሲሰደድና በሰፋሪዉ፣ በወታደሮችና በገዢዎች ከሰዉ በታች ተገዛ፡፡ ይህ ሁሉ የህልዉና ማጣትና፣ ቀጥሎም በዉስጥም ጉዳይም፣ ራሱን ማስተዳደር በመከልከሉ፣ የደረሰዉን ሁሉ መናገር ቀርቶ፣ ማሰብም ይጨንቃል፡፡

 

ይህ ሁሉ የመደራጀት፣ የራስ አመራርና የራስ አስተዳደር ያለመኖር ዉጤት ነበር፡፡

 

የካፋ ህዝብም፣ በአዲሱ አስተዳደር ሥር ሆኖም መብቱን ለማስጠበቅ ጥረት ከማድረግ ተቆጥቦ አያዉቅም፡፡ ለዝርዝሩ በዚህ ጉዳይ የተፃፉትን ማንበብና፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማነጋገር ይጠቅማል፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ጥረቶች ተወሰኑ ቆራጥ የህዝብ ወገኖች በአነስተኛ ቡድኖች የተደረጉ ከመሆን ያለፈ፣ በሚገባ በተደራጀ ዝግጅት፣ ባለመሆናቸዉና፣ ለስኬት አልበቁም፡፡ ምንም እንኳን፣ በዉስጡ የተሰገሰገዉ ሃይል፣ የካፋን ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደቀደምቶቹ ሁሉ ቢገድቡም፣ በወታደራዊዉ መንግሥት ጊዜ፣ በመሬት ለአራሹ ሰበብ፣ የካፋንም ህዝብም በአንፃራዊነት ቢያንስ ባለመሬት ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም ለተሻለ ልማት እድሉ አልተሰጠዉም፣ ጥቂት የአካባቢዉ ልጆች ሃሳብም ቢሆን፣ በተሻለ ሁኔታ በተደራጁ አደናቃፊዎች ሲከሽፍ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ፣ በ20ኛዉ ክ/ዘመን መጀመሪያ በዉጭ ሰዎችና፣ በገዢዎች የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ጭምር እየተነቀሉ ሲወሰዱ፣ ህዝቡ ከመታዘብ ዉጭ አቅም አልነበረዉም፡፡

 

ይህም ሁሉ አሁንም የመደራጀት፣ የራስ አመራርና የራስ አስተዳደር ያለመኖር ዉጤት ነበር፡፡

 

በመጨረሻ ግን ካፋ ህልዉናዉንና፣ መሬቱን ማለትም የሃብት መሰረቱን፣ ያጣዉ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ነዉ፡፡ ለሃብትና ለመሬት ዘረፋ እንዲመቸዉ፣ ኢህአዴግ ካፋንና አጎራባች ህዝቦችን ከፖለቲካ ሥልጣን ዉጭ በማድረግ፣ ከሚወራለት የፌደራል ሥርዓት አሰራር ዉጭ፣ በዉስጥ ጉዳይ ጭምር እንዳይወስን አደረገ፡፡ በመጀመሪያ ፣ ከአካባቢዉ የመለመላቸዉን ካድሬዎች በራሱ ቅኝት አስተምሮ፣ በብሄር አደራጀ፡፡ ከዚያም በደቡብና፣ በካፋ አካባቢ የተመሰረቱ ተቃዋሚ ድርጅቶችን፤ “ኦነግ ሊዉጣችሁ ነዉ” ብሎ አስፈራርቶ “የደቡብ ህብረት” የተባለ ድርጅት እንዲመሰርቱ አደረገ፡፡ ከዚያም ራሱ የፈጠራቸዉን፣ የክልል ባለሥልጣናት ደግሞ፣ “ተቃዋሚዎች ቀደሟችሁ” በማለት፣ “የደቡብ ግንባር የተባለ (አሁን የደቡብ ንቅናቄ) ድርጅት” እንዲመሰርቱ አድርጎ፣ ቀጥሎም የደቡብ ክልልን እንዲመሰርቱ አደረገ፡፡ በርግጥ ከህብረቱም ከግንባሩም ለዓላማዉ የተመቻቹም ሆነ፣ ቀዝቃዛ ስሜትና ተቃዉሞ የነበራቸዉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የህብረት አባል የነበረ፣ ግን እስካዛሬም ለራሱ ክልል እየታገለ ያለዉን፣ የሲዳማ ህዝብ በምሣሌነት መዉሰድ ይቻላል፡፡

 

ይህ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የተደራጀን ህዝብ አመራርና፣ በተናጠል የሚደረግ ጉዞን ለማነፃፀር ይረዳል፡፡

 

በዚህም ካፋ እና አጎራባች ህዝቦች ከሺህ ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘዉ ደቡብን ሲቀላቀሉ፣ ሴራዉም፣ ለቀጣዩ አፈናና ዝርፊያ ዝግጅት መሆኑ አሁን ግልፅ ሆኗል፡፡ በራሳቸዉ ሲተዳደሩ የነበሩ፣ አሁን ግን ከአዋሳ ርቀት ሌላ፣ እንደማንኛዉም ክልል፣ የራሳቸዉን ፖሊሲ፣ ህግና ደንብ እንዳያወጡና እንዳይተገብሩ፣ የራሳቸዉ አመራር እንዳያቋቁሙ ሆነ፡፡ በደቡብ ክልልና የበላያቸዉ ሆኖ፣ ከሚመራቸዉ የህወሃት ቁልፍ ሰዉ በሚሰጥ ትዕዛዝ የሚፈልጉትን ሁሉ አደረጉ፣ ህዝቡም ወደ ባሰ ድህነት ወረደ፡፡ ደቡብ፣ በየደረጃዉ ተላላኪዎቹን እየመደበ ሲፈልግ አወረደ፣ የፈለገዉን መሬት በተለይም ጥቅጥቅ ደን ወረሰ፣ ግንድና ጣዉላ ነገደ፣ በወታደር እያሰገደደ የማይጠቅመዉን ማዳበሪያ ለገበሬዉ አደለ፣ ክፍያዉንም ጥሪቱን በማሸጥ አስከፈለ፣ ወጣቱ መሬትና ሥራ አልባ ሆኖ ሲቦዝን የሚፈልገዉን በመሬቱ አሰፈረ፣ ለአካባቢዉ ከዉጭ ጭምር የተገኘ ሃብትና ድጋፍ አደናቀፈ፣ ሌላም…. ወዘተ. አደረገበት፡፡

 

ይህ ሁሉ፣ እንደሌሎች ህዝቦች፣ ከግል ሥልጣንና ጥቅም ይልቅ ለህዝቡ የወገነ፣ ለእዉነት፣ ለህሊናዉና፣ ለህግ ተገዢ የሆነ ለህዝቡ የቆመ ድርጅትና ተከራካሪ ድርጅትና አመራር ባለመኖሩ ነዉ፡፡

 

የህዝቡን ብሶትና ግፍ፣ ነፃነት ለማምጣት የሚያደራጅ፣ የሚያስተምረዉና የሚመራዉ አካል ባለመኖሩ ነዉ፡፡ በየግላቸዉ የሚንጨረጨሩ ግለሰቦች መኖራቸዉ ባይካድም፣ የተደራጁ ባለመሆናቸዉ ጥረታቸዉ የትም አልደረሰም፡፡

ህዝቡም፣ ጫናዉን መሸከም ስለከበደዉ፣ ባጋኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ስሜቱን መግለፅ ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ ለደቡብ ንቅናቄ ሊ/መንበርና፣ ለአፈ-ጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል፣ የክልል ጥያቄን ጨምሮ፣ ደረሰበትን ዘረፋና በደል በምሬት አቅርቧል፡፡ ቢሆንም ይህንን ጥያቄ ክልሉና አለቃቸዉ የፈጠረዉ ተላላኪ ሊያከሽፍ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ሥልጣንና ጥቅም የተሰጣቸዉ አስፈፃሚዎች፣ የአገዛዙ ምስለኔዎችና ሹመኞች ሃላፊነታቸዉን ይወጣሉ፡፡ የወቅቱ ለዉጥም ከዚህ ሥልጣንና ጥቅም ስለሚነቀንቃቸዉ፣ የህዝቡን ጥያቄም ሆነ ማንኛዉንም የለዉጥ ሂደት ማደናቀፋቸዉ አይቀርም፡፡ ምናልባትም ቆዳቸዉን ለዉጠዉ በአዲስ መልክ ሥልጣን መቆናጠጥ፣ ለዉጡን ማሰናከልና፣ ህዝቡን መደፍጠጥ መቀጠላቸዉ የማይቀር ነዉ፡፡ ይህንንም ለማገለጥና ለዉጡን ለማገዝ የሚችል ድርጅት ስለሌለ፣ በግላቸዉ የሚታገሉ ንፁሃንም ብዙ መጓዝ አይችሉም፡፡

 

ይህም የተደራጀ፣ ለህዝቡ ወገናዊና ተዓማኒ ድርጅትና አመራር ባለመኖሩ እየቀጠለ ያለ ግፍና ጫና ነዉ፡፡

 

ህዝቡ ከዚህ የሚያወጣዉ በቁርጠኝነት ተማምኖበት የሚከተለዉ ድርጅትና አመራር ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አዲስና ተዓማኒ ድርጅትና አመራር ካልተፈጠረና ህዝቡን ካልመራዉ፣ የካፋ ህዝብ እስካሁን ካጣዉ ጥቅም በባሰ ሁኔታ ወደ ዉድቀት ማምራቱ የማይቀር ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተፈጠረዉን አጋጣሚ ተጠቅሞ በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ፣ የለዉጡ አካል መሆን፣ አስተዋፅኦ ማድረግና፤ ከለዉጡም ተጠቃሚ መሆን፣ ወቅታዊ ጥያቄ ነዉ፡፡ የመደራጀቱ መነሻም የቆየዉን የህዝቡን ጥያቄ መመለስ እንጂ፣ በማንም ግፊት አይደለም፡፡

 

ዓላማዉ ደግሞ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ቢቻል ለምሥራቅ አፍሪካ አንድነት ነዉ፡፡ ጤነኞች ሁሉ፡ ለዚህ መሰረታዊ መርህና ግብ ሊቆሙ ሲገባ፣ በመከባበርና በፍትሃዊነት ሊሆን ግን ይገባል!!

 

 

II. የአመራር አማራጮች፣ ሥጋቶችና፣ ዕድሎች

 

II.1. ለዉጡ በኢህአዴግ አማካይነት እንዲመጣ መጠበቅ፤

 

ኢህአዴግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃዉ የተመደቡ ካድሬዎችና ከአስተዳዳሪነት እስከ ኤክስፐረትነት እየተቀያየሩ ያሉት፣ በኢህአዴግ ዉስጥ ራሳቸዉን ያደራጁ፣ በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበሩ፣ የጓደኛሞች ስብስብ ነዉ፡፡ ይህ ቡድን ገፍቶ፣ ግምገማ ሲበረታባቸዉ በመደጋገፍ መሰረታዊ ወንጀላቸዉን በቡድናቸዉ አማካይነት ተደባብቀዉ ምንም መሰረታዊ ጉዳት ሳይደርስና መጠየቅ ሣይኖርበት፣ ከሃላፊነት ለጊዜዉ እንዲገለሉና ይደረጋሉ፡፡ በዚህም ወቅት ጥቅማቸዉ ተጠብቆ ዝቅ ባለ የሃላፊነት መደብ ተሸሸገዉ ይቆያሉ፡፡ ሆኖም ጉዳያቸዉ ሲረግብ ቀስ በቀስ፣ በቀሩትና በተረፉት፣ ምናልባትም ከፍ ወዳለ ቦታ ተመድበዉ በቆዩ የቡድን አባሎቻቸዉ ተጎትተዉ በተሻለ ቦታ፣ ወደ ወሳኝ ቦታቸዉ እየተመለሱ የቆዩ ናቸዉ፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን አካባቢዉን የሚዘዉሩት በአንድ ወቅት በመሃላ ተሳስረዉ የተሰባሰቡ በቡድን የተሳሰሩ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ ከነበረበት ከፍተኛ ሥልጣን የተወገደ አባላቸዉ እንኳን ቢሆን በወቅቱ ሥልጣን ላይ ባይሆንም፣ ሁሉም ወሳኝ መረጃ ከነዚሁ አባላቱ ይደርሰዋል፡፡ በዓመታት ባዳበሩት የድርጅት አሰራርና ልምድ፣ የቢሮክራሲ ልምድ፣ ሥልጠናና፣ ሥልት ተጠቅመዉ በየወቅቱ የሚነሱ የአካባቢዉን ጥያቄዎች ተረባርበዉ የማለዘብ ሥራ በጋራ ይሰራሉ፣ የተዳፈነ ተግባራቸዉ እንዳይወጣ ይረባረባሉ፡፡ በአፈ-ጉባኤዋ የተመራዉ ስብሰባ ላይ ህዝቡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብዙ የጠየቀ ቢሆንም ይህ ቡድንና ሰንሰለቱ ግን አሁንም ተኮፍሰዉ በየመድረኩ ታይተዋል፡፡ ምናልባትም የለዉጡን ሂደት በተመለከተ አለቆቻቸዉ ሃላፊነት የሰጡት ለእነርሱ፣ አዲስ እየተመረጡ ነዉ የተባሉትም የእነርሱ ታዛዥና ጉዳይ አስፈፃሚ አለመሆናቸዉን ለማረጋገጥ ገና ነዉ፡፡ ሆኖም ግን ሰንሰለቱ በሥልጣን ላይ የሌሉትን ጭምር ይዞ መቀጠሉንና ዉዥንብር እየፈጠረ እንደሆነ የሚያሳዩ ጭምጭምታዎች አሉ፡፡ ይህ ቡድን በየወቅቱ እይተዋለደ፣ ተስፋፍቶ በአካባቢዉ ምንም ዓይነት መሰረታዊ ለዉጥ እንዳይመጣ ተብትቦ የያዘ ስለሆነ እነዚህን ይዞ፣ ለዉጥ በኢህአዴግ አማካይነት ይመጣል ማለት የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ካፋና አጎራባች ዞኖች ዉስጥ እንደሌሎች አካባቢዎች የሚታመንበት የለዉጥ ሃይል አለመከሰቱ፣ አሁን በማዕከል ደረጃና በሌሎች አካባቢዎች፣ ከሚታየዉና ከመሪዎቹ ከሚነገረዉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ አኳያ ሲታይ አለመታደል ሲሆን አሁንም አካባቢዉ ሌላ ዕድል እንደሚያመልጠዉ አመላካች ነዉ፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በአካባቢዉ ያሉትን እስካሁን ህዝቡን ያስመረሩ አባላቱን ሙሉ በሙሉ በአንዴ ጠራርጎ በአዲስ ይተካል የሚል ግምት አይኖርም፡፡ ምሁራንና ሃቀኛ የአካባቢዉ ልጆችም ከአሁን በሁዋላ በኢህአዴግ ይታቀፋሉ፣ ጠቅላይ ሚ/ሩ የሚሉትን አይነት አካሄድና አመራር ቢመኙም በድርጅቱ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ለዉጥ ይመጣል ብለዉ ይጠጋሉ ወይም አምነዉ ይቀርባሉ ማለት ከባድ ነዉ፡፡

 

II.2. ከኢህአዴግ ጋር የሚደጋገፍ አዲስ ሃይል፤

 

የአካባቢዉ ህዝብ በመሰረታዊነት፣ የኢህዴግ መርህ ተቃዋሚ አይደለም፡፡ በማንነቱ የተበደለና የተናቀ በመሆኑ በአግባቡ ቢተገበር ኖሮ ባህሉን፣ ታሪኩንና ቋንቋዉን ማሳደግ ሚፈልግ ነዉ፡፡ መሬትን በተመለከተም በተፃፈዉ ህግ መሰረት ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፣ በቂ የራሱ መሬት ኖሮት፣ የወልና የመንግስት ተብለዉ የተከለሉ፣ የግጦሽና የደን መሬቶችን፣ ከራሱ ማሳ በላይ ጠብቆ የሚያለማ ሥራ ወዳድና ታታሪ ህዝብ ነዉ፡፡ ጥቃቅን በደሎች እየተደራረቡም ቢሆን በሂደት ይስተካከላል በሚል በትዕግስት የቆየ ህዝብ ነዉ፡፡ በተለያየ መንገድና በተለይም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በሰፈራ ከመጡ በርካታ የኦሮሞ፣ አማራ፣ የትግራይ ተወላጆች ጋር፣ እንዲሁም በራሳቸዉ ጊዜ እየመጡ ከሰፈሩ በርካታ ህዝቦች ጋር በሰላም የሚኖር የአብሮነት ምሣሌ የሆነ ህዝብ ነዉ፡፡ ለዘመናት ከአያት፣ ቅድመ-አያቶቻቸዉ ጀምሮ የጠበቁትንና የሚሳሱለትን ጥቅጥቅ ደን በአጭር ጊዜ ሲዘርፉና ሲያወድሙም በአግባቡ የሚለማ ከሆነ፣ በሚል ትዕግሥት ሲታዝቡ የቆዩ ህዝቦች ነዉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአካባቢዉ ችግር በአሁኑ የኢህአዴግ የለዉጥ ጉዞና በተፈጠረዉ ሃገራዊ የተስፋ ጭላንጭልና ዕድል ብቻ የማይፈታ፣ በአካባቢዉ በተከማቹ የአካባቢዉ የኢህአዴግ አባላትና በክልሉ ባሉ አለቆቻቸዉ ምክንያት፣የተገመደ ዉ ስብስብ ችግር ስለሆነ፣ በኢህዴግ በኩል ሊለወጥ የሚችል አይመስልም፡፡

አዲስ ድርጅት ተመስርቶ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ ሊሰራ ይችላል ወይ የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም እንዳይባል ደግሞ ኢህአዴግ ራሱ ከአንድ አካባቢና ህዝብ የወጣ፣ ከአንድ በላይ አባል ድርጅት ማቀፍ ስለማይፈቅድ ዕድሉ የመከነ ነዉ፡፡ ምናልባት የሚቻለዉ የትብብር መንገድ፣ ኢህአዴግ በያዘዉ የመለወጥ መንገድ ከቀጠለ ፣ በማዕከልና በተወሰኑ ክልሎችና አካባቢዎች የሚታየዉ አዝማሚያ ከቀጠለና፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ከተቻለ ሌላዉ አማራጭ ሊኖር ይችላል፡፡ ይኸዉም፣ ኢህአዴግ በአባላቱ አማካይነት ከደረሰዉ ግፍ አኳያ፣ በዚህ አካባቢ የማሸነፍ ዕድሉ አነስተኛ ስለሆነ፣ አካባቢያዊም ሆነ አገር አቀፍ ድርጅት እንደሌሎቹ ማሸነፉ ስለማይቀር፣ አጋር ድርጅት ሆኖ ግን ነፃነቱን አስጠብቆ መቆየት ከቻለ፣ ለአገሪቱ፣ ለኢህዴግ፣ ለመጪዉ ድርጅትም ሆነ፣ ለአካባቢዉ ህዝቡ የሚበጅ ይሆናል፡፡

 

II.3. የተሻለዉ፣ ዘላቂዉና ተመራጩ መንገድ፤

 

ተጨባጩ ሁኔታ ሲታይና ቃል የተገባዉ ዲሞክራሲያዊነት ተግባራዊ ከሆነ፣ በአካባቢዉ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በአዲስ መልክ የሚደራጅ ሃይል፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራጅተዉ ግን ደግሞ የአካባቢዉን ህዝብ ጥያቄ ከግምት የሚያስገቡ ድርጅቶች ተጠናክረዉ በአካባቢዉ ሥልጣን ቢይዙ ይመረጣል፡፡ ካለዉ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ይህ ቅድመ- ሁኔታ ከተሟላ፣ በአካባቢዉ ባሉ፣ መልካም ስም ባላቸዉ የአካባቢዉ ምሁራን የሚመራ፣ ህዝባዊ ወገንተኛና ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያን፣ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎችና፣ ገበሬዎች የተሳተፉበትና፣ በተለይም ለዉጥ ፈላጊ የለዉጥ አራማጅ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ የሚመሰረት ድርጅት ይመረጣል፡፡ የህ ዓይነቱን ድርጅት መስርቶ ማጠናከር አድካሚ ቢሆንም፣ በዚህም ሆነ በዚያ ግን ሥልጣን መያዙ የማይቀር ነዉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጅትዕዉን ከሆነ ደግሞ አካባቢዉንና ህዝቡን ከሌላዉ የኢትዮጵያዊ አካባቢዎች እኩል እንደሚያለማና እንደሚያሳድግ መተማመን ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጅት፣ ከሁሉም በላይ በባለሙያ የሚመራ፣ የሃገሪቱን ህግ የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን በትጋት የሚጠብቅ፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ ለሌሎች አካባቢዎች ምሣሌ የሚሆን አሰራር የሚያሳይ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም፣ ቀጣዩ የአካባቢዉ አስተዳደር ፈተና ከባድና ዉስብስብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ህዝቡና በተለይም አሁንስ በቃኝ ብሎ የተነሳዉን ህዝብና ወጣት በብልህነት ማሳተፍፈ የሚችል ከአካባቢዉ በቀለ ድርጅት ለዉጥ ለማምጣት ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ የአካባቢዉ ህዝብ ደግሞ ጨዋ፣ ጠንቃቃና ራሱን በራሱ አደራጅቶ የሚጠብቅ ስለሆነ፣ ተገቢዉን የሚያምነዉን ፖለቲካዊ አመራር ካገኘ ካፋም ሆነ ሌላዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተስፋ ብሩህ ኢንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ የአካባቢዉ ህዝብ ለዓመታት በሰንሰለት ታስሮ፣ አካባቢዉ ሃብቱ ሲዘረፍና መብቱ ሲረገጥ የቆየ መሆኑ በአደባባይ ስለወጣና፣ ብሶቱን ማቅረብ ስለጀመረ፤ ያለዉ አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ከሚታየዉ አጓጊ ለዉጥ፣ እና ከተፈጠረዉ አመቺ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከህዝቡ አደረጃጀትና ንቃተ-ህሊና አኳያ ሲታይ ወቅቱ አሁን መሆኑን ያሳያልና፣ መፍጠን ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ ወደ ሁዋላ መመለስ በማይችልበት መስመር ዉስጥ መግባቱ ግልፅ ነዉ፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ያግበሰበሳቸዉን አባላት እስከሚያጠራ ጊዜ ይወስዳል፡ አካባቢ በቀልና በህዝቡ ተዓማኒ ድርጅት ካልመጣ፣ አሁንም የ27 ዓመቱ የጅቦች ቡድን በለመደዉና ባካበተዉ ልምድና ሥልት፣ እንደእባብ ቅርፊቱን አዉልቆ፣ ከለዉጡ ሃይል ጋር ተለጥፎና ተመሳስሎ፣ የህዝቡን ጥያቄ እንደሚነጥቅና እንደሚያኮላሽ፣ ህዝቡንም ለባሰ ጥያቄ ልያነሳሳና፣ ምናልባትም ወደ አደጋ ሊያመራ ይችላል፡፡ ፡ እስካሁን ማመን የምንችለዉ በጣም ጥቂት አመራሮች የሚናገሩትንና የበላይ አመራሩ ተግባራዊ እያደረገ ያለዉን ብቻ ነዉ፡፡ ከሚመሰረተዉ ድርጅት ከሚጠበቁት፣ በአካባቢዉ ያሉ ንቁና፣ ዝግጁ፣ በመረጃ የተሞሉ ወገኖችን ማሳተፍ፣ ቃል የተገባዉ ለዉጥ በተግባር እስኪዉልና፣ የክልል ጥያቄን ጨምሮ ገና ያልተነሱ ጉዳዮች እስኪመለሱ፣ በሰለጠነና በተረጋጋ ሁኔታ መታገልና ጥያቄዉን መቀጠል ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡ የሚየምነዉ፣ ህጋዊ ድርጅት ከአካባቢዉ መፈጠርና አማራጭ ሆኖ መገኘት ለአካባቢዉ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር አቀፉ የለዉጥ ሂደት ድጋፍ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡

ከG.C

ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: