Leave a comment

ካፋን ማወቅ አፍሪካን የመረዳት ጅማሮ ነው ያለው ታሪክ ተመራማሪ ማን ነበር?


በተስፋዬ ወልደሚካኤል ገብረማርያም (BSc, MSc, MA)

የካፋ ኪንግደም የወርቅ ዘውድና ሌሎች ባህላዊ ቅርሶች ከስዊዘርላንድ እንዴት እንደተመለሱና 
የካፋ ሕዝብ የቅርሱ ባለቤትነት የመብት ጥያቄ
ለንጉሥ ጋኪ ሸረቾ 100ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ የተዘጋጀ
ሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲሰ አበባ
በተስፋዬ ወልደሚካኤል ገብረማርያም (BSc, MSc, MA)

የካፋ ኪንግደም የወርቅ ዘውድ ሌሎች ቅርሶች ወደ ስዊዘርላንድ እንዴት ሄዱ?

እ.አ.አ በ1897 ዓ.ም. የአፄ ምኒልክ ጦር በራስ ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራ፣ እነ ደጃዝማች ደምሴ ነሲቡ፣እነደጃዘማች ተሰማ ናደውና የጂማው አባጂፋር ተሳታፊነትና የጦር ርዳታ የካፋን መንግሥት ሠራዊት በማሸነፍ የካፋን ንጉሥ ጋኪ ሸረቾን ከብዙ ደም መፋሰስን ንብረት መውደም በኋላ በምርኮ መጀመሪያ አዲስ አበባ ከዚያም አንኮበር መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡ አፄ ምኒልክ እ.አ.አ. በ1913 ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ንጉሥ ጋኪ ሸረቾ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ እ.አ.አ. በ1919 ወይም የዛሬ 100 ዓመት አርፈዋል፡፡

የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ  The crown of Kafa

የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ The crown of Kafa

64205695_2320303071391242_536863155289063424_o

በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ The stool of Kafa,

ከጦርነቱ በኋላ ከካፋ በምርኮ ወደ አዲስ አበባ ከተወሰዱት ዋና ዋና ቅርሶች መካከል የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ፣በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ፣ የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦችና የነገሥታት አልባሳት ይገኙበታል፡፡ሌሎቹ ቅርሶች የት እንደደረሱ ባይታወቅም፣ የካፋ ነገሥታቶች በዘመናቸው የወርቅ ዘውድ፣የወርቅ ቀለበት፣የወርቅ አምባር፣ባለሁለት ስለት ጦር፣የብርና የወርቅ በትረ መንግሥት፣በወርቅ የተለበጠ ጎራዴ፣ በወርቅ የተለበጡ የንጉሡ አጃቢዎች የሚይዙት 12 ጋሻዎችና በብር የተለበጡ ከበሮዎችና በብርና ወርቅ የተለበጡ በርጩማዎች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ከነዚህ ቅርሶች መካከል የወርቅ ዘውዱ 23 ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው በወርቅና በብር የተሰራ ሲሆን ከላይ የሰጎን ላባዎችና ሶስት ወደፊት ወጣ ያሉ ከልቻዎች ያጌጠ ነበር፡፡ከታች በኩል ከዘውዱ ጋር በሰንሰለት የተያያዙ ትናንሽ ቃጭሎች ከወርቅ የተሰሩ ናቸው፡፡ በካፋ መንግሥት ዘመን ይህ የወርቅ ዘውድ ልዩ ቦታና ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ በካፋ ብሔር ባሕል ይህ ዘውድ የተቀደሰ ከመሆኑም በላይ የካፋ መንግሥት ልዩ መለያ ስለሆነ፣ዘውዱ ካፋ ውስጥ እስካለ ድረስ፣ ዘውዱን በቁጥጥሩ ያደረገ ሕጋዊ ንጉሥና መሪ ይሆናል፡፡ከዚህም በመነሳት ይመስላል የዘመኑ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎችና አጼ ምኒልክ ለካፋ ዘውድ የሰጡት ግምት ከላይ የተሰጠውን መደምደሚያ በሚገባ የሚያረጋግጥ መሆኑን ያሳዩት ባህሪና ተግባር ምስክር ሁኖ ለዘመናት የዘለቀው፡፡

የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች The Ear Pendants of Kafa

የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች The Ear Pendants of Kafa

እ.አ.አ 1918 ሲዊዛዊ የአጼ ምኒልክ አማካሪ የሆነው ኢንጂነር አልፍሬድ ኢልግ የታሪክ ዘጋቢ ፕሮፌሰር ኮንትራድ ከለር እንደገለፁት የካፋ ወርቅ ዘውድ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች አድራሻው እንዳይታወቅ በድብቅ እየተዘዋወረ ይጠበቅ ነበር፡፡በምን መንገድ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ እንደገቡ እስካሁን እንቆቅልሽ ቢሆንም፣ ይህንን በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉ የነበሩ ምርጥ የካፋ ጀግና ተዋጊዎች የወርቅ ዘውዱንና ሌሎች የካፋ መንግሥት ቅርሶች እጃቸው አስገብትው ጉዞ ወደ ካፋ በማድረግ ጊቤ ወንዝ አቅራቢያ እንደደረሱ፣ ከኋላቸው ሲያሳድዷቸው በነበሩ የራስ ወልደጊዮርጊስ ጦር ተሰውተው ቅርሶቹ አዲስ አበባ እንደገና ሊመለሱ ችለዋል፡፡ የዚህ ክስተት በአዲስ አበባው ቤተ መንግሥት ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሮ ነበር፡፡ ካፋዎች የወርቅ ዘውዱንና የንግሥና ቅርሳቸውን በማንኛውም ጊዜ በእጃቸው ካስገቡ የራሳቸውን መንግሥት ከመመስረት የሚያግዳቸው ምንም ምድራዊ ኃይል አለመኖሩን ያሳየ ድንቅ ክስተት ነበር፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ አጼ ምኒልክ በሁለት አጣቢቂኝ አማራጮች ወደቁ፡፡ አንደኛው የካፋዎችን የወርቅ ዘውዱንና የንግሥና ቅርሶች ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ወይም ሁለተኛው ከአገር ውጪ ማሸሽ፡፡በመጨረሻም አጼ ምኒልክ ለግል አማካሪያቸው ኢንጂነር አልፍሬድ ኢልግ የካፋን መንግሥት የወርቅ ዘውድ፣40 ሴንት ሜትር ከፍታ ያለውን በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ፣ አንዱ 33 ሴንት ሜትር ሌላው 32 ሴንት ሜትር የሆኑትን ሁለት የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች ከኢትዮጵያ አውጥቶ ሲዊዘርላንድ እንዲወስድ ትዕዛዝ ለመስጠት እንዲገደዱ አድርጓቸዋል፡፡

የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች The Ear Pendants of Kafa

የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች The Ear Pendants of Kafa

ከኢትዮጵያ ሲዊዘርላንድ በኢልግ አማካኝነት የወጣው ይህ ብርቅዬና ድንቅ የካፋ ሕዝብ ቅርስ በሲዊስ ባንክ ከሃምሳ ዓመታት በላይ በአደራ መቀመጡን የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡ በኋላም እ.አ.አ በ1954 ዓ.ም. የአልፍሬድ ኢልግ ቤተሰቦች እነዚህን ሶስት ቅርሶች እና ከኢትዮጵያ የወሰዳቸውን 700 የተለያዩ የኢልግ ሌሎች የቅርስ ስብስቦች ለዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ኢትኖግራፊክ ሙዝየም በውሰት መሰጠታቸው ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ድርጊት ነበር፡፡እ.አ.አ. ኦገስት 5 ቀን 1953 ዓ.ም. የአልፍሬድ ኢልግ ልጅ ፍሊክስ ኢልግ ለፕሮፌሰር ስቴይንማን ለዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ኢትኖግራፊክ ሙዝየም ኃላፊ በጻፈው ደብዳቤ በተለይ ከካፋ የመጡ ሶስት ቅርሶች የአልፍሬድ ኢልግ ቤተሰቦች የግል ንብረት መሆኑን በደብዳቤው መግለጹ፣ እነዚህ ቅርሶች ምን ያህል ዋጋ እንዳለቸው አመልካች ብቻ ሳይሆን፣ ያለኢልግ ቤተሰብ ፍቃድ በቅርሶቹ ላይ ማንም መወሰን እንደማይችል ማሳያ ነበር፡፡እጅግ በጣም የሚያስገርመው ጉዳይ እነዚህን ቅርሶች ካላቸው ታሪካዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ አንጻር የናዚው አለቃ ሂትለር ቀኝ እጅ የሆነው ሄርማን ጎርንግና ራሱ የፋስሽቱ ጣሊያን መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ የራሳቸው ለማድረግ ለኢልግ ቤተሰቦች የእንግዛ ጥያቄዎች ማጉረፋችው ላቅ ያለ ትርጉም ያላቸው ቅርሶች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ስቴይንማን Die Krone von Kaffa, Neue Zurcher Zeitung, 30th of March 1954 በሚል መጽሐፋቸው በማያሻማ ቋንቋ ማስቀመጣቸው ግርምት የሚጭር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ እ.አ.አ. ጁላይ 6, 1936 ዓ.ም. ሌላው አልፍሬድ ኢልግ ልጅ አልፍሬድ የሚባለው ለካፋ ታሪክ ተመራማሪዊ ፍሬድሪክ ቢቤር ልጅ ለኦቶ ቢቤር በጻፈው ደብዳቤ ሦስቱን የካፋ ቅርሶች ከ100 ሺህ የሲዊስ ፍራንክ በታች እንደማይሸጡ ጠቅሶ፣ የኢትዮጵያና የጣሊያን መንግሥታት ቅርሶቹን ለመግዛት ፍላጎት እንዳሳዩ በዚሁ ደብዳቤ ገልፆ ነበር፡፡ይህ የገንዘብ መጠን ባለንበት ዘመን ሲሰላ ብዙ ሚሊዮን የሲዊስ ፍራንክ ወይም ብዙ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ይሆን ነበር፡፡

የካፋ ኪንግደም የወርቅ ዘውድ ሌሎች ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ተመለሱ?

እ.አ.አ. 1954, ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመንግሥታዊ የሥራ ጉብኝት አውሮጳ በሄዱበት ጊዜ ሲዊዘርላንድን ከኖቨምበር 25 እስከ ኖቨምበር 28 መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱና ለኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ክብር ኖቨምበር 26 የዙሪክ አካባቢያዊ መንግሥት በታዋቂው ዙሪክ ግራንድ ሆቴል ባዘጋጀው የእራት ሬሰፕሽን ግብዣ የአልፍሬድ ኢልግ ባለቤት የ92 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ወ/ሮ ፋኒ ኢልግና ልጃቸው ፌልክስ ኢልግ በዚህ እራት ተጋብዘውና ተገኝተው ግርማዊ ጃንሆይን ማነጋገራቸውን በሲዊዘርላንድ ፌደራል ቤተመዛግብት ኖቨምበር 27፣ 1954 ዓ.ም. በጆርናል ቲርቡን ዲላሳኔ የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል፡፡ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሲዊዘርላንድን ጉብኝት አጠናቅቀው ወደ ቬይና ኦስትሪያ ቢያቀኑም፣ በሚያስገርም ሁኔታ ዲሰምበር 1 ቀን 1954 ዓ.ም. ወደ ዙሪክ ሲዊዘርላንድ እንደገና ለመመለስ ተገድደው ነበር፡፡ለዚህ ለሁለተኛው የዙሪክ ጉዞአቸው ጃንሆይ የተመለሱበት ምክንያት በኦስትሪያ ቤይና አጭር ቆይታቸው ወቅት በቬይና ኢትኖግራፍ ሙዝየም በታዋቂው የካፋ ታሪክ ተመራማሪ በፍሬድርክ ቢቤር አማካኝነት የተሰበሰቡ ምርጥ የካፋ ቅርሶችና የካፋን ነገሥታት የወርቅ ዘውድ ፎቶ በመመለከትና የቢቤርን ልጅ ኦቶ ቢቤርን የወርቅ ዘውዱ የት እንደሚገኝ ጠይቀው በኢልግ ቤተሰቦች እጅ ወይም ይዞታ ስር ዙሪክ ሲዊዘርላንድ እንደሚገኝ ካረጋገጡ በኋላ ነበር፡፡

ዙሪክ ከተማ ቤተ መዘክር በተገኘው መረጃ እ.አ.አ ዲሴምበር 2 ቀን 1954 ዓ.ም. በጆርናል ቮለከሰርችት እንደተጻፈው ቀኃሥ በቬይና ያቀዱትን ቆይታ በማሳጠራቸው ለኦስትሪያ ምክትል ቻንሰለር ስቻርፍና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ዙሪክ ኦፊሴላዊ ላልሆነ ድጋሚ ጉብኝት የመሄዳቸው ሚስጥር የካፋን የወርቅ ዘውድና ሌሎች ቅርሶች በዙሪክ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው ኢትኖግራፊክ ሙዝየም በዓይን ለማየትና የአልፍሬድ ኢልግን ቤተሰቦች ለማግኘትና ለማነጋገር ነበር፡፡ጃንሆይ በዚህም ጥረት የካፋን የወርቅ ዘውድና የብርና የወርቅ በርጩማ ለማግኘት ከ10 ቀን በላይ የወሰደ እልህ አስጨራሽ ድርድር ለማድረግ መገደዳቸውን የኦቶ ቢቤር ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እጅግ የሚያስገርመው ነገር የኢልግ ቤተሰቦች ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እነዚህን የካፋ ድንቅ ቅርሶች በስጦታ ወይም ቅርስ ለባለቤት አገር በነጻ ለመመለስ ፍቃደኛ ያለመሆናቸው ነው፡፡ስለሆነም የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በግዢ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ነበር፡፡ ከቀኃሥ የአውሮጳ ጉብኝት የልዑካን ቡድን አባል የሆኑትና በዘመኑ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ጀነራል ዳይሬክተር የነበሩ ክቡር አቶ ፋንታዬ ወልደዘሊባኖስ በአማርኛ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1999 ዓ.ም. በጻፉት የአባ ጠቅል ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ዘመን በተባለው መጽሐፍ የኢልግ ቤተሰቦች 52 ሺህ የሲዊስ ፍራንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ካዚና እንደተከፈላቸው ማረጋገጣቸውና ይህም ገንዘብ ሲዊስ ባንክ ለቆየበት የ 50 ዓመታት የጥበቃ ወጪን ጨምሮ የተሠጠ ማካካሻ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ባለንበት ዘመን አሁን ሲሰላ ብዙ ሚሊዮን የሲዊስ ፍራንክ ወይም ብዙ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ይሆን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በዘመኑ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ አውጥቶ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅና የተከበረ ቦታ ያለውን የካፋ ሕዝብ ቅርሶች ማስመለሱ አድናቆት ሊቸረው እንደሚገባ ያሳያል፡፡

አሁን የካፋ ኪንግደም የወርቅ ዘውድ እና ሌሎች ቅርሶች የት ነው ያሉት?

ከላይ እንደተገለፀው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በብዙ ድካምና ጥረት የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ እና በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ቅርሶቹ እ.አ.አ. 1963 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ የት እንደነበሩ የሚያሳይ ምንም መረጃ ማግኘት ባይቻልም ፣ እንደ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት (Institute of Ethiopian Studies-IES) ካታሎግ ካርዶች መረጃ መሠረት ቀኃሥ ለተቋሙ በተመሰረተበት ዓ.ም. ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1956 ዓ.ም. በስጦታ ማስረከባቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኦርጂናሎቹ የት እንደተቀመጡ ባይታወቅም፣ የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ (The crown of Kafa, Museum of the Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa, Accession No. 1936a; height: 23 cm (helmet) plus 60 cm (the upper ostrich feather በሚል ካታሎግ) እና በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ (The stool of Kafa, Museum of the Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa, Accession No. 1936b; height: 40 cm በሚል ካታሎግ) እስከ እ.አ.አ. 2013 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት ኢትኖግራፊክ ሙዝየም ይገኙ እንደነበር የሚከተሉት የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት display ላይ ያሉት ቅርሶች በትክክል በባለሞያ ታይተውና ተጠንተው ኮፒ ያልተደረጉ ኮፒ መሳይ የካፋ ንጉሥ የወርቅ ዘውድ እና በብርና ወርቅ የተለበጠ በርጩማ ማሳያ ቅርሶች ናቸው፡፡ የካፋ የነገሥታት ካባም አምስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም የካፋ ባላባቶች የክብር ካባ በሚል የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ካባ በፖስት ካርድ መልክ በነጠላ እስካሁን በሁለት ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ሁለት የወርቅ የጆሮ ጌጣጌጦች አንዱ 33 ሴንት ሜትር ሌላው 32 ሴንት ሜትር የሆኑት በአሁኑ ጊዜ በዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ኢትኖግራፊክ ሙዝየም (The Ear Pendants of Kafa, Ethnographic Museum of the University of Zurich, Inventory No. 12099a and 12099b; length 32 cm and 33 cm በሚል ካታሎግ) ዙሪክ ሲዊዘርላንድ ይገኛል፡፡ሌሎች ብዛት ያላቸው በታዋቂው የካፋ ታሪክ ተመራማሪ በፍሬድርክ ቢቤር አማካኝነት የተሰበሰቡ ምርጥ የካፋ ቅርሶች በአሁኑ ወቅት በቬይና ኦስትሪያ ኢትኖግራፍ ሙዝየም እንደሚገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የካፋ ሕዝብ የቅርሶቹ ባለቤትነት የመብት ጥያቄ

በዚህ አጋጣሚ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የካፋን ሕዝብ ቅርስ ከሲዊዘርላንድ ለማስመለስ ያደረጉትን ጥረትና ድካም በኋላም በኢትዮጵያ ሙዝየሞች በክብር እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን ከልብ እናደንቃለን፡፡ምስጋናም ይገባቸዋል፡፡ እነዚህን ቅርሶች ወደ ባለቤቱ የካፋ ሕዝብ ለመመለስ ከ1990 ዓ.ም. እስከ የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም ምረቃ በዓል ድረስ (2007 ዓ.ም.) የተደረጉ ጥረቶች የተሳኩ አልነበረም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃውን ያልጠበቀ ሙዝየም ካልተሰራ ቅርሶቹ የአገር ሀብት በመሆናቸው ይጠፋሉ በሚል ፍራቻ እንደነበር የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት ኃላፊዎችና መሪዎች መግለጻቸው አግባብነት አለው ሊባል ይችላል፡፡ የትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ካፋ ቦንጋ ከተማ ከተሠራ በኋላ የእምቢተኝነት መልስ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡

ስለዚህ ምን ይደረግ? ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው የዓለም አቀፍ ሕጎች ቅርሶች ለባለቤቱ እንዲመለስ ያስገድዳል፡፡ይህ ማለት የካፋ ኪንግደም የወርቅ ዘውድ እና ሌሎች ቅርሶች የካፋ ሕዝብ ታሪክና ማንነት የሚያመልክቱ ልዩ ምልክቶች በመሆናቸው ለዘመናት የካፋ ሕዝብ ያደረጋቸው ተጋድሎዎች ይመሰክራሉ፡፡ በነገራችን ላይ የካፋ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ምን ጊዜም ተደራድሮ የማያውቅ ሕዝብ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጹ አግባብነት አለው፡፡ይህ ሕዝብ ከአፄ ምንልክ ጋር ለጦርነት ዝግጅት በሚያደርግበት ጊዜ ከዩጋንዳ የእንግሊዝ ተወካዮች ካፋ ድረስ በመምጣት የጦር መሳሪያና የወታደር ርዳታ ለማድረግ የመጣውን ልዑክ በጀግናው ንጉሡ አፄ ጋኪ ሸረቾ አማካይነት ” እኔ የምዋጋው ከወንድሜ ከምንልክ ጋር ነው፡፡ ይህ የወንድማማቾች ጦርነት ነው፡፡ እሱ ካሸነፈን ካፋን ይጠቅልል፡፡ እኔ ካሸነፍኩ ኢትዮጵያን እጠቀልላለሁ፡፡” ብሎ ለሥልጣን ኢትዮጵያን ለባዕድ አሳልፎ ያልሰጠ ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡በካፋ ውስጥ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ቤተክርሰቲያናት ጥንታዊ የሙስለም መስግዶችና የኦሪት እምነት እስከ አሁን በፍቅር ተሳስረውና ተቃቅፈው የሚኖሩበት አገረ ህዝብ ነው፡፡ይህ ሕዝብ የራሱን አስተዳደር ክልል የመመስረት ታሪካዊ፣ሥነልቦናዊ፣ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊና ጂዖግራፊያዊ ምክንያቶች እንዳሉት ለመግለጽ ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችና ውሳኔ ማገናዘቡ ለዘመኑ መሪዎች የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ከላይ የተገለፁ ቅርሶችም በካፋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም የኢትኖግራፊክ ክፍል በዘመናዊ መልክ ቢቀመጡ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የቱሪስት መናኸሪያ ቦታ ይኖራታል፡፡

ይህ ሕዝብ በዘመኑ የፍትሕ መጽሔት አምደኛ ቻለቸው ታደሰ ባልተገራ አንደበት የሚቀለድ ታሪክ የለውም፡፡ በቧልተኛው በዕውቅቱ ስዩም አውቅኩ ባይ ታሪኩን ጥላ እሸት የመቀባት ዝባዝንኬ ከቁብ አይቆጥረውም፡፡ በእነ ከድር ሰቴቴ የተቃወሰ እእምሮ ትርክት መሠረቱን አይስትም፡፡ በእነ ኤርምያስ ለገሰ የመሸታ ቤት ፉገራ መጽሐፍ አይደነቅም፡፡ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች እነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም፣ ኢነጅነር ቅጣው እጅጉ፣የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረሰት ፣ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ወዘተ… የተከበረ ውብና ድንቅ ታሪክ እንዳለው የተመሰከረለት ሕዝብ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መሪዎችም ከጥንት ከአብርሃ አጽብሃ ዘመን ጀምሮ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከፍተኛ ክብርና ትኩረት የሚሰጡት ሕዝብ እንደነበር የታሪክ ማሰረጃዎችን ማገላበጥ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በእነ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ተጀምሮ በጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርም ደሳለኝ ተመርቆ እስካሁን ሥራ ያልጀመረውን ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የአገር ሀብት የፈሰሰበትን የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዘየም ሥራ ማስጀመር ሞራላዊና አገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ የቦንጋ ዩኒቨርሰቲም ልክ እንደ ዙሪክ፣ ቬይናና የኢትዮጵያ ኢትኖግራፊክ ሙዝየም በቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም የኢትኖግራፊክ ዲፓርትመንት በማቋቋም ቅርሶችን ከዙሪክ ሲዊዘርላንድ፣ ቤይና ኦስትሪያና አዲስ አበባ ኢትዮጵያ…ወዘተ ማሰባሰብ፣መጠበቅ፣ማስተማር መመራመር የትውልድና የሙያ ግዴታ እንዳለበት በዚህ አጋጣሚ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ዋቢ ማስረጃዎች
1. AAbbink J., 2007, Kafa History, in Uhlig S. (ed.), Encyclopaedia Aethiopica, vol. 3, Wiesbaden, Harrassowitz Verlag, 322-324.
2. Abbink J., 2010, Tato, in Uhlig S. (ed.), Encyclopaedia Aethiopica, vol. 4,Wiesbaden, Harrassowitz Verlag, 872.333
3. Anonymous, 1954a, Haile Selassie wieder in Zurich, Volksrecht, 283/2.12., n. p.
4. Anonymous, 1954b, Glossen zum Besuch Haile Selassies, Volksrecht, 283/2.12., n. p.
5. Bairu Tafla, 2000, Ethiopian Records of the Menilek Era—Selected Amharic Documents from the Nachlassof Alfred Ilg, 1884-1900,Wiesbaden, Harrassowitz Verlag.
6. Biasio Elisabeth, Gerber Peter R. The Return of the Crown of Kafa from Switzerland to Ethiopia: A Case of Restitution? /Le retour de la couronne du Kafa de la Suisse à l’Éthiopie: un cas de restitution?. In: Annales d’Ethiopie. Volume 31,année 2016. pp. 25-43; doi : https://doi.org/10.3406/ethio.2016.1622፣ https://www.persee.fr/doc/ethio_0066-2127_2016_num_31_1_1622
7. Bieber F. J., 1923, Kaffa—Einaltkuschitisches Volkstum in Inner Afrika, 2, Wien, Verlag der “Anthropos”- Administration, St. Gabriel-Modlin.
8. Bieber O., 1948, Geheimnisvolles Kaffa—Im Reich der Kaiser-Gotter, Wien, Uni- versum Verlags gesellschaft. M.B.H.
9. Braukamper U., 2007, Kingship, divine, in Uhlig S. (ed.), Encyclopaedia Aethiopica, vol.3,Wiesbaden, Harrassowitz Verlag, 401-403.
10. Bustorf D., 2007, Kallaa, in Uhlig S. (ed.), Encyclopaedia Aethiopica, vol. 3, Wiesbaden, Harrassowitz Verlag, 333-334.
11. Fantaye W/Zelibanos, 2007 (1999 E.C.), Ya-abba taqel atse Hayla Sellase zamana mangest (TheTime ofReign of Abba Taqel EmperorHaile Selassie),AddisAbaba, Mereb.
12. Fuchs E., 1992, Gotter, Graber und Geschafte. Von der Plunderung fremder Kulturen, Zurich, Erklarung von Bern (EvB).
13. Ganslmayr H., 1980,Wemgehort die Benin-Maske? Die Forderungnach Ruckgabe von Kulturgut an die Ursprungslander, Vereinte Nationen, 3/80, 88-92.
14. Holzapfel J., 2012, Friedrich Julius Bieber,Wien, BezirksmuseumHietzing. Im Hof U., 1977, Ancien Regime, Handbuch der Schweizer Geschichte, Zurich, Berichthaus, 2, 673-784.
15. Keller C., 1918, Alfred Ilg—Sein Leben und sein Wirkenals schweizerischer Kulturbote in Abessinien, Frauenfeld and Leipzig, Verlag Huber & Co.
16. Kung H., 1999, Staatsminister Alfred Ilg (1854-1916)—Ein Thurgauer am Hof KaiserMeneliks II. von Athiopien, Zurich, Thesis Verlag.
17. Lange W. J., 1982, History of the Southern Gonga (Southwestern Ethiopia), Wies- baden, Franz Steiner Verlag.
18. LuscherG., 2010,Himmel und Erde. Der altesteerhaltene Erd – und Himmelsglobus der Welt, NZZ Neue Zurcher Zeitung, 14 February, URL: http://www.nzz.ch/ aktuell/startseite/himmel-und-erde-1.4954311.
19. Onneken D., 1956, Die Konigskultur Kaffas und der verwandten Konigreiche, Frankfurt am Main, Inaugural Dissertation.
20. Shiferaw Bekele, 2007, Kafa dynasties (14th to end of 19th cent.), in Uhlig S. (ed.), Encyclopaedia Aethiopica, vol. 3,Wiesbaden, Harrassowitz Verlag, 324-326.
21. Steinmann A., 1954, Die Krone von Kaffa, Neue Zurcher Zeitung, 30th of March, n.p.

Figure 2.The crown of Kafa, Museum of the Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa, Accession No. 1936a; height: 23 cm (helmet) plus 60 cm (the upper ostrich feather)
Source: Peter R. Gerber, 2013.

Figure 3.The stool of Kafa, Museum of the Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa, Accession No. 1936b; height: 40 cm
Source: Peter R. Gerber, 2013

.
Figure 4፣ The Ear Pendants of Kafa, Ethnographic Museum of the University of Zurich, Inventory No. 12099a and 12099b; length 32 cm and 33 cm
Source: Silvia Luckner, 2013

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: