Leave a comment

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት እና ከጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የቀረበ ጥሪ


ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት እና ከጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የቀረበ ጥሪ

የተከበራቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በሃገራችን ላይ እየደረሠ ያለውን ጭቆናና የግፍ አገዛዝ በመቃወም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር በመደራጀት በትግል ላይ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ። ለ26 ዓመታት በወያኔ መንግስት የግፍና የጭቆና ቀንበር አገዛዝ ሥር በመውደቅ ለበርካታ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች የተጋለጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃውሞውንና እንቢተኝነቱን በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ማሰማት ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል።  በመሆኑም የወያኔ መንግስት እየተከተለ ያለው የዘረኝነት ፖለቲካ በአንድነቷ ፀንታ የቆየችውን ኢትዮጵያን በመበታተን ህዝቡን እርስ በእርስ እንዲጋጭና ሃገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ እያመራች በመሆኑ ምሬትና ብሶት ያንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆቹ ገሚሱ ለእስር እና ለስደት በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለነገይቱ ኢትዮጵያ ነጻነት ውድ ህይወታቸውን በመገበር ልይ እንደሚገኙ ይታወቃል። የተከበራቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከቀን ወደቀን እየበረታ የመጣውን የህዝብ ተቃውሞ ለመቀልበስና የግፍና የጭቆና አገዛዙን እድሜ ለማራዘም ወያኔ በተለያዩ ወቅቶች የማዘናጊያና የማደናገሪያ ሥልቶች ሲጠቀም እንደነበር የማይካድ ሃቅ ነው።

ስለሆነም በቅርቡ በጭንቀትና በውጥረት የተሞላው የወያኔ ኢህአደግ የ17ቀናት ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ የፖለቲካና አንድአንድ የታሰሩ ግለሰቦችን እፈታለሁ ብሎ የተምታታና እርስ በእርሱ የሚጣረዝ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። እንደሚታወቀው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች የመሰደዳቸው ፣የመታሰራቸውና የመሰዋታቸው ዋነኛ ሚስጢር በቁም እና በህሊና እስረኝነት የሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃ ለማውጣት እንደነበር ወያኔዎችም የሚጠፋቸው እውነታ አይመስለንም። ሆኖም የወያኔ መንግስት ከተደቀነበት ውጥረትና ከተጋረጠበት የገነፈለ የህዝብ ሥሜት ለመሸሽና ውንብድናውን አጠናክሮ ለመቀጠል የዘየደውን ከንቱ ዘዴ መላው የሃገራችን ህዝብ በጥንቃቄ እንዲመለከተውና እንደሚያጤነው እንገነዘባለን። በገዛ ሃገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቆጠር ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት ረገጣ የተዳረገውና ላለፋት 26 ዓመታት በጉስቁልና ህይወቱን እየገፋ የሚገኘው ጀግናው የኢትዮጱያ ህዝብ በወያኔ የማደናገርያና የማዘናጊያ ታክቲክ ሳይታለል ትግሉን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደምገባው በአፅንኦት እንገልፃለን። ከራሳቸው ክብርና ርካሽ ጥቅም ይልቅ ለህዝባቸው ነፃነት መከበር አምርረው በመታገል ላይ የሚገኙ ብርቅዬ የገዥው ፓርቲ አባላትና አመራሮች በጀመሩት ያላሰለሰ ትግል የመላውን ህዝብ የልብ ትርታ በማዳመጥ ለላቀ ድል ወደ ፊት መገስገስ እንደሚገባቸው ለመጠቆም እንወዳለን።

በቡድንና በፖለቲካ ድርጅት በመታቀፍ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የኢትዮጵያን ህዝብ ከወያኔ የግፍ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በመታገል ላይ የምትገኙ ሁሉ ምንም እንኳን በአደረጃጀት ባህሪ በተለያየ መንገድ ብንደራጅም የመዳረሻ ግባችን አንድ ነውና ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በውስጣችን ያለውን ልዩነት በማጥበብ ተቀራርበን በኢትዮጵያ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የወያኔ መንግስትም ቢሆን በመላ አገሪቱ የሚገኙ የህሊና ታሳሪ የሆኑ የፖለቲካ፣የሲቪክ ማህበራት መሪዎችንና ጋዜጠኞችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታትና ተገቢውን ካሳ በመክፈል  ሥልጣኑን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለባለቤቱ ለተከበረው ህዝብ እንዲያስረክብ እንጠይቃለን።

በመጨረሻም የፖሊስ እና የተከበራቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም እየተረገጠ እና እየተጨቆነ ያለው የወገናችሁ ብሶትና በደል ተሰምቶአችሁ እስከዛሬ ለግድያና ለድብደባ የወሰዳችሁትን የመሣሪያ አፈሙዝ ወደ ላይ በማንሣት ለህዝብ ነፃነት እየታገሉ ካሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ጎን በመቆም በወርቅ መዝገብ ላይ የማያልፍ ታሪክ እንድታስመዘግቡ በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ለዘመናት ፀንቶ የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ዛሬም ሆነ ለወደፊት እንደተጠበቀ ይኖራል!!!

http://kaffamedia.com

Posted by: Kumilachew Gebremeskel Ambo

Advertisements
Leave a comment

የነፃነት ትግል ጥሪ


የነፃነት ትግል ጥሪ

በረዥሙ ታሪክህ በአስተዳደር ጥበብ፣ በጀግንነትህና በተፈጥሮ ሀብትህ የምትታወቀው ውድ የካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች እና ማጂ ህዝብ ሆይ ምንም እንኳ ባለፉት ተከታታይ መንግስታት በደረሰብህ ግፍ፣ ጭፍጨፋ፣ ጫና እና በደል አንገትህ ደፍተህ ለመኖር ብትገደድም አሁን የግፍ ፅዋ ሞልቶ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ እህቶችህና ወንድሞችህ ጨቋኙን ሥርዓት ለማስወገድ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም መጪው ሥርዓት ላንተ እና ለልጆችህ የተሻለ ዕድል ይዞ ይመጣ ዘንድ ያንተ በትግሉ የጎላ ተሳትፎ ማድረግ ለነገ የማይባል ነው። ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ዛሬውኑ ተነስ! ለሌሎች ወገኖችም አለኝታነትህን አስመስከር! በመላው ኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን ትግል ተቀላቀል! ነፃነትህን በራስህ ትግል ተቀዳጅ!እኩልነትህን በትግልህ አረጋግጥ! ፍትሕን በትግልህ አስፍን! ጭቆና በቃን! የሀብት ዘረፋን አንታገስም!

ልጆችህ ትግሉን ለማስተባበር እየሠሩ ነው! ተነስ! ተዘጋጅ!

ኖ ወራፎ ከፊነ ኖሚምዮና ሽገችነ!

http://kaffamedia.com

Posted by: Kumilachew Gebremeskel Ambo

2 Comments

የደኢሕዴን ዝምታ ሚስጢሩ ምን ይሆን?


የደኢሕዴን ዝምታ ሚስጢሩ ምን ይሆን?

የህወሃት የትግል ታሪክ እንደሚያስረዳን ከሆነ የትግራይ ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ለመመለስና ነፃ ለማውጣት ቢሆንም ወዳጆቻቸው በነበሩ ባለፈርጣማ ክንድ ሃገራት ድጋፍና ጣልቃ ገብነት በለስ ቀንቶአቸው የደርግ መንግስት (አገዛዝ) እንደተገረሰሰ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ሥልጣን ቁንጮ ላይ ሊወጣ ችሏል። ህወሃትም በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠ ከዓመታት በኋላ በአመራሩ መካከል የተፈጠረው መፈረካከስና ቡድንተኝነት ተከትሎ የአንደኛው አንጃ አቀንቃኝ ነው ተብሎ በጥርጣሬ ቀለበት ውስጥ የገባውና በራሱ በህወሃት አምሣል የተፈጠረው የዚያኔው ደኢህዴግ የአሁኑ ደኢህዴን በወቅቱ ሥር እየሰደደ የመጣውን የህወሃት የበላይነት ሊቆም ይገባዋል ፓርቲው ከሞግዚት አስተዳደር ወጥቶ በራሱ ቁመና መመራት አለበት የሚለው ተቃውሞ መበርታቱን ተከትሎ ፓርቲውና አባላቱ መታደስ አለባቸው የሚል ሥልት ተቀይሶ ሥራ ላይ እንዲውል ተደረገ ። ይህንን ተሃድሶ በበላይነት የሚመራ እና የህወሃትን ተልዕኮ በታማኝነት የሚያስፈጽም መልዕክተኛ ሲፈለግ ደግሞ በውቅቱ የኦህዴድ አመራር የነበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ለመድረኩ ይመጥናሉ ተብለው ተመደቡ። አቶ አባዱላም የተሰጣቸውን የሞግዚትነት ተልዕኮ ተቀብለው መላው የደኢህዴግ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሃዋሳ ከተማ ላይ የተሃድሶ ፕሮግራም ለተከታታይ ሁለት ወራት እንዲካሄድ ተደረገ።በዚህ የግምገማ ሂደትም የህወሃት ስወር ደባ አስፈጻሚ አባዱላም ለህወሃት ያላቸውን ታማኝነት በፅናት ለማስፈፀም ከነበራቸው ቁርጠኝነት የተነሣ በግምገማው ላይ ጠንካራ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ብርቅዬና ምን አልባትም እስከዛሬ ቢቆዩ ኖሮ በአሁኑ የኢትዮጵያ የተቃውሞ አብዮት ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ይሆኑ የነበሩ በርካታ ጓዶች ሠለባ እንደሆኑና ጥቂት የማይባሉትም ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን በውቅቱ የግምገማው አካል የነበሩ ጓዶች የማይዘነጉት ሃቅ ነው። እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የደኢህዴግ ጓዶች አንዱና ዋነኛ ትግል የነበረው በግምገማ ወቅትና ከዚያም በፊት በድርጅታዊ ድጋፍ ሥም ለስለላ ተግባር ተመድበው የነበሩ ለምሳሌም ያክል እንደ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ያሉ የህወሃት ካድሬዎች ክልሉንና መድረኩን ለቀው እንዲወጡ የሚል ግፊት በመበርታቱ እነሱም ለቀው ወጥተዋል። የደኢህዴግ እና የአባላቱ አጠቃላይ ጥንካሬና እንቢታ ያሰጋው የህወሃት መንግስት ብዙም ሳይቆይ በ1995 ዓ.ም ደግሞ ተሃድሶ እንዲካሄድ ባሳለፈው ውሳኔ ድራማዊ በሆነ መንገድ በሃሰት በተቀነባበረ የቪድዮና የጹሑፍ መረጃዎች እንዲቀርቡ ተደርጎ የህወሃት ሸፍጥ የተሞላበት የጭቆናና የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሻቸው የቁርጥ ቀን የህዝብ ልጆች የሆኑና በጥንካሬአቸው የሚታውቁ ካድሬዎች እንዲወገዱና በምትካቸውም የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ ነገር ግን በተቃራኒው የክልሉን ህዝብ ጥቅም አሳልፈው የሸጡ ተላላኪዎች ሥልጣን እንዲይዙ ተደረገ። በመሆኑም አሁን በዳቦ ሥሙ ደኢህዴግ ከየትኞቹም መሠል ብሔራዊ ድርጅቶች ቀድሞ ገና በጠዋቱ የህወሃትን ጋጠወጥ የጭቆና አገዛዝ በመቃወም ለወከሉት ህዝብ ያላቸውን ታማኝነት በቁርጠኝነት የገለጹ ካድሬዎች ስብስብ የነበረው የኸው ድርጅት ምንም እንኳን በህወሃትና በተላላኪዎቹ የበረታ ክንድ ተመቶ በአንፃሩ በራሱ ሰዎች እንደገና እንዲዋቀር ቢደረግም ዛሬም ቢሆን ህዝባዊ ወግንተኝነት ያላቸው የህወሃት ግፍ አገዛዝ የመረራቸው ግን ደግሞ ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የሚያስደነግጥ ቁዘማ ውስጥ ቢሆንም በእኔ በፀሀፊው ደምሳሳ ግምት **የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይቀልድም** ወደ ሚለው ወደ አበው ብሂል ይወስደናል ብል ተሳስተሃል አልባልም። ዛሬ እንደምናስተውለው ብሶትና ምሬት የወለደው ትግል በተለይም በኦህዴድና ብአዴን አከባቢ እየገነፈለ በመጣበት ወቅት የደቡብ ክልልን በበላይነት የሚመራው ደኢህዴንና የህዝቡ ዝምታ እውነት ለመናገር ህወሃትን ተቃውመዋል። በመላው የኦሮሞ ህዝብ ላይ በህወሃት መንግስት እየደረሰ ያለው ግፍና በደል እሳቸውንም አንገሽግሾአቸዋል የተባሉት አባዱላንም ሣያስገርም አልቀረም። ስልሆነም የህወሃት መንግስት ፀረ- ዴሞክራሲያዊና ኢ- ፍታዊ ብሎም አምባገነናዊ አገዛዝ እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የደቡብ ህዝብንም በእጅጉ የጎዳና ለምሬት የዳረገ እኩይ ድርጊት ስለመሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው። አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስተርነት የሚመሩ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝን ጨምሮ በርካታ አመራሮችና ካድሬዎች ያሉበት ደኢህዴን አብጦ ሊፈነዳ የተቃረበውን ህዝባዊ ተቃውሞ በህወሃት አመራሮችና ካድሬዎች የጀርባ ግፊት ከማፈንና ከመድፈቅ አባዜ ተላቀው በዚህ ታሪካዊ የትግል ምዕራፍ እነርሱም ተነቃቅተው መላውን ሕዝብ በማንቀሣቀስ ጨቋኙንና አምባገነናዊ ሥርዓት በቃ ሊሉት ይገባል።

ጎዲ ጃሹ godi72@yahoo.com

http://kaffamedia.com

Posted by: Kumilachew Gebremeskel Ambo

Leave a comment

ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨቱ የወያኔ ሤራ በከፋ፣ ቦንጋ ከሸፈ


ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨቱ የወያኔ ሤራ በከፋ፣ ቦንጋ ከሸፈ

በዓለማችን ላይ ለሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮ በአስፈላጊነታቸው ከታወቁ መሠረታዊ የምግብና መጠጥ ፍላጎቶች ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብርን በመፍጠርና በማጠናከር አብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት ህዝቦች ራሳቸውን ከድብርትና ከድካም የምያላቅቁበት ምናልባትም ትልልቅና ባለ ብርቱ ክንዳማ ሀብታም ሃገራትን አብላጫውን የሀብት ሚዛናቸውን በማጦዝ የሚታወቀው አረንጓዴ ወርቅ ቡና ስለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ነው

ዘርና ሃይማኖት ሣይለይ የጾታ ልዩነት የእድሜ ገደብ ህግ ሣያግደው አብዛኛዎቹን የዓለም ህዝቦች የፍላጎት ማዕከል የሆነው በሃገራችን ደግሞ **የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና ** የተባለውን የተፈጥሮ ፀጋ ሣትሣሣና ሳትነፍግ ያበረከተችው የኢትዮጵያዊቷ ምድር የካፋ አውራጃ ናት።

ኢትዮጵያ በዓለማችን አንዱ አድናቆት ያተረፈችው የሰው ልጅ መገኛነቷ በተጨማሪ የቡና መገኛ ምድር መሆኗ የዓለምን ትኩረት ያለምንም ማንገራገር የሳበ ትልቅ ጉዳይ ነው።

በቀድሞ ሥርዓቶች በነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር በኢትዮጵያ 14 ክፍለ ሃገራት የነበሩ ሲሆኑ አንዱ የካፋ ከፍለሃገር ነው ። የካፋ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ ጅማ ሆኖ በሥሩ 6 አውራጃዎች እንደነበሩትና ከ6ቱ አንዱ ካፋ ነች። በካፋ አውራጃ ሥር 10 ወረዳዎች መካከል የዴቻ ወረዳ ማኪራ ቀበሌ ደግሞ አረንጓዴ ወርቃችን የተገኘችበት ወርቃማ ምድር ነች።

ኮፊ(coffee) የሚለው ሥያሜ ካፋ ከተሰኘው የእንግሊዝኛው ሥርወ ቃል የመጣ ስለመሆኑ በርካታ የታርክ ጸሀፍዎች በድርሣናቶቻቸው ከትበውታል። ካፋ ከቡና መገኛነቷ ጋር በተያያዘ ቀደም ባሉት ዘመናት የዛይላና በርበራ ወደብን የንግድ መስመር ተከትሎ የበርካታ ዓረብ ሃገራት ነጋዴዎችን ከቀያቸው አርቆ ያተመማቸው ትልቅ የንግድ ማዕከል እንደነበረ የመካከለኛው ዘመን የታርክ ጸሀፊዎች ሳያቅማሙ ይስማሙበታል።

ካፋ የቡና መገኛነቱዋ ስለመሆንዋ እውነታውን በየጹህፎቻቸው ካስከመጡልን ከቢቤር ፣አምኖን ኦረንትና ሌሎችም የውጭ ጸሀፊዮች በተጨማሪ ከሃገራችን የታሪክ ምሁራን መካከል የእነ ፕሮፌሰር ላጲሶ ዴልቦ ሥራም የምጠቀስ ነው።

ከእነዚህና ከሌሎችም ታርካዊ እውነታዎች በመነሣት በ2000 ዓመተ ምህረት የተከበረውን ተኢትዮጵያ ሚኒሊየም በዓል ምክንያት በማድረግ እንደ ሃገር ከተሠሩት ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ላይ የተገነባው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ኢትዮጵያ ከዛም ካፋ የቡና መገኛ ቦታ ስለመሆኗ ታሪካዊ እውቅና ስለመሆኑ የማያከራክር ሃቅ ነው።

ይሁን እንጅ በተለይም ወያኔ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረበት ካልፉት 26 ዓመታት ወዲህ ግን በከፋፍለህ ግዛ የብሔር ፖለቲካ መነሻነት ርካሽ የሆነ ያልተገባ የታሪክ ሺሚያ በማቆጥቆ ላይ ይገኛል።

እንደሚታወቀው ጅማ በቀደሞው አስተዳደራዊ መዋቅር የካፋ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ግዛት ወይም ዋና ከተማ እንድትሆን ሲወሰን ያለ አንዳች መነሻ አልነበረም፣ ከጊቤ ማዶ የሚገኘው አጠቃላይ ግዛት የካፋ ህዝብ አሠፋፈርን መሰረት ያደረገና ጅማም የካፋ ህዝብ መናገሻ ማዕከል ከማድረጉም ባለፈ ጅማና የካፋ ህዝብ የ አንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ስለመሆናቸው ተፈጥሮ በራሷ እውነተኛ ምሥክር ነች።

በመሁኑም በወያኔ አገዛዝ ሥርዓት ወቅት የኦሮሚያ ህዝብና ክልል መንግስትን የማይውክሉ እንዲሁም የሁለት ህዝቦች የብዙ መቶ ዓመታት ወዳጅነትና ዝምድና መተሳሰብ ብሎም በተለያዩ ሁኔታዎች በትስስር መኖራቸው ያሳሰባቸው የወያኔ ካድሬዎች በወጠኑት ሴራ ቡና የተገኘው ካፋ አዎራጃ ማኪራ ቀበሌ ሣይሆን ጅማ ዞን ነው እየተባለ የሚናፈሠው የተዛባ መሠረተ ቢስ ታርክ በእጅጉ አሳዝኖናል።

ቡና ካፋ በመገኘቱ አጠቃላይ እውቅናው የኢትዮጵያ እንጅ የካፋ አለመሆኑ በግልፅ እየታወቀ ግን ደግሞ ታሪክን በእውነትነቱ ከመቀበል በአፈንጋጭነት ዝንባሌ በፀብ አጫሪውች ግፊት ወደ አልተፈለገ ድምዳሜ መድረሱ ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ነው።

በኦሮሞ ህዝብና ክልል ሥም የሚነግዱ የወያኔ ካድሬዎች ድብቅ አጀንዳና መፈክር ጎላ ብሎ መስተጋባት የጀመረው በተለይም የቡና ሙዚየሙ እንዲገነባ በፌደራል መንግስት ከተወሰነበት ግዜ ጀምሮ ሲሆን አሁን በቅርቡ ከታህሣሥ 7 ጀምሮ ቀናት የፌደራል መንግስትባዘጋጀው የቡና አፈላል ሲምፖዚየም ላይ ከቡና መገኛነት ጋር ተያይዞ የተዘጋጀው ፓናልውይይት ከኦሮሚያ መጡ በተባሉ ተወካዮች እንቢተኝነት ሣይካሄድ መቅረቱ ይህ የተዛባእውነታና የወያኔ መንግስት ግጭት የመፍጠር ዝንባሌ ፍላጎት የቱን ያክል ወደ አበቃለትየአስተሳሰብና የአመለካከት ብልሽት ጫፍ ስለመድረሱ ማሣያ ነው።

የዚህ ጹህፍ አዘጋጅ አመለካከትና እምነት ከሆነ በተሣሣተ ፍላጎትና ግፊት በመነሣሣት ለበርካታ ዘመናት በአብሮነት የኖረውን ህዝብ ከማጋጨት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ በቅጡ እንድረዳው እያሳሰብን ምን አልባትም የግጭት ፈላጊ ኃይሎች አጀንዳ ከማራገብ አኳያ አውቀውም ይሁን ሣያውቁት የዚህ አስተሣሰብ ሠለባ የሆነ መንአልባትም የኦሮሞን ህዝብና የክለሉን መንግስት ሣይሆን የግል አመለካከታቸውን የሚያራምዱ ኃይሎች ከዚህ ድርግታቸው እንድቆጠቡ ሌላው መልዕክታችን ነው።

የካፋ ዞን( የቀድሞ የካፋ አውራጃም) ቢሆን የቡናን ጥራት ሣያስጠብቁ ቡና አብቃይ በሆነችው ብርቅዬ ምድር የሚኖረው ህዝብ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በአግባቡ ሣያረጋግጡ ብሎም የራሱን አቅምና ሃብት አስተባብሮ የአረንጓዴ ወርቁን ተፈጥሮአዊ ጣዕም ለማጣጣም የተመሠረተውን የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን እንኳን ከረጃጅም ሌባ እጆች መታደግ ሣይችል የቡና መገኛ ነኝ ማለት ብቻውን የትም አያደርስም።

ስለሆነም ከብዙ ዘራፊዎች ማለትም ከነብርሃኑ አዴሎና ታምሩ ታደሠ የዝርፊያና የምዝበራ መዕከል በትንሹም ቢሆን ተርፎ በመንገታገት ላይ የሚገኘውን ዩኒዬን በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ እንድቀስምና ራሱን አጠናክሮ ከዘርፉ  ከሚገኘው ጥቅም ተቋዳሽ እንዲሆን ማድረግ።

በአርሶ አደሩ መንደር ከቡና ተክል እስከ ለቀማ በግንዛቤ እና በእውቀት እጥረት የሚስተዋለዎን የቡና አያያዝ መሠረታዊ ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመቅረፍ የአርሶ አደሩ ህይወት ከቡና ግብይት በሚገኘው ገቢ እንዲለውጥ ማድረግ።

የካፋን ቡና ተፈጥሮአዊ ጣዕምን የሚያውቁና የተለየ ግምት ያላቸው እንዲሁም የካፋን ቡናን በዓለም ገበያ በማቅረብ ረገድ ተሞክሮ ካላቸው የአውሮፓውን በተለይም የጀርመን ባለሃብቶች ጋር ኢኮኖሚያዊ ቁርኝነት በመፍጠር ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው ቡና በመጠንና በጥራት ከፍ እንድል ማድረግ የዘርፍን ጥቅም ያሣድጋል።

ሌላውና ሊታለፍ የምይገባው ጉዳይ የዞኑ አብዛኛው መሬት ለቡና ማብቀል የተስማማ በመሆኑ መሬት በባንክ እያስያዙ ለሚኮበልሉና ደን እየጨፈጨፉ ዞኑን እርቃኑን አስቀርተው የራሳቸውን ሃብት ለሚያካብቱ ባለሃብቶች ነን ለሚሉ የጠራራ ፀሃይ ዘራፊዎች ጋር እየተባበሩ የዞኑን ህዝብ የበይ ተመልካች ከማድረግ እና በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮችና ወጣቶችን በማስተባበር እውነትም ካፋ የቡና መገኛ የሚለውን ታርክ በድጋሚ በወርቃማ ቀለም አድምቆ ማደሱ ተገቢ ነው እንላለን።

http://kaffamedia.com

Leave a comment

የእናት ሀገር ጥሪ


የእናት ሀገር ጥሪ

ነቃ በሉ ልጆች ምንድነው ዝምታው

ቀስቅስ ወንድምህን ወቤ ወቤ በለው

ከሰሜን አማራ ከኦሮሚያ ቄሮ

እየተጣራ ነው በአንድነት አብሮ

ቡሾ ቤቶ ጩሎ እያለ ሲጣራ

ፋኖ ከቄሮ ጋር አብሮ እያቅራራ

አለሁኝ በልና ተነስ ተቀላቀል ከትግሉ ጎራ

ከፋ፡ ሸካ፡ ማጂ፡ በንች፡ ደቡብ መልስ ስጡ ድምጻችሁ ይሰማ

ዝምታ አያዋጣም እናት ሀገር ታማ

የምች መድሀኒት ካለ ከጓሮአችሁ

ፈጥናቹ ድረሱ መድሀኒት ይዛችሁ

እየታመሰች ነው እናት ኢትዮጵያ

በገዛ ልጆቹዋ በወጡት ከሷ ጉያ

ምን ዓይንት ዘመን ነው የዘመን እላቂ

በደሉ የከፋ ግፉም አሰቃቂ

እስት ለደቂቃ ቆማቹሁ አስቡ

ማየት ተስኖኛል ግራ ስትጋቡ

መሬቱ ጠቦ ነው ወይስ ሀብቴ አንሷች ሁ

ተስማምቶ ለመኖር ዛሬ ያቃታች ሁ

ከውጭም ከውስጥም በቃኝ አታምሱኝ

እባካች ሁ ልጆቼ ሰከን በሉልኝ

በህብረት ተነሱ ድምፄን አሰሙልኝ

በአንድነት ቁሙና ከጥፋት ታደጉኝ

ጎኔ መሬት ነክቶ እንቅልፍ እንድተኛ

ልቦና ይስጣችሁ የላይኛው ዳኛ

ሲባል ሰማ ነበር የውለደ አልፀደቀ

በኔም ላይ ደረሰ በናንተ መናቆር ሰውነቴ አለቀ

በሰላም በፍቅር ኑሩ ባንድነት

የተሰደዳቹ ግቡና አገር ቤት

ልጆቼ በሙሉ አደራ የምላች ሁ

ተባብራችሁ ኑሩ እንደ አባቶቻች ሁ

ነፋስ ሳታስገቡ በመካከላችሁ

ሆኜ እንድቀጥል የአፍሪካ ተምሳሌት የነጻነት ጮራ

ቃኪዳን ግቡልኝ ከእንግዲህ አደራ

ታፊሬ እንድኖር በናንተ እንድኮራ

ከፋንታዬ መኮ

http://kaffamedia.com

Leave a comment

ከደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ኅብረት እና ከጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤


ከደቡብ–ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ኅብረት እና ከጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤

እንደሚታወቀው የህወሓት–ኢሕዴግ መንግሥት ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጦ የአፈና፣ ጭቆና፣ ብዝበዛና ግድያ ቀንበሩን በመጫን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመርገጥ አልፎ ለዘመናት ገንብቶት የኖረውን አብሮነትና የመቻቻል ባህል በብሔር ተኮር ፖለቲካ በመተካት የዘር ጥላቻ እንዲነግሥና ሃገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫና ብተና እንዲሁም ወደ ትርምስ እንድታመራ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።

እኛ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጽያ  ሕዝብ ህብረት እና የጋምቤላ ሕዝብ አንድነት በጋራ በመሆን ይህንን መግለጫ እንድናወጣ የተገደድንበት ዋነኛ ምክንያት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሰው ልጆች በመደብ መተዳደር ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የውጭ ጠላትን በጋራ መከላከል እንጂ ተጋጭቶ የማያውቁትን የአሮሞና ሱማሌ ህዝቦች የራሱን ሠራዊት አስቁሞ እልቂ ት እያካሔደ የሚገኝ ሲሆን ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ሃ/ማርያም ደሳለኝ የሰጡት አድሎአዊነት የተሞላበት መግለጫ አሳዝኖናል። በመሆኑም ይህ ስርዓት ካልተወገደ ሀገራችን አደገኛ መንገድ ላይ ስለምትገኝ ሁሉም እውነተኛ ሀገር ወዳድ ተቃዋሚ ሃይሎች ህዝባችንን አስተባብረን በሁለንተናዊ ትግል በአስቸኳይ በጋራ እንድንቆም እናሳስባለን።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት፣ ህብረትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያበሳጨውና ያንገበገበው የወያኔ ባለሥልጣናት በተለይ በምሥራቁ ኢትዮጵያ የተመደቡት ኮንትሮባንድ ነጋዴ ጀኔራሎች የኢትዮጵያን ሱማሌ ፕሬዝዳንት በግልጽ በመርዳትና በመወገን  የሚያቀነባብሩት ይፋዊ አድሎ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን አንድነት ቀውስ የሚፈጥር ሴራ ሁሉንም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያሳዘነና ያስቆጣ ስለሆነ በአስቸኳይ ለማስቆም ሁላችንም በጋራ መስራት ይጠበቅብናል።

እንደሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ከሕዝብ ጥቅምና መብት መከበር  ዓላማ ላይ የተመሰረተው ድርጅታችን ይህንን አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት  ለመገርሰስ በሚደረገው ወሳኝ የታሪክ ትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።በመሆኑም ሃገር ወዳድና  ተራማጅ ሃይሎች ሁሉ የጀመሩት መራራና ወሳኝ ትግል ሲኬታማ የሚሆነው የተለያየ የፖለቲካ አካሄድ የሚከተሉ ነገር ግን ወደ አንድ ግብ ለመድረስ የተሰለፉ ሁሉ ልዩነታቸውን በማቻቻልና በማቀራረብ ዛሬ ሃገሪቱ ከገጠማት የብተናና የዜጎችን እልቂት መታደግ ሲቻል ብቻ ነው ብለን በጽኑ እናምናለን።

በዚህ ፈታኝ በሆነ የትግል ሂደት ውስጥ ለያንዳንዳችን ለነገ ነፃነት ውድ ሕይወታቸውን በየቀኑ መስዋዕት እያደረጉ ላሉ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ድርጅታችን ያለዉን ታላቅ አክብሮት እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ትግሉን እያስቀጠሉ ላሉ የትግል አጋሮቻቸው መፅናናትን ይመኛል፤ በተለይ በቅርቡ በወያኔ ቅንብር በኦሮሞና ሱማሌ ወገኖቻችን ላይ በደረሰውና እየደረሰ ላለው እልቂትና ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልጻን።

የወያኔ መንግሥት ዕድሜውን ለማራዘም እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ ስትራተጂ ለማክሸፍ የኦሮሞና ሱማሌ ክልል መንግሥታትና በተለይም ሕዝቡ በሰከነና በሳል አመለካከት የተፈጠረውን የዘር ጥላቻ በፍቅርና በመቻቻል እንደሚተካው እምነታችን የጸና ነው።

ስለሆም በተለይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከጊቤ መለስ ከየም እስከ ማጂ፤ ደቡብ ሕዝቦች ከሚባለው አሣፋሪና ጥገኛ አሸንጉልት የወያኔ ድርጅት ራሱን አግልሎ የማይቀረውን ለውጥ በመቀላቀል ታርክ እንድትሠሩ በጥብቅ እናሳስባለን።

በመጨረሻም በደቡብ–ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላንም ጨምሮ የወያኔ ሥርዓት አራማጅ  ባለሥልጣናት፣ ካድሬዎች፣  ምሁራንና በየደረጃው የምትገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች  በሙሉ!! በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ከተበደለውና ከተጨቆነው ወገናችሁ ጎን በመሰለፍ የትግሉ አካል እንድትሆኑና ከታሪክ ተወቃሽነት እራሳችሁን ነፃ እንድታወጡ በተበዳዩ ሕብረተሰባችን ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ።

ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲና እኩልነት ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ከደቡብ–ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕብረትና የጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር

Leave a comment

መቋጫ ያልተገኘለት የሸካ ህዝብ የዘመናት ውስብስብ ችግር መፍትሔው ማን እጅ ነው ያለው?


መቋጫ ያልተገኘለት የሸካ ህዝብ የዘመናት ውስብስብ ችግር መፍትሔው ማንእጅ ነው ያለው?

በሐገራችን በተለያዩ ወቅቶች በተፈራረቁ ሥርዓቶች የተለያዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እና ሥያሜዎች ሥትጠራ የቆየችው የቀድሞዎ የሞቻ አውራጃ አሁን ባለው ሥርዓት ደግሞ በደቡብ ክልል ሥር ከሚገኙ ዞኖች አንዷየሆነችው የሸካ ዞን ተፈጥሮ የቸራት ውብና ድንቅ ምድር በውስጧበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፍ ትገኛለች::

የሸካ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ካሉት ዞኖች በጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ባለቤትነቷ ከመታወቛም ባሻገር የተፈጥሮ ቡና አብቃይና በማርና ቅመማ ቅመም ምርቶቿ የበርካቶችን ቀልብ የሳበች የታታርና የእንግዳ ተቀባይነቱ እንድሁም በጅግንነቱ የምታወቅ ህዝብ መገኛ ለምለም ምድር ስለመሆኑዋ ዛሬም በታርክ ጸሃፊዎችና ነዋርዎች አንደበት በአድናቆት ትዘከራለች።

በሸካ ምድር የምገኙት ሸከቾች ብቻ ሳይሆኑ መዠንንግር፣ ሸኮ፣ ካፋ፣ ቤንች፣ ኦሮሞ፣ እና ሌሎችም ህዝቦች በመፈቃቀድ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ እንደ አንድ ህዝብ ሆነው ይኖራሉ።

እነዚህ ህዝቦች በሰላምና በመከባበር ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን በረከት እየተጋሩ የሚኖሩ ሲሆን ባለፉት ሥርዓቶች በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተቃራኒ የሚነሱ ኢፍትሀዊ አሰራሮችን በመቃወም ለመብቶቻቸው መከበርና ለዘላቂ ጥቅማቸው መረጋገጥ የህይወት መስዕዋትነትን እስከመክፈል የደረሰ የጀግንነት ታርካቸው አሁን እስካለው ትውልድ ለውደፊትም እስከሚመጣው በዘመን ተሻጋርነት ሲወሳና ሲዘከር ይኖራል።

ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችው የሸካ ዞን ፈጣሪ በኪነ ጥበቡ ውብና ድንቅ አድርጎ የፈጠራት ብትሆንም ካለፉት ሥርዓቶች እስከዛሬ ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አንጻር በእጅጉ የተበደለችና የተረሳች ምድር ነች።

እንደው ከቅርብ ጊዜ ታሪክ ማለትም የወያኔ መንግስት ሃገርቱን አስተዳድራለሁ ብሎ የ አፈናና የጭቆና ሥርዓቱን ካሰፈነበት ግዜ ጀምሮ በዚህ ኩሩና ታታሪ በሆነው ህዝብ ላይ በዓይነቱ አሣዛኝና ዘግናኝ ድርጊት እየተፈጸመ ሥለመሆኑ ምንም ማጣቀሻ ሳያስፈልግ ወይንም ማስረጃ መዘርዘር ሣያሻ መሬት ላይ ያለው እውነታ በዳይ የሆነውን ሥርዓትና ተበዳዩን ህዝብ የሚያግባባ እውነታ ስለመሆኑ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ሊጠቁም ይወዳል።

የኸው ሃገርቱን እየገዛ ያለው አፋኝና ጨቛኝ ሥርዓት የፈጠራቸውና ከህዝቡ አብራክ የተገኙ ህሊና የጎደላቸው ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ታማኝ የወያኔ ሎሌዎች አባሪ ተባባሪ በመሆኑ እየፈጸሙት ያለው ልክ ያጣ ግፍና በደል ሌላኛው የሸካ ህዝብ ሰቆቃ ነው።

ዞኑን ያስተዳድሩ ተብለው በተለያዩ ወቅቶች የተሾሙ የዞኑ ተወላጆች ነን የሚሉ የወያኔ ታማኝ አገልጋዮች አቶ ወዶ አጦ እና አቶ በፍቃዱ ድሉ የተባሉት በአስተዳደር ዘመናቸው ከፈጸሟቸው ታሪካዊ ሥህተቶችና በህዝቡ ላይ ካደረሷቸው በደሎች በጥቅቱ ለመግለጽ ያክል፣

1 ፥ በኢንቨስትመንት ሥም ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር በሽርክና እና በተባባሪነት ለሚንቀሳቀሰው ሼክ መሀመድ ዓላሙዲን ከ 10 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ገማድሮ አካባቢ ለቡና ተክል የሚሆን መሬት በርካታ አርሶ አደሮች እንዲፈናቀሉ ተደርጎ ተሰጥቷል።

የሚገርመው ለጥቂት ወያኔ ባለሥልጣናት ወኪል ሆኖ የዞኑን እጭቅ የተፈጥሮ ሀብት እንድበዘብዝ እና እንዲዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ሼክ መሀመድ ዓላሙዲን በለመደው የዘረፋና የሽንገላ ሥልቱ ለዞኑና ለአከባቢው ህዝብ ሆስፒታልና ለሎችንም መሰረተ ልማቶች እዘረጋለሁ ብሎ የማለውን ማሀላ እና የገባውን ቃል ኪዳን ከላይ ሥማቸው የተገለጹት ተላላኪ አስተዳዳሪዎች ነን ባዮች በራሳቸው ጥቅም በእጃዙር ኪሳቸውን በጉቦ በማደለብ የዞኑን ህዝብ ሂሳብ አወራርደዋል።

2፥ ሌላው ኢስት አፍርካ ለተባለው ድርጅት በተመሳሳይ በርካታ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ከመረታቸው ቴናቅለው የሻይ ተክል ማምረቻ እንድሰጣቸው በመደረጉ ዛሬ እነ አቶ በፍቃዱ ዲሎ አዲስ አበባ ላይ በተንጣለለ እና ውድ በሆነ ዋጋ በተገዛ እቤት እንዲኖሩ መደረጉ አሳዛኝ እና ልብ የሚሰብር አስነዋሪ ድርጊት ነው።

3፥ በእነ በፍቃዱ ዲሎ አስከፊ ድርጊት በዚህ ሳያበቃ በትንደላቀቀ ኑሮ ለሚኖሩና ለህዝብ ደንታ ለሌላቸው ለእነ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ለበላይ ወላሻ እንዲሁም ለሚሊዮን ወልዴ በኢንቨስትመንት ሥም የዞኑ ህዝብ የተጎሳቆለ ህይወቱን የሚመራበትን መሬት በመንጠቅ በራሳቸው የጥቅም ሥሌት አሳልፈው በመስጠት ህዝቡን የበይ ተመልካች በማድረግ ለረሃብና ለእርዛት የመደረጋቸው ምሥጥር ባለቤቷን ያመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች´´በሚለው የአበው ተረት ይደመደማል።

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ታዋቂነቱን በመጠቀም ግን ደግሞ ጥቂት ሆዳም እና ህሊናቸውን ለጥቅም አሳልፈው ከሰጡ ዘራፊና ወንበዴ ከሆኑ የዎያኔ ባለሥልጣናት ጋር በመደራጀት በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ሲሰጠው እሱም ልክ እንደ ሼክ ዓላሙዲን ለአከባቢው ህዝብ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እዘረጋለሁ ብሎ ምሎ ተገዝቶ ጥቅሙን ቢያስከብርም እንኳን ይህንን ሊያደርግ ይቅርና በድርጅቱ ላይ ተቀጥረው ለሚሰሩ  ምንደኛ ህጻናት ሊከፈል የሚገባውን የወዛደርነት እራፊ ሣንቲም በአግባቡ እየከፈለ አለመሆኑ ሲታይ የበደሉን እና የግፍን መጠን በእጅጉ ያጎለዋል።

በፍቃዱ ዲሎ በአስተደኣደር ዘመኑ ከፈጸማቸው እነዚ ታርካዊ በደሎችና የግፍ አስተዳደር አኳያ በተለያየ መንገድ በዞኑ ህዝብ ጥቅም ላይ ተደራድሮ ያካበተው ሃብት እንዲያጣትም በሥመ ግምገማ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በተገዛለት እቤትና በእነ አትሌት ኃይሌ እና በመሰሎቹ በሌላ ሰው ሥም የተከፈተለትን የ፭ሚሊዬን ብር ሂሳብ እየመነዘረ የተደላደለ ኑሮ እንዲኖር ሲደረግ መቸም ታማኝ እና ለዞኑ ህዝብ ጥቅም የሚቆረቆሩ ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው እነ አዝመራው ያሉበት ሥብስብ ዞኑን ተረክቦ የማስተዳደር እድል አግኝቷል።

ይሁን እንጂ በአቶ አዝመራው አስተዳዳርነት የሚመራው የካቢኔ አባላት በእነ ፍቃዱ ዲሎ የተፈጸመውን ግፍና በደል በማጣራት ለክልሉ ፀረ ሙሲና ኮሙሽን ዝርዝር መረጃ በማቅረቡ የተነሳ የእነ ፍቃዱና የግብረ አበሮቹ የዘራፊ ባለሃብቶች ኃይል በፈጠረው ተፅዕኖ በተገላቢጦሽ የተራማጅ አስተሳሰብ ባለቤቶች ስብስብ በአጭር ግዜ ውስጥ የተለያየ ታርጋ ተሰጥቶአቸው ወደ ማረሚያ እንዲወርዱ መደረጉ ሁኔታውን ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል።

እነዚህንና ሌሎችንም አስተዳደራዊ በደሎችን ሲፈፅም የቆየው በፍቃዱ ዴሎ እና ከእርሱ ጀርባ ሆነው የዞኑን ህዝብ ደም የሚመጡ የዎያኔ ባለሥልጣናት እና የተደራጁ ዘራፊ ባለሃብቶች ሁኔታ የክልል መንግስት ነኝ እያለ ራሱን በሚጠራው በደቡብ ክልል መስተዳድር ቁልጭ ብሎ እየታወቀ አንዳችም ዓይነት እርምጃ ባለመወሰዱ ዛሬም የበፍቃዱን ፍላጎት የሚያሟሉና ጉዳይ የሚያስፈፅሙ የዞኑ አስተዳደርና ካቢኔዎች በዞኑ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል የተደራረበ እና ማቆሚያ የሌለው እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ዛሬ የጠጠር መንገድ ለሼካ ዞን ህዝብ የቅንጦት ጉዳይ ሆኖ የህልም እንጀራ በመሆኑ የበርካታ እናቶች ህይወት በወሊድ ምክንያት እየተቀጠፈ ይገኛል። ያ ኩሩና ታማኝ እንዲሁም ከልክ ባለፈ ሁኔታ በትዕግስተኝነት የሚታወቀው ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ባለመደረጉ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ በመጠጣት በተለያየ ህመም እና ብሶታቸውና በደላቸው እስከ ወዲያኛው  በሞት እየተሰናበቱ መሆናቸው ሲታይ የዚህ ዓይነቱ ግፍና በደል ማቆሚያው የት ይሆን መፍትሔውስ በማን እጅ ነው ብሎ መጠየቅ ግድ ያለበት ግዜ ላይ ደርሰናል።

ውድ አንባቢያን ከላይ የተዘረዘሩት  ችግሮችና የዞኑ ህዝብ እየተጋፈጣቸው ያሉ በደሎችን ለማስቀረት የተከበረው የሸካ ዞን ህዝብ ዛሬም ልክ እንደ ትናንቱ በገነፈለ የወትሮ የጀግንነት ወኔ እና አልደፈር ባይነት አካኪ ዘራፍ ብሎ ጫካ መግባት ጦር በመማዘዝ የተነጠቀውን መብት ማስመለስ ጥቅሞቹን ማስከበር ጠፍቶት ሳይሆን ከዛሬ ነገ ይሻላል በግል ጥቅም ዓይናቸው የታወሩ ግፈኞች ወደልቦናቸው ይመለሳሉ፣ ግድ የለሹ የወያኔ ሥርዓትም ምን አልባት ከረፈደም ቢሆን የዘገየ ፍትህ ይሰጠኝ እንደሆን ብሎ በተለመደው አስትዋይነቱ በትዕግስት በመጠባበቅ ላይ ቢገኝም ሁሉም በየፊናው አሻፈረኝ ብሎ በእኩይ ድርጊቱ ቀጥሎበታል።

እናም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢና ሌሎችም መላው ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው አካላት እንደሚያምኑት በኢትዮጵያ አሁን ያለው የወያኔ አገዛዝ በህዝቡ ላይ እያደረሠ ያለው የግፍ አገዛዝ እንዲያቆምና መፍትሔ እንዲበጂለት ሁሉም በያለበት ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛል።

ስለሆነም እንኳን በሸካ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጭቆናና በደል በቅርጹም በይዘቱም በጥልቀቱም ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ጠንከር ያለ ቢሆንም ይህም የሥርዓቱ ብልሽት ድምር ውጤት በመሆኑ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት አንድ የሚያደርጉ መሠረታዊ ምክንያቶች አኳያ ሁሉም ያገባኛል ባይ በያለበት ድምጹን ከፍ አደርጎ የሚያሰማበት ትክክለኛ ግዜው አሁን ነው።

የሸካ ህዝብ ከኖረበት ከልክ ያለፈ ትዕግስት አዘቅት ውስጥ በመውጣት በተለያዩ ወደ መፍትሔ አቅጣጫ ሊያደርሱ የሚችሉ የትግል አማራጮችን በጠንካራ የአልበገር ባይነት ሥሜት ዝምታውን በመስበር የተጠማውን ፍትሕ የተነፈገውን መብት ያስከብር ዘንድ የችግሩ ሰለባ እንደሆነ ሁሉ መፍትሔውም በእጁ ነው እላለሁ። በሌላ ግዜ በተመሳሳይ እና ወቅታዊ መረጃዎች እስከምንገናኝ የሸካ ህዝብ መብት ለማስከበር ዛሬም ወሳኝ ቀን ነው አልረፈደም በማለት የምሰናበታችሁ እውነቱ አይቀርም ነኝ

ቸር እንሰንብት።

moderator@kaffamedia.com