Leave a comment

የክልል ጥያቄ እንቆቅልሽ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እንጂ በጥናት አይፈታም::


የክልል ጥያቄ እንቆቅልሽ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እንጂ በጥናት አይፈታም::

ሲጀመር የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በአግባቡ መተግብር እንጂ ጥናት ለምን አስፈለገ?? ቀደም ሲል ክልል የሆኑ አካባቢዎች ላይ ክልል ሆነው ከመዋቀራቸው በፊት ለምን ጥናት አልተደረገባችውም? አሁን የክልል ጥያቄ ያቀረቡትን ከፊተኞቹ የሚለያችው ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? ሲዳማ የጥናቱ አካል ሳይሆን ጥያቄው ለምርጫ ቦርድ እንዴት ተላለፈ? ለሌሎቹ ያልተፈቀደው በምን ምክንያት ከሕግ ውጭ ያለ ጥናት የሲዳማ ጥያቄ ህጋዊ ሆነ? እነዚህንና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ሲገባ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ ከሆነ የህዝብን ንቃተ ህሊና ያለመረዳት ችግር ይሆናል::ሕገ መንግሥቱም ቢሆን ተቀርፆ ከመፅደቁና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ለህዝብ ቀርቦ ውይይት ያልተደርገበትና አስተያየት ያልትሰጥበት በመሆኑ ውሎ አድሮ በሂድት የሚያመጣው ችግርና መፍትሔው በጥናት ባለመደገፉ ዛሬ ላይ አወዛጋቢ የክልል ጥያቄ ሊያስከትል ችሏል:: የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ እንዲሉ በውቅቱ የኢሃዲግ ዓላማ ኤርትራን ገንጥሎ ለሻቢያ ለመስጥትና እርሱም ከተደላደለ በኃላ ትግራይን ለመገንጠል እቅድ ስለነበረው አንቀፅ 39ን ደንቅሮ ዛሬ ላይ መዙዙ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተንና ሆነም ቀረ አንድንቱን ጠብቆና አስጠብቆ የኖረውን ህዝብ መበታተን ሆኗል::

ምን ግዜም ቢሆን የብዙሀኑን ይሁንታ ያላገኘ ሕግም ሆነ ድርጅት ውሎ እድሮ ቅሬታ ማስነሳቱ አይቀሬ ሲሆን የወቅታዊው የክልል ጥያቄም እንቆቅልሽ እየሆነ የመጣው አንድ ሀገር አስተዳደራዊ መዋቅር ሲዘረጋና ሕገ መንግሥት ሲያረቅ ዘላቂነት እንዲኖረውና ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር መሆን ሲገባው መንግሥት በተለወጠና በተቀየረ ቁጥር የሚለዋወጥ ከሆነ የዚህ ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ አስተዳደራዊ ችግር ይከሰታል:: መጨረሻውም አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይሆናል::

አሸዋ ላይ የተገነባ ቤት መሰረት እንደሌለው ሁሉ ህዝብ ያላመነበትና ውክልና ያልተሰጠው የጥቂት ቡድኖች ስብስብ ራሱን ደኢሕዴን ብሎ የሚጠራው ድርጅት በ56 ብሔር ብሔረሰቦች ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለምለምና በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማእድናት በባህልም ሆነ በእሴት በመልካ ምድር አቀማመጥም ሆነ በቱሪስት መስህብነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ የአረንጏዴ አልማዝ (diamond) ቡና መገኛ የሆነውን ጨምሮ የአንበሳውን ድርሻ በሁሉም ዘርፍ ለማዕከላዊ መንግሥት አስተዋፅኦ የሚያደርገውን የካፋንና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አካባቢ ደቡብ ክልል በሚባል ኮንቴነር/ኮሮጆ ውስጥ ያለውዴታችው በጉልበት ጨፍልቆ አንተ ዝም በል እኔ አውቅልሃለሁ የአንተ ሚና የተባልከውን ማድረግ ነው በሚል ከበላይ የተቀበለውን ትእዛዝ እንደ ወረደ ህዝቡ ጫንቃ ልይ በመጫን የኢሀዲግ አጋር በመሆን ላለፉት 27 ዓመታት ስውር ቅኝ አገዛዝ በተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካይነት ሲረገጥና ለኢ-ሰብዓዊና ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ተጋልጦ በሁሉም አቅጣጫ የኃሊት በመጏዝ ዛሬ ላይ ደርሷል::

ወጡን የሚያጣፍጠው የጉልቻ መቀያየር አለመሆኑ እየታወቀ ብቃት የሌላቸው ግለሰቦች በፖለቲካ አመለካከታቸውና ኢሀዲግዊ ድጋፍ ሰጪነታቸው እንደ ብቃት ተወስዶ የሲዳማ ተወላጆች እየተፈራረቁ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ተቀምጠው የ55 ብሔር ብሔረሰቦችን ህልውና ጨፍልቀው አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ከ1,000 ኪ/ሜ በላይ እንድጏዝና ከማእከላዊ መንግሥት የሚመደበውን በጀት የአንበሳው ድርሻ በመመዝበር ሐዋሳን በማበልፀግ ሌሎችን በማቆርቆዝ ሲዳማን በኢኮኖሚና በመሠረታዊ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ ላይ አድርሶ ከሌሎች አጋሮቹ በተለየ ሁኔታ የክልል ጥያቄውን ተቀብሎ በማፅደቅና የሌሎችን ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ ተፈፃሚ ከማድረግ ይልቅ በዛቻ ብጫና ቀይ ካርድ አሰናብቷቸዋል::ይህ አካሄድ ሕገ መንግሥቱን ከመፃረሩም በላይ የሕግ የበላይነትን ጥሶ የብሔር የበላይነትን የሚያመላክት በመሆኑ ደእህዴን ወገናዊነቱ ለአንድ ብሔር እንጂ ለ56 ያለመሆኑን በአደባባይ በማስመስከር የሲዳማን ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ ተላልፎ በምርጫ ቦርድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞ 55 ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል:: ሰላማዊ እንስቃሴ እያደረጉ የሚገኙትን ብሔር ብሔረሰቦችን ኮማንድ ፖስት በሚሉት የአፈና መዋቅር በማፈን ዳግም የክልል ጥያቄ እንዳያነሱ ማእቀብ ተጥሎባቸዉ ይገኛሉ:: ደኢህዴንም የማስተዳደርም ሆነ የመምራት ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል:: ብቻ ድሮውንም አልነበረውም::

የደእሕዴን አመራሮችና ሥልጣን የተቸራችው ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያትም ጌታዋን የተማመንች በግ ጅራቷን ውጭ ታሳድራለች እንዲሉ መጀመሪያም የተሾሙት ክልሉን የማስተዳደር ብቃት ኖሯችው ሳይሆን ቁልፍ ቦታ ላይ የኦሮሞ ተወላጆችን የመመደብ ሥራ የተያያዙት በኢትዮጵያዊነትና በኦሮሞ ብሔርተኝነት መካከል ዥዋዥዌ በመጫወት ላይ የሚገኙት የጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ አስተዳደር የኦሮሞ ብሔርተኝነትና ወገናዊነት ሲንፀባረቅ ይስተዋላል:: ደእህዴንም ሆነ አመራሩን ወደ ፊት ለማስቀጠል ምንም ዓይነት ጥገና ቢያደርጉም የተንቃነቀ ጥርስ መፍትሄው አውልቆ ጥሎ በአዲስ መተካት ስለሆነ የግለሰብዋ በሥልጣን ለመቆየትም ሆነ ደእሕዴንን እንደ ድርጅት ለማስቀጠል መሯሯጥና መሞከር ከወደቁ በኃላ መንፈራገጥ ቢሆንም የመጨረሻ ሰዓትም ቢሆን ሕገ መንግሥቱን በመተግበር ለክልል ጥያቄው እልባት መስጠት አንዱና የመጨረሻው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይሆናል::

ወደ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመልስ የበላችው ያገሳታል በላይ በላዪ ያጎርሳታል እንዲሉ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ተብሎ የሚጠበቀው ለውጥም ከድጡ ወደ ማጡ በመሄድ ላይ ይገኛል::ሰላምና ፍቅር በዲስኩር ይመጣ ይመስል ሰባኪው የለውጥ ሐዋርያና ፓስተር ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ ቀንና ሌሊት ሲሰብኩን እውነት መስሎን አፋችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ከፍተን በሞቀ ጭብጨባ የተቀበልናቸው ቢሆንም እሳቸው ግን ሲያሻቸው አንድ ወቅት አንድ እግራቸውን ከኢሀድግ ሌላውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጭነው ከላይ እታች ቢሉም ማሩ አንደበታቸው በተግባር ሲለወጥ እሬት ሆኗል:: መገደሉ መፈናቀሉ ስደቱ ንብረት ውድመቱ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉ ምእመናን መሞታቸው እግዚኦ ምን መአት ወረደብን?? አሁን ሀግሪቱን የሚመራው ማነው? ኢሃዲግ ወይስ ጁዋር መሐመድ ወይስ የለውጥ ኃይሉ? ኢሃድግ ከሆነ ጨርቁን ጠቅሎ እግሬ አውጭኝ ብሎ ከነግብረ አበሮቹ መቀሌ ከመሸገ አመት አስቆጥሯል:: ማንም እንደማይደፍረው አረጋግጧል:: አድር ባዮች ወደ መቀሌ ይጎርፋሉ እንጂ እርሱ ወደ አአ ለመምጣት አልደፈረም:: አዲስ አበባን የኦሮሞ ባለሥልጣናት መፈንጫ በማድረግ የተደበቀ ቢመስልም ውስጥ ለውስጥ ጉልበቱን አጠናክሮ ትንፋሹን ሰብስቦ አሁንም ያለ እኔ ኢትዮጵያ አይሆንላትም እያለ ተመልሶ የሥልጣኑን በትረ መንግሥት ለመጨበጥ አድርባዮችንና ሆዳሞችን ሰብስቦ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል:: የለውጥ ኃይሉም እንዳነሳሱ ሳይሆን የውስጥ ችግርን ችላ ብሎ ከዛፍ ችግኝ ተከላ መልስ ውጭ ውጭ ማለት አዘውትሯል:: ታዲያ አሁን ማን ውክልና ሰጥቷቸው ነው ጁሐራውያን ሀገር የሚያተረማምሱት??

ዛሬ ብዙዎች እንደሚተነብዩት ከሆነ ኢትዮጵያ ሀገራችን ላይ ትልቅ የመበታተን አደጋ ተጋርጦባታል:: የቀረበው የክልል ጥያቄ ህገ መንግሥቱን ተከትሎ እልባት ማግኘት ሲገባው ህገ መንግሥቱን ጥሶ ሣይንሳዊ ጥናት አደርጋለሁ በማለት ግራ የተጋባው ደእሕዴን አመራሮቹን ከሐዋሳ አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ በማመላለስ ሕገ መንግስቱ በማያሻማ መልክ ያስቀመጠው መፍትሔ በእጁ ላይ እያለ የሀገሪቱን ሀብት በአበልና በትራንስፖርት ያላአግባብ ሲያባክን ይታያል::

ይድህዴን አስተዳደር ካለፉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳየው የመዋቅሩ እንቅስቃሴ ለአንድ ብሔር (ለሲዳማ) እድገትና ብልፅግና በመወገንና በመቆም ዓላማውን ከግቡ አድርሷል:: የ55 ብሔር ብሔረሰቦች እድልና እጣ ፋንታ ግን እንቆቅልሽ ሆኗል:: ሕገ መንግሥቱ በአግባቡ ካልተተገበረና የሌሎች ክልል ጥያቄአቸው አዎንታዊ መልስ ካላገኘ ካፋም ሆነ ሌሎች የድርጅቱ አባላት በህልውናችን ላይ የተቃጣው ጥቃት እልባት ካላገኘ ትግሉ በሰላማዊ መንገድ መቀጠሉ አያጠያይቅም:: እዚህ ላይ የካፋ ምሁራንና የካፍ ህዝብ መጨቆንም ሆነ በመሠረታዊ ልማት ኃላ መቅረት ሀብትና ንብረቱን መበዝብዝና የመሬት ዝርፊያው ፍትህ ማጣቱ ያገባኛል የሚል ማንኛውም የአካባቢው ብሔረሰብ ትግሉን ተቀላቅሎ አጋርነቱን የሚገልፅበት ወሳኝ ወቅት ላይ በመሆኑ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረት (ደምኢሕህ) ጎን እንዲቆምና የክልል ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ እስከሆነ ድረስ በአስቸኳይ ምላሽ እስኪያገኝ ሰላማዊ ትግሉን በነፍስ ወከፍ መደገፍ አማራጭ የሌለው ስለሆነ ዳር ቆሞ መመልከት ዋጋ ስለሚያስከፍል ከወዲሁ ግንዛቤ መውሰድና አቋምን ማስተካከል ግድ ይላል:: ጥያቄው የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ለድርድር አይቀርብም:: ጊዜ ይውሰድ እንጂ ካፋ ክልል መሆኑ አይቀሬ መሆኑን የደብብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት በፅኑ ያምናል:: ለተግባራዊነቱም የፓርቲው አባላትም ሆኑ ወጣቶችና ምሁራን በአጡቃላይ ህብረተሰቡ በህልውናው ላይ የተቃጣውን ጥቃት አንድ ላይ በመቆም በሰላማዊ መንገድ የክልል ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ያስገንዝባል::

<<ሀገር ለነበረ የካፋ ህዝብ ክልል መሆን ያንሰው እንደሆነ እንጂ አይበዛበትም>>

በመጨረሻም አመራሮችም ከህዝብ ጎን ለመቆም ወሳኝ ወቅት ላይ ስለሆናችሁ ከህዝብ ጎን በመቆም የሚያልፍ ጥቅምን ወደ ኃላ ትታችሁ ለትውልድ የሚተላለፍና የሚያኮራ ታሪክ አስመዝግቡ:: ስም ከመቃብር በላይ ይዉላልና ለልጅ ልጆቻችሁ አኩሪ ታሪክ በማስመዝገብ ከወቀሳና ከውርደት ራሳችሁን አውጡ::

ድል ለተጨቆነው ህዝባችን::
የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ያለአድልዎ ይመለስ!!!
ክልል መሆን ኢትዮጵያዊነትን ያጠናክራል እንጂ አያፋልስም::

ፋንታዬ መኮ
ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓም
2 September 2019
ካፋ ሚድያ kaffamedia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: