Leave a comment

የካፋ እና የአጎራባች ህዝቦች የክልልነት ጥያቄ፤ ታሪ ካዊ መሰረት፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችና፣ የሚጠበቅ ምላሽ፡፡


ከኬሮ ኬቶ ጋዎ

የካፋ እና የአጎራባች ህዝቦች የክልልነት ጥያቄ፤
ታሪ ካዊ መሰረት፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችና፣ የሚጠበቅ ምላሽ፡፡

I. መነሻና መግቢያ

በታሪክ እንደሚታወቀዉ፣ አገሮች በጦርነትት በወረራ፣ በህዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እና ተመሳሳይ መንገዶች መመሥረታቸዉና፣ መስፋፋታቸዉ ይታወቃል፡፡ አብዛኛዎቹ ገዢዎች የራሳቸዉን ማብራሪያ ቢሰጡም፣ የትም ቢሆን በወረራ የተፈጠረ ግንኙነት በዋናነት የሚካሄደዉ፣ ሃብት ለመቆጣጠር፣ ግዛት ለማስፋፋትና፣ የራስን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ሆኖም በዚህም መንገድ ቢሆን የተመሰረቱ አገሮችና የህዝቦች ግንኙነት በሂደትና ጊዜዉን ጠብቆ፣ ሁኔታዎች ሲረጋጉና አብሮነቱ ሲዳብር፣ በወረራ የተቀላቀሉትም ህዝቦች በሂደት ክብራቸዉና መብታቸዉ ተጠብቆ፣ የአገራቱ እኩል ዜጋ ሆነዉ ሲቀጥሉ፣ በባርነትም ሆነ በሌላ መንገድ የተቀላቀሉና በዘራቸዉ ጭምር የተገለሉት ሁሉ ሳይቀሩ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸዉ ተረጋግጦ፣ የመሪነት ሥልጣን ሲይዙ ጭምር ታይቷል፡፡ በዚህ መንገድ የተመሰረቱ አገሮች አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ ብለዉ አይከፋፍሉም፣ በእዉነትም ያለፈዉን ለታሪክ ትተዉ አንድነታቸዉን አጠናክረዉ በጋራ አገራቸዉን ያለማሉ፣ ይጠብቃሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች ግን እስካሁንም ድረስ የተወሰኑ ማህበረሰቦችን እኩል ባለማስተናገዳቸዉ፣ በሚቀሰቀሱ የመብት ጥያቆችና እንቅስቃሴዎቸ የተነሳ፣ ሰላም ሲደፈርስ፣ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሲደርስ ይታያል፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን የተወረሩም ሆኑ፣ በባርነት ሥር የነበሩ ህዝቦችን እኩል የማያዩ መንግሥታት ቁጥር አነስተኛ ነዉ፡፡
ጥንታዊና፣ በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቀደምትና ጉልህ ታሪክ ከነበራቸዉ ህዝቦችና መንግሥታት አንዱና፣ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ነፃነቱን ጠብቆ የቆየዉ፣ የካፋ ንጉሰ ነገሥት መንግሥትና ሥርዓቱ በወታደራዊ ድርጅትና በመሣሪያ ኃይል ተበልጦ በ1889 ዓ ም ህልውናወን አጥቷል፡፡ ይህንን አዉዳሚ ጦርነት ተከትሎም፣ በንጉሱና በመሪዎቹ ላይ ግፍ፣ እንዲሁም፣ በቅርሶቹና በሐብቱ ላይ ለመግለፅ የሚከብድ ዉድመት ደረሰበት፡፡ ከዚያም በኋላ በካፋ ላይ የተፈራረቁበት ገዢዎችም ባደረሱት የሥነ ልቦና ጫና፣ የሃብት ዘረፋና፣ ጭቆና ህዝቡም በአጠቃላይ ነፃነቱን፣ ስብዕናዉንና ክብሩን በሙሉ አጣ፡፡ ይህ ተፅዕኖ እስካሁንም ቀጥሎ፡ ካፋ፣ ከሌሎች ህዝቦች በባሰ ሁኔታ፣ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ተገልሎ፣ ማህበራዊና እኮኖሚያዊ ልማትም ተጠቃሚ ሳይሆን ቀጥሏል፡፡ እንኳንና በአገሪቱ ጉዳይ ሊሳተፍ ይቅርና፣ የራሱን የውስጥ ጉዳይ ጭምር በራሱ እንዳያስተዳደር ተደርጎ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪና በሚመደቡ ሹመኞች፣ አዛዦችና ገዢዎች ሲገፋ፣ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ አሳልፏል፡፡ ገዢዎቹም የካፋን የመንግሥት ሥርዓት ማፈራረስ ብቻ ሳይሆን፣ ባህሉንና ታሪኩን አጥፍተዉ እና፣ መሬቱን ቀምተዉ፣ሕዝቡን ከቀዬዉ በማፈናቀልና፣ እንዲሰደድ በማድረግ፣ በቦታዉ ከተለያዩ አካባቢዎች ሰፋሪዎችን በማስፈር፣ ህልዉናዉን አጠፉት፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደርና፣ የራስን ባህልና ታሪክ መንከባከብ በፖሊሲ ደረጃ በተፈቀደበት በኢህአዴግ ዘመን እንኳን ካፋ ወደ ዞን ደረጃ ዝቅ ሲደረግ፣ በዞን በወረዳና፣ በቀበሌ ጭምር መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ባለሙያዎች እንኳን የሚመደቡት አሁንም በገዢዎቹ ተመርጠዉ መሆኑ ቀጥሏል፡፡
በዚህም ጊዜ ሁሉ የካፋ ህዝብ ህልዉናዉን ለማስጠበቅ ጥረት ከማድረገ የተዘናጋበት ጊዜ ባይኖርም በአብዛኛዉ ለልምድና ለቀጣዩ ትዉልድ ትምህርት ከመሆን ባለፈ፣ ቀጣይነት ያለዉ፣ በአግባቡ የተደራጀና የተሳካ ሆኖ ወጥቷል ማለት ይከብዳል፡፡ ከተሞከሩት ጥረቶችም ለምሣሌ ያህል፣ ከወረራዉ በሁዋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት፣ የካፋን መንግሥት መልሶ ለማቋቋም፣ ዘዉዱንና ቅርሶችን ወደ ካፋ ለመመለስ ጥረት ተደርጎ የነበረ ሲሆን ከነበረዉ የመገናኛና አንፃራዊ አቅም የተነሳ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ይልቁንም፣ ይህ ሙከራ አፄ ምኒልክንና፣ በተከታታይ ካፋ ላይ የተሾሙ ገዢዎችን፣ የበለጠ አፋኝና ጨካኝ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ገዢዎች ቅርሶቹን ወደ አዉሮፓ በመላክ ተገላገሉት፡፡ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ዘዉዱና በርጩማዉ ቢመለስም፣ ይባስ ተብሎም በኋላ ደግሞ፣ ስለካፋ የተፃፉ የታሪክ መፅሐፍት እንኳን ከዉጭ እንዳይገቡ ተከልክሎ፣ ተከታታይ ትዉልዶችና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ስለካፋ እንዳይገነዘቡ ሆኖ፣ ህዝቡ ማንነቱን እንዲረሳ ተደረገ፡፡
በሌላ በኩልም የተቀነጨበ ወይም በአብዛኛዉም የተዛባ ታሪክ እንዲፃፍ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህም ሴራ እስከዛሬዉ ትዉልድ ቀጥሎ፣ በቅርቡ እንኳን ያዉም ታሪክና ባህል ማሳደግ በተፈቀደበት ዘመን፣ በካፋ ታሪክ ላይ በካፋ ልጆች ተነሳሽነት የተደረጉ ሙከራዎችን ለይስሙላ እንዲፃፉ ተደርጎ፣ በኋላ ግን በተግባር እንደታየዉ፣ የተፃፉትን የታሪክ መፅሐፍትና የባህል ዉጤቶች ለህዝቡ እንዳይሰራጩና እንዳይደርሱ፣ ወይም የተለያዩ ማደናገሪያና ማስፈራሪያ ወሮዎችን በማሰራጨትና በማጥላላት ጭምር፣ በረቀቀ መንገድ የማደናቀፍ ሥራ ሲተገበር ታዝበናል፡፡
ነፃነት አንዱ ለሌላዉ ህዝብ በሽልማት (ወይም በችሮታ) የሚሰጠዉ ሥጦታ አይደለም፡፡ ህዝቦቹ ራሳቸዉ ይገባኛል ብለዉ የሚቀናጁት፣ እንጂ ማንም ሊከለክላቸዉ ወይም በፈቃዱ የሚሰጣቸዉ አይደለም፡፡ የተሰጠ ነፃነት ደግሞ ሰጪዉ በፈለገዉ ጊዜ መልሶ የሚወስደዉ ድርጎ ስለሆነ የራስ (ነፃነት) አይደለም ማለት ነዉ፡፡
የ1889ኙን ወረራ ተከትሎም ህዝቡን በተለይም የነቁ እና ሊያምፁ ይችላሉ ተብለዉ የሚጠረጠሩትን ካፈቾዎች እንቅስቀሴ አብረዉ በሚኖሩ ሰፋሪዎች አማካይነትና፣ በግልፅ በየቀበሌዉ በተመደቡ ነጭ-ለባሾች አማካይነት በአይነ ቁራኛ መከታተል ቀጥሎ ነበር፡፡
ህዝቡን በኢኮኖሚ ለማቆርቆዝም፣ ሐብቱን ከመዝረፍ ባለፈ፣ የተለየ የመሬት ሥሪትና፣ አፋኝ አገዛዝ በመመስረት፣ ተመልሶ በራሱ እንዳይቆም ተደረገ፡፡ የካፋን ንጉሰ-ነገሥት ሥርዓት የዕድገትና የጥንካሬ ደረጃ፣ የህዝቡን ብልፅግናና ለዚህ ሲባል ስለተካሄደዉ ጦርነትም ሆነ ስለደረሰዉ ተከታታይና ሰፊ ግፍና፣ አፈና በዚህ ፅሑፍ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ሆኖም በዚህ ላይ በተለይም የተወሰኑ የዉጪ ዜጎችና ጥቂት አገር በቀል ፀሐፊዎች በጥልቀት የፃፉ ስለሆነ ማንበብ ይቻላል፡፡ አሁንም ቢሆን ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ሲተላለፍ ከቆየዉ መረጃ መረዳት ስለሚቻል በተገቢዉ ሥልት ባለሙያዎች ቢያጠኑትና ቢፅፉት ይጠቅማል፡፡ ሆኖም ለዚህ ፅሑፍ ርዕሥና ዓላማ በሚረዳ ደረጃ፣ ጥቂቶቹን በመጠኑም ቢሆን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአጭሩ በካፋ ላይ ጫናዉ እስከ ዛሬም መቀጠሉና ይልቁንም በባሰ ሁኔታ በሁሉም ረገድ እየከበደ መሄዱን ማየት እና፣ በሌላም በኩል ደግሞ ህዝቡ መብቱን ለማስከበር ያደረጋቸዉን ጥረቶች፣ መጠቆም ተገቢና ወቅታዊ ይሆናል፡፡ በዚህም ረገድ ሊጠቀሱ የሚችሉ የመብት ጥያቄዎችና እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆኖ፣ የካፋ ህዝብ አብዛኛዉን ጊዜ ገዢዎች ወደ ልባቸዉ እንዲመለሱ ዕድል እየሰጠ፣ በአርቆ አስተዋይነትና፣ በተረጋጋ መንፈስ ለመቀጠል ግን ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች በገደብ መንቀሳቀስ ቢመርጥም፣ የተለወጠ ተጨባጭ ነገር አልታየም፡፡
በርካታ የዓለም ምሁራንና ፖለቲከኞች እንዳስተማሩት፤ ዕዉነታዉና መታወቅ ያለበት “ነፃነት ማለት አንዱ ለሌላዉ ህዝብ በሽልማት (ወይም በችሮታ) የሚሰጠዉ ሥጦታ አይደለም፡፡ ህዝቦቹ (ባለመብቶቹ) ራሳቸዉ ለእኔ የሚገባኝ መብቴ ነዉ ብለዉ የሚቀዳጁት እንጂ፤ ማንም ሊከለክላቸዉ ወይም በፈቃዱ ሊሰጣቸዉ የሚገባ ጉዳይ አይደለም”፡፡ የተሰጠ ነፃነት ደግሞ ሰጪዉ በፈለገዉ ጊዜና መንገድ መልሶ የሚወስድበት ወቅት ሊመጣ እንደሚችል ታዉቆ፣ የራስን ነፃነት ባለቤቱ ራሱ መዉሰድ አለበት ማለት ነዉ፡፡
​በአሁኑ ጊዜ እንደካፋ ሁሉ በታሪክ አጋጣሚ መብታቸዉን የተነጠቁ የራስን አስተዳደር የጠየቁ የደቡብ ህዝቦች እየሄዱበት ያለዉ መንገድና ጥልቀት ሲታይ፣ ይህንን የተረዱና፣ ነፃነታቸዉን ራሳቸዉ ለመዉሰድ ቁርጠኛ መሆናቸዉን ያሳያል፡፡ የካፋ ህዝብም ብዙ ሳይርቅ ከነዚህ ተምሮና ከራሱ ተሞክሮ ቀምሮ፣ በመለማመጥ የሚያገኘዉ ነፃነት፣ ክብርና ዕዉቅና እንደማይኖር በግልፅ አዉቆ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ህገ-መንግሥቱን ጠብቆ በዞን ምክር ቤት የክልል ጥያቄ ላቀረበ ባለታሪክ ህዝብ “የክልል ጥያቄዉ፣ ፋሽን እንጂ የብዙሐን ጥያቄ አይደለም” እስከማለት የሚደፍሩ ገዢዎች ለትህትናዬ ተመጣጣኝ ምላሽ ይሰጡኛል፣ መብቴንና ክብሬን ያስጠብቁልኛል ማለት የዋህነት፣ ምናልባትም ስንፍና ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ እንደአሁኑ የቴክኖሎጂዉ ደረጃ ባልዳበረበትና በተለያየ ዘርፍ የተማሩና፣ ለመረጃም የቀረቡ ምሁራን ልጆች ባልነበሩበት ጊዜም ቢሆን የሚደርስበትን አፈና በአስተዋይነትና በተረጋጋ መንገድ ሲከላከል የቆየ ሲሆን፣ ከበድ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ግን አሜን ብሎ የተቀበለበት ጊዜ አለመኖሩን ማወቅና፣ ይልቁንም ቁጭ ብሎም በጠበቀባቸዉና በአርቆ አስተዋይነቱ አለዝቦ በሚያቀርባቸዉ የመብት ጥያቄዎች ላይ ገዢዎች በተነፃፃሪነት ተረድተዉት፣ ክብሩንና ጥቅሙን የጠበቁለት ጊዜ አልነበረም፡፡ ስለዚህ መብቱን ራሱ ማስከበር፣ የተነጠቀዉን ነፃነቱንና ክብሩን ራሱ ታግሎ መዉሰድ አለበት፡፡ በእርጋታ ለፋቸዉንና ታግሎም ያገኛቸዉን የተሳኩና፣ ባይሳኩም ለሁሉም ወገኖች ትምህርት ሰጥተዉ ያለፉ አጋጣማዎች በጥቂቱ ከዚህ በታች ለመጥቀስ ተሞክሯል፡፡

➢ ከ1889 ጀምሮ እስከጣሊያን ወረራ ድረስ በነበሩት ዓመታት፣ የቀድሞዉ የካፋ ንጉሰ-ነገሥት ግዛት፣ ለማዕከላዊዉ የኢትዮጵያ ን/ነ/ መንግሥት
ተጠሪ ከነበሩት 12 ግዛቶች አንዱ ሆኖ ቀትሎ ነበር፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜም፡ ጣሊያን ቀድሞዉንም ሲያጠና እንደቆየ በሚያሳይ ሁኔታ፣ የካፋን ንጉሳዊን ቤተሰቦች ከተሰደዱበት ፈልጎ ወደ ካፋ ሲያመጣ፣ አባ ቀስቶ የሚባሉትን የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል እንደራሴ በማድረግ ማስተዳደር ቀጥሎ ነበር፡፡ በወቅቱም የካፋን መኳንንትና ነቃ ያሉ ወጣቶችን በመጠቀም፣ የተወሰነ የልማት እንቅስቃሴ፣ የባህልና የቋንቋ ማጎልበት ሥራ ተጀምሮ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ወደ ነበረዉ አፈና ላለመመለስ፣ በ1933 ዓ ም አፄ ሃይለ ሥላሴ ወደ ሥልጣን ሲመለሱ፣ የካፋ የወቅቱ ምሁራንና አርበኞች በግራዝማች ጳዉሎስ (ቆጭቶ) መሪነት አምፀዉ ለኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ላለመገዛት ሞክረዉ ነበር፡፡ ይህም አመፅ በካፋ ምድር ከተመዘገቡት ዋና ዋና ጦርነቶች (የአንድራቻ ጦርነት በካፋ ንጉሰ-ነገሥት መንግሥትና በኢትዮጵያ ሰራዊት መካከል የተደረገዉ የ1889 ጦርነት ሲሆን)፣ ሁለተኛዉ ሲሆን፣ በካፋ ህዝብ ዘንድም የጳዉሎስ ጦርነት የሚባለዉ ነዉ፡፡ ሆኖም ገና ከነፃነት መመለስ በኋላ ለመጠናከር ጊዜ ያስፈለገዉ ማዕከላዊ መንግሥት ባደረገዉ፣ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ጦርነቱ ቆሞ፣ በዕርቅ የተቋጨ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዕርቁ መሰረት የአመፁ መሪ በሰላም ወደ አዲስ አበባ ተወስደዉ መጠነኛ ዕዉቅና ተሰጥቷቸዉ መደበኛ ህይወት እንዲኖሩ ቢደረግም፣ ብዙም ሳይቆይ፣ በረቀቀ ሁኔታ በመኪና ተገጭተዉ እንዲሞቱ መደረጉን በህይወት ያሉ ወገኖች ይመሰክራሉ፡፡

➢ ከዚያም በኋላ፣ እንደገና በተዋቀረዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ-ነገሥት ግዛት ዉስጥ፣ ካፋ ለማዕከል ተጠሪ ከነበሩት ጠቅላይ ግዛቶች ደረጃ ወርዶ፤ አዲስ
በተዋቀረዉ “ጅማ ጠቅላይ ግዛት” ሥር አንድ አውራጃ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ በዚህም ካፋ የሚባለዉ ሥያሜ ጭምር ከታሪክ በመፋቁ ሌላ የመረረ ተቃዉሞ በካፋ ልጆች ተነሳ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ዉሳኔዉን አሻሽሎና፣ አቻችሎ፣ በ1935 ዓ.ም. እንደገና ጠቅላይ ግዛቱ፣ ጅማ መባሉ ቀርቶ፣ “ካፋ ጠ/ግዛት” እንዲባል፣ ዋና ከተማዉ ግን ጅማ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የቀድሞዉ ካፋ ደግሞ በጠ/ግዛቱ ሥር ከተዋቀሩት ስድስት አዉራጃዎች አንዱ ሆኖ “በካፋ ጠቅላይ ግዛት ሥር ሆኖ፣ የካፋ አዉራጃ” እንዲባልና የአዉራጃዉ ዋና ከተማዉም ቦንጋ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ይህም ማለት ከዚህ በኋላ ካፋ ከማዕከላዊ መንግሥት ሁለት ዕርከን ርቆ አዉራጃ ሆነ፡፡ ካፋ አዉራጃም በጠቅላይ ግዛቱ ገዢና በሥሩ በተመደቡት የአዉራጃ ገዢዎች ሙሉ ቁጥጥር ሥር ሲገባ፣ የጠቅላይ ግዛቱን ማዕከልና ገዢዎች ለማበልፀግ ሃብቱ ሲገፈፍ፣ ህዝቡም በየትኛዉም ዕርከን በዉሳኔ ሰጪነት ቀርቶ ይህ ነዉ በሚባል ሃላፊነት ቦታ እንዳይመደብ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጎበት ታፈነ፡፡
➢ ከዚህም ቀጥሎ፣ በካፋ ላይ የተወሰነዉን ልዩና ገፋፊ የመሬት ሥሪት ዕዉቅ የካፋ ልጆች እስከ ዙፋን ችሎት ድረስ ተከራክረዉ እንዲስተካከልና
በመጠኑም ቢሆን እንዲስተካከል አደረጉ፡፡
➢ የኢትዮጵያን የ1966 አብዮት ተከትሎም፣ ወደ ሥልጣን በመጣዉ ወታደራዊ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ደግሞ፣ በአገሪቱ ተበታትነዉ
የሚገኙ የካፋ ምሁራን ተጠራርተዉ ወደ ካፋ ገብተዉ አካባቢያቸዉን ለማልማትና፣ ህዝቡን ለማንቃት ሞክረዉ ነበር፡፡ ሆኖም ከ1889 ዓ.ም. በኋላ በተመሰረተዉና በንጉሳዊዉ ዘመን በተደራጀዉ የስለላና የአፈና መዋቅር ቅሪቶች ሴራና፣ የወታደሩ የሥልጣን ሥጋትና፣ ብስለት ማነስ ታክሎበት፣ እነዚህም ምሁራን እንደገና እንዲገፉ ተደረገ፡፡ ይኸዉም የካፋ ምሁራን በመሰባሰባቸዉ ህዝቡ እንደገና እንዲያንሰራራ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት የፈጠረባቸዉ ሴረኞች፣ “የካፋ ነፃ አዉጪ ተመሰረተ፣ ካፋ ከኤርትራ ቀጥሎ ነፃ ሊሆን ነዉ” የሚል የፈጠራ ዜና አቀነባብረዉ ለደርግ ኢንዲደርስ በማድጋቸዉ፣ ምሁራኑ እንዲሰደዱና ተስፋ እንዲቆርጡ ሆነ፡፡ የቀሩትም ለምክክርም ቢሆን ግንኙነታቸዉ ሁሉ ከዚህ በኋላ ህቡዕ ሆነ፡፡ ደርግ በመርሁ ብሄረተኛ አለመሆኑ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት የቆመ መሆኑ ቢታወቅም ምናልባትም ዉስጥ ለዉሥጥ ስለተቦረቦረና፣ ይልቁንም በተለይ የነጭ ለባሾች ሴራ ሰለባ በመሆኑ የተለመደዉ ጫና በካፋ ልጆች ላይ ቀጠለ፡፡ የታላቁ የካፋ ልጅ የገብረ ፃዲቅ ሻዎ በግፍ መገደልም ለደርጉ አባል እንዲደርስ በተደረገ የዚሁ ሰንሰለት የተቀነባበረ መረጃ መሆኑ ሲታወቅ፣ ቀሪዎቹ ምሁራንም በተለያየ ሰበብ ሲታሰሩና ሲገረፉ፣ ሲሳደዱና ዓላማቸዉ ሲኮላሽ ለካፋ የሚቆም ሰዉ ሁሉ በሥልታዊ መንገድ ተወገደ፣ የቀረዉም ታፈነ፡፡
ህጉን ጠብቆ በዞን ምክር ቤት የክልል ጥያቄ ላቀረበ ባለታሪክ ህዝብ “የክልል ጥያቄ፣ ፋሽን እንጂ የብዙሐን ጥያቄ አይደለም” እስከማለት የሚደፍሩ ገዢዎች ትህትናዬን አይተዉ መብቴንና ክብሬን ያስጠብቁልኛል ማለት የዋህነት፣ ገፋ ሲልም ሥንፍና ይሆናል፡፡ የካፋ ህዝብ እንደአሁኑ ቴክኖሎጂ ባልዳበረበትና በተለያየ ዘርፍ የተማሩ ምሁራን ልጆች ባልነበሩበትም ጊዜም ቢሆን ሚደርስበትን አፈና አሜን ብሎ የተቀበለበት ጊዜ አለመኖሩን ማወቅና፣ ቁጭ ብሎም መብቱና ክብሩ የተጠበቀበት ጊዜ አልነበረም፡፡
ይህ የረጅም ዘመናት የነጭ ለባሽና፣ የአፈና መዋቅርና ተፅዕኖዉ እስከ ዛሬም ድረስ አለመቀጠሉንና በሥራ ላይ አለመሆኑን በአሳማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ባይቻልም፣ በርካቶች ግን ተፅዕኖዉ መቀጠሉን ይስማሙበታል፡፡ ይልቁንም ከህዝቡ ጋር ተሰባጥረዉ አብረዉ እየኖሩ፣ የፈጠራ ወሬ በመንዛት ህዝቡን ማሸበርና
መብቱን ከመጠየቅ እንዲያፈገፍግ ማደናገር፣ ምሁራንን ደግሞ በረቀቀ ሁኔታ
ጠልፎ መጣል‹ ማስበርገግና ከዞኑ ማባረር፣ ወደ ሥልጣን ለሚወጡ ባለጊዜዎች ደግሞ የተዛባ መረጃ በማቅረብ የፍርሃትና የጥርጣሬ መንፈስ መፍጠር፣ ከተቻለም በአመራሩ ዉስጥ ሰርጎ በመግባት በቀጥታ ጥቃት ማድረስ፣ እና በዚህም በሁሉም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ረገዶች፣ የካፋ ህዝብ ቀና እንዳይል ማደናቀፍ እንደሚታይ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ይህ ደግሞ በየዘመኑ ለሚመጡ ቅጥረኛ ገዢዎች ሰፊና ነፃ የመጫወቻ ሜዳ ስለሚፈጥርላቸዉና፣ ለህዝቡ የሚቆም ሐቀኛና አቅም ያለዉ የሥልጣን ተቀናቃኝ እንዳይወጣ ስለሚያደርግ፣ ለገዢዎቹ ያለድካምና ወጪ የሚቀርብ አጋዥ አቅም ሲሆን፣ ለካፋ ህዝብ ግን ተጨማሪ እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ቀጣይ የአፈና ተግባር የተነሳ ካፋ በደርግ ዘመንም ጭምር ከካፋ ዉጪ በሚመጡ አስተዳዳሪዎችና ፖለቲከኞች ወይም ካፋ ዉስጥ በተወለዱ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሲተዳደር ቆይቷል፡፡
በወታደራሪዉ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት፣ በመልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር፣ በልማት ደረጃ፣ በኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ በታሪካዊ፣ ባህላዊና፣ ሥነ-ልቦና መቀራረብ መሰረት፣ የካፋ አስተዳደር አካባቢ የሚባል ክልል እንደገና ሲዋቀር ዋና ከተማዉ ግን አሁንም ሚዛን ተፈሪ ሆኖ ተመሰረተ፡፡ የካፋ አዉራጃም ተከፋፍሎ ሁለትና ሶሥት ወረዳዎች በአንድነት አዉራጃ እየተባሉ ሲዋቀሩ ቦንጋና በዙሪያዉ ያሉት አካባቢዎች የቦንጋ አዉራጃ ተባሉ፡፡ በዚሁ (ኢህዲሪ) አወቃቀር በየአካባቢዉ ብሔርን መሰረት ያደረገ ምደባ በመላ አገሪቱ የተደረገ ሲሆን፣ በካፋ አስተዳደር አካባቢ ግን ከካፋ ተወላጆች አንድ የሸንጎ ፀሐፊና ሁለት ምክትል አስተዳዳሪዎች ብቻ ቢመደቡም ከዋና አስተዳዳሪና ከፓርቲ ፀሐፊዎች ጀምሮ በክልሉም ሆነ በአዉራጃዎች አንድም የአካባቢዉ ተወላጅ አልተመደበም ነበር፡፡ ይህም ካፋ በአይነ-ቁራኛ መታየቱን የመሰከረ ሌላዉ ዘመን ሆኖ አልፏል፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣኑን በ1993 ዓ.ም. ሲቆጣጠርም በሽግግሩ ወቅት ይህ ክልል በ4 ዞኖች (ካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች እና ማጂ) ተከፋፍሎ፤ ክልል 11 ተብሎ በአዋጅ ተወቅሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ተረጋግቶ በራሱ ቅኝት በአካባቢዉ የመለመላቸዉን ታዛዥ ካድሬዎቹን ካዘጋጀ በኋላ የራሱን ካድሬዎች ጭምር እና፣ በደቡብ አካባቢ የተመሰረቱ ተቃዋሚዎችን አደናግሮ ወደ አንድነት በማጠቃለል፣ ክልሉን ጨፍልቆ በደቡብ ሥር ከህግ ዉጭ አወቀረ፡፡ በዚህም ካፋ እና አጎራባች ህዝቦች ከሺህ ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘዉ ደቡብን ተቀላቀሉ፡፡ በወቅቱ በደቡብ ሥር መደራጀትን የተቃወሙትን የራሱን ካድሬዎች ጭምር በተለመደዉ ሥልት አባርሮ፣ አጎብዳጆችን ይዞ ቀጠለ፡፡ ይህም ካፋንና አጎራባች አካባቢዎችን፣ በደቡብ ሥር የመጠቅለል ሴራ፣ ለቀጣዩ አፈናና ዝርፊያ ዝግጅት መሆኑ በሂደት ግልፅ ሆኗል፡፡ ካፋም ሆነ አጎራባች ህዝቦች፣ ከአዋሳ ካላቸዉ ርቀትም በላይ፣ በዕድገት ደረጃቸዉና በሌሎች ብዙ ጉዳዮች የተለዩ ቢሆኑም፣ በደቡብ ክልል ሥር ሆነዉ፣ የሚመጥናቸዉንና የሚስማማቸዉን የልማት መስመር እንዳያስቡ፣ የራሳቸዉን ፖሊሲና አመራር እንዳያቋቁሙ ተደርጎ የደቡብ ክልል አንድ አካል የመሆን መንፈስና፣ አስተሳሰብ እንዲላበሱና ትዕዛዝ ፈፃሚዎች ሆነዉ፡ ለደቡብ ክልል ባለሥልጣናት አጎብድደዉና፣ በክልሉ የሚወጣዉን ፖሊሲና ስትራቴጂ ብቻ ሳይሆን፣ ደቡቦች የሚፈቅዱላቸዉን ዝርዝር ዕቅዶች እንዲፈፅሙ፣ ተለማምጠዉም እንዲኖሩ ተደረገ፡፡ ሁሉም ፖሊሲና ስትራቴጂ ለደቡብ ማዕከላዊ አካባቢዎች በሚመች ሁኔታ የሚቀረፅ፤ አተገባበሩም በደቡብ ባለሥልጣናት በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ህዝቡና አካባቢዉ ከነበረበት ወደ ባሰ ድህነትና ኋላ ቀርነት ወርዶና ቆርቁዞ፣ ገዢዎችም እንዳለሙት የአካባቢዉንና ቀድሞ የለሙትን የአገር ሃብቶች ያለ ምንም ሃይ ባ መዝረፍ ቀጠሉ፡፡
ለዚህም የወያኔና የደቡብ ታማኝ የሆኑ ጥቂት ምስለኔዎችን በማዕከል፣ በክልል፣ በዞንና በየወረዳዉ ቁልፍ ቦታዎች በመመደብና ከፍተኛ ሥልጣንና ጥቅም በመስጠት፣ ህዝቡንና ሃብቱን መቆጣጠር ተግባራዊ ሆነ፡፡ ይህ ህዝብ አሁንም በደቡብ ሥር በመሆኑ ሰቆቃዉ ቀጥሏል፡፡ በዚህም ወቅት እንኳን የተፈጥሮ ደኖችን ለማዉደም መሬቱን ለገዢዉ አባላት ፈርመዉ እንዲያስረክቡ ታዘዉ ያንገራገሩ የአካባቢዉ ሰዎችና፣ በተለያዩ የህዝቡ መብቶች ጉዳይ የተከራከሩ ሁሉ ተባረሩ፣ አንዳንዶቹም ታስረዉ ተሰቃዩ፡፡
➢ ይህንን ጫና መሸከም የከበደዉ ህዝብ፣ በተላያየ ጊዜያት ባገኘዉ መድረክ ብሶቱን ማሰማቱን አላቆመም፡፡ ለምሣሌም በ1998 በተካሄደዉ የካፋ
ልማት የምክክር ፎረም ላይ የካፋ የክልልነት ጥያቄ ጎልቶ የተነሳ ሲሆን ይህም አወቃቀር በጥልቀት እንዲጠና የሚለዉ፣ በወቅቱ ከተላለፉ የህዝቡ ዉሳኔዎች አንዱ ነበር፡፡
➢ በቅርቡም ለደኢህዴን ሊቀ-መንበር (አሁን በወቅቱ አፈ-ጉባኤና አሁን የሰላም ሚኒስትር) ለሆኑት ለወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የክልል ጥያቄን ጨምሮ፣
የደረሰበትን በደል በምሬት አቅርቧል፡፡ ክብርት አፈ- ጉባኤዋ ግን፣ በደቡብ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ “የምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ የጥቂቶች እንጂ መሰረት የሌለዉ” እንደሆነ ቢናገሩም፣ ተጨባጩ ምሬትና የህዝቡ ግፊት ያስገደደዉ የካፋ ዞን ምክር ቤት ግን ብዙም ሳይቆይ፣ በህዳር 06 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገዉ ጉባዔ “የካፋ ዞን በክልል ደረጃ እንዲዋቀር” ሲል ወስኗል፡፡
ይህም ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ ሌሎች አምስት ዞኖች ጋር ሲታይ ድሮም ከመርህ ዉጭ የተመሰረተዉን ክልልና፣ መሪዉን ድርጅት ጭምር ግራ ያጋባ ሲሆን፣ ከህገ-መንግሥቱ መርህ በተቃራኒዉ “ይጠናል” የሚል መግለጫ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ጥያቄ ካቀረቡትም ዉስጥ ሲዳማና ወላይታ በተደጋጋሚ ዉሳኔያቸዉ ተግባራዊ እንዲሆን በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ ሲሆን፣ ከሲዳማ በስተቀር ስድስት ወር የሞላዉ የካፋ ዉሳኔም ሆነ የሌሎቹን በተመለከተ ክልሉ በዝምታ ማቆየቱ፣ ዉሳኔዉ ዓመት ሲሞላዉ ምን እንደሚከተል ሲታሰብ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ለማንኛዉም የካፋን የክልልነት ጥያቄ መሰረቶችና ማስረጃዎች ማየቱ ለቀጣዩ ህጋዊም ሆነ፣ ፖለቲከዊ ሂደት ስለሚጠቅም ማየቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡
የካፋ የክልልነት ጥያቄ የወቅቱ ፋሽን፣ ወይም የጥቂቶች ጥያቄ አለመሆኑን፣ ታሪካዊ መሰረት፣ አሳማኝና ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት ያለዉ፣ በሁሉም አዕምሮ ሲጉላላ የነበረና ተገቢዉ ህጋዊ ምላሽ ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ካፋ አስከ ዛሬም ከአገሪቱ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ልማት፣እንዲሁም ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መገለሉ በመቀጠሉ፣ የዛሬዉም ትዉልድ ወቅቱን የሚመጥኑ ጥያቄዎች ማቅረብና፣ የህዝቡን መብቶች በህጋዊ መንገድ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥትም እንደሌሎች የሰለጠኑ ሥርዓቶች ተገቢዉን ምላሽ በመስጠት፣ የካፋ ህዝብ የጋራ አገሩን በእኩልነት እንዲያለማ መፍቀድና ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

II. የካፋ ክልል የመሆን ተጨባጭ ምክንቶችና መሰረቶች
ቀድሞዉንም የካፋ መንግሥት ህልዉና ሲጠፋ በህዝቡ ላይ የደረሰበት ግፍና በደል፣ አሁንም ካፋ በደቡብ ክልል ሥር እንዲገዛ ሲጨፈለቅ የደረሱበት አፈናዎች ተመሳሳይ የገዢዎች ዓላማዎች ሲሆኑ ይህም እንደታቀደዉ፣ ከፍተኛ የሃብት ዘረፋ ለመፈፀምና፣ በዚህም በተመሳሳይ ሁኔታ አካባቢዉንና ህዝቡን ወደ ኋላ ቀርነት መገፍተር ነዉ፡፡ ይህንን ግፍ፣ ገዢዎቹ ያቀዱትንና ተግባራዊ ያደረጉትን ሁሉ፣ ለማካካስ ዘመናትን የሚፈልግ ሲሆን ዋና ዋናዎቹን አፈናዎች ብቻ ለመጠቆም የሚከተሉትን ማየት ይጠቅማል፡፡
ሁሉም ፖሊሲና ስትራቴጂ ለደቡብ ማዕከላዊ አካባቢዎች በሚመች ሁኔታ የሚቀረፅ፤ አተገባበሩም በደቡብ ባለሥልጣናት በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ህዝቡና አካባቢዉ ከነበረበት ወደ ባሰ ድህነትና ኋላ ቀርነት ወርዶና ቆርቁዞ፣ ገዢዎችም እንዳለሙት የአካባቢዉንና ቀድሞ የለሙትን የአገር ሃብት መዝረፍ ቀጠሉ፡፡ ይህ ሁሉ የተፈፀመዉ፣ አካባቢዉን በደቡብ ክልል ሥር በማድረግ፣ ለራሱ የሚመጥን ህግ፤ ፖሊሲ ስትራቴጂና ደንብ እንዳያወጣ ተደርጎ፣ የደቡብ ተገዢ፣ ታዛዥና ፈፃሚ፣ በማድረግ ነበር፡፡
II.1. የካፋ ህዝብ የራሱን አስተዳዳሪ መምረጥ አልቻለም፣ በገዢዎቹ በሚመደቡና ታማኝነታቸዉ ለነርሱ በሆኑና፣ ህዝቡ በማይቆጣጠራቸዉ ምስለኔዎች መገዛቱ ቀጥሏል፡፡
የካፋ ህዝብ መሪዎቹን የመምርጥ፤ የመገምገም፤ የመቆጣጠር፣ የመገሰፅ፤ ብሎም የማዉረድና፣ በአጠቃላይ ራሱን በራሱ የመምራት
የደረጀ የረጅም ዘመናት ልምድና ባህል ባለቤት የነበረ መሆኑን ሁሉም ያዉቃል። ንጉሥ እስከማዉረድ የሚችል በጠቅላይ ምንስተር የሚመራ የተለያ ሴክተሮችን (ዘርፎችን) የሚመሩ ምኒስትሮች ምክር ቤት (ምክረቾ) የሚመራና በክልል ዉስጥ ወሳኝ የክፍለ ሃገር ገዢዎችና፣ በየደረጃዉም የራሳቸዉ ሃላፊነት ያላቸዉ ባለሥልጣናት የሚታደደር ሥርዓት ነበረዉ፡፡ ይሁን እንጂ ላለፈዉ ምዕተ-ዓመትና፣ እየባሰ መጥቶም ላለፉት 27 ዓመታት፣ በአብዛኛዉ የአካባቢና የወረዳ አስተዳደሪ መርጦም ሆነ አዉርዶ አያዉቅም፡፡ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች በክልል ባለስልጣናት ሲሾሙ፣ ሌሎችም ሃላፊዎች በክልልና፣ የክልሉ ምስለኔ በሆኑ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ሲመደቡና፣ ህዝቡ በማያዉቀዉ ምክንያት ከኃላፊነት ሲወገዱ፣ የህዝብ አቤቱታ የበዛባቸዉ ደግሞ ዕድገት ሲሰጣቸዉ፣ በየቀበሌዉም ሥራ አሥኪያጅ የሚባሉ መንግሥት መረጃዎች የሆኑ ደሞዝተኞች ሳይቀሩ በድርጅት ሃላፊዎች ሲመደቡበት ሰላማዊ ታዛዥና ተገዢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ በየደረጃዉ ያሉ ባለስልጣናት ተግባር፣ የሚመድቡአቸዉንና የሚያወርዱአቸዉን የክልል ኃላፊዎችና፣ ምስለኔዎቻቸዉን ማስደስት፣ ትዕዛዝ ማስፈፀምና መፈፀም ሲሆን፣ ከህዝቡ የራቁ የማይታወቁ የማይታመኑና የተጠሉ ናቸዉ፡፡ አብዛኛዎቹም ራሳቸዉ ጨቋኝ፣ ዓላማቸዉና ተግባራቸዉም አስኪወርዱ ሃበት ማግበስበስ፣ ቢሆኑም ከአለቆቻቸዉ በስተቀር ማንም አይጠይቃቸዉም፡፡ ህዝቡ በብቃታቸዉ የተሻሉትንና የሚያምንባቸዉን አስተዳዳሪዎች የሚመርጥበት ዴሞክራሲያዊ መብቱን ከተቀማ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በአካባቢዉ በሁሉም ደረጃ፣ የህዝቡን ጉዳዮች የሚወስነዉ የማይመለከተዉ የደቡብ ባለሥልጣን ሲሆን፣ የሚተላለፈዉን ዉሳኔም፣ በየደረጃዉ ያሉ ሃላፊዎች ቢፈልጉም ባይፈልጉም ተቀብለዉ መፈፀምና ማስፈፀም አለባቸዉ፡፡ ምክንያቱም የሚያስቀምጣቸዉም ሆነ የሚያነሳቸዉ የደቡብ ባለስልጣን እንጂ፣ የሚመለከተዉ የአካባቢዉ ህዝብ አይደለም ፡፡ ይህም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ሁኔታዎች ለማመቻቸት ወሳኙ ሂደት በመሆኑ በገዢዎቻችን ታስቦበት የተደረገ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
II.2. ህዝቡ ለአካባቢዉ ተገቢ ፖሊሲ ስትራቴጂና ደንብ ማዉጣት መተግበርና፣ መልማት አልቻለም፡፡
ማዕከላዊ መንግሥት ያወጣዉን ህግና ፖሊሲ፣ የክልል መንግሥት ወደራሱ ሁኔታ አጣጥሞ፣ ተግባራዊ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከክልል በታች ያሉት መዋቅሮች ሁሉ ፈፃሚና አስፈፃሚ ብቻ ናቸዉ፡፡ በደቡብ ክልል የምዕራብ ዞኖችን ባላማከለ መልኩ ማዕከሉ አዋሳ በመደረጉ፣ ክልሉ ደግሞ ፖሊሲዎችና ደንቦችን የሚያወጣዉ፣ ከማዕከሉ በቅርበት ያሉ፣ አብዛኛዉን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ባለሥልጣናትና ተወካዮቻቸዉ የመጡበትን፣ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ ማዕከላዊ የደቡብ አካባቢዎችን ታሳቢ አድርጎ ነዉ፡፡ የካፋና የሌሎችም የምዕራብ ዞኖች ተግባር የራሳቸዉን ልምድ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ ሀብትና፣ የኢኮኖሚ መሠረት፣ ማህበረ-ኤኮኖሚያዊ መስተጋብር፣ ስነ-ልቦና፣ ታሪክና የዕድገት ደረጃ፤ ታሳቢ ያላደረገዉን የክልሉን ዕቅድ፣ በኮታና በጫና ተቀብለዉ መፈፀም ብቻ ነዉ፡፡ ለምሳሌ፡-የክልሉ የማዳበሪያ አጠቃቀም ፖሊሲና ሥርዓት የምዕራብ ዞኖችን አፈር፣ ለምነትና የማዳበሪያ ፍላጎት ከግመት የማያስገባ፣ በኮታ፣ በግዴታ የሚታደል፣ ዕዳዉም የህዝቡን ጥሪት በግዳጅ እንዲሸጥ በማድረግ የሚከፈል፣ የድህነት ምንጭ ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ መሬቱ በግድ ማዳበሪያ ከለመደ በኋላ አቅርቦቱ በመቀነሱና በመቆራረጡ ወደ ባሰ ችግር ህዝቡን አስገብቷል፡፡ በሌላ በኩል የደቡብ ባለሥልጣናት ህዝቡን ሳያማክሩ በበሚያደርጉት ሰፈራ የተነሳ መሬቱ ሲወረስ፣ በተመሳሳይ የይስሙላ ፖሊሲና ዕቅድ ወደሰፈራ የተጓዙ መሬት አልባ የአካባቢዉ ተወላጆች የሰፈሩበት ቦታ ግን፣ መሰረተ-ልማት ያልተሟላበት፣ ይልቁንም የፀጥታ ችግር ባለባቸዉ አካባቢዎች በመሆኑ ለጥቃት ሲዳረጉ፣ ቦታዉን እየለቀቁ ተመልሰዉ ሥራ-ፈትና፣ የቤተሰብ ጥገኛ እንዲሆኑ ተዳርገዋል፡፡ ይህንንም ለማርገብ ክልሉ ወሰደዉ እርምጃ፣ ይባስ ብሎ የህዝቡን የግጦሽ መሬት ለአካባቢ ወጣቶች በማከፋፈል ህዝቡ ከብቶቹን የሚያሰማራበትን በማሳጣት ወደ ሁሉ-አቀፍ ድህነት ዳርገዉታል፡፡ የካፋና ሌሎች ምዕራብ ዞኖች የልማት መሰረት፣ በደንና የደን ዉጤቶች፣ እንዲሁም ከአካባቢዉ የአፈርና የእርሻ ባህል ጋር የተጣጣመ የግብርናና የእንስሳት እርባታ ጥምር ሥርዓት፣ ከዚህ ጋር የተገናኘ ንግድ ሲሆን፣ መሻሻልና መጠናከር ያለበት ስትራቴጂም ከዚህ ጋር የተጣጣመ የኢንዱስትሪና፣የኢኮ-ቱሪዝም ልማት መሆን ይገባዉ ነበር፡፡ ለይስሙላ በክልሉ የሚጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችም በጥራትና፣ በጊዜ ባለመፈፀማቸዉ፣ አንዳንዴም ጉዳት በማድረሳቸዉ፣ ህዝቡ በዝርፊያ፣ በፍትህ፣ በልማትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡
II.3. ለገዢዎችን ጥቅምና፣ ጠያቂ በሌለዉ የመሬት ወረራ፣ የህዝቡ ኑሮ ተናግቷል፣ የተፈጥሮ ሃብቱም ዉድሟል፡፡
በሂደት ግልፅ የሆነዉ የምዕራብ ዞኖች በደቡብ ክልል ሥር መዋቀር ዋናዉ ሚስጥር፣ አካባቢዉ ራሱን ባለማስተዳደሩ፣ የህልዉናዉን መሰረት በማጣቱ ተረጋግጧል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ልማትና ኢኮኖሚ የተመሰረተዉ በተፈጥሮ ሃብትና ተጓዳኝ ዘርፎች መሆኑ ከላይ ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢዉ በአጭር ጊዜ፣ ታይቶ በማያዉቅ ፍጥነት የመሬት ወረራ (Land Grabing) ተፈፅሟል፡፡ ይህም የተፈፀመዉ በዋናነት በገዚዎቻችን (የህወሃት መሪዎች) ዘመዶች፣ ከድርጅት አባልነት በተሰናበቱ ግለሰቦችና፣ በአጋሮቻቸዉ ስም ነዉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ተረኞቹ የደቡብ ገዢዎችና ዘመዶቻቸዉ ሆነዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በካፋ½ በቤንች ማጂና½ ሸካ ዞኖች በርካታ ተደፍረዉ የማያዉቁ ደኖች እየተከለሉ ሰፋፊ የቡና፣ የሻይና ሌሎች እርሻዎች ተመስርተዋል፡፡ ይህ የሆነዉ በተጠናና በየደረጃዉ ለዚህና፣ ለሌላ አፈና ማስፈፀሚያ፣ ተመርጠዉ በተቀመጡ ሹመኞች፣ ቅጥረኞችና ምሥለኔዎች ፊርማና አስፈፃሚነት ነዉ፡፡ በዚህ የተቀናበረ፣ ወረራ፣ “ጥብቅ የደን ክልል” ተብለዉ፣ ማንም እንዳይደርስባቸዉ ተጠብቀዉ የቆዩ፣ በእድሜ-ጠገብ ዛፎች የተሞሉ ጥቅጥቅ ደኖች ያለገደብ ወድመዋል፡፡ እነዚህ “ኢንቨስተሮች” ካለሙት በላይ በግንድና በጣዉላ ንግድ ያገኙት ሃብት ለሥሌት አዳጋች ነዉ፡፡
እነዚህ ግለሰቦች፣ በተቋማዊ ደረጃ ልዩ እንክብካቤና፣ ድጋፍ ተደርጎላቸዉ፣ ከባንኮች በመመሪያና በትዕዛዝ ከአገር ዉስጥ፣ በመንግሥት ዋስትናም ከዉጭ ባንኮች ብድር ተሰጥቷቸዉ፣ ከቀረጥ ነፃ በርካታ ማሽኖችና፣ ተሽከርካሪዎች አስገብተዉ እንዲሸጡ ሲደረግ፤ ብድሩንም ለከተማ ኢንቨስትመንት ሲያዞሩት፣ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን አየር በአየር ሽጠዉ፣ መሬቶቹን በብዙ ሚሊዮን ብር ደጋግመዉ እየሸጡ ከምንም ተነስተዉ፣ እዉነተኛ ባለሃብት እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በዚህም ከደኑና፣ የተፈጥሮ ሃብቱ ዉድመት ሌላ፤ ህዝቡ ከደኑ ያገኝ የነበረዉ የጫካ ቡና፣ ማር፣ ኮሮሪማና ጥምዝ፣ ለመድሐኒትነትና ለምግብነት የሚጠቀምበት የኑሮዉ መሰረት የተናጋ ሲሆን፣ ለአገሪቱና ለዓለም የአየር ንብረት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለዉ ዕፅዋትና፤ በሽታን የሚቋቋምና ለወደፊቱ ለአገሪቱና ለዓለም ዋስትና የሆነ የቡና ዝሪያን ጨምሮ በርካታ የብዝሀ-ህይወት ወድሟል ፡፡
እነዚህ ኢንቨስተር የተባሉ ሰዎች ለመሬት ኪራይ ለዞን (ለወረዳ) የሚከፍሉት በጣም አነስተኛ ግብር ሲሆን ለአገር የሚገባ ካለም ለፌደራል መንግሥት የሚገባና፣ ለዚህም ምንም ማካካሻ ለዞኖቹ የማይደረግበት ነዉ፡፡ አንዳንዶቹም ከህግ በላይ ሆነዉ ከወረዳና ከዞን ቁጥጥርና ዕዉቅና ዉጪ አካባቢዉን ህዝብ ራሳቸዉ የሚያስሩበትና የሚያሰቃዩበት፣የራሳቸዉ እስር ቤት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ ከዚህ ሌላ፣ በግፍና በአድሎአዊነት የወሰዱትን መሬት ካላሙት ይልቅ፣ የሚያጠፉት ዕድሜ ጠገብ ዛፎችና፣ እስካሁንም እያጓጓዙ ያለዉ ግንድና፣ ጣዉላ፡- 1) በህጉና በዉላቸዉ መሰረት፣ በየትኛዉም የኢንቨስትመንት ሥፍራ የሚገኘዉን የተፈጥሮ ሃብት ሁሉ መጠቀም የሚችለዉ የአካባቢዉ መንግሥት መሆኑ እየታወቀ 2) በክልሉ የደን ህግ መሰረት፣ ዛፍ መቁረጥ ክልክል በመሆኑ፣ ገበሬዉ እንኳን በጓሮዉ ተንከባክቦ ያሳደገዉን ዛፍ ቆርጦ ለመጠቀም የሚከለከል በሆነበት ሁኔታ ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ህዝቡ አቅም በማጣት፣ ባለሥልጣናቱ በጥቅም በመገዛትና፣ በገዢዎቻቸዉ ተፅዕኖ በፍራቻ ዝምታን በመምረጣቸዉ ነዉ ሲሆን፣ ይህ ሁሉ፣አካባቢዉ ባለቤት-አልባ፣ በራሱ ጉዳይ የማይወስን፣ ኋላ-ቀርና የራሱ ገዢ ባለመሆኑ ነዉ፡፡
II.4. ከሌሎች በልማትና በተፈጥሮ ከማይመሳሰሉት ጋር በመጨፍለቁ፣ ለኋላ ቀርነቱ ተመጣጣኝ ድጋፍ አጥቷል፡፡
አካባቢዉ በአንፃራዊነት ከለማዉ የደቡብ ክልል ሥር በመሆኑ፣ከማዕከላዊ መንግሥትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለታዳጊ አከባቢዎች የሚደረገዉ ድጋፍ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ በደቡብ ክልልም በጋራ በጀት የአስፋልት መንገዶች፣ ስታዲየሞች፣ ተቋማት፣ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ኮንዶሚኒየም፣ አዳራሾች፣ ቢሮዎችና ሌሎች ህንፃዎችና ተቋማት በማዕከላዊ ከተሞች ሲገነቡ፣ ለምዕራቡ ዞኖች ግን ከማዕከልም ሆነ ከክልሉ አንድም ድጋፍ አልተደረገም፡፡ ይህ ሁሉ አካባቢዉና ህዝቡ፣ ታሪኩና ማንነቱ የጠፋ፣ ስነ-ልቡናዊ፤ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ዉድመት ለዘመናት የደረሰበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉ ሲገባ የተገላቢጦሽ ደቡብን ሲያለማ ቆይቷል፡፡ ይልቁንም የመንግስትና የግለሰቦች ሃብት በጉዞ ሲያልቅ፣ ተጓጉዞም መፍትሄ አለማግኘት የተለመደ ክስተት ነዉ፡፡ አካባቢዉ ከኋላ ቀርነቱና፣ ከክልሉ ማዕከል ካለዉ ርቀት የተነሳ በበጀት ሊደጎም ሲገባዉ፣ የሚመደበዉ ትንሽ በጀት ወደ ማዕከል በሚደረገዉ ምልልስ በአበል፤ በነዳጅና በመኪና ጥገና በማለቁ ዋናዉን የልማት ክፍተት ከማስፋቱም በላይ በወቅታዊና አዳዲስ ፍላጎቶች ጭምር አካባቢዉ የባሰ ወደሚባል ደረጃ እየተንሸራተተ ነዉ፡፡ ከዚህም ጋር በተገናኘ ባለስልጣናት በስራ ቦታቸው ባለመገኘታቸዉና ዉሳኔ ስለማይሰጡ፣ በዞኖቹም ዉስጥ ቢሆን ጉዳይ ማስፈፀም አልተቻለም፡፡ ህዝቡም ለፍትህ፣ ለንግድ ፈቃድ፣ ለግብር ጉዳዮች ወደ ክልሉ ማዕከል ሲሄዱ ብዙ ዕንግልትና ወጪ ይዳረጋል፡፡ በነዚህ ጉዞዎች ዕንግልት፣ ወጪ፣ ጊዜና፣ አካላዊ ድካም ማህበረሰቡን ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አካባቢያቸዉን ለማልማት የመጡ ምሁራንና አሁን ደግሞ፣ ሲታትሩ የነበሩ ነጋዴዎች ዞኖቹን እየጣሉ መሄድ ይሄዳሉ፡፡
በየደረጃዉ ተገቢዉን ዉክልናና በማጣቱና፣ በክልሉ ቢሮዎችም ጉዳዮችን ለማስፈፀም፣ ባለጉዳዩ ከመጣበት አካባቢ የወጣ ሃላፊ ወይም ባለሙያ ከሌለ፣ ባለዉ መመሪያ መሰረት ብቻ ጉዳይ ማስፈፀም ሰሊሚከብድ ሌላዉ ህዝቡን በተለይም ባለሙያዎችን ለምሬት የዳረገ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ ተደማጭነትና ትኩረት መነፈግና፣ ዉክልና ማጣት የመዋጡ አንዱ ዉጤት ነዉ፡፡ የደቡብ ክልል፣ ምዕራባዊ ዞኖችን እንደክልሉ አካል አለማየቱን፣ ለማሳየትና አካባቢዉም ተከራካሪና፣ የሌለዉ መሆኑን ለማሳየት በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር ፅ/ቤት ቀርቦ በመንግሥት በተወሰነዉ መሰረት፣ የካፋንና የኢትዮጵያን የቡና መገኛነት ዕዉቅና የሰጠዉን ዉሳኔና፣ በዚህም መሰረት በ1999 ዓ.ም. በፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መሰረቱ ተጥሎ፣ በጠቅላይ ሚ/ር አቶ ሃይለማሪያም የተመረቀዉን ብሔራዊ የቡና መዚም በተመለከተ ክልሉ የያዘዉ አቋም ማጥ ይበቃል፡፡ ይህ ሙዚየም ሥራ ሳይጀምር ዓመታት በማስቆጠሩና፣ ህንፃዉ ሲፈራርስ ፌደራል መንግሥትም፣ ሆነ ክልሉ ዝምታን ሲመርጡ፣ የህዝብ ጥያቄ ሲበረታ፤ የክልሉ ሃላፊዎች “የታሪክ ሽሚያ አለ፣ የፌደራል አካላት መልስ አልሰጡም፣ ይጠናል ወዘተ” እያሉ ጉዳዩ እንደማይመለከታቸዉ በተደጋጋሚ የለበጣ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡም የማዕካለዊ መንግሥት አንድ ሃላፊ በሃገሪቱ ቲሌቪዥን ቀርቦ ከእዉነታዉ ዉጪ በዞኑ ተነሳሽነት የተሰራ ነዉ በማለቱ፣ የህዝቡ ቁጣ ሲገነፍል፣ የክልሉ ገዢ “እየተጠና ነዉ” በማለት በአጠቃላይ አካባቢዉና ህዝቡ እንደሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተወከለ፣ የተዘነጋ፣ ተከራካሪ የሌለዉ፣ ከልማትና ከዲሞክራሲ የተገለለ፣ ለሀገር ግንባታ ሊያበረክት የሚችለዉን ዕድል የተነፈገ መሆኑን መስክሯል፡፡
ሁሉም ጉዳይ በደቡብ ክልል ይሁንታና ዝንባሌ የሚወሰን፣ በእርዳታና በማዕከላዊ መንግሥት የሚላኩ ቴክኖሎጂዎችና ፕሮጀክቶች ሁሉ ወደ ማዕከላዋዊዉ የክልሉ አካባቢዎች ያደላበት፣ በመሆኑ ምዕራቡ የተገለለ፣ በሁሉም አመልካች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሆኗል። በዚህም፣ የመዘንጋትና የኋሊት ጉዞን የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች ቢኖሩም፣ ለምሳሌ ቦንጋ ዉስጥ፣ በአገሪቱ ከመጀመሪያዎቹ ኤክስፖት ካምፓኒዎች ቀዳሚ የነበረዉንና በሂደት የጠፋዉን የቡና ፕሮሰሲንግና ኤክስፖት ካምፓኒ እንዲሁም፤ በአዉሮፓ አቆጣጠር በ1920 ዓ ም ቦንጋ ከተማ ዉስጥ የተሟላ አገልግሎት የሰጥ የነበረዉ ሆስፒታል የተዘጋበትን ሁኔታና ሌሎች በሂደት የከሰሙ የአካባቢዉን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩ በርካታ ጉዳዮችን በዝርዝርና በመረጃ ማስደገፍ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ በራሱ የሚወስን ህዝብና ለህዝቡ የቆመ አመራር ባለመኖሩ የመጣ ነዉ፡፡
II.5. ባህሉን፣ ታሪኩንና ቋንቋዉን ማጎልበትና ማሳደግ ባለመቻሉ፣ በራስ መተማመንና ተነሳሽነት አጥቷል፡፡
ህዝቡ ቋንቋዉንና ባህሉን፣ ታሪኩንና ቅርሱን እንዲዘነጋና ማንነቱን እንዲረሳ በተቀናጀና በተቀነባበረ ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ጫና ተደርጎበታል፡፡ የህዝቡ ቅርሶች ወደባህር ማዶ ጭምር ተወስደዉ ተሰዉረዋል፡፡ ቋሚ መረጃ ሊሆኑ የሚችሉት ንጉሳዊ ቤተ መንግስት፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፤ የጥበብ መሠረቶች እንዲወድሙ ተደርጓል፡፡ የአሁኑ ትዉልድ እነዚህን ሁሉ እንዳያዉቅ ስለካፋ የተፃፉ መፅሐፍት ጭምር ወደ አገር እንዳይገቡ የተደረገ ሲሆን፣ ባለፉት 25 ዓመታት በካፋ ተወላጆች የተፃፉ የታሪክ መፅሀፍትና የኪነ ጥበብ ዉጤቶች ለህዝቡ በተለይም ለወጣቱ እንዳይሰራጩና እንዳይደርሱ ሥልታዊ በሆነ መንገድ፤ በወቅቱ ካድሬዎች አማካይነትና በቀደምት የካፋ ማንነት አፋኞች ተዘምቶባቸዋል፣ ታፍነዋል፡፡ በካፋ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦች ቅርሶችና፣ የኢኮ- ቱሪዝም ሃብቶች ቢኖሩም፣ በአግባቡ እንዳይተዋወቁ ሲደረግ፣ ዉስን ሥርጭት የሚደረገዉም አልፎ አልፎና በዋናነት በዉጭ ዜጎችና ሚዲያዎች ብቻ ነዉ፡፡ የህዝቡን ባህልና ታሪክ ለማሳደግና ለማዳበር፣ የተደረጉ ጅማሮዎች በባለሥልጣናት ትዕዛዝና በፖለቲካ አመራሩ አማካይነት፣ በረቀቀ መንገድ እንዲቆም፣ እንዲዛባና፣ እንዲዳፈን ተደርጓል፡፡ የነገሥታት መቃብር፣ የዉጭ ፀሐፊዎች ጭምር ከቻይና ግንብ ቀጥሎ የሰዉ ልጅ የሰራዉ የመከላከያ ሥልት ተብሎ የተደነቁት፤ ሂሪዮ፣ ኩሪፖ እና ኮትኖ እንኳን ጥበቃና ማስተዋወቅ ሊደረግባቸዉ፤ ይልቁንም በሰፈራ፣ በእርሻና በመሰረተ ልማት ግንባታ ስም እንዲጠፉ እየተደረገ ነዉ፡፡ ብዙ ሊጠኑ የሚገባቸዉ ባሕላዊ የልቅሶ ሥርዓቶች (ሂቾ እና ጎሞ) እና ሌሎች የካፋን ማንነት የበለጠ ለማጥናት የሚረዱ ሥርዓቶች በሃይማኖት ተቋማት ጭምር እየተዘመተባቸዉ እንዲረሱ ሲሆን፤ በአንፃሩ ኢሬቻና፣ ፍቼ ጨምባላላ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ብዙ ተለፍቷል፡፡ በአንድ ወቅት በተጀመረዉ መነሳሳት ወቅት፣ በካፋ ዞን ዋና ከተማ በቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት፣ የካፋ ሰማዕታት ኃዉልትና፣ የካፋ የባህልና የታሪክ ሙዝየም እንዲዳፈን ተደርጎ በቦታቸዉ ሌላ ግንባታ ተፈፅሟል፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡ፣ በተለይም አዲሱ ትዉልድ ባህሉን ታሪኩንና ማንነቱን እንዳያዉቅና ስነ-ልቦናዉ እንዲኮላሽ በርካታ ተግባራት ተፈፅመዋል፣ በርካታ ዝክረ-ታሪኮችና ዉጥኖችን በማደብዘዝና በማደናቀፍ፣ የሥነ-ልቦና ዘመቻ ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ በመንግሥት ሃላፊነትና በፖለቲካ አመራር ላይ በየዘመኑ በተቀመጡ፣ ተላላኪዎችና ቀጥተኛ ጉዳይ ባላቸዉ አካላት የተፈፀመ አፈና ሲሆን፤ ይህንን የሚመክት ለካፋ የቆመና ተቆርቋሪ የፖለቲካ አመራር ባለመኖሩ የደረሰ፣ ግን እስከወዲያኛዉ የማይረሳ ግፍና ጭቆና ዉጤት ነዉ፡፡

III. የካፋንና አጎራባች ህዝቦች ለማፈን ተግባራዊ የተደረገና ሊወገድ የሚገባዉ ሥልት፡፡
ካፋንና አጎራባች ህዝቦችን አፍኖ ለመግዛት ተግባር ላይ የዋሉና መወገድ ያለባቸዉ ሥልታዊ በሆነ መንገድ የተደራጁና የተፈፀሙ በርካታ ድርጊቶች የሚታወቁ ቢሆንም ጉልህ የሆኑትንና በአፋጣኝ መስተካከል ያለባቸዉና መጥቀስ ያለባቸዉ የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
III.1. ካፋንና ሌሎችን በታማኝና ታዛዥ ምስለኔዎች አማካይነት መግዛት፤
ሁሉንም አፈና የሚያቀናብሩት በሴረኝነታቸዉ የታወቁ፣ ከገዢዎቻቸዉ የሚሰጣቸዉን ትዕዛዝ በትጋትና በታማኝነት ለመፈፀምና ህዝቡን ለማፈን ባላቸዉ ዝግጁነት፣ የተመረጡ፣ ለክልሉና ለዋናዎቹ የበላይ አለቆቻቸዉ ጥቅም ብቻ የቆሙ፣ እነርሱም በተራቸዉ በህዝባ ላይ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ እነዚህ በክልል ወይም በማዕከል፣ በማይመጥናቸዉ ከፍተኛ ቦታ ተመድበዉ፣ ከፍተኛ ጥቅም ተስጥቷቸዉ በወጡበት አካባቢ ህዝብ ላይ ባለሙሉ ሥልጣን የሆኑ፣ ተቆጣጣሪና፣ ገዢ እንዲሆኑ የሚመደቡ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ ሌሎቹ በአካባቢዉ ተወልደዉ ያደጉና በከፊል ወይም በሙሉ ከሌላ ብሔር የሚወለዱ፣ የህዝቡን ሥነ-ልቦናና ሥርዓት ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ ተመሳስለዉ የኖሩና የሚኖሩ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሁለቱም ዓይነት ግለሰቦች ዋና ተግባራቸዉ የአለቆቻቸዉን ትዕዛዝ መፈፀም፣ መረጃ ማሰባሰብና ማስተላለፍ እና ለራሳቸዉም ሃብት ማካበት ነዉ፡፡ እነዚህን ህዝብ በደንብ እያወቀ ዝም ብሎ ቢታዘብም፣ የገነፈለ ጊዜ ዉጤቱን መገመት ይከብዳል፡፡ ገዢዎች ህዝቡን በነዚህ አማካይነት ከመግዛት ታቅቦ፣ ካስፈለገም ለዉለታቸዉም የፈለጉትን ሰጥተዉ፣ ከህዝቡ ጫንቃ ማዉረድ ይገባቸዋል፡፡
III.2. በየደረጃዉ ላሉት ገዢዎች ታዛዥና ታማኝ ግን ደግሞ ከህዝቡ የራቁ አስፈፃሚዎች፤
ከላይ በተጠቀሱት ምስለኔዎች ዋና መሪነትና ዕዉቀት በየደረጃዉ፣ ተመሳሳይ ሚናና ጥቅማ ጥቅም የሚሰጣቸዉ አስፈፃሚዎች እንደሚመደቡ ሁሉም ያዉቃል፡፡ እነዚህ ወደ ህዝቡ በቀረበ የአስተዳደር እርከን ላይ የሚመደቡ ሰዎች፣ የህዝቡን ስሜት መከታተልና ማፈን፣ ለገዢዎቻቸዉ ሁሉንም ማመቻቸት፣ ማስፈፀምና መፈፀም ዋና ተግባራቸዉ ነዉ፡፡ አንዳንዴም ህዝቡ በይፋ እየተቃወመ፣ መነግሥት ስለመረጣቸዉ ብቻ በሃላፊነት ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ከሚመደቡት፣ አልፎ አልፎ ህሊናቸዉ የቆረቆራቸዉ ቢኖሩ እንኳን፣ ለራሳቸዉ ስለሚሰጉና ሥርዓቱ የሚያደርስባቸዉን ስለሚያዉቁ ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜም፣ የሚሰጣቸዉን ትዕዛዝ ላለመፈፀም ያንገራገሩ ወይም ያፈነገጡ ሲያጋጥሙ ምክንያት ተፈልጎ፣ ከቦታዉ ገለል ስለሚደረጉና፣ ባብዛኛዉ ወደ እሥር ቤት ስለሚወረወሩ አደብ ገዝተዉ ይቀጥላሉ፡፡ በመሰረቱ ኢህአዴግ የሚመለምላቸዉ አብዛኛዎቹ ፣ ሆነ ተብሎ ለዚህ የተመቹ መሆናቸዉ ሲታወቅ፣ ጥቂቶችም በጊዜ ገብቷቸዉ ከመድረክ ራሳቸዉ በጊዜ ይጠፋሉ፣ ወይም ፀባቸያዉን አሳምረዉ መስለዉ ማደር ይቀጥላሉ፡፡
አንዱ ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ሥልት ደግሞ ገዢዎች የሚፈልጉትን ጉዳይ በቀላሉ፣ ከህግ ዉጭ በሥልክ ትዕዛዝ ብቻ ለመፈፀም የማይመቹ ሲገኙ፣ ወይም አልፎ አልፎ እንደታየዉ መጠየቅና፣ መከራከር የጀምሩትን በሂደት ማስወገድ ነዉ፡፡ በዋናነት ግን ከመጀመሪያዉ ለአካባቢዉ መብትና ጥቅም ተቆርቋሪና፣ ተወዳጅ የሆኑ ካድሬዎች ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ ይደረጋል፡፡ በስህተት ሚስጥር ያወቁ ካሉም ተሸማቅቀዉ ጥጋቸዉን ይዘዉ ዝም እንዲሉ፣ የዉስጡን ሥርዓትና አሰራር ስለሚያዉቁም፣ አፋቸዉን ዘግተዉ፣ ራሳቸዉን እንዲያገልሉ፣ ክትትልና ጫና ማድረግና፣ በርግገዉ እንዲጠፉ በሴራ ጠልፎ መጣል ይደረግባቸዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት አማካይነት የሚገዛዉ ህዝብም ጊዜ ይጠብቃል እንጂ በደንብ ያዉቃቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ከቻሉ የፖለቲካ ዕምነታቸዉን ይዘዉ ዋናዉ አዛዣቸዉና ዋስትናቸዉ ህዝቡ መሆኑን አዉቀዉ ንስህና ገብተዉ በወቅቱ መስመራቸዉን ማስተካከልና፣ ሳይመሽ የበደሉትን ህዝብ በመካስ የክልል ጥያቄና አንገብጋቢ ህዝቡን ጉዳዮች ዕልባት መስጠት ይገባቸዋል፡፡ ካልሆነም በህዝብ ልጆች ሊተኩ ይገባል፡፡
III.3. ወጣቶችና ምሁራንን ማባረርና ማግለል፤
የካፋ ወጣቶች (ጉርማሾ) በአሁኑ ወቅት ከሚያነሷቸዉ ጉዳዮች አንዱ የካፋ ምሁራን ዝምታ፣ ከትግል መራቅና መደበቅ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ለጉርማሾ እስካሁን የተደረገዉንና ያለዉን ዕዉነታ ማሳወቅ ወቅታዊ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ አንዱ በካፋ የ 120 ዓመታት ታሪክ በተደጋጋሚ የታየዉ ካፋንና ሌሎች ተመሳሳይ አካባቢዎችን በቀላሉ ለመግዛትና ለመጋለብ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየዉ የማስፈፀሚያ መንገድ ምሁራንንና ወጣት ምሩቃንን አስበርግጎ መባረር መሆኑን ምሁራኑ ብቻ ሳይሆኑ በአጭር ጊዜም ቢሆን በቆይታቸዉ የፈፀሙትን አኩሪ ተግባር የተመለከቱ የአካባቢዉ ነጋዴዎችና ገበሬዎች ጭምር ያዉቃሉ፡፡ ሆኖም የኢህአዴግ ሥርዓት ሁሉም ዜጎች አካባቢያቸዉን ማገልገላቸዉን የሚደግፍ መስሏቸዉ፣ የህዝባቸዉና የአካባቢዉ ኋላ ቀርነት ቁጭት የፈጠረባቸዉ ምሁራን ከ1984/85 ጀምሮ ወደ አካባቢዉ የጎረፉበት ወቅት ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ያሉ ወገኖችም ተመራቂዎችን፣ ደግሰዉ መርቀዉና አስመርቀዉ ወደ አካባቢያቸዉ ሂደዉ እንዲያገለግሉ ማበረታታት ልምድ ሆኖ ነበር፡፡
ይህንን ተከትሎም ወጣቶች ከኮሌጅ ሲመረቁ በጉጉትና በወኔ ወደ አካባቢያቸዉ የጎረፉ ሲሆን፣ ከላይ የተጠቀሱት እንቅፋቶች ግን፣ መጀመሪያ በየምክንያቱ ላለመቀበልና ላለመቅጠር ማንገራገር፣ ከተቀጠሩም በየምክንያቱ ተስፋ በማስቆረጥ አካባቢዉን ለቀዉ እንዲሄዱ በማድረግ፣ ምሁሩ በራሱ፣ በአካባቢዉና በመንግሥት እንዳይተማመን በማድረግ ወገናዊነትና ብቃት ያላቸዉ፣ ጠያቂ ባለሙያዎች በየተራ አካባቢዉን ጥለዉ እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ በጉጉት ወደአካባቢዉ የጎረፉ በርካታ አንቱ የተባሉ ልምድ ያካበቱ ምሁራንና ወጣት ምሩቃን መሃንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የዉሃና የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያዎች፣ የኮምፒዩተርና የቴክኖሎጂ ባላሙያዎች፣ ተማርረዉና ተበሳጭተዉ፣ ተስፋ ቆርጠዉ፣ አካባቢዉን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ በዚህም ሥልት፣ እነዚህ ዓይነቶቹ፣ የሚከናወኑትን ዝርፊያዎችና በደሎች እያዩ ማለፍም ሆነ የማያምኑበትን ታዘዉ ለመፈፀም ስለማይመቹ እስከወዲያኛዉ ርቀዉ እንዲሸሹ ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ ዘራፊዎችና፣ ፍርፋሪ ለቃሚ አገልጋዮች እንደልብ፣ ያለ ተከራካሪና፣ ያለታዛቢ በህዝቡ፣ በአካባቢዉና በሃብቱ ላይ እንዲፈነጩ ተመቻችቷልÝÝ
ከነዚህ ምሁራንና ወጣት ምሩቃን መካከል፣ ቁርጠኛ የሆኑ፣ ከሙያዊ አገልግሎት ባለፈ፣ የድርጅት አባል በመሆን ጭምር ለዉጥ ለማምጣት ቢሞክሩም፣ በተለመደዉ ድርጅታዊና ቡድናዊ ሰንሰለት፣ ተጠልፈዉ በመዉዳቸዉና፣ በተለመደዉ የመፈታተንና የማስጨነቅ ሥልት እንደሌሎቹ እንዲጠፉ፣ ወይም በመሸማቀቅ ዝም እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብቁ ባለሙያዎች በአካባቢዉ እንዳይኖሩ፣ ካሉም ሞራላቸዉ ወድቆ ተስፋ እንዲቆርጡ ተደርጎ፣ ልዩ ክትትል እየተደረገባቸዉ ከአገልግሎት ዉጪ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ በይትኛዉም አካባቢ በዚህ ደረጃ ያልተፈፀመ፣ ከቀደምት መንግሥታት ዘመን ጀምሮ የነበረዉ አያያዝ ጋር ተመሳሳይ የሆነ፣ ዉጤቱም በጣም አደገኛ የሆነ አፈና ክስተት ነዉ፡፡ ይህም አካሄድ በአካባቢዉ በሚፈጠሩ ወገንተኛና ቁርጠኛ የፖለቲካ መሪዎች አማካይነት ሊስተካከል የሚገባዉ፣ ከዚያም እንዳይደገም በግልፅ በመነጋገር ሊነቀልና ሊታከም የሚገባዉ ነቀርሳ የሆነ ቁስል ነዉ፡፡ ከዚህ ልምድ ስንነሳ፣ በአሁኑ ወቅት በወጣቶች (ጉርማሾ) የተጀመረዉ ንቅናቄና ተነሳሽነት ተመሳሳይ ዕድል እንዳይገጥመዉ በተለይም በቅርቡ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በትጋትና በጥንቃቄ ሊያስቡበትና ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡ አስፈላጊም ከሆነ በዝርዝር ተዘግቦ፣ መንግሥት በሚያዉቀዉ መድረክ ዉይይት ተደርጎበት ለወደፊቱ ዋስትና ሊበጅለት የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

IIII. ማጠቃለያ
የራስ አስተዳደር ማጣት ከመጀመሪያዉ እስከዛሬ ዓላማዉና ዉጤቱ የተረጋገጠ፤ ራስን የማስተዳደር ጥያቄም በተገላቢጦሽ የሚታይ ጉዳይ ነዉ፡፡ በገዢዎች ረገድ ዓላማዉ፣ ሥልጣንና ሃብት መቆጣጠር ሲሆን፣ በተገዢዎች ረገድ ደግሞ፣ ራስን ለማስተዳደር የሚፈለገዉ መታፈን፣ ሞትና ስደት፣ የሃብት ዝርፊያና ድህነት፣ እንዲወገድ፣ ባህል ቋንቋና ማንነትን በማሳደግ በራስ መተማመን፣ ለማጎልበትና፣ እንደማንኛዉም ዜጋ እኩል መጓዝ ነዉ፡፡ አሁንም ሆነ ቀድሞ የነበሩት ገዢዎች፣ ምስለኔዎችና ሁሉም አስፈፃሚዎች የገዢዎችን ትዕዛዝና ጉዳይ ከማስፈፀም ሌላ፣ በተራቸዉ ዓይን ባወጣ መልኩ፣ ሥልጣናቸዉንና ሰንሰለታቸዉ በመጠቀም ታማኞቻቸዉን በየደረጃዉ በማሰማራትና መረባቸዉን በማጠናከር በህዝቡ ላይ ዝርፊያና አፈና ማድረግ ዋና ተግባራቸዉ ነዉ፡፡ ለነዚህ ደግሞ የክልሉና የበላይ አለቆቻቸዉ ከለላና ድጋፍ በማድረግ እነርሱም የሚፈልጉትን ማስፈፀም ችለዋል፡፡
ስለሆነም የክልል ጥያቄን የዛሬዉ ትዉልድ በህጋዊና በአርቆ አስታዋይነት እንዲገፋበት፣ መንግሥትና የፖለቲካ ሃይሎችም ወቅቱን የሚመጥን መፍትሄ በመስጠት የህዝቡን መብቶች፣ ጥቅምና ክብር በህጉ መሰረት እንዲስከብሩና ታሪካዊ ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡ የካፋና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎችም ዕዉነት ለህዝብ የቆሙ ከሆኑ የቱንም ያክል ልዩነት ቢኖር በጋራ ጉዳይ፤ ይህም ­ የካፋ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የማደግ፣ ተገቢዉን ክብርና ጥቅም የማግኘት ­ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸዉ፡፡
የካፋ ህዝብ ራሱን ማስተዳደር መጀመር፣ በኢትዮጵያ ጥላ ሥር በአግባቡ የሚወክለዉን፣ የሚመራዉንና የሚያስተዳድረዉን፣ ተጠሪነቱና፣ ተጠያቂነቱ በቅድሚያ ለራሱ ለካፋ ህዝቡ የሆኑ፣ መሪዎቹን መምረጥ አለበት፡፡ ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖሊስ፣ ስትራቴጂና ደንብ ማዉጣት፣ የአካባቢዉንና የአገርን ሃብት መጠበቅ፣ ማልማትና መጠቀም፣ አብሮ ማደግና መበልፀግ አለበት፡፡ ህዝቡ ራሱን አስተዳድሮ፣ እንደዜጋ እኩል መታየት፣ ሰብአዊ መብቱን ማስከበርና፣ እኩልነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ አስተዋፅኦና ተሳትፎ ማድረግ፣ ተከባብሮና ተማምኖ መኖር ይገባዋል፡፡ ለአገሪቱም ዕድገት ብልፅግና፣ ሰላምና ዲሞክራሲ ተገቢዉን ሚና መጫወትና፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ አንድ ጉልህ አካል ሆኖ መቀጠል ጊዜ የማይሰጠዉ የወቅቱ አጀንዳ ነዉ፡፡ በዚህም ሂደት በአሁኑ ወቅት የተጀመረዉ የህዝብ ጥያቄ በተለይም የጉርማሾ እንቅስቃሴ ወደ አልተገባ አቅጣጫ እንዳያመራ፣ በዋናነት በለዉጡ ወቅት የተመሰረቱ የፖለቲካ ሃይሎች ሊያስቡበትና በትጋት ሊሰሩበት ይገባል፡፡ የካፋና የደቡብ ክልል ምዕራብ ዞኖች የክልል ጥያቄ፣ መሰረት የሌለዉ የጥቂቶች ጉዳይ ወይም ሌሎች የደቡብ ዞኖች የጠየቁትን ተከትሎ እንደፋሽን ኮፒ የተደረገ ጉዳይ ሳይሆን ተጨባጭ ማህበራዊና ታሪካዊ መሰረት ያለዉ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንድምታዉ የጎላ፤ የቆየ ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ቀጣይ ሂደት ነዉ፡፡ የካፋ ህዝብ አስከ ዛሬም ድረስ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ እንዲሁም ከአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መገለሉ የተደበቀና የሚሸፋፈን ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለሆነም የክልል ጥያቄን የዛሬዉ ትዉልድ በህጋዊና በአርቆ አስታዋይነት እንዲገፋበት፣ መንግሥትና የፖለቲካ ሃይሎችም ወቅቱን የሚመጥን፣ መፍትሄ በመስጠት የህዝቡን መብቶች፣ ጥቅምና ክብር በህጉ መሰረት እንዲስከብሩና ታሪካዊ ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ እንጠብቃለን፡፡
የካፋና የደቡብ ምዕራብ የፖለቲካ ሃይሎችም ዕዉነት ለህዝብ የቆሙ ከሆኑ የቱንም ያክል ልዩነት ቢኖር በጋራ ጉዳይ፤ ይህም ­ የካፋ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የማደግ፣ ተገቢዉን ክብርና ጥቅም የማግኘት ­ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸዉ፡፡

ከሮ ኬቶ ጋዎ
03/06/2019
Source ካፋ ሚድያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: