Leave a comment

ከራሳችን ላይ ውረዱ


ከራሳችን ላይ ውረዱ

የሰው ልጅ የሚዉለድበትና የሚሞትበትን ቦታ ቀንና ዘመን ከማን መወለድ እንደሚፈልግ መምረጥ ኣይችልም:: የመምረጥ እድሉ ቢሰጠን ብዙዎቻችን ከሃብታም ቤተሰብ ብንፈጠር ከታዋቂ ቤተሰብ ብንወለድ እንመርጥ ነበር ከራሴ ጀምሮ:: የሰው ልጅ መኖሪያውን መምረጥ ይችላል:: በህይወት ዘመኑም ምን መሥራት እንደሚፈልግ ምን ኣይነት የህይወት ጏደኛ መያዝ እንዳለበት በትምህርትም ምን መማርና ማን መሆን እንደሚችል ቢሳካም ባይሳካም በራሱ ምርጫ መሄድ ይችላል:: መምረጥ የማይችለው ዘሩን ቀለሙንና ፆታውን ሀገሩን የትውልድ ቦታውን ነፃነቱን ሲሆን የሚታደለው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው::

እኛ በተለያየ የዛሬይቱ የኢትዮጵያ ምድር ላይ ስንፈጠር በኛ ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ምንም እንኳን ሁላችንም የኣዳምና ሔዋን ልጆች ብንሆንም ኣሁንም ደም ሥጋና ኣጥንታችን ኣንድ ነው:: ይህም የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ ሊደነቅ ይገባል:: በሂደት በተፈጠረው የነገድ ክፍፍል ኣፍሪካ እሲያ ኣውሮፖና ኣሜሪካ እንዲሁም በተለያየ የዓለም ክፍል ተሰራጭተን በመኖር ላይ እንገኛለን:: ቀለማችን ባህላችንና ወጋችን ቋንቋችን ኣለባበሳችንና ኣመጋገባችንም ተመሳሳይነትና ልዩነት ኣለው::

ባይገርማችሁ ያኔ ድሮ በልጅነቴ የፈረንጅ ፎቶ በወረቀት ላይ ሳይ ፈረንጅ ሰው ሳይሆን መልኣክ ይመስለኝ ነበር:: እህል የሚበላ ውሀ የሚጠጣ የሚታመም ወይም የሚሞት ኣይመስለኝም ነበር እንደማንኛውም ሰው:: እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቻችን የእኔ ኣይነት እይታ ዛሬም ድረስ እንዳላችሁ እገነዘባለሁ:: ፈረንጅ ሁሉን የሚያውቅና ቆዳው ስለነጣ ብቻ ከኛ የተሻለ የሚመስለን ኣለን:: ለራሳችን ሰው ምን ቢማር ያን ያህል እውቅናና ኣክብሮት መስጠት የተለመደ ኣይደለም:: የራሳችንን ማጣጣል የውጭውን ማንገስ እንወዳለን::

በርግጥ ፈረንጅ በኣንዳንድ ነገሮች ይበልጠናል:: ኣንዱ ሲሰራ ለመልካም ስራው እውቅና ሰጥቶ ያበረታታል:: እኛ ኣንዱ የሰራውን እናፈርሳለን እንጂ ጎሽ በርታ ኣንልም:: ፈረንጅ እውቀቱን ያካፍላል እኛ ግን ከኛ በላይ ኣዋቂ እንዲኖር ኣንፈልግም እውቀታችንን ለትውልድ ከማስተላለፍ ይልቅ ይዘን እንቀበራለን:: ለልጆቻችን እንኳን ኣናስተላልፍም:: እኛ ኣንዱ ሲገነባ ሌሎቻችን ከሥር ከሥሩ እየሄድን እናፈርሳለን:: መንግሥታት በተለዋወጠ ቁጥር ህገ መንግሥት እንቀይራለን ለራሳችን ኣገዛዝ በሚያመች መልኩ:: ብቻ ስንገነባ ስናፈርስ እንደ ልጆች እቃ እቃ ጨዋታ ስንጫወት ፈረንጅ ብልጡ በኛ ሥራ እየሳቀ በኣንድም ሆነ በሌላ መልኩ ዘመድ መስሎ ይጠጋንና ጥሬ ሀብታችንን ጠራርጎ በመውስድ ወደ እንዱስትሪ ውጤት ይለውጥና መልሶ ለኛን በውድ ዋጋ ይሸጥልንና ሀገሩን ያሳድጋል:: የደቡብ ምዕራብ ደን ተጨፍጭፎ ኣረብ ሀገር ወይም እስያ ተወስዶ የኢንዱስትሪ ውጤት ወደሀገራችን ቢገባም የካፋ ህዝብ ግን ተጠቃሚ ኣይደለም:: የካፋን ቡና ስታር በክስ (Starbuks) የተባለው ድርጅት በተዘዋዋሪ ከሲዳማው ይርጋጨፌ ኣስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ከሚደረግለት ቡና ላኪ ጅርጅት በኣለም ገበያ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጎ የቡናው ባለቤት ካፋ ግን መንግሥትና ግብረ ኣበሮቹ ባቀነባበሩት ሴራ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ከጨዋታ ውጭ እንዲሆን ተደርጎ የበይ ተመልካች እንዲሆን ተወስኖበት ኣንድ እግር ቡና የሌላት ኤርትራ በኣንድ ወቅት ቡና ኢክስፖርት እንድታደርግ ተደርጏል:: ይህ ህዝብ የደረሰበትና እየደረሰበት ያለው ግፍና በደል ተዘርዝሮ ኣያልቅም:: ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልና::

ሰሞኑን ደግሞ ከወደ ሀገር ቤት የቡና ቀን ተቆርጦ በኢትዮጵያ ኣየር መንገድ ኣስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የቡና ቀን ሊከበር ሽር ጉድ እየተባለ ነው:: በእርግጥ ኣየር መንጉዱ ሰላምታ በተሰኘው መፅሔት ላይ ኣንድ እትሙ ላይ ቡናን ለማስተወወቅ ሞክሯል::ከኣየር መንገዱ ቀድመው የውጭ ፀሐፍት ቡናን ለዓለም ኣስተዋውቀዋል:: ኣየር መንገዱ ግን ለዚህ የቡና መገኛና የኢኮኖሚ ዋልታ ለሆነው ካፋ ለውለታው ለምን ሌላው ቢቀር የሀገር ውስጥ በረራ የኣየር ማረፊያ ኣልሰራለትም ??? ለምንስ የቲኬት መሸጫ ቢሮ ከፍቶ ካፋን ለምን ለጎብኚዎች ኣላስተዋወቀም?? የቡና ሙዝየም ሲሰራ ምን ኣስተዋፅኦ ኣርጏል?? ካልሆነስ ኣሁን የቡና ቀን ብሎ ሽርጉድ ማለቱ ለካፋ ህዝብ የሚያመጣው ምን ፋይዳ ኣለ ወይስ ኣላሙዲንን እግዚአብሔር ቢያላቀን ሌላ ኣላሙዲን ልታመጡብን ይሆን?? ጠርጥር ነው በቅርቡ ዶ/ር ኣቢይ በድብቅ በቃል ኣቀባያቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የህዝብ ማወያየት ሰበብ እሳቸውም የጫካ ቡናውን ኣካባቢ ጎብኝተው ህዝቡን ግን ሳያጉኙት ተመለሱ የሚል ሀሜት ነበር:: እውነቱን እነሱና እግዚአብሔር ያቀዋል ከሆነ ለምን? የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ኣዜብም እንዳይታወቅባቸው በእስልምና ሃይማኖት ልብስ ተከናንባ በሚዛንና በቴፒ ጉብኝት ኣድርገዋል እየተባለ ይታማል:: ይህ ወሬ ከየት እንደመነጨና ለምን እንደተወራም ግልፅ አይደለም:: በዚያው ሰሞን ታዲያ እናንተ ሰዎች እባካችሁ ከህዝቡ ራስ ላይ ውረዱ!!! የቡናውን ቀን እኛ በተመቸን ጊዜ እናዘጋጀዋለንና እጃችሁን ስብስቡ:: መበዝበዝ በቃን ይላል የደቡብ ምዕራብ ህዝብ::

በቱጨማሪ ከኛ የወጡ ፈረንጅ ኣንላቸው የፈረንጅ ሥራ ኣይሰሩ ኣልተማሩም ኣንላችው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፕሮፌሰርነት የደረሱ ወገኖቻችን የወጡበትን ህብረተሰብ ከመርዳት ይልቅ ሥልጣን ሲይዙ ደሀው ገበሬ በማዳበሪያ ዕዳ ማንቁርቱን ተይዞ (በነገራችን ላይ የደቡብ ምዕራብን የመሰለ ለም ምድር ማዳበሪያ ለምን ኣስፈለገው???) ከኣቅሙ በላይ የተጣለበትን ግብር ከፍሎ ነጋዴው የተጣለበት ታክስ ሰማይ ጠቀስ በመሆኑ ሱቁን እስከ መዝጋት ደርሷል:: ራሱ ሳይመገብ ልጆቹን ኣብልቶና ኣልብሶ ኣስተምሮ ሥልጣን ላይ ሲቀመጡ ከባለሥልጣን ጋር በመመሳጠር እከክልኝ ልከክልህ ሆነና ለህዝቡ ብሶትና እሮሮ ጆሮ ዳባ በማለት ዳር ላይ ቆሞ የሚመለከት ብዙ የተማረ ወገን ኣለ:: ለመሆኑ የመማር ጥቅሙ ምንድነው? ኣንዲት እናት እሳቸው ፊደል ኣልቆጠሩም ነገር ግን የሀገራቸው ጉዳይ ያንገበግባቸዋል:: ቶሌቪዥን ላይ ተተክለው ነው የሚውሉት እና ምን ኣሉ መሰላችሁ “እኔ ባለመማሬ በጣም ይቆጨኝ ነበር ኣሁን ግን ባለመማሬ እግዚአብሔርን ኣመሰገንኩት” ኣሉ ለምን ብላቸው ኣሁን እንደማየው ሀገራችንን እየበጠበጡ ያሉት ተማርን የሚሉት ናችው:: ድሮ በሰላም ተስማምተን በፍቅር እንኖር ነበር ዛሬ ግን ኣንዱ ኣንድ ሀሳብ ሲያመጣ ሌላው ይቃወማል::ዘጠና ዘጠኝ ቦታ ተከፋፍሎ እኛንም ግራ ኣጋባን የተማረው ብለው ኣማረሩ:: እውነት ኣላቸው ኣሁንም ኣንዱ ሲገነባ ሌላው እየናደ ከ2010 ወደ 2011 ብንሸጋገርም ኣሁንም በኣዲሱ ዓመት ማግስት በኦነግ ደጋፊዎችና በሌሎች መካከል ኣዲስ ኣበባ ላይ የተነሳው ግጭት ኣባባላቸውን ያጠናክረዋል:: መማር እንዲህ ከሆነ ያለመማር የሚበጀው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: የዱቡብ ምዕራብ ምሁራን እባካችሁ ወዱፊት ኑና ህዝባችሁን ታደጉ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ:; ምነው ሳይንቲስት ኢንጅነር ቅጣው እጅጉን ሞት ባይቀድመው ኖሮ:: ሰው ብቻ ኣይደለም የካፋ ጠላት ሞትም የኛ ጠላት ነው:: ጋኪ ሻሮችን የመሰለ ጀግና ንጉሣችንን ነጠቀን በዛ ብሎ ደግሞ ስንት ራዕይ የሰነቀውን ቅጣውን:: በቃ ተውን እንደመዥግር ተጣብቃችሁ ደማችንን ኣትምጠጡ:: ደማችን ኣልቋል እስቲ ሄድ በሉና ህዝቡን ተመልከቱት:: ሥጋው ኣልቆ በኣጥንቱ የቆመ ህዝብ ነው:: ለቆጮ ምሥጋና ይግባውና ተራብኩ ብሎ ኣደባባይ ወጥቶ ኣለመነም:: በነገራችን ላይ ልመናን የሚጠየፍ ኩሩ ህዝብ ያለው ደቡብ ምዕራብ መሆኑን የምታውቁ ስንቶቻችሁ ትሆኑ??? ይህ ብቻ አይደለም ከጥንት ጀምሮ የራሷ ታሪክ ያላት ሚክርቾ(ምክር ቤት) ጊጄ ራሾ (ገንዘብ ሚ/ር) ካተመራሾ (ከንትባ) ናሌ ጣኦ (ፍ/ቤት) የዋሻ ጉርጉቶ የተፈጥሮ ድልድይ ለምለምና አረንጓዴ ደኑ የቀርቀሀ ሀብቱ የፍል ውሀ እና ወዘተ ያላት ውብ ምድር ነች!!
ከፋንታዬ መኮ
ካፋ ሚዲያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: