Leave a comment

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦንጋ ጉብኝት ቅኝት


እሑድ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ፣ ከደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውና ከቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን ከ50 በላይ ጋዜጠኞችን አስከትለው በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ ከሚነሳባቸው አንዱ በሆነው የካፋ ዞን ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዞኑ ዋና ከተማ ቦንጋ ሲደርሱ፣ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በከተማው መለስተኛ ስታዲየም ታድመው ሲጠብቋቸው በነበሩ የቦንጋና አካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስታዲየሙ ተሰብስበው ሲጠብቃቸው ለነበረው የአካባቢው ኅብረተሰብ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት፣ የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ያስተላለፉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ ከዓመት በፊት ሠልፍ በተደረገበት ሥፍራ ተገኝተው ሕዝቡን ማግኘት በመቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው በመግለጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተዋወቁት ‹‹የመደመር ፍልስፍና›› በመመራት አስተምህሮቱን ዕውን ለማድረግ፣ አገራዊ ኃላፊነቱንና አደራውን ለመወጣት በመትጋት ላይ የሚገኝ ሕዝብ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ማስረሻ የካፋ ዞን እየተመናመነ ከለው የአገሪቱ የደን ሽፋን ከ700 ሺሕ ሔክታር በላይ ጥብቅ ደን በመያዝና በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በዩኔስኮ በመመዝገብ የአገሪቱ ሳንባ ሆኖ የዘለቀ ሥፍራ መሆኑን በመጠቆም፣ ዞኑ ካለው አቅም የተነሳ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ሊጠቅም የሚችልና ትልቅ አቅም ያለው ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በለውጡ ማግሥት በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ሲከሰቱ በውዥንብሮች ሳይፈታ ራሱን ጠብቆ የቆየ አካባቢም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ሺሕ ዓመት ቀደም ብሎ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ በምንጃ፣ ማቶና ሚንጃ ሥርወ መንግሥታት እየተመራ የቆየ ሕዝብ እንደሆነ የገለጹት አቶ ማስረሻ፣ ካፋ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ከተቀላቀለ በኋላም ፍፁም ኢትዮጵያዊነቱን ጠብቆ የኖረና እየኖረ ያለ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ምንም እንኳ በተለያዩ የብዝኃ ሕይወትና ሌሎች ሀብቶች የታደለ አካባቢ ቢሆንም በአስፈጻሚ አካላት ትኩረት ማጣት የተነሳ ለበርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጠ ነው በማለት ዞኑ መንገድ፣ ውኃና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ የመሠረተ ልማቶች ችግር በስፋት የሚስተዋሉበት ነው ብለዋል፡፡

ለአካባቢው የተሻለ ጥቅም ሊያመጡ ይችሉ የነበሩና ባለው አቅም የተነሳ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ማዕከል ሊያደርጉት ይችሉ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክቶች እንኳን እንደተነፈጉት የጠቆሙት አቶ ማስረሻ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ሲንከባለሉ የመጡ የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት እንደሚያስችል ትልቅ ተስፋ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የካፋን ሕዝብ ባህልና ምድር በተለያዩ አገላለጾች ያሞካሹ ሲሆን፣ ‹‹ዓብይ! ዓብይ!›› እያለ የተቀበላቸውን ሕዝብ፣ ‹‹ለ2012 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!›› በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹2012 ኢትዮጵያን ከብልፅግና የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን፣ የተራራቁ ወንድማማቾች የሚጠያየቁበት ዓመት በመሆኑ እኛ ወንድሞቻችሁ ካለንበት ልንጠይቃችሁ መጥተናልና አዲሱን ዓመት የፍቅር፣ የብልፅግና፣ የሰላምና የመደመር ያድርግላችሁ፤›› በማለት በድጋሚ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የካፋ ሕዝብ ለማዕከላዊ መንግሥት ሥርዓት የመተዳደር ልምድ ያለው፣ በሚካረቾ የአማካሪዎች ድጋፍ የሚደረግለት መንግሥት የነበረው መሆኑን፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት የነበረው መሆኑን፣ እንዲሁም ለፍትሕ የቆመ አስተዳደራዊ ሥርዓት የነበረው መሆኑን በመጠቆም፣ ይኼ ልምድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚከበርባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹ኢትዮጵያን የማስፋት እንጂ የማሳነስን ልምድ ለልጆቻችን የማናወርስ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፤›› በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡

ከዚህ የስታዲየም ቆይታ በኋላ በዞን አስተዳደር አዳራሽ ከተሰበሰቡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህ የአዳራሽ ውይይት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመንገድ፣ ከውኃ አቅርቦት፣ ከጤና አገልግሎት፣ ከድልድይና ከሥራ ዕድል እስከ ክልልነት ጥያቄ የዘለቁ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ ሁሉም ጠያቂዎች ግን ሳያነሱ ያላለፉት ዞኑ በክልል እንዲደራጅ ለክልል ምክር ቤት የቀበረውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ነው፡፡

የመጀመርያውን ጥያቄ ያቀረቡትና ከነጋዴ ማኅበር ተወክለው እንደመጡ የጠቆሙ ወይዘሮ የክልልነት ጥያቄን የመጀመርያው ነጥባቸው በማድረግ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ ጥያቄው በተለያየ መንገድ ሲነሳ የቆየ ቢሆንም ዛሬ ግን ይኼንን ጥያቄ የምታነሱ ጠባብ ናችሁ የሚል ሳይኖር ሰሚ ያገኘ ጥያቄ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ክልልነቱ ቢሰጠን ብቻችንን እንኑር አላልንም፣ ሁሉንም አቅፈን እንኖራለን፤›› ያሉት ወይዘሮዋ፣ ዕምቅ ሀብት ያለውና ለማደግ የሚችል አካባቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ ጥያቄ ሌላው ስለጠየቀ ዛሬ የሚጠየቅ አይደለም፤›› ብለው፣ እነዚህ ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን የሚመጡ ኢንቨስተሮች አካባቢውንም ሆነ ነዋሪዎችን የማይጠቅሙ እንደነበሩ በመጠቆም፣ ‹‹ጫካ መንጥሮ ጣውላ ሸጦ የሚወጣ ሳይሆን ጠንካራ ኢንቨስተር ይምጣ፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ከእሳቸው ጋር የመጡትን እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለትና በማመስገን የጀመሩት ሌላ የስብሰባ ተሳታፊ አባት፣ ራሱን በራሱ በንጉሣዊ ሥርዓት ሲያስተዳድር የቆየ ሕዝብ እንደነበር በመጠቆምና በኋላም በአውራጃና በእገሌ አገር ደረጃ ሲጠራ የቆየ አካባቢ በደቡብ ክልል መካተቱን በመጠቆም፣ ይኼ ለውጥ የሚጠላ ባይሆንም የዞኑን ነዋሪዎች የት ነው ያሉት በማለት የሚጠይቅ፣ ብሎም ክፍተቶች ሲገኙ የሚያስተካክል ሰው አለመኖሩ ቅር ያሰኛቸው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ተሟግተን ወደ ላይ መውጣት አልቻልንም፣ አቅማችን አነሰ፡፡ ብዙ ነገር ነው የቻልነው፡፡ አሁን አደራ ለእናንተ እንስጥ ብለን ነው፤›› ሲሉም ዞኑ ለክልል ከተማ ያለውን ርቀት በመጥቀስ መፍትሔ ሽተዋል፡፡

በሌላ ወገን በሚሊኒየም አከባበር ብሔራዊ ምክር ቤት በዕቅድ ተይዞ የተገነባው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ከዓመታት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቢመረቅም፣ አገልግሎት መስጠት ሳይችል መቅረቱ ‹‹የብዙዎችን ቅስምና ልብ የሰበረ፤›› እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሌላ ጥያቄ አቅራቢ የክልልነት ጥያቄ የሚነሳው እንዲሁ ከርቀት አንፃር ሳይሆን ፍትሕን ከማግኘት አንፃር ነው በማለት፣ ክልል ድረስ አመራሮች ለተለያዩ ጉዳዮች ሲሄዱ የሚወጣው ገንዘብ ብክነት እንደሆነና ለአካባቢው ልማት መዋል የሚችል እንደሆነም አክለዋል፡፡

‹‹እኛ ለብቻችን ክልል እንሁን ሳይሆን ከአጎራባች አብረውን ለመሆን የሚፈልጉ ካሉ እናቅፋለን፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ የቦንጋ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከመንገድ መቅረቱ፣ የሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት የመስጠት አቅም አናሳ መሆን፣ እንዲሁም የአካባቢውን አቅም በማጥናት የኢኮኖሚ ቀጣና ማድረግ ይገባ እንደነበር በመጠቆም ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ከጥያቄዎቹ በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የልማትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በሚመለከት እንዴት በበጀት በማካተት መመለስ እንደሚቻል እናያለን፤›› በማለት፣ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ቤተ መጻሕፍትና ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩላቸው የቀረበላቸውን ጥያቄ በማስመልከት የእሳቸው ጽሕፈት ቤት እንደሌለውና እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በልመና የሚሠራ በመሆኑ፣ ገንዘብ ሲገኝ የሚታሰብበት ሥራ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

ለአካባቢውና ለነዋሪው የሚጠቅም ኢንቨስተር ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግና እየተሠራበት እንደሆነ በመጠቆም ስለመዋዕለ ንዋይ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እኛ ኢንቨስተር እንጋፋለን፣ እነሱም እየፈሩ መጥተዋል፤›› በማለት፣ በመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ላይ የደረሱ የተለያዩ ጥቃቶች ባለሀብቶችን እያራቁ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ሕዝቡ ደኑን ለመጠበቅና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ያዳበረውን ባህል በማድነቅ፣ ‹‹ሥርዓት የለመደ ካልሆነ በስተቀር ደን አስቀምጦ የሚቸገር ሕዝብ እኮ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

የክልልነት ጥያቄን አስመልክተው ‹‹ዋናው ጥያቄ›› በማለት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አደረጃጀትን የሁሉ ነገር መፍቻ አድርገን አንውሰድ፤›› በማለት ክልልነት መብት እንደሆነና የቀረቡት ምክንያቶችም ልክ እንደሆኑ ተናግረው ክልል ሆነው የቆዩት ‹‹ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች እንደ እናንተ የመንገድና የድልድይ ጥያቄ እያነሱ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ርቀትንም በሚመለከት ከሞያሌ አዳማ ያለው ርቀት፣ እንዲሁም ከምንጃር አካባቢ ባህር ዳር ድረስ ያለው ርቀት ጋር ተመሳሳይ ዓይነት ችግር እንደሚደቅን በመግለጽ በሌላም አካባቢ ያለ ችግር ነው ብለዋል፡፡

ሞያሌ ያለ ሶማሌ ጅግጅጋ ድረስ የሚሄደው ከ1,000 ኪሎ ሜትሮች በላይ በማቋረጥ እንደሆነ በመግለጽ፣ በሌላ ሥፍራም ያለ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ክልሉ ከእናንተ ጋር በመወያየት ለካፋ ሕዝብ የሚጠቅመው ይኼ ነው የሚል ከሆነ ለፌዴራል መንግሥት አይከብደውም፣ ምንም ማለት አይደለም፤›› ብለው፣ ‹‹ያሉትን ሕዝቦች ካሳመነ ማንም ሊያስቆም አይችልም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕዝብ ከተስማማበት የማይሆን ነገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይኼንን በሚመለከት የተጠናው ጥናት ሕዝብ ካልተስማማበት በሌላ ባለሙያ ማስጠናትና የተሻለ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሆኖም ‹‹የዕለት ተዕለት ጥያቄን ብቻ እየመለስን ዘላቂ ሥራ ሳንሠራ እንዳንቀር፤›› በማለትም አሳስበዋል፡፡

ሙዚየሙን በተመለከተ በቂ መረጃ እንደሌላቸውና ለምን ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻለ እንደማያውቁ በመግለጽ፣ ጉዳዩን በማጣራት በአቶ ርስቱ በኩል ምላሽ ይሰጣል ብለዋል፡፡

ከልማት ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎችንም በተመለከተ፣ ‹‹እኛ የተቀመጥነው እናንተን ለማገዝ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹በተቻለ መጠን ለማገዝ ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

ከውይይቱ መልስ የቦንጋ ጤና ጣቢያና የቡና ሙዚየምን ከጎበኙ በኋላ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይኼ ሁሉ ሚዲያ ወደ ሥፍራው የተወሰደው አካባቢውን በማየት መስህብነቱን እንዲያስተዋውቅ በማለም ነው ብለዋል፡፡

Source: Reporter  https://www.ethiopianreporter.com/article/16787?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: