Leave a comment

”በአንድ ሃገር ሁለት አይነት ዜግነት! እንዱ ሲወጋ የሚወጣው ደም ነገር ግን ሌላኛ ሲወጋ የሚወጣው አቧራ ይመስል!”


በአንድ ሃገር ሁለት አይነት ዜግነት! እንዱ ሲወጋ የሚወጣው ደም ነገር ግን ሌላኛ ሲወጋ የሚወጣው አቧራ ይመስል!

በመጀመሪያ ይህ ፅሁፍ በሰፈራ ስለመጡት ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቻችን በፍፁም እንዳልሆነ እንዲታወቅ እንፈልጋለን:: ኢትዮጵያዊ ይትም ሄዶ የመኖር የመሥራት መብት እንዲጠበቅለት ከሚሟገቱ ዝጎች አንዱ ነን:: ነገር ግን የዚህ ፅሁፍ ዓላማና ትኩረቱ የካፋ ዞን አስተዳዳሪዎችን ብቻ እንደሚመለከት በቅድሚያ ግልፅ እንዲሆንልን እንፈልጋለን::

ዛሬ ከካፋ ተፈናቅለዋል የተባሉት የካንባታ ተወላጅ ወንድም እህቶቻችን አቀባበል ተደርጎላቸው ወደ ዴቻ ወረዳ ተመልሰዋል::

ለእነዚህ ወንድም እህቶች መምጫ መንገድ ለማመቻቸት በካፋ ዞን አመራሮች ጥሪ መሰረት ካፋ ውስጥ ችግር እንዳለና አከባቢው የጦር አውድማ እንደሆነ ተደርጎ ልብ ውለድ ተፅፎ ቲያትር ተሰርቶ የመከላከያ ሃይል መጋበዝ ነበረበት:: የተጋበዘው የመከላከያ ሃይሉም አዲስ የክርስትና ስም ተሰጥቶት ኮማንድ ፖስት በመባል መግባት ነበረበት ገብቶም ሁኔታዎችን አመቻችቶ የተፈለገው እቅድ ተሳክቶ ዛሬ ዓይተናል::

የካፋ ልጅ መሬት አያስፈልገውም? የሚወለደው ልጅ የሚወርሰው ፎቅ የለውም ፋብርካ የለውም የባንክ አካውንት የለውም:: የካፋ ሕዝብ ለልጆቹ ማውረስ የሚችለው መሬቱን ብቻ ነው:: ያም መሬቱ በወረራ ተወስዶበታል:: የአከባቢው ወጣት እትብቱ በተቀበረበት ሃገር ሰርቶ እንዳይበላ መሬት እየተከለከለ ለምንድነው ቁጥሩ ለማይታወቅ ሰፋሪ መሬት እንደፈለገ የሚሰጠው? ነዋሪው ሕዝብ ባልመከረበት ባላወቀበት ሁኔታ ለምን ድራማ ይሰራበታል? ለመሆኑ ሲጀመር ስንት ሰፋሪ ነበር በሕጋዊ መንገድ የገባው? ስንት ሰፋሪ ነው ተባርሬአለሁ ብሎ የሄደው? አሁንስ ስንት ሰፋሪ ነው በአውቶቢስ ተጭኖ የመጣው? ይህ አካሄድ ኢትዮጵያዊን እርስ በእርሳቸው ተከባብረውና ተዋደው እንዳይኖሩ የሚደረግ ሴራ ነው:: አንዱ በአንዱ ላይ ጠላት እንዲሆን ታቅዶ የተሰራ እኩይ ተግባር ነው:: ሕዝቡ ቢያውቅ ቢመክርበት ሃላፊነትን ቢጋራ ለሁሉም ይበጅ ነበር::

ግን ለምን ይህን ሁሉ እቅድና ድርጊት ከሕዝብ መደበቅ አስፈለገ? ሲጀመር የካፋ ሕዝብ አላባረራቸውም:: ሲባረሩ የካፋ ሕዝብ አልቅሷል እነሆ ሲመለሱም ደስታውን እየገለፀ ነው:: ምንድነው በካፋ ሕዝብ ላይ እየተሰራ ያለው ሴራ? ካፋን የሚያስተዳድር ማነው? የዞኑ መሪዎች ለካፋ ሕዝብ ነው የቆሙት ወይስ በቁመናው ቸርችረው ሊሸጡት? የሕዝቡ መሪ ከሆኑ እና ለሕዝቡ ቆመናል ካሉ ለምን ሁሉን ነገር ከሕዝቡ ደብቀው በጨለማ ይፈፅማሉ? እወክላለሁ የሚሉትን ሕዝብ ለምን እንደ ሕፃን ያታልሉታል? እነዚህን ጥያቄዎች አመራሮቹ ሳይሆኑ የካፋ ሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መመለስ አለበት::

ቁጥሩ ያልታወቀ ሕዝብ ተባረረ ተብሎ ስንሰማ ቁጥሩ ያልታወቀ ሕዝብ ያለ አከባቢው ሕዝብ ዕውቅና እየገባ ነው:: የካፋ ወጣት የተወለደበትን መሬት እግዜር በደግነቱ የቸረውን ሃብት እንዳይጠቀም እየተደረገ ለምን ከሌላ ቦታ ለሚመጡት ትልቅ ባጀት ተመድቦ የሃገር መከላከያ ተገንብቶ ልዩ ጥቅምና ልዩ ጥበቃ ይደረግላቸዋል? የካንባታ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ሲሆን የከፋ ተወላጅ ዜግነት የለውም? የሚወክለውና የሚቆረቆርለት ተወካይ ወይም መንግሥት የለውም? የካፋ ሕዝብ ሆይ ይህንን ጥያቄ መልስ::

ሕዝቡን ንቀውና አንቅረው ተፍተው ሲያበቁ በጨለማ ያቀዱትን እቅድ ለቴለቪዥን መስኮት ውበት እንዲሆን በቀን ፀሃይ ምንም የማያቁትን ህፃናትን ሳይቀር ዛሬ ከየትምህርት ቤቱ እያስወጡ የመጣውን አውቶቢስ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው እያጨበጨቡ እንዲቀበሉ አድርገው ተሳለቁበት:: እንዲያጨበጭብ ታዞ የወጣው ህዝብ በአውቶቢሱ ውስጥ ዕቃ ይሁን ሰው ወይም ሌላ ነገር እንዳለ የሚያውቀው ነገር አልነበረም:: በማያውቁት ነገር ውጡና አጨብጭቡ ተባሉና አጨበጨቡ:: እንዴት ሰው ራሱን መልሶ ይንቃል ያንቋሽሻል? እነዚህ አመራሮች ሕዝቡን ሳይሆን የናቁት ያንቋሸሹት ራሳቸውን ነው:: የተናቀ ምን ጊዜም ቢሆን ያው የተናቀ አይደል::

እነዚህ አመራሮች በሸካ ዞን ቴፒ ላይ የሸካና የካፋ ሕዝብ ሲፈናቀል ቤት ንብረቱ ሲቃጠል በየሜዳው እንደ አይጥ ሲገደል የት ነበሩ? አንድም ቀን ተሳስተው እንኳ ስለ ሸካና ካፋ ሕዝብ ትንፍሽ ብለው አያውቁም:: ሌላው ቢቀር ሚድያ አማራ ከቴፒ ተባረረ እያለ በአከባቢው ያለውን ችግር ማጋለጥ ቢሞክርም እነዚህ የሕዝብ መሪ ነን የሚሉት ባንዳዎች የተባረረውም የተፈናቀለውም ቤቱ ንብረቱ የተቃጠለውም በየሜዳው የተገደለውም ሸካና ካፋ የመሆኑን እውነት እንኳ ደፍረው ሊናገሩ አንደበት አልነበራቸውም:: ፍላጎቱም ጭራሽ አልነበራቸውም::

ታዲያ ዛሬ ለምን ለካንባታ ተወላጆች ልዩ ትኩረት መስጠት ፈለጉ? ፍቅር ከቤት ይጀምራል የሚባለውን አባባል አልሰሙት ይሆን? ወይስ የካንባታ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ የካፋና የሸካ ተወላጆች ዜግነት የሌለው ዕቃ ነው ማለት ነው? የሸካና የካፋ ተወላጆች በቴፒ ለአንድ ዓመት ሙሉ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በረሃብና ቸነፈር ሲጠበሱ ሰዎች አይደሉም ማለት ነው? ቤት አጥተው በማትረባ ፒላስቲክ ድንኳን ሲጠለሉና መጠለያ አጥተው በየጫካውና ቋጥኙ በብርድ ውርጭ ፀሃይና ዝናብ ሲደበደቡ ሰዎች ሳይሆኑ አይጥ ናቸው ማለት ነው? የካምባታ ተወላጅ ሲገደል ሰው ሞተ ተብሎ ተለቀሰለት ሲወጋ ደሙ ፈሰሰ ተባለ:: ታዲያ ሸካና ካፋ ሲገደል ሰው አይደለም ማለት ነው? ሲወጋ የሚወጣው ደም ሳይሆን አቧራ ነው ማለት ነው?

አሁን እንደሚገባን ከሆነ ሰፋሪዎቹ እንዲወጡ የተደረገው ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ነው ማለት ነው:: ጥቂት ሰፋሪዎችን እንደተባረሩ አድርጎ በማስመሰል ድራማ ከሰሩ በሗላ መልሶ በብዙ ቁጥር በማስገባት የካፋን ለም መሬት ያለ ሕዝቡ እውቅናና ፈቃጅነት ማስወረር:: ስለዚህ የሰፋሪዎቹ ለብዙ ዓመታት ከነበሩበት እንዲባረሩ የዞኑ አመራሮች እጅ ያለበት ይመስላልና ሕዝቡም ይህንን በተገቢው መንገድ ማጣራትና ማፅዳት ይኖርበታል::

የነጭ ለባሽ ታሪክ ከአያቶቻችሁ ሰምታችሗል?

ምንሊክ የካፋን ንጉስ ካሸነፈ በሗላ የካፋ ቆራጥ ልጆች እስከ ምንሊክ ቤተመንግሥት በመግቦት የካፋን ንጉሥ ዘውድ ማንም ሳያውቅ መንጠቅ አድርገው የካፋን መንግሥት እንደገና ለማቆም ጉዞ ጀምረው ጊቤ አከባቢ ሲደርሱ ተያዙ:: ይህ ድፍረታቸው ያስደናገጣቸው ምንሊክ የካፋ ምድር ሁሉ በነጭ ለባሽ እንዲጥለቀለቅ አደረጉ:: ነጭ ለባሾቹም አንድ ካፋ እንኳ አንገቱን ቀና ካደረገ ለአከባቢው ተቆርቋሪነትን ካሳየ ሁለተኛ ቀና እንዳይል አድርገው እንደ እባብ ጭንቅላቱን ጨፍልቀው ያጠፉት ነበር:: ስለዚህ ካፋ በምንም መልኩ በፖለቲካ ሆነ በኤኮኖሚ በሃገሩ እንዳያንሰራራ ተደርጎ እስከ ዛሬ በጨለማ ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል:: እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለትም እስከ ደርግ ጊዜ እነዚህ ነጭ ለባሾችና የነጭ ለባሽ ልጆች ጠንክሮ መውጣት የሞከረውን ካፋ ባለበት ሁሉ እንዳይታይ አድርገው እንደሚያጠፉት ቤተሰባቻችን ሲያወሩ እየሰማን ነበር ያደግነው:: ታዲያ የአሁኖቹ አዲሱ ነጭ ለባሽ መሆናቸው ነው ወይ? እንግዲህ ማን ጉዳችንን ይንገረን? ተሸጥን እንደ ዕቃ ተለወጥን በገዛ ልጆቻችን::

ካፋ በምንም መልኩ ራሱን እንዳይችልና እንዳይከላከል እየተደረገ ነው:: ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ በልጆቹ ታግዞ የሚመጣውን ሁሉ ለመጋፈጥ እየተዘጋጀ ነው:: በሁሉም ቦታ ሰው ሌላው ቢቀር መሳሪያ ሳይቀር እየታጠቀ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው:: ካፋ አጋዥና አሳቢ ልጅ የሌለው ሕብረተሰብ እየሆነ ነው:: ካፋ ዱላ ቆርጦ እንኳ ራሱን እንዳይከላከል ዱላ አብቃይ ጫካው በሰፍሪና በእንቬስትመንት ስም ተመንጥሮ አልቋል:: ታዲያ ይህ ሕዝብ የት ይህድ? የት ይግባ? ለማን አቤት ይበል? ከሌላ ቢመጣ ሌላ ስለሆነ ነው ይባላል:: ነገር ግን ይህ ክህደትና ሸፍጥ የሚፈፀሚበት በገዛ ልጆቹ ነው:: የገዛ ልጆቹ አሳልፈው ሸጡት አዋረዱት በእግሩ እንዳይቆም ሰው እንዳይባል አደረጉት:: የገዛ ልጆቹ እንደ ሕፃን አታለሉት እንደ እቃ በጥቅም ቀየሩት አፌዙበት አላገጡበት አንቅረውም ተፉበት:: ገና በሕዝቡ ጭቅላት ላይ ቆሞ የሚሸናውን ክንደ ብርቱ መንግሥ ፈጥረው ወይም ፈልገው አምጥተው ማንገሳቸው የማይቀር ነው:: ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንደተባለው ካፋ ሆይ ለራስህ ስትል ንቃ የራስህ ዕድል በራስህ ወስን:: ካለፈ በሗላ መቆጨትና ማልቀስ ትርጉም አይኖረውም::

ዲጎና
ካፋ ሚድያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: