2 Comments

የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው᎓᎓ ይድረስ ለእሳት ጋዜጠኛ ለክቡር ኤርሚያስ ለገሰ


47054593_119579559055790_3639942439277428736_oየደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው᎓᎓ ይድረስ ለእሳት ጋዜጠኛ ለክቡር ኤርሚያስ ለገሰ
ከቶጴ ማላ  ኖቨምበር 27 ቀን 2018
ክቡር ኤርሚያስ
አንተ ማነህ?ብሉኝ ስለራሴ እምብዛም የማወረው ያሸበረቀ ገድል የለኝም᎓᎓ ማንነቴ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ግን አይጠራጠሩኝ᎓᎓ ለዚያውም የኮራሁ᎓᎓ ስለኢትዮጵያም ሆነ ኢትዮጵያዊነት የእርስዎኑ ያህል በሚገባ አውቃለሁ ብዬ በድፍረት መናገር እችላላሁ᎒ ምናልባትም የአተያየታችን መነጽር በጥቂቱ የሚለያይ ልመስል ይችል ይሆናል እንጂ᎓᎓ ይቅርታ ያድርጉልኝና እርስዎን ያወቅሁት ከሰሞኑ ነው᎓᎓ እርስዎ እዚያ ካናዳ ቶሮንቶ ከተማ ኖቬምበር 17 ቀን 2018 ዓመተ ምህረት በተካሃደው የኢሳት fundraising ስብሰባ ላይ ያሰሙትን ንግግር ሰማሁ᎓᎓ ንግግርዎን በጥሩ መንፈስ እያደመጥኩ ሳለሁ ወደኋላ ላይ የደቡብን ህዝብ ደጋግመው ከከብት ጋር ሲያመሳስሉ በአድማጭዎቾ ጭብጨባ እርስዎ በፈገግታ ስሞሉ᎓ እኔ ደነገጥኩ᎓᎓ ደቡብ “የብሄር ክልል ነው᎒ የዘር ክልል ነው᎓᎓ እኔ ማቆነጃጀት አልፈልግም᎓᎓ የዘር ክልል ነው አሁን” ስሉ ግርም አለኝ᎓᎓ ለመሆኑ የአማራ ክልል የምን ክልል ነው?የብሄር አይደለምን?የዘር አይደለምን?የትግራይ ክልል የምን ክልል ነው? የብሄር አይደለምን?የዘር አይደለምን?የኦሮሚያ ክልል የምን ክልል ነው?የብሄር አይደለምን?የዘር አይደለምን?ሌሎችስ ቢሆኑ የምን ክልል ናቸው?ካነሱት አይቀር እስካሁን በዘር ያልተከለለ የኢትዮጵያ ክፍል ቢኖር ደቡብ ብቻ ነው᎓᎓ የክልል ትርጉሙ ዘር ወይም ብሔር የሚሆነው የደቡብ ሕዝቦች እንዴሌላው ህዝብ የመብት እኩልነታችን ይከበርልን በማለታቸው ነው ወይ? ያሰኛል᎓᎓ ይህን ሳስብ ስለኢትዮጵያ ያሰላሰልኩትን ባካፍልዎ ቅር እንደማይሰኙ እገምታለሁ᎓᎓

ኢትዮጵያ ሁለት ስብዕና ያላት ሀገር ነች᎓᎓ ሁለት የተለያየ ስብዕና የተላበሰች ሀገር᎓᎓ ባንድ በኩል የዕድሜ ባለጸጋነቷን በገሃድ የሚያሳይ ያረጀ የሰከነ የአዛውንትነት ስብዕና ስኖራት᎒ በሌላ በኩል ደግሞ በሁለንተናዊ ማንነቷ ገና ያልተማመነች ተሰርታ ያላላቀች ወጣት ስብዕና አላት᎓᎓ እድሜ ልኳን እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ስብዕናዎች እንዳሏት በውስጠ ልቦናዋ አሳምራ ቢታውቀውም ቅሉ᎒ በውጫዊና በገሃዳዊ ማንነቷ ስትክድ ነው የኖረችው᎓᎓ ራሷን እንከን የለሽ ምሉእ አድርጋ መቁጠር ብቻ ሳይሆን እንከን የለሽነቷን ለማሳመን ከርሷ የተሻለ አንደበተ ርቱዖችንም አፍርታለች᎓᎓ነባራዊ እውነትን ወይም ፈረንጆቹ ኦብጀክቲቭ ሪያሊቲ የሚሉትን ሐቅ አምና ባለመቀበሏ ከራሷ ጋር ትግል ስትገጥም ትታያለች᎓᎓ ልጆቿን ስትጎሽምና ልጆቿም ስጎሽሟት ማየት የተለመደ አሳዛኝ ታሪኳ ሆኖ ቆይቷል᎓᎓ ልብ ብሎ ለተመለከተ ሰው ግን የዚህ ክፍልፍል ስብዕና (schizophrenic personality ) መሰረታዊ መንሥኤው ከባሎቿ የወረሰች አባዜ መሆኑን መገንዘብ አዳጋች አይሆንም᎓᎓ እንደ ዕድሏ ሆኖ እስከዛሬ ያገቧት ባሎቿ በሙሉ በጥፊና በእርግጫ ናላዋን ከማዞር በቀር እሷንም ሆኑ ልጆቿን በወጉ ሰብስበው በፍቅር ከማሳደግ ይልቅ ወደጡጫ የሚያዘነብሉ አመለ ቢሶች ነበሩ᎓᎓ ለነገሩ ባሎቿ በሙሉ ያለፍላጎቷ የመጡ እንጂ እሷ ፈቅዳና ወዳ ያገባቻቸው አልነበሩም᎓᎓ ብዙዎቹን ያገባችው ተጠልፋ ሲሆን᎒ ሌሎቹ ደግሞ በቤተሰብና በዘመድ ተመርጠው የቀረቡላት ነበሩ᎓᎓ የምገርመው ነገር ሁሉም ከእኔ በቀር ማን አለ ባዮች በመሆናቸው በትዳሯ ደስታና ሰላም አልነበራትም᎓᎓ ሁሌም ጭቅጭቅና ንትርክ᎒ ሁሌም ብጥብጥና ድብድብ የነገሰበት ጋብቻ ነበር᎓᎓ ሰላም የመሰለበት ጊዜም ቢሆን ለነፍሷ ፈርታ የሆዷን በሆዷ አምቃ የኖረችባቸው ዘመናት ናቸው᎓᎓
ታዴያ ከዚህ አይነት ጋቢቻ ከአብራኳ የወጡ ልጆቿም ጸባያቸው ለየቅል ነው᎓᎓ ባሎቿም ቢሆኑ በልጆቻቸው መካከል አድልዎ የሚያደርጉ᎒ አንዱን ከሌላው አስበልጠው ወይም አሳንሰው የሚያዩ ስለነበሩ᎒ አንዳነዶቹ ልጆች የአባታቸውን ፈለግ ስከተሉ ማየት የተለመደ ሆኗል᎓᎓ ስለዚህም ከእናት በኩል ካላቸው የጋራ ወንድማማችነት ይልቅ የአባት ልጅነትን ሲያስበልጡ ይታያሉ᎓᎓ የአንድ እናት ልጆች መባባሉ ቀላልና ትርፋማ ቢሆንም ቅሉ የአባቶቻቸውን ወገን ፍለጋ ማትኮሩን መርጠውታል᎓᎓ ችግሩ አባታቸውን በወጉ የማያውቁ የእናት ኢትዮጵያ ልጆች የእንጀራ ልጆች ሆነው መቅረታቸው ነው᎓᎓
ክቡር ኤርሚያስ
እነዚህ የኢትዮጵያ የእንጀራ ልጆች ተከማችተው የሚገኙት በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ስለሆነ “ደቡቦች” የሚል የግድየለሽነት ታርጋ ተለጥፎባቸዋል᎓᎓ ሌሎቹ እያንዳንዳቸው በግል ስማቸው እየተጠሩ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተደርጎአል᎓᎓ መኖሪያ አካባቢያቸውም በራሳቸው ስሞቸ ተሰይሞና ተከልሎ ተሰጥቷል᎓᎓ ለአማራው የአማራ ክልል ተብሎ ተሰጥቶታል᎒᎒ ለትግሬው የትግራይ ክልል ተብሎ ተሰጥቶታል᎒᎒ ለኦሮሞው የኦሮሚያ ክልል ተብሎ ተሰጥቶታል᎒᎒ ለሱማሌውና ለአፋሩም እንዲሁ᎓᎓ ሌላው ቀርቶ በአንድ የጀጎል ግንብ ውስጥ ለሚኖሩ ሀራሪዎችም የራሳቸው ክልል ተፈቅዶላቸው ሳለ ᎒ ወደ 60 የሚጠጒ የኢትዮጵያ የእንጀራ ልጆች ግን በጅምላ “ደቡብ” የሚል የወል ስም ተሰቶተዋቸው በአንድ ጎተራ እንድታጨቁ ተደርጓል᎓᎓ እነዚህ የየራሳቸው ቋንቋ᎒ ባህል᎒ ወግና ሰፊ ምጣኔ ሃብት ያላቸው እያንዳንዳቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦችን ያቀፉ ናቸው᎓᎓ ይሁንና ከጥንት እስካሁን የተፈራረቁ የሀገሪቱ መሪዎች ትኩረት ሰጥተው የቆዩት በህዝቡ ላይ ሳይሆን በምጣኔ ሀብታቸው ላይ ብቻ መሆኑ የማይካድ ነው᎓᎓
ክቡር ኤርሚያስ
የክልል ነገር በኢህአድግ ብቻ አልተጀመረም᎓᎓ ኢህአድግ ለግዛትና አንዱን ከሌላው ጋር ለማላተም እንዲመቸው አደባባይ አወጣው እንጂ᎓᎓ የጥንቱን ሁሉ ትተን ከአያት ቅድም አያቶቻችን ጀምሮ ያለውን እንኳ ብንቃኝ የደቡብ ህዝቦች በዘፈቀደ በሚወሰኑ ክልሎች ሲታጎሩ የቆዩት በተለይም ከ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ አንሥቶ ነበር᎓᎓ ይህን ማንሳቱን እንደማይፈቅዱ ይሰማኛል᎓᎓ እኔም ማንሳቱን አልሻም ነበር᎓᎓ ነገር ግን እርስዎ᎒

“ደቡብ ክልል ተሰነጣጥቆ ተሰነጣጥቆ አሁን 4 ነው 5 ክልል ሊሆን ነው አሁን᎓᎓ የብሄር ክልል ነው የዘር ክልል ነው እኔ ማቆነጃጀት አልፈልግም የዘር ክልል ነው አሁን᎓᎓ ሥማቸውን መጥራት ይቻላል ስለዚህ ተሰነጣጥቀን ተሰነጣጥቀን ወደ ዘር ክልሎች እየሄድን ነው ያለነው᎓᎓ የህዝብ መብት ምናምን ምናምን መብት ነው እሱ᎓᎓ እኔ የማልቀበላቸው የሲዳማ ክልል᎓᎓ የወላይታ ክልል᎓᎓ የከምባታ ክልል᎓᎓ የከፋ ክልል᎓᎓ ነገ ከነገ ወዲያ የጉራጔ ክልል᎓᎓ የብሄር ክልሎች᎓᎓ … በፍጥነት በህግ በብሄር በዘር መካለልን የማገድ ሥራ ካልተሰራ ኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገበው….አለዚያ ተሰነጣጥቀን ተሰነጣጥቀን ተሰነጣጥቀን የምናስባት ኢትዮጵያ ሃሳባዊ እንዳትሆን እፈራለሁ ᎓᎓ በየቦታው የሚነሱ የእንከለል ጥያቄ᎒ ክልል ለከብት ነው የሚሆነው᎓᎓ መከለል ለከብት ነው᎓᎓ ከብት ነው የምከለለው᎓᎓”
ብለው በምሬት ከተናገሩት አኳያ ከውስብስቡ የኢትዮጵያ ታሪክ ለቅምሻ ያህል ማንሳቱን መረጥኩ᎓᎓
የደቡብ ህዝቦች (ኦሮሞን ጨምሮ)በ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ አንሥቶ እሰከ 20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ መነሻውን ከሸዋ መንዝ ካደረገው ከአጼ ምንልክ መራሽ የሸዋ ጦር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኙበት ዘመን አንሥቶ እስካሁን ድረስ እንደዘመኑ መሪ ፍላጎትና ፈቃድ ካንዱ ወደ ሌላው ክልል ስለጠፉ᎒ ስደመሩ᎒ ስቀነሱና ስሰነጠቁ ነው የኖሩት᎓᎓ የዚህ አሰራር ሰለባዎቹ እነርሱ እንጂ ማንም አልነበረም᎓᎓ እርስዎ “እኔ የማልቀበላቸው” ብለው ስለጠቀሷቸው ብሔሮች (ሲዳማ ወላይታ ከምባታና ከፋ) ብቻ ትንሽ ልበልና ፍርዱን ለርሶ እተዋለሁ᎓᎓

እነዚህና በመላው የደቡብ ክልል የሚገኙ ህዝቦች በአጼ ምንልክ ጦር ተሸንፈው ከመጠቃለላቸው በፊት በራሳቸው ንጉሥ የሚተዳደር ሥርዐተ መንግሥት ከላይ እስክ ታች ዘርግተው የሚያስተዳድሩ ኪንግደሞች ነበሯቸው᎓᎓ እርሷ ወደጠቀሷቸው ስንመለስ የወላይታ ንጉሥ ካዎ᎒ የሲዳማ ንጉሥ ሞቲ᎒ የከምባታ ንጉሥ ዎማ᎒ የከፋ ንጉሥ ታቶ በመባል ይታወቁ ነበር᎓᎓ በወቅቱ የነበሩ የነዚህ ብሔር ነገሥታት የወላይታው ካዎ ጦና ጋጋ᎒ የሲዳማው ሞቲ ባልቻ ወራቦ᎒ የከምባታው ዎማ ድልበቶ ደጎዬ እና የከፋው ታቶ ጋኪ ሼሬቾ ይባላሉ᎓᎓ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የምንልክ ጦር ወረራ እጃቸውን ዘርግተው ባለመቀበላቸው ያተረፉት ጠባሳ እስከዛሬ በወጉ አልዳነም᎓᎓ የሲዳማው ሞቲ ባልቻና የከምባታው ዎማ ድልበቶ ሲዋጉ ተገደሉ᎓᎓ ግዛታቸው ተነጥቆ ተወሰደ᎓᎓ ገባር ሆኑ᎓᎓ የወላይታው ካዎ ጦናና የከፋው ታቶ ጋኪ የምንልክን ጦር በተደጋጋሚ ድል አድርገው መልሰዋል᎓᎓ ከምንልክ አስቀድሞ የጎጃሙ ራስ አዳል (በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) የመስፋፋት ሙከራ አድርጎ በነበረበት ጊዜ ታቶ ጋኪ ድል አድርጎ መልሷል᎓᎓ ምንልክ ወላይታን ለማሸነፍ ያዘመቱት ጦር ቁጥር ሥፍር አልነበረውም᎓᎓ የወሎው ራሥ ሚካኤል ጦር᎒ የፊታዉራሪ ገበየሁ ጦር᎒ የሊቀ መኳሰ አባቴ ቧያለው ጦር᎒ የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ጦር᎒ የራሳቸው የምንልክ የቤተመንሥት ጦር᎒ የራስ ወልደ ጊዮርጊስ ጦር እና የጂማው አባ ጅፋር ጦር ያካተተ ነበር (ባህሩ ዘውዴ ኤ ሄስትሪ ኦፍ ሞደርን ኢትዮጵያ ይመልከቱ)᎓᎓ ከብዙ ዉጊያ በኋላ ካዎ ጦና በመማረካቸው ወላይታ ተሸነፈ᎓᎓ ከዚህ በኋላ የወላይታ ህዘብ ዕጣው የጅምላ ባርነትና ጭሰኝነት ሆነ᎓᎓ ካዎ ጦና በምርኮ አዲስ አበባ ተወስደው ክርስትና እንዲነሱ ተደርጎ ታሰሩ᎓᎓ የከፋው ታቶ ጋኪ የተሸነፉት ከአድዋ ጦርነት በኋላ ነው᎒ ከዚያ በፊት በራስ ጎበና ጭምር የተደረጉ ሙከራዎች ከሽፈዋል᎓᎓ ከጣሊያን ከተማረኲት መሳሪያዎች ጋር ከፋ ላይ የዘመቱት የራስ ወልደ ጊዮርጊስ ጦር᎓ የራስ ተሰማ ናደው ጦር᎓ የደጃዝማቸ ደምሰው ጦር᎓ የጂማው አባ ጂፋር ጦር᎓ እና የኩሎ ኮንታ ጦሮች ነበሩ᎓᎓ በራስ ወልደ ጊዮርጊስ ሥር ብቻ 30᎖000 ጦር ሰራዊትና 20᎖000 ነፍጥ ነበረ᎓ ይህ ሁሉ ዘምቶ ታቶ ጋኪን እስከ 8 ወር ድረስ ለማሸነፍ አልተቻለም ነበር᎓᎓ ታቶ ጋኪ በመያዙ ከፋ በመጨረሻ ተሸነፈ᎓᎓ የከፋ ህዝብ እንደ ወላይታው ለጅምላ ባርነት ከመዳረጉም በላይ የራስ ወልደ ጊዮርጊስና ተከታዮቹ የግል ንብረት/ዕቃ ሆኖ ቀረ᎓᎓ ታቶ ጋኪ ከ22 ዓመታት አስከፊ የግዞት እስር በኋላ ወደከፋ ሳይመለሱ በእሥር ላይ እንዳሉ ሞቱ᎓᎓

እንደ ሌላውም የደቡብ ሕዝብ ሲዳማ ወላይታ ከምባታና ከፋ ከዚያን ጊዜ አንሥቶ እስከዛሬ(ከምንልክ እስከ ኢህአዲግ) ድረስ ሲበደሉ ኖሯል᎓᎓ ልማት አልደረሰንም᎒ በብሄራዊ ደረጃ ተወካይ የለንም᎒ ሰፊ ህዝብ᎒ መሬት᎒ የተማረ የሰው ሀይል አለን᎒ ክልል ይፈቀድልን᎒ የኢትዮጵያዊነት ዜግነታችን ይከበርልን ብለው በሰላማዊ መንገድ መጠየቃቸው እንዴት ቢሆን ነው “ክልል ለከብት ነው” የሚያሰኝው᎓᎓ ሲዳማ ከህይሌ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ የትጥቅ ትግል ሲያካሄድ የኖረ ሰፊ መሬትና ሀብት ያለው ህዝብ ነው᎓᎓ የራሱ ክልል አያስፈልገውም?ከምባታ የኢህአዲግ ተቃዋሚ ተደርጎ በመወሰዱ 27 ዓመት ሙሉ አንድም አይነት ልማት ተነፍጎት ለስደት የተዳረገና እየተዳረገ የሚገኝ ህዝብ ነው᎒ በተማሪና በተማረ የሰው ብዛት የምታወቀው ከምባታ አንድ ዩኒቨርሲቲ እንኳን እንዳይከፈት ተከላክሎ የቆየ ህዝብ ነው᎓᎓ የራሳችንን ክልል እንፈልጋለን ማለቱ እንዴት ሆኖ ነው ለኢትዮጵያ “አደገኛ” የሆነው? የወላይታና የከፋም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው᎓᎓
ክቡር ኤርሚያስ
“ተቀናንሰን ተቀናንሰን” ላሉት እንዴት ነው የምንቀናነሰው? እንጨምራለን እንጂ᎓᎓ ከማንስ ስሌት ነው የምንቀናነሰው? ልብ ማለት የሚያስፈልገው ነገር ደቡብ የተባለው ክልል ከአድስ አበባ ግርጔ አንሥቶ እስከ ኬኒያና ሱዳን ድንበሮች የተዘረጋና ለአንዳነዶቹ አዋሳ መሄድ አሥመራ የመሄድ ያህል እሩቅ የሚሆንበት ሁኔታ ያለበት ነው᎓᎓ ይሄ ተገቢ ነው እንደማይሉ አስባለሁ᎓᎓እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ እንኳ 14 ክፍለ ሀገሮች ነበሩን እኮ᎓᎓ ያኔም ቢሆን የደቡብ ህዝቦች ተዳብለው ነው የኖሩት᎓᎓
ሰኔ 16 ቀን የአዲስ አበባ ህዝብ ለዶ/ር አቢይ ድጋፍ ሲያደርግ በከምባታ ከተሞች ተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፎች እየተደረጉ ነበር᎓᎓ የደቡብ ህዝቦች ሁነኛና የዶክተር አቢይ አይነት መሰረታዊ ለውጥ እንደሚሹ ገልጸዋል᎒ እየገለጹም ነው᎓᎓ በአማራና በኦሮሞ ክልሎች የገባው ለውጥ እስካሁን ድረስ ለደቡብ ህዝቦች አልደረሰም᎓᎓ ታዲያ የነዚህ ህዝቦች ጥያቄና ጩሀት ከግቡ እንዳይደርስ ኢሳት ከመንግሥት ጋር ሆኖ ተግቶ እንድሰራ ማሳሳቢያ መስጠትዎ ምን ይባላል?እስካሁን ልገባኝ አልቻለም᎓᎓ ኢሳት የቀድሞው ኢቲቪ እንድሆን ነው ወይስ….? እርስዎ “ኢሳትን መርዳት ማለት ኢትዮጵያን መርዳት ነው” ብለዋል᎓᎓ እኔ ግን የደቡብ ህዝቦችን መርዳት ኢትዮጵያን መርዳት ነው እላለሁ᎓᎓ የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች መሆናቸው ያብቃ᎓᎓
በቸር ይግጠመን
ቶጴ ማላ © us4lsm149@aol.com

https://www.facebook.com/meri.john.

2 comments on “የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው᎓᎓ ይድረስ ለእሳት ጋዜጠኛ ለክቡር ኤርሚያስ ለገሰ

 1. ‘’የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው’’ እዉነት ነዉ ግን የዘር ክልል ህዝቦች አይደሉም፡፡

  1. የታሪክ እዉነታ፣ የስሜትና የፕሮፓጋንዳ አቀራረብ ግጭት
  አቶ ቶጴ ማላ፤ ስለደቡብ ህዝቦች ታሪክ ቀንጭበዉ የጠቃቀሱት ለጊዜዉ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ህዝቦች መካከል በትንሹ መጥቀስ የምፈልገዉ፤ ስለካፋ ህዝብና መንግሥት ሲሆን ይህም፣ ከ500 እስከ 1897 እ.አ.አ ድረስ በሶስት ሥርወ ምንግሥታት የተዳደረ፣ በንጉሡ የሚሾም ጠቅላይ ሚ/ር እና የመከላከያ ሚ/ር ሰብሳቢነት የሚመራ ከሰባት እስከ 9 ሚንስትሮች ባሉት ምክር ቤት (ምክረቾ)፣ የበታች ንኡሳን ሚኒስትሮችና የክልል (ዎራፎ) የወረዳ (ዱቢዮ) ገዢዎች የሚተዳደር መንግሥት ነበር፡፡ መቼም በንፁህ መንፈስ ማንበብ፣ መተንተንና መረዳት ለሚፈልግ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚ/ር መሥሪያ ቤት የተመሰረተበትን ዘመን በማስተዋል ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 20ኛዉ ክ/ዘመን ድረስ፤ ንጉሡ የቅርብ ባለሟሎቹ ፍርድ ሰጪ፣ የንግድ ተቆጣጣሪ፣ ግብር ሰባሳቢ፣ የጦር መሪና አዛዥ፣ የግንባታ ሥራ መሪ፣ የመረጃ ወዘተ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩባት አገር ናት፡፡
  ያዉ እነዚህ ናቸዉ፣ ካፋን ጨምሮ፣ አሁን “የዘር ክልል” የሚባሉትን ጭምር ሲገዙ የነበሩት፡፡ ሁሉም ሊቀበል የሚገባዉ እዉነታ ደግሞ፣ ያኔም ሆነ አሁን የኢትዮጵያ ገዢዎች የሚፈልጉት ሰፊና ለም መሬት፣ የተፈጥሮ ሃብትና ብዙ ቁጥር ያለዉ ገባር ህዝብ በመያዝ ሃብቱን መቆጣጠር ነዉ፡፡ ወያኔም ሆነ ኢፈርት ከዚህ የተለየ ያደረጉት የለም፡፡
  አቶ ኤርሚያስ ልክ ስለደቡብ ክልል እንደተናገረዉ፣ ስለመፅሐፉ ሲተርክ፣ “ብሔራዊ የቡና ሙዚየም” በተመለከተ፣ ጉዳዩ ለአቶ መለስ በቀረበ ጊዜ፣ “ካፈቾዎችም እንደ ወላይታ አንድ …. ታሪክ አላቸዉ መሰለኝ” እየተሳለቀ ሲናገር፣ አቶ መለስም በዚህ የተነሳ ተቆጥቶ ሙዚየሙ ቦንጋ ላይ እንዲሰራ አዘዘ ብሎ ነበር፡፡ በመሰረቱ አቶ መለስ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንዳነበቡና እንደሚያዉቁ፣ ግልፅ ሲሆን፤ ሲፈልጉም እየዘረዘሩ መጠቀማቸዉን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንድ ጋዜጠኛና ደራሲ (ወይም ፀሐፊ?) ለሚፅፈዉና ለሚናገረዉ፤ ማጣፈጫነት ለሚጠቅሳቸዉ በቂ ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመረጃ ዕጥረት ከሌለ፣ የደቡብ ክልል የዘሮች ስብስብ ተብሎ የሚሾፍበትና የሚሳለቁበት አይደለም፡፡ ወደዚያዉ ከመግባቴ በፊት ከሌሎች ተማሳሳይ ስሕተቶች አንዱን ልጥቀስ፡፡
  ያን ሰሞን አንዱ ጨዋታ ማጣፈጥ የለመደ “ፀሐፊ” “የካፋ ንጉሥ ጥጋበኛ ስለሆነ በአጉራሽ እንጂ፣ በእጁ አይበላም” ብሎ ፅፎ ነበር፡፡ ይህ ሰዉ ቢያነብ ኖሮ ተሳስቶ አያሳስትም ነበር፡፡ በብዙ አዉሮፓዊያን ጭምር የተፃፈዉና፣ ሽማግሌዎችም የሚናገሩት እዉነታ የሚከተለዉ ነዉ፡፡ ከመንገሡና “ካፊ ታቶ” ከመሆኑ በፊት ይህ ሰዉ እንደማንኛዉም ዜጋ፣ የፈለገዉን የሚበላና የሚጠጣ ነበር፡፡ ንጉሥ ሲሞት ደግሞ ካሉት አማራጮች፤ በብቃቱ፣ በሥነ ምግባሩና፣ በንጉሣዊ ቤተሰብነቱ፤ በምክረቾ ተመርጦ የሚነግሥ ነዉ፡፡ ከነገሠ በሁዋላ ግን የሚበላዉና የሚጠጣዉ እንደቀድሞዉ ራሱ በፈለገዉ መንገድ ሳይሆን፤ በተወሰነ ሥርዓትና በቁጥጥር ነዉ፡፡ የዚህ ሥርዓት መነሻ፣ ፍልስፍናና ዓላማዉም ንጉሡ እንደሥልጣኑ፣ ጠግቦ ከበላና፣ ከጠጣ ድሃዉን ይረሳል፣ ይሰንፋልም ተብሎ እንጂ፣ በተቃራኒዉ ጥጋበኛ ስለሆነ አይደለም፡፡
  በካናዳዉ የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ የታሪክ አዋቂዎች ካልነበሩ፣ እያሉም በሹፈቱና፣ ሲጨበጨብም ዝም ብለዉ ከነበረ፣ ያስተዛዝባል፡፡

  2. የደቡብ ክልል አመሰራረት፣ ታሪካዊ ሂደትና ዉጤቱ
  የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመደብ (የሃብት ባለቤትነት) እና በብሔር ጥያቄ ላይ እስካሁንም እየተሽከረከረ መቀጠሉን መካድ አይቻልም፡፡ ወታደራዊዉ መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ፣ ትኩረቱ በመደብ (የሃብት ባለቤትነት) ላይ ቢሆንም፤ በሂደት የሁለተኛዉን ጥያቄ ክብደት ተረድቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ወደመጨረሻዉ ዓመታት፣ በብሄረ-ሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት አስጠንቶ፣ ማጂ፣ ቤንች፣ እና ካፋ አዉራጃዎችን፣ ከካፋ ክፍለ ሃገር፣ የኪና ጎደሬን ጨምሮ ሞቻ ሲባል የነበረዉን የአሁኑን ሸካ፣ ከኢሉባቦር ወስዶ የካፋ አስተዳደር አካባቢ የሚባል ክልል አዋቀረ፡፡ ይህም በሽግግሩ ወቅት ክልል 11 የተባለዉ ማለት ነዉ፡፡ ሌሎችንም የአሁኑን የደቡብ ህዝቦች በተመሳሳይ መንገድ ከፋፍሎና አዋህዶ፤ ሰሜን ኦሞ፣ ደቡብ ኦሞ፤ ሲዳሞ፣ ቦረና፣ ደቡብ ሸዋ አስተዳደር አካባቢዎች ብሎ አዋቀረ፡፡ በዚህም በአብዛኛዉ የየአካባቢዉን ተወላጆችና፣ ሌሎች ብቁ ኢትዮጵያዊያንን በሃላፊነት መድቦ፣ ከሞላ ጎደል ህዝቡን ከታሪኩና ከባህሉ ከመልክዓ ምድሩ አኳያ የተጣጣመ አስተዳደር መሰረተ፡፡ በዚህም ኢህዲሪ ተመሰረተ፡፡ ወታደራዊዉ (በሁዋላ የኢህዲሪ) መንግሥት፣ ሲወድቅ፤ በሽግግር ወቀት ከቦረና በስተቀር እነዚህን በአምስት ክልሎች (ክልል7-11) ተዋቀሩ፡፡
  ሆኖም ክልሎቹ ገና ሥራ ሳይጀምሩ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ጨፍልቆ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያደራጃቸዉን አባል ድርጅቶች ጠርቶ፤ ለቁጥጥርና ቅልጥፍና (span of control) እንዲመቸዉ በአንድ ቅርጫት አድርጎ፣ ለመሪዎቹም ሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም አመቻችቶ በአንድ ደቡብ በሚባል ክልል ተዳደሩ” ብሎ፣ ማዕከሉንም አዋሳ አደረገ፡፡ ትኩስ ምልምሎቹንም ለይስሙላ የባለሥልጣን ስም ሰጥቶ፣ ከላይ ግን በአንድ የህወሃት ቁልፍ ሰዉ በአቶ ቢተዉ በላይ ማስተዳደሩን ቀጠለ፡፡ በወቅቱ፤ የተወሰኑ የራሱ ምልምል ካድሬዎችና የአምስቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ሲያንገራግሩ ያለመዉን ለመፈፀምም፣ ያደረገዉ ሴራና ጨዋታ ቀላል ነበር፡፡ ይኸዉም ሲአንና፣ በሽግግሩ ወቅት በነዚህ አካባቢዎች ባሉ ህዝቦች ስም የተደራጁ “ተቃዋሚ ድርጅቶች” ሰብስቦ “ኦነግ ሊዉጣችሁ ስለሆነ፣ ካልተሰባሰባችሁ አለቀላችሁ” አለ፡፡ እነርሱም በፍጥነት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረትን ሲመሰርቱ፣ ቀጥሎም፣ በአምስቱ ክልሎች ሥልጣን የሰጣቸዉንና ለመሰባሰብ ያንገራገሩ አባሎቹን ሰብስቦ “የደቡብ ህብረት ቀደማችሁ” አለ፡፡ እናም “የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር (አሁን ንቅናቄ)” ፤ እና ቀጥሎም የደቡብ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ክልል ተመስርተ፡፡ የይሰሙላ ፕሬዝዳንት፣ አቶ አባተ ኪሾ (ከሲዳማ)፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጀ ዳኬ ጉቾ (ከካፋ)፣ ፀሐፊ አቶ ጴጥሮስ (ከወላይታ)፣ ሆነዉ ከየብሄረሰቡም የዘርፍ አለቆችና የቢሮ ሃላፊዎች ተሰየሙ፡፡ ሆኖም እዉነተኛዉ ገዢ፤ የህወሃቱ ቁልፍ ሰዉና በ1993 የህወሃት ክፍፍል ወቅት ተባረሩ ከተባለ በሁዋላ አሁንም አፋርን የሚዘዉሩት፣ አቶ ቢተዉ በላይ ነበሩ፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ከእነዚህ ህዝቦች የተወሰኑትን በአንድ ላይ ለመጨፍለቅ ያቀደዉ ቀድሞ ነበር፡፡ እናም እንደነርሱ የተቸገረ የዉጭ ፀሐፊ በፃፈዉ አንድ መፅሐፍ ላይ ‘’Lacuranistic people’’ ብሎ ያጠቃለላቸዉን፣ በስምጥ ሸለቆ ዉስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ታሪክ ያነበበ ሰዉ፣ ገና በረሃ እያሉ ምርኮኞችን አደራጅቶ “የስምጥ ሸለቆ ህዝቦች ድርጅት” በማለት ጠፍጥፎ የዚህን ጥንስስሰ መስርቶ ነበር፡፡ ልዩነቱ ፈረንጁ ሥያሜዉን የሰጠዉ፣ እንደአጠራሩ፣ በስምጥ ሸለቆ ዉስጥ ያሉትን ህዝቦች ሲሆን፣ ህወሃት ግን አስፋፍቶ፤ ከስምጥ ሸለቆ ዉጭ ሉትን፤ የየም፣ ካፋ፣ ቤንች፣ ማጂ እና ሸካ ህዝቦችን ጭምር አካተተ፡፡
  በዚህ ሂደት፤ በተመሰረተዉ የደቡብ ክልል፣ በሁሉም ረገድ ሲታይ በክልል 11 የነበሩትን ማካተቱ ትርጉም አልነበረዉም፡፡ ከርቀቱ ሌላ በተጨምሪ፣ በስምጥ ሸለቆ ዉጭ ያሉ በመሆናቸዉ፣ የተለየ ሥነ ምህዳር ለምለምና፣ በደን የጠሸፈኑ አካባቢዎች፣ ግን ደግሞ በኩታ ገጠም የሰፈሩ፣ በጋራ መተዳደር የለመዱ፣ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና እና ባህል ያላቸዉ፣ በሁዋላ ቀርና ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ያሉ ናቸዉ፡፡ በመጨፍለቃቸዉም ከዚህ ጋር የሚስማማ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና፣ የልማት አቅጣጫ እንዳይከተሉ፣ ሆነ፡፡ ከሁሉም በላይ እስከ 1500 ኪ.ሜ. በመጓዝ፣ ለከፍተኛ ወጪ፣ ለክልሉ ባለሥልጣናት ማጎብደድና፣ ማገልገል፣ ለምነዉ ጉዳይ ማስፈፀምን ተላመዱት፡፡
  በሂደት ግን ይህ ያልጣማቸዉ፣ ከደቡብነት ጋር መዋሃድ ያልቻሉና፣ በግል ባህርይ ጭምር ሊጣጠሙ ያልቻሉ የክልል 11 ሰዎች በራሳቸዉ ጊዜ መንገድ እየፈለጉ፣ ክልሉን ለቀቁ ወይም ተወገዱ፡፡ ዞኖቹም በሂደት ዉክልና ሲያጡ፣ ከጠየቁም፣ “ጠባብ፣ ጎጠኛ ወዘተ” እየተባሉ ተሸማቀቁ፡፡ በምትካቸዉም ለክልሉና ለዋናዎቹ የማዕከል አለቆቻቸዉ መረጃ አቅራቢና፣ ሲያስፈልግም ህዝባቸዉን አደናግረዉ፣ ወይም አስፈራርተዉ ዝም የሚያሰኙ፣ አንዳንድ ሆዳሞች እየተመለመሉ ተመደቡ፡፡ በመጨረሻም የደቡብ ምዕራብ አካባቢ (ክልል 11) እስከ መኖሩ፣ የክልሉም ሆነ የአገሪቱ አካል መሆኑ ተረሳ፡፡
  በዚህ ጊዜ ግን ህወሃት እንደተለመዉና፤ እንዲሁም ጉዳይ ፈፃሚ የደቡብ ባለሥልጣናት፣ በዚህ አካባቢ በየደረጃዉ ባስቀመጧቸዉ ታማኞችና ምስለኔዎቻዉ በኩል ዝርፊያዉን ተያያዙት፡፡ በዚህ አካባቢ ብቻ በህወሃት አባላትና በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ሰዎች ጭምር ሰፊ፣ ጥቅጥቅና ጥብቅ ደን እየተመነጠረ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡና፣ የሻይና ሌሎች “ልማቶች” ተመሰረቱ፡፡ ከልመቱ የበለጠ ግን የግንድና የጣዉላ ንግድ አጧጧፉ፣ በደኑ ዉስጥ ለብዙ ትዉልድ ተጠብቆ የቆየ የአገሪቱን የዕፅዋትና ሌሎች ሃብቶች አወደሙ፣ መሬቱን ግን አስይዘዉ በሚሊዮኖችና በቢሊዮኖች ከባንክ ተበድረዉ ወደ ክልላቸዉና ወደ ዉጪ አሻገሩ፡፡ ወታደራዊዉ መንግሥት ካለማቸዉ ዋና ዋና የሃገር ሃብቶች፤ ደግሞ የበበቃ፣ የቴፒ፣ የዉሽዉሽና የጎጀብ፣ ከኦሮሚያም የጉማሮና የሊሙ የቡናና የሻይ ልማቶች፤ ህወሃት ወይም ኢፈርት በዝቅተኛ ዋጋ ወረሰ፣ ለሽፋን ግን የአላሙዲን ናቸዉ ተባሉ፡፡
  የደቡብ ክልል የምዕራብ ዞኖች ህዝብ፣ በደቡብ ገዢዎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸዉ፣ ከአካባቢዉ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና ደንብ ማዉጣት ተከለከሉ፣ ባለሥልጣናቱም በደቡብ አለቆች ስለሚመረጡና ስለሚመደቡ ሹመኞችም ለህዝቡ ተጠያቂ ከመሆን ይልቅ ለደቡብ መታዘዝን መረጡ፣ በሌላ አባባል የራሱን አስተዳዳሪ መምረጥ ተነፈገ፣ በፌደራል መንግሥት የሚሰሩ ተቋማት ሁሉ አዋሳና አቅራቢያዉ ሆነ፣ ከኋላ-ቀርነቱ አኳያ ተመጣጣኝ ትኩረትና ድጋፍ እንዳያገኝ በደቡብ መጋረጃ ተደረገበት፣ የመንግስትና የግለሰቦች ሃብትም በክልል ጉዞ አለቀ፣ ባላሥልጣናትና ባለሙያዉ በጉዞ ላይ ጊዜዉን ስለሚያሳልፍ በዞንም ሆነ በየወረዳዉ ጉዳይ ማስፈፀም አልተቻለም፣ ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች አኳያ ሲታይ ምንም የልማት ስራ አለመሰራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባህልና ቋንቋዉን ጭምር እንዳያጎለብት ተደናቀፈ፡፡ ተገዶ በተቀላቀለበትና በሚገዛበት ክልል ዉክልናና ተከራካሪ አጣ፤ ለምሳሌ፤ የቡና መገኛ ባለቤትነት ከካፋ ሊዘረፍ ሲሞከር ክልሉ ዝምታን መረጠ፣ የማጂ ህዝብ በደቡብ ሱዳን ዜጎች ሲገደልና ሲዘረፍ ጠባቂና አለኝታ አጣ፤ በአጠቃላይ ለዜጎች የሚገባቸዉን አገልግሎትና መብት ተከለከሉ፡፡
  ስለዚህ በኢትዮጵያ ዉሥጥ ክልል ሆነዉ፣ የራሳቸዉ አስተዳዳሪ ለመሆን፣ አካባቢያቸዉንና አገሪቱን አልምተዉ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን፣ በድጋሚ ጠየቁ፡፡ በዚህም አብሮ ለማደግና ለመበልፀግ፣ ተከባብሮ ለመኖር፣ ለአገሪቱና ለቀጠናዉ ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግና፣ የአገሪቱም አንድ ጉልህ የለዉጥ አካል ለመሆን ጠየቁ፡፡
  እና ይህ ሁሉ የደረሰበት፣ እስከ 1897 ድረስም ራሱን ችሎ መንግሥት የነበረ ካፋ፤ አሁን ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመሆን መጠየቁ ለምን ያስገርማል? በወታደረዊ መንግሥት ራሳቸዉን ችለዉ ይተዳደሩ የነበሩ ህዝቦችስ ክልል ለመሆን መወሰናቸዉ እንዴት ድሮም “የዘር ክልል ነበሩ” ያሰኛል? የአስተዳደር ክልል የህዝብን አሰፋፈርና አቀማመጥ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ መሰረትን፣ ለአስተዳደር አመቺነትን ማዕከል ያደረገ አይደለም? በዚህ ሂደት የደቡብ ክልል ወደ ብዙ ክልሎች ቢከፋፈል በማን ላይ ምን ጉዳት ይመጣል ተብሎ ነዉ ይህ ሁሉ ከበሮ የሚደለቀዉ? የአሁኑ ደቡብ እኮ በኢህዲሪ ጊዜም ሆነ በሽግግሩ ዘመን አምሥት ክልሎች ነበሩ፡፡ እነዚህ በአንድ ላይ ሲጨፈለቁ ማን አስተያየት ሰጠ፣ ለምንስ ያኔ አላስገረመም? በኢህዲሪም ሆነ በሽግግር ወቅት ቢያንስ አምስት ክልሎች ነበሩ፡፡
  የህዝቦቹ ጥያቄ ማንንም ለመጉዳት ሳይሆን የራሳቸዉን መብትና ጥቅም ለማስከበር ብቻ ነዉ፡፡ የደቡብ ክልልነት ግን ከአሁን በሁዋላ ወደ ታሪክ ማህደር ተላልፏል ከማለት የሚያስቆመዉ የለም፡፡ የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄም ጉዳይ ይቀጥላል፡፡
  ባይሆን መወያየት የሚገባዉ ስለአፈፃፀሙና ከዚያ በሁዋላ ስለሚከተለዉ አገራዊ አንድነትና ትብብር ቢሆን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እንደእዉነቱ ከሆነ፣፣ በደቡብ ክልል ሥር ያሉ ህዝቦችና፣ ከክልሉ ዉጭ ያሉ የእነዚህ ተወላጆች ከሌላዉ የኢትዮጵያ ወገናችን በተለየ ሁኔታ የአንድነትና የደቡባዊነት መንፈስ የለንም፣ አልነበረንም፡፡ በሰላምና በመግባባት መለያየቱ ግን ህዝቦቹ፣ ኢትዮጵያዊነታቸዉን ጠብቀዉ፣ ከፍራቻና ጥላቻ አንዱ ሌላዉን ከመጠራጠር ተላቀዉ፣ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ እኩልነት፣ በዜግነታቸዉ፣ ኮርተዉ አንድነታቸዉን ይበልጥ አጎልብተዉ በትክክለኛዉ አገራዊና ሰዉአዊ መንገድ፣ በክልላቸዉ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተከባብረዉ እንዲቀጥሉ ያስችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ያስጨነቀዉ በተለይ ኢሳትን ይመስላል፡፡ መፍትሄዉ ግን ተረጋግተን፣ አስተዉለን፣ ተጨባጩን መረጃ ይዘን በሃላፊነት ስሜት መፃፍና፣ መነጋገር፣ ለህዝባችን ይጠቅማል፡፡

  ከሮ ኬቶ

  Liked by 1 person

 2. ኬቶ ጋዎ
  እጅግ አደርገን እናመሰግናለን ስለሰጠሄን ጥልቅ የሆነ ማብራሪያ፣ ይሄን ጽሁፍ ሁሉም ሰው ሊያነበውና ሊገነዘበው ይገባል፣ ካፋንና ማንነቷን ለማያውቁ ሁሉ በተቻለን አቅም እስክገባቸው ደጋግመን እንነግራቸዋለን ”ባይሆን መወያየት የሚገባዉ ስለአፈፃፀሙና ከዚያ በሁዋላ ስለሚከተለዉ አገራዊ አንድነትና ትብብር ቢሆን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እንደእዉነቱ ከሆነ” ያልከው ትክክለኛ መንገድ ነው መንግስትም ሆነ ሃገርቷ ሊረዱት የገባል::

  Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: