Leave a comment

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት(ደምኢህህ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ


38023561_282102385890705_1514103197361242112_nበደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ማለትም በታሪክ፣በባህል፣ በማህበራዊና ኤኮኖሚ እሴቶች ለዘመናት ተዛምደው የዘለቁ የቀድሞ የካፋ ክፍለ ሀገር ከዚያም የካፋ አስተዳደር አካባቢ በሚኖረው ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው አፈናና የመብት ረገጣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ውድመትና ብዝበዛ በአስቸኳይ እንዲቆምና የመላው ህዝብ ጥያቄ ይመለስ ዘንድ ድርጅታችን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት (ደምኢህህ) ከዚህ የሚከተለውን መግለጫ ለማውጣት ተገዷል።

እንደሚታወቀውና በተደጋጋሚ ለመግለፅ እንደሞከርነው ከአፄዎቹ ሥርዓት ጀምሮ እጅግ አስከፊ ለሆነ የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰትና ረገጣ ተጋልጦ የቆየው የቀድሞ የካፋ ክፍለ ሀገር ከዚያም የካፋ አስተዳደር አካባቢ ይተዳደር የነበረው ሕዝባችን ለዘመናት ሲንከባለል ዛሬ የደረሰው ዘርፈ ብዙ ችግር ወደ ባሰና አስፈሪ ወደ ሆነ ቀውስ በማምራት ላይ ይገኛል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በውስጡ አቅፎ የያዘው ይህ የአገራችን ክፍለ ግዛት ለሃገሪቱ የኤኮኖሚ ጀርባ አጥንት የሆኑትን ለዓለም ካፋ-ማኪራ ያበረከተችውን ቡናን ጨምሮ ሻይ፣ ማር፣ ወርቅ፣ ቅመማ ቅመም እና ሌሎችንም የከርሰምድርና የደን ሃብት ባለቤት ስለመሆኑ የሚታወቅ ሃቅ ነው። ይሁንና በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት ሃገሪቱን ሲያስተዳድር በነበረው ጨቋኝ አስተዳደር አካል ለጥቂት ግለሰቦችና ባለስልጣናት በቢሊዬን ደረጃ ገቢ የሚያስገኙትን ሃብት ለምሳሌ የቴፒ፣ የበበቃ ቡና፣ የጉመሮና የውሽውሽ ሻይ ተክል፣ የጎጀብ እርሻ ልማት በግፍ ተላልፎ መሰጠቱን በሰፈራ ሥም የመሬት ወረራ ሲካሄድ መቆየቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመግለጽ ሞክረናል።

እነዚህንና መሠል ሕዝብና አገር አፍራሽና ገዳይ የሆኑ ሥራዎች ሲሠራ የቆየው የአስተዳደር አካል በሠፊው ህዝብ መራር ትግል የተገረሰሰ ቢሆንም ከጅምሩ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ መራሹ አካል ከቀድሞ በከፋ ሁኔታ አግላይና በማን አለብኝነት የተዛባ አመራር እየተመራ በመሆኑ፤ ይህ ታላቅ ህዝብ በሠላማዊነቱ ፈንታ በተቀነባበረና በመንግስት አካላት በታገዘ መሰደድና አለመረጋጋት፣ለትዕግስተኝነቱ ምላሽ ደግሞ የሃብት መዘረፍና የመንግሰት ትኩረት ተነፍጎት ይገኛል።
ለአብነት ያክል በሸካ ዞን ውስጥ ቴፒና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የአካባቢውን ዜጎች አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ በማረጋጋት ወደቀያቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ አሁን ሃገርቱን እመራለሁ የሚለው ኢ-ሚዛናዊ ስርዓት የፈረጠመውን የመከላከያ ጡንቻ በማሳየት ኮማንድ ፖስት በማቋቋምና ህዝቡን በማሸማቀቅ ላይ መገኘቱ በእጅጉን አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል። በተጨማሪም በቤንች ማጂ ለመብት ጥያቄ የወጡ ህፃናት ሳይቅሩ የጥይት ሰለባ የሆኑበት፤ የማጂ ህዝብ መብቱን በጠየቀ ለስቃይና ለስደት የሚዳረግበት፣ የጅማ ህዝብና ወጣት በቀዬው ባይተዋርና ሁለተኛ ዜጋ የሚሆንበት ጊዜ ልያበቃ ይገባል። ብሎም የየም ህዝብ ለዘመናት ከኖረበት ቀዬው ተገፍቶ እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታም ሳይፈታ ይሄው ዘልቋል።

በሌላ በኩል ከካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ተፈናቀሉ የተባሉትን ወደቄያቸው እንዲመለሱ በሚል ሳብያ ቁጥራቸው በውል የማይታውቅ አዳዲስ ሰፋሪዎች እንዲገቡ መደረጉ የፈደራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት በእርግጥ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት ፍላጎት እንደሌለውና ብሎም ለአካባቢው ህዝብ ያለውን ንቀት አጉልቶ ያሳየ አሣፋሪ ድርጊት መሆኑን ተረድተናል።
የሰፈራ ዓላማው የህዝቦችን ህይውት መለወጥ ከሆነ በአካባቢው ያሉ መሬትና ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀትና እገዛ በመስጠት የመሬት ባለቤት ማድረግ አይቻልም ነበርን? ህዝቦች ባሉበት፣ በለመዱነትና በስነልቦና በተሳሰሩበት ቀዬ ሆነው ህይውታቸውን የሚለውጡ የኤኮኖሚ አማራጮችን መፍጠርስ አይቻልም ነበርን?
በተለይ የፖለቲካና ዴሞግራፊ ለውጥ ለማድረግ ተብሎ በህዝቦች መካከል ኢ-ፍትሃዊና አድሎአዊ ድርጊቶችን እየፈፀሙ እንደ አገር አስተዳድራለሁ ማለት ዘለቄታ የለውም። ምክንያቱም ይህ ህዝብ በታሪኩ አገር መስርቶና አገር ሆኖ የሚያውቅም ነበርና።
በአጠቃላይ እነዚህንና ሌሎችንም በርካታ ችግሮችን እስከ ዛሬ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲከታተልና ምላሽ ለማግኘት ሲጠባበቅ የኖረው ህዝብ ላይ እየደተደረገ ያለው መጠነ ሰፊ አስከፊ ድርጊት በአፋጣኝ እንዲቆም ድርጅታችን በመላው ህዝባችን ስም በጥብቅ ያሳስባል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባሁኑ አወቃቀር ያለው የደቡብ ክልል መሪዎች ሁሉንም እኩል መምራት የማይችሉና ፍላጎትም የሌላቸው መሆናቸውን በተግባር በአደባባይ እያሳዮ የሚገኙ መሆኑ ለቀድሞ ካፋ ክ/ሀገር ሕዝብ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው:: ስለሆነም የመጪው ምርጫ ከመታሰቡ በፊት የጋራ ተቋማትን መገንባትና ህዝባችንን በጋራ አጀንዳ ላይ አስተሳስሮ ከመሄድ ጎን ለጎን የደቡብ ምዕራብ ህዝብ የክልል መዋቅር ጥያቄ በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል። ይህ ጥያቄ ከምክንያታዊም በላይ ነውና ለሕዝቡ ጥያቄ መፍትሔ ማበጀት ለአገራችን መረጋጋትና ቀጣይነት ትልቅ መፍትሔ ይሆናል ብለን እናምናለን።
ሕዝባችንም የሥርዓት መሪና ፈጣሪ እራሰ መሆኑን እንደሚገነዘበው ሁሉ በአንድነት በመሆን ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡና ይባስ ብለው አሁን እየከፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በእጁ ለመጨበጥ ከምን ግዜውም በላይ መታገል ይጠበቅበታል።

ሌላው የሲዳማን ክልል መሆን እያመቻቸ ያለው የደቡቡ መረን መንግስት ነኝ ባይ በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን ምንም ዓይነት ዓላማና ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ከአሁን በሗላ የዚህ አከባቢ ጉዳይ የማይመለከተው መሆኑን አውቆ እጁን እንዲያነሳና በፌደራልም ደረጃ አለሁኝ ሃገርቱን እየመራሁ ነኝ የሚለው መንግስት አድሎአዊ አሠራሩን በአፋጣኝ በማቆም እንደ ህዝብ ይህንን ታላቅ ህዝብ በማክበር ለአንዴና ለመጨረሻ የዘመናት የክልል ጥያቄያችንን ባጠረ ጊዜ እንዲመልስልንና ለሌሎችም መፍትሔ ለሚያሻቸው አንገብጋቢ ችግሮች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ እየጠየቅን ይህ ተግባራዊ ባይሆን የአከባቢው ሕዝብ የራሱን እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን እናሳውቃለን:: ድርጅታችንም የሕዝቡ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ምላሽ እስኪያገኝ ሁሉንም የትግል አማራጭ ለመጠቀም የሚገደድ መሆኑን እንገልፃለን::

በአጠቃላይ በአገሪቱ ደረጃ በመንግስት እየተካሄደ ነው የሚባለው የለውጥ እንቅስቃሴ የአንድና የሁለት ብሄሮች አገር ብቻ አስመስሎ እየቀረበና እየተካሄደ ያለ መሆኑ ፍንትው ብሎ የሚታይ ነውና፤ መንግስት የማያዝልቀውን የአንድና የሁለት የብሄር የበላይነትን መንገድ ትቶ ሁለንም ዜጎችና ህዝብ ያማከለ የለውጥ መንገድ ሳይረፍድና ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት በአስቸኳይ እንዲከተል በጥብቅ እናሳስባለን:: ጥቂቶች ተሰባስበው በኢትዮጵያ ስም የሚቀራመቱን የቅርጫ ስጋ አይደለንምና።

እራስን በራስ የማስተዳደር እና የመሬትና የሃብት ባለቤትነታችን በህዝባችን የጋራ ትግል ይረጋገጣል።

ደምኢህህ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: