Leave a comment

‘’የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው’’ እዉነት ነዉ ግን የዘር ክልል ህዝቦች አይደሉም፡፡


‘’የደቡብ ህዝቦች የኢትዮጵያ እንጀራ ልጆች ናቸው’’ እዉነት ነዉ ግን የዘር ክልል ህዝቦች አይደሉም፡፡

1. የታሪክ እዉነታ፣ የስሜትና የፕሮፓጋንዳ አቀራረብ ግጭት
አቶ ቶጴ ማላ፤ ስለደቡብ ህዝቦች ታሪክ ቀንጭበዉ የጠቃቀሱት ለጊዜዉ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ህዝቦች መካከል በትንሹ መጥቀስ የምፈልገዉ፤ ስለካፋ ህዝብና መንግሥት ሲሆን ይህም፣ ከ500 እስከ 1897 እ.አ.አ ድረስ በሶስት ሥርወ ምንግሥታት የተዳደረ፣ በንጉሡ የሚሾም ጠቅላይ ሚ/ር እና የመከላከያ ሚ/ር ሰብሳቢነት የሚመራ ከሰባት እስከ 9 ሚንስትሮች ባሉት ምክር ቤት (ምክረቾ)፣ የበታች ንኡሳን ሚኒስትሮችና የክልል (ዎራፎ) የወረዳ (ዱቢዮ) ገዢዎች የሚተዳደር መንግሥት ነበር፡፡ መቼም በንፁህ መንፈስ ማንበብ፣ መተንተንና መረዳት ለሚፈልግ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚ/ር መሥሪያ ቤት የተመሰረተበትን ዘመን በማስተዋል ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 20ኛዉ ክ/ዘመን ድረስ፤ ንጉሡ የቅርብ ባለሟሎቹ ፍርድ ሰጪ፣ የንግድ ተቆጣጣሪ፣ ግብር ሰባሳቢ፣ የጦር መሪና አዛዥ፣ የግንባታ ሥራ መሪ፣ የመረጃ ወዘተ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩባት አገር ናት፡፡
ያዉ እነዚህ ናቸዉ፣ ካፋን ጨምሮ፣ አሁን “የዘር ክልል” የሚባሉትን ጭምር ሲገዙ የነበሩት፡፡ ሁሉም ሊቀበል የሚገባዉ እዉነታ ደግሞ፣ ያኔም ሆነ አሁን የኢትዮጵያ ገዢዎች የሚፈልጉት ሰፊና ለም መሬት፣ የተፈጥሮ ሃብትና ብዙ ቁጥር ያለዉ ገባር ህዝብ በመያዝ ሃብቱን መቆጣጠር ነዉ፡፡ ወያኔም ሆነ ኢፈርት ከዚህ የተለየ ያደረጉት የለም፡፡
አቶ ኤርሚያስ ልክ ስለደቡብ ክልል እንደተናገረዉ፣ ስለመፅሐፉ ሲተርክ፣ “ብሔራዊ የቡና ሙዚየም” በተመለከተ፣ ጉዳዩ ለአቶ መለስ በቀረበ ጊዜ፣ “ካፈቾዎችም እንደ ወላይታ አንድ …. ታሪክ አላቸዉ መሰለኝ” እየተሳለቀ ሲናገር፣ አቶ መለስም በዚህ የተነሳ ተቆጥቶ ሙዚየሙ ቦንጋ ላይ እንዲሰራ አዘዘ ብሎ ነበር፡፡ በመሰረቱ አቶ መለስ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንዳነበቡና እንደሚያዉቁ፣ ግልፅ ሲሆን፤ ሲፈልጉም እየዘረዘሩ መጠቀማቸዉን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንድ ጋዜጠኛና ደራሲ (ወይም ፀሐፊ?) ለሚፅፈዉና ለሚናገረዉ፤ ማጣፈጫነት ለሚጠቅሳቸዉ በቂ ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመረጃ ዕጥረት ከሌለ፣ የደቡብ ክልል የዘሮች ስብስብ ተብሎ የሚሾፍበትና የሚሳለቁበት አይደለም፡፡ ወደዚያዉ ከመግባቴ በፊት ከሌሎች ተማሳሳይ ስሕተቶች አንዱን ልጥቀስ፡፡
ያን ሰሞን አንዱ ጨዋታ ማጣፈጥ የለመደ “ፀሐፊ” “የካፋ ንጉሥ ጥጋበኛ ስለሆነ በአጉራሽ እንጂ፣ በእጁ አይበላም” ብሎ ፅፎ ነበር፡፡ ይህ ሰዉ ቢያነብ ኖሮ ተሳስቶ አያሳስትም ነበር፡፡ በብዙ አዉሮፓዊያን ጭምር የተፃፈዉና፣ ሽማግሌዎችም የሚናገሩት እዉነታ የሚከተለዉ ነዉ፡፡ ከመንገሡና “ካፊ ታቶ” ከመሆኑ በፊት ይህ ሰዉ እንደማንኛዉም ዜጋ፣ የፈለገዉን የሚበላና የሚጠጣ ነበር፡፡ ንጉሥ ሲሞት ደግሞ ካሉት አማራጮች፤ በብቃቱ፣ በሥነ ምግባሩና፣ በንጉሣዊ ቤተሰብነቱ፤ በምክረቾ ተመርጦ የሚነግሥ ነዉ፡፡ ከነገሠ በሁዋላ ግን የሚበላዉና የሚጠጣዉ እንደቀድሞዉ ራሱ በፈለገዉ መንገድ ሳይሆን፤ በተወሰነ ሥርዓትና በቁጥጥር ነዉ፡፡ የዚህ ሥርዓት መነሻ፣ ፍልስፍናና ዓላማዉም ንጉሡ እንደሥልጣኑ፣ ጠግቦ ከበላና፣ ከጠጣ ድሃዉን ይረሳል፣ ይሰንፋልም ተብሎ እንጂ፣ በተቃራኒዉ ጥጋበኛ ስለሆነ አይደለም፡፡
በካናዳዉ የኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ የታሪክ አዋቂዎች ካልነበሩ፣ እያሉም በሹፈቱና፣ ሲጨበጨብም ዝም ብለዉ ከነበረ፣ ያስተዛዝባል፡፡

2. የደቡብ ክልል አመሰራረት፣ ታሪካዊ ሂደትና ዉጤቱ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመደብ (የሃብት ባለቤትነት) እና በብሔር ጥያቄ ላይ እስካሁንም እየተሽከረከረ መቀጠሉን መካድ አይቻልም፡፡ ወታደራዊዉ መንግሥት ሥልጣን እንደያዘ፣ ትኩረቱ በመደብ (የሃብት ባለቤትነት) ላይ ቢሆንም፤ በሂደት የሁለተኛዉን ጥያቄ ክብደት ተረድቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ወደመጨረሻዉ ዓመታት፣ በብሄረ-ሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት አስጠንቶ፣ ማጂ፣ ቤንች፣ እና ካፋ አዉራጃዎችን፣ ከካፋ ክፍለ ሃገር፣ የኪና ጎደሬን ጨምሮ ሞቻ ሲባል የነበረዉን የአሁኑን ሸካ፣ ከኢሉባቦር ወስዶ የካፋ አስተዳደር አካባቢ የሚባል ክልል አዋቀረ፡፡ ይህም በሽግግሩ ወቅት ክልል 11 የተባለዉ ማለት ነዉ፡፡ ሌሎችንም የአሁኑን የደቡብ ህዝቦች በተመሳሳይ መንገድ ከፋፍሎና አዋህዶ፤ ሰሜን ኦሞ፣ ደቡብ ኦሞ፤ ሲዳሞ፣ ቦረና፣ ደቡብ ሸዋ አስተዳደር አካባቢዎች ብሎ አዋቀረ፡፡ በዚህም በአብዛኛዉ የየአካባቢዉን ተወላጆችና፣ ሌሎች ብቁ ኢትዮጵያዊያንን በሃላፊነት መድቦ፣ ከሞላ ጎደል ህዝቡን ከታሪኩና ከባህሉ ከመልክዓ ምድሩ አኳያ የተጣጣመ አስተዳደር መሰረተ፡፡ በዚህም ኢህዲሪ ተመሰረተ፡፡ ወታደራዊዉ (በሁዋላ የኢህዲሪ) መንግሥት፣ ሲወድቅ፤ በሽግግር ወቀት ከቦረና በስተቀር እነዚህን በአምስት ክልሎች (ክልል7-11) ተዋቀሩ፡፡
ሆኖም ክልሎቹ ገና ሥራ ሳይጀምሩ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ጨፍልቆ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያደራጃቸዉን አባል ድርጅቶች ጠርቶ፤ ለቁጥጥርና ቅልጥፍና (span of control) እንዲመቸዉ በአንድ ቅርጫት አድርጎ፣ ለመሪዎቹም ሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም አመቻችቶ በአንድ ደቡብ በሚባል ክልል ተዳደሩ” ብሎ፣ ማዕከሉንም አዋሳ አደረገ፡፡ ትኩስ ምልምሎቹንም ለይስሙላ የባለሥልጣን ስም ሰጥቶ፣ ከላይ ግን በአንድ የህወሃት ቁልፍ ሰዉ በአቶ ቢተዉ በላይ ማስተዳደሩን ቀጠለ፡፡ በወቅቱ፤ የተወሰኑ የራሱ ምልምል ካድሬዎችና የአምስቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ሲያንገራግሩ ያለመዉን ለመፈፀምም፣ ያደረገዉ ሴራና ጨዋታ ቀላል ነበር፡፡ ይኸዉም ሲአንና፣ በሽግግሩ ወቅት በነዚህ አካባቢዎች ባሉ ህዝቦች ስም የተደራጁ “ተቃዋሚ ድርጅቶች” ሰብስቦ “ኦነግ ሊዉጣችሁ ስለሆነ፣ ካልተሰባሰባችሁ አለቀላችሁ” አለ፡፡ እነርሱም በፍጥነት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረትን ሲመሰርቱ፣ ቀጥሎም፣ በአምስቱ ክልሎች ሥልጣን የሰጣቸዉንና ለመሰባሰብ ያንገራገሩ አባሎቹን ሰብስቦ “የደቡብ ህብረት ቀደማችሁ” አለ፡፡ እናም “የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር (አሁን ንቅናቄ)” ፤ እና ቀጥሎም የደቡብ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ክልል ተመስርተ፡፡ የይሰሙላ ፕሬዝዳንት፣ አቶ አባተ ኪሾ (ከሲዳማ)፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጀ ዳኬ ጉቾ (ከካፋ)፣ ፀሐፊ አቶ ጴጥሮስ (ከወላይታ)፣ ሆነዉ ከየብሄረሰቡም የዘርፍ አለቆችና የቢሮ ሃላፊዎች ተሰየሙ፡፡ ሆኖም እዉነተኛዉ ገዢ፤ የህወሃቱ ቁልፍ ሰዉና በ1993 የህወሃት ክፍፍል ወቅት ተባረሩ ከተባለ በሁዋላ አሁንም አፋርን የሚዘዉሩት፣ አቶ ቢተዉ በላይ ነበሩ፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ከእነዚህ ህዝቦች የተወሰኑትን በአንድ ላይ ለመጨፍለቅ ያቀደዉ ቀድሞ ነበር፡፡ እናም እንደነርሱ የተቸገረ የዉጭ ፀሐፊ በፃፈዉ አንድ መፅሐፍ ላይ ‘’Lacuranistic people’’ ብሎ ያጠቃለላቸዉን፣ በስምጥ ሸለቆ ዉስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ታሪክ ያነበበ ሰዉ፣ ገና በረሃ እያሉ ምርኮኞችን አደራጅቶ “የስምጥ ሸለቆ ህዝቦች ድርጅት” በማለት ጠፍጥፎ የዚህን ጥንስስሰ መስርቶ ነበር፡፡ ልዩነቱ ፈረንጁ ሥያሜዉን የሰጠዉ፣ እንደአጠራሩ፣ በስምጥ ሸለቆ ዉስጥ ያሉትን ህዝቦች ሲሆን፣ ህወሃት ግን አስፋፍቶ፤ ከስምጥ ሸለቆ ዉጭ ሉትን፤ የየም፣ ካፋ፣ ቤንች፣ ማጂ እና ሸካ ህዝቦችን ጭምር አካተተ፡፡
በዚህ ሂደት፤ በተመሰረተዉ የደቡብ ክልል፣ በሁሉም ረገድ ሲታይ በክልል 11 የነበሩትን ማካተቱ ትርጉም አልነበረዉም፡፡ ከርቀቱ ሌላ በተጨምሪ፣ በስምጥ ሸለቆ ዉጭ ያሉ በመሆናቸዉ፣ የተለየ ሥነ ምህዳር ለምለምና፣ በደን የጠሸፈኑ አካባቢዎች፣ ግን ደግሞ በኩታ ገጠም የሰፈሩ፣ በጋራ መተዳደር የለመዱ፣ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና እና ባህል ያላቸዉ፣ በሁዋላ ቀርና ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ያሉ ናቸዉ፡፡ በመጨፍለቃቸዉም ከዚህ ጋር የሚስማማ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና፣ የልማት አቅጣጫ እንዳይከተሉ፣ ሆነ፡፡ ከሁሉም በላይ እስከ 1500 ኪ.ሜ. በመጓዝ፣ ለከፍተኛ ወጪ፣ ለክልሉ ባለሥልጣናት ማጎብደድና፣ ማገልገል፣ ለምነዉ ጉዳይ ማስፈፀምን ተላመዱት፡፡
በሂደት ግን ይህ ያልጣማቸዉ፣ ከደቡብነት ጋር መዋሃድ ያልቻሉና፣ በግል ባህርይ ጭምር ሊጣጠሙ ያልቻሉ የክልል 11 ሰዎች በራሳቸዉ ጊዜ መንገድ እየፈለጉ፣ ክልሉን ለቀቁ ወይም ተወገዱ፡፡ ዞኖቹም በሂደት ዉክልና ሲያጡ፣ ከጠየቁም፣ “ጠባብ፣ ጎጠኛ ወዘተ” እየተባሉ ተሸማቀቁ፡፡ በምትካቸዉም ለክልሉና ለዋናዎቹ የማዕከል አለቆቻቸዉ መረጃ አቅራቢና፣ ሲያስፈልግም ህዝባቸዉን አደናግረዉ፣ ወይም አስፈራርተዉ ዝም የሚያሰኙ፣ አንዳንድ ሆዳሞች እየተመለመሉ ተመደቡ፡፡ በመጨረሻም የደቡብ ምዕራብ አካባቢ (ክልል 11) እስከ መኖሩ፣ የክልሉም ሆነ የአገሪቱ አካል መሆኑ ተረሳ፡፡
በዚህ ጊዜ ግን ህወሃት እንደተለመዉና፤ እንዲሁም ጉዳይ ፈፃሚ የደቡብ ባለሥልጣናት፣ በዚህ አካባቢ በየደረጃዉ ባስቀመጧቸዉ ታማኞችና ምስለኔዎቻዉ በኩል ዝርፊያዉን ተያያዙት፡፡ በዚህ አካባቢ ብቻ በህወሃት አባላትና በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ሰዎች ጭምር ሰፊ፣ ጥቅጥቅና ጥብቅ ደን እየተመነጠረ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡና፣ የሻይና ሌሎች “ልማቶች” ተመሰረቱ፡፡ ከልመቱ የበለጠ ግን የግንድና የጣዉላ ንግድ አጧጧፉ፣ በደኑ ዉስጥ ለብዙ ትዉልድ ተጠብቆ የቆየ የአገሪቱን የዕፅዋትና ሌሎች ሃብቶች አወደሙ፣ መሬቱን ግን አስይዘዉ በሚሊዮኖችና በቢሊዮኖች ከባንክ ተበድረዉ ወደ ክልላቸዉና ወደ ዉጪ አሻገሩ፡፡ ወታደራዊዉ መንግሥት ካለማቸዉ ዋና ዋና የሃገር ሃብቶች፤ ደግሞ የበበቃ፣ የቴፒ፣ የዉሽዉሽና የጎጀብ፣ ከኦሮሚያም የጉማሮና የሊሙ የቡናና የሻይ ልማቶች፤ ህወሃት ወይም ኢፈርት በዝቅተኛ ዋጋ ወረሰ፣ ለሽፋን ግን የአላሙዲን ናቸዉ ተባሉ፡፡
የደቡብ ክልል የምዕራብ ዞኖች ህዝብ፣ በደቡብ ገዢዎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸዉ፣ ከአካባቢዉ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና ደንብ ማዉጣት ተከለከሉ፣ ባለሥልጣናቱም በደቡብ አለቆች ስለሚመረጡና ስለሚመደቡ ሹመኞችም ለህዝቡ ተጠያቂ ከመሆን ይልቅ ለደቡብ መታዘዝን መረጡ፣ በሌላ አባባል የራሱን አስተዳዳሪ መምረጥ ተነፈገ፣ በፌደራል መንግሥት የሚሰሩ ተቋማት ሁሉ አዋሳና አቅራቢያዉ ሆነ፣ ከኋላ-ቀርነቱ አኳያ ተመጣጣኝ ትኩረትና ድጋፍ እንዳያገኝ በደቡብ መጋረጃ ተደረገበት፣ የመንግስትና የግለሰቦች ሃብትም በክልል ጉዞ አለቀ፣ ባላሥልጣናትና ባለሙያዉ በጉዞ ላይ ጊዜዉን ስለሚያሳልፍ በዞንም ሆነ በየወረዳዉ ጉዳይ ማስፈፀም አልተቻለም፣ ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች አኳያ ሲታይ ምንም የልማት ስራ አለመሰራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባህልና ቋንቋዉን ጭምር እንዳያጎለብት ተደናቀፈ፡፡ ተገዶ በተቀላቀለበትና በሚገዛበት ክልል ዉክልናና ተከራካሪ አጣ፤ ለምሳሌ፤ የቡና መገኛ ባለቤትነት ከካፋ ሊዘረፍ ሲሞከር ክልሉ ዝምታን መረጠ፣ የማጂ ህዝብ በደቡብ ሱዳን ዜጎች ሲገደልና ሲዘረፍ ጠባቂና አለኝታ አጣ፤ በአጠቃላይ ለዜጎች የሚገባቸዉን አገልግሎትና መብት ተከለከሉ፡፡
ስለዚህ በኢትዮጵያ ዉሥጥ ክልል ሆነዉ፣ የራሳቸዉ አስተዳዳሪ ለመሆን፣ አካባቢያቸዉንና አገሪቱን አልምተዉ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን፣ በድጋሚ ጠየቁ፡፡ በዚህም አብሮ ለማደግና ለመበልፀግ፣ ተከባብሮ ለመኖር፣ ለአገሪቱና ለቀጠናዉ ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግና፣ የአገሪቱም አንድ ጉልህ የለዉጥ አካል ለመሆን ጠየቁ፡፡
እና ይህ ሁሉ የደረሰበት፣ እስከ 1897 ድረስም ራሱን ችሎ መንግሥት የነበረ ካፋ፤ አሁን ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመሆን መጠየቁ ለምን ያስገርማል? በወታደረዊ መንግሥት ራሳቸዉን ችለዉ ይተዳደሩ የነበሩ ህዝቦችስ ክልል ለመሆን መወሰናቸዉ እንዴት ድሮም “የዘር ክልል ነበሩ” ያሰኛል? የአስተዳደር ክልል የህዝብን አሰፋፈርና አቀማመጥ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ መሰረትን፣ ለአስተዳደር አመቺነትን ማዕከል ያደረገ አይደለም? በዚህ ሂደት የደቡብ ክልል ወደ ብዙ ክልሎች ቢከፋፈል በማን ላይ ምን ጉዳት ይመጣል ተብሎ ነዉ ይህ ሁሉ ከበሮ የሚደለቀዉ? የአሁኑ ደቡብ እኮ በኢህዲሪ ጊዜም ሆነ በሽግግሩ ዘመን አምሥት ክልሎች ነበሩ፡፡ እነዚህ በአንድ ላይ ሲጨፈለቁ ማን አስተያየት ሰጠ፣ ለምንስ ያኔ አላስገረመም? በኢህዲሪም ሆነ በሽግግር ወቅት ቢያንስ አምስት ክልሎች ነበሩ፡፡
የህዝቦቹ ጥያቄ ማንንም ለመጉዳት ሳይሆን የራሳቸዉን መብትና ጥቅም ለማስከበር ብቻ ነዉ፡፡ የደቡብ ክልልነት ግን ከአሁን በሁዋላ ወደ ታሪክ ማህደር ተላልፏል ከማለት የሚያስቆመዉ የለም፡፡ የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄም ጉዳይ ይቀጥላል፡፡
ባይሆን መወያየት የሚገባዉ ስለአፈፃፀሙና ከዚያ በሁዋላ ስለሚከተለዉ አገራዊ አንድነትና ትብብር ቢሆን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እንደእዉነቱ ከሆነ፣፣ በደቡብ ክልል ሥር ያሉ ህዝቦችና፣ ከክልሉ ዉጭ ያሉ የእነዚህ ተወላጆች ከሌላዉ የኢትዮጵያ ወገናችን በተለየ ሁኔታ የአንድነትና የደቡባዊነት መንፈስ የለንም፣ አልነበረንም፡፡ በሰላምና በመግባባት መለያየቱ ግን ህዝቦቹ፣ ኢትዮጵያዊነታቸዉን ጠብቀዉ፣ ከፍራቻና ጥላቻ አንዱ ሌላዉን ከመጠራጠር ተላቀዉ፣ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ እኩልነት፣ በዜግነታቸዉ፣ ኮርተዉ አንድነታቸዉን ይበልጥ አጎልብተዉ በትክክለኛዉ አገራዊና ሰዉአዊ መንገድ፣ በክልላቸዉ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተከባብረዉ እንዲቀጥሉ ያስችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ያስጨነቀዉ በተለይ ኢሳትን ይመስላል፡፡ መፍትሄዉ ግን ተረጋግተን፣ አስተዉለን፣ ተጨባጩን መረጃ ይዘን በሃላፊነት ስሜት መፃፍና፣ መነጋገር፣ ለህዝባችን ይጠቅማል፡፡

ከሮ ኬቶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: